Saturday, 02 July 2022 17:33

“ከማይመስልህ ጋር መጋባት፣ አሳ ከዐይብ ጋር መብላት”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  ደራሲ ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌ ፪ መፅሐፍ የሚከተለውን ጽፈውልናል፡፡
ከዕለታ አንድ ቀን የንጉስ ግምጃ ቤት ሆኖ የሚሰራ አንድ ሰው ነበር፡፡ እሱም የንጉሱን ገንዘብ እየሠረቀ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ሀብት ሰብስቦ ከበረ፡፡ ኋላም ከንጉስ ዘንድ ቀርቦ፤ “ከእንግዲህ ወዲያ እየነገድሁ ለመኖር አስቤአለሁና ግርማዊነትዎም ፈቅዶልኝ ቢያሰናብተኝ እወድ ነበር” ብሎ ለመነው፡፡
ንጉሡም፤
“መልሱን በኋላ እሰጥሃለሁ” አለና አሰናበተው፡፡
እሱም እጅ ነስቶ ወጣ፡፡ ንጉሱም የፈቃድ ጠያቂውን አለቃና ተቆጣጣሪውን አስጠርቶ፤
“ይህ ግምጃ ቤት ሥራውን በትክክል ይሰራልን?” ሲል ጠየቀው፡፡
 ተቆጣጣሪውም፤የጎደለውን ገንዘብ ሁሉ በትክክል አመልክቶ፤ ከመዝገቡ እየጠቆመ ለንጉሡ አስረዳው፡፡
 ንጉሡ ከዚህ በኋላ ግምጃ ቤቱን አስጠርቶ እንዲህ አለው፡-
“አንድ ሰው ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከገበታው ላይ አንድ ጠርሙስ ወተት አስቀምጦ፣ ሳይወትፈው ረስቶ ትቶት ሄደ፡፡ አንድ እባብ በጠርሙስ አፍ ገብቶ ወተቱን ሁሉ ጭልጥ አድርጎ ጠጣው፡፡ ከጠጣውም በኋላ ተመልሶ በዚያው በጠርሙሱ አፍ ሊወጣ ቢሞክር፣ ሰውነቱ በጣም ደነደነና የጠርሙሱ አፍ አላስወጣህ አለው፡፡ ምንም ቢታገል ለመውጣት የማይቻል ሆነበት፡፡
እንግዲህ እንዳንተ ሀሳብ ይህ እባብ ከጠርሙሱ ውስጥ ለመውጣት እንዲችል ምን ማድረግ ይገባዋል?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ግምጃ ቤቱም፤
“ንጉስ ሆይ! የጠጣውን ሁሉ ወተት መመለስ ያሻዋል፡፡ ይህን ያደረገ እንደሆነ ሰውነቱ እንደቀድሞው ተመልሶ ይቀጥንና የጠርሙሱ አፍ ያስወጣዋል፡፡ አለዚያ ግን ለመውጣት አይችልም” ብሎ  መለሰለት፡፡
ንጉሡም፤
“መልካም ብለሃል፡፡ ያንተም ነገር እንደዚሁ ያለ ነው” ብሎ በምሳሌ አስረዳው፡፡
በአደራ በተረከብከው ሥራ ላይ ለመንግስቱና ለንጉሡ ታማኝ ሆኖ መገኘት  ከቀረው ሙያ ሁሉ የበለጠ ቁም ነገር ነው፡፡ “ደሞዙ 250 ብር፣ የሚነዳው ቮልቮ መኪና!” የሚለውን የደርግ ጊዜ አባባል ያስታውሷል፡፡
***
እነሆ ከላይ በጠቀስነው ትርክት ውስጥ ሰው በጥቂት ጊዜ ውስጥ መክበርን እንደሚሻ አይተናል። በርግጥም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማሸነፍ ድል ማግኘትና በጦርነት አይበገሬ ሆነው ስመጥርነትን ማረጋገጥ፣ ዋና ፍሬ ነገር ነው፡፡ ማሸነፍን እንሻለን፡፡
ቀጥሎም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ፈጣን ልማትን ማስተናገድ፣ታላቅ ተግባር ነው እንላለን። ይህንንም ለማስፈፀም ስርቆትንና ሙስናን መዋጋት ይዋል ይደር የማይባል ተግባር መሆኑንም እንገነዘባለን፡፡ ተገቢውን/ ሰው ሳይሆን፣ሀብት ለማፍራት ይበጀኛል ያሉትን የጥቅም አካፋይ፤ ብቻ መርጦ ማስሾም ማስሸለም ከፍተኛ ሸፍጠኝነት እና ዐይን- ያወጣ ወንጀል  ነው፡፡
በሀገር ውስጥም በውጪም አንቱ ለመባል አልያም ዝናን አትርፎ ዕውቅናን ለመቀላወጥ ማኮብኮብ ከንቱ ጀብደኝነት ነው!! ይሄንንም በቅጡ እናሰምርበታለን፡፡ ከፍተኛ የአገር ዕዳ፣ ለልጅ ልጆች ማቆየት ምነው!
ከላይ ያነሳናቸውን ፍሬ ጉዳዮች አውጠንጥኖ የማያይ ማናቸውም ድርድር፣ ፋይዳ አልባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ነው፡፡ ሁሉንም ስምምነት፣ ግጭት ወይም ያለ ውጤት መለያየት (ፓሪ መውጣት) ለህዝብ ግልጥ ማድረግ ከማንኛውም ብልህ መሪ የሚጠበቅ እርምጃ ነው፡፡ “ተደብቀው ያረግዙታል፤በአደባባይ ይወልዱታል” እንደሚባለው የአልጋ ወግ፣ ተሸፋፍኖ መጓዝ አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም በማናቸውም ድርድር የኃይል ሚዛንን ጠብቆ በአሸናፊነት ለመወጣት መጣጣርና፣ ፖለቲካዊ ትግልንና ዲፕሎማሲያዊ አቋምን በጥበብ አቆራኝቶ ወደፊት መራመድ ክህሎት ነው! መንገዳችንን/ቀና ያደርግልናልም፡፡ በየትኛውም ዘመን የምናደርገው ድርድርም ሆነ መሰረታዊ ትግል የማጥቃትና የመከላከልን ሕግ የተከተለና አስፈላጊ ሲሆንም፣ ገለል የማለትን መርህ የሚከተል መሆንን ይጠይቃል፡፡ የአራዳ ልጆች “አይቶ ቢቀፍ” እንደሚሉት ነው፡፡
እዚህ ላይ፡-
“ወዳጅና ወዳጅ፣ የተጣላ እንደሆን
መታረቅም አይቀር፣ እንደ ጥንቱም አይሆንም”
የሚለውን የአበው ብሒል አለመዘንጋት ነው፡፡ የምንቆምበት ቦታ የማያዳልጠን፣ ለክፋት የማይሰጠን ወይም የማይቀጨን መሆን አለመሆኑን ለማወቅ  ቅድመ ጥናት አድርጎ መንቀሳቀስና፣ የደረስነበትን ደረጃ መፈተሽ ይሻል፡፡ ብንሸነፍ ተንሰራርተን መነሳትን፣ ብናሸንፍ  በድላችን አለመኩራራትን ማወቅ የረቀቀ ጥበብ ነው፡፡ “መሬቱ ቢገለበጥ ኩንቲ (የወፍ ቆሎ) እን|ጠግብ ነበር፤ ግን የት ላይ ሆኜ?” እንዳለችው ዝንጀሮ፤ መነሻን፣ መላወሻንና ማረፊያን ታሳቢ አድርጎ፣ አርቆ- አስቦ፣ አገር መምራት የአንድ መሪ ግዴታ ነው። አርኪሜደስ የተባለው የግሪክ ሳይንቲስት፤ “Give me a lever and a place to  stand, and I will move the earth” ብሏል፡፡ (ሽብልቅ አዘጋጁልኝና የምቆምበት ቦታ ስጡኝ፤ ከዚያ መሬትን አንቀሳቅስላችኋለሁ) ብሏል - ይባላል፡፡ “የት ጋ ሆኜ?” ብሎ ራስን መጠየቅ የበሳልና የአስተዋይ ሰው ጥበባዊ አካሄድ ነው፡፡ መቆሚያ ቦታ ካመቻቹና መደላድሉን ከሰሩ በኋላ አነጣጥሮ መተኮስ፣ዒላማንና ዓላማን ማጥበቅን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡
ማናቸውንም ድርድር (negotation) ስናደርግና ስምምነት (compromise) ላይ ልንደርስ ስንሻ፣ ከማን ጋር ነው ድርጊቱን የምንፈጽመው? የሚለውን ሁነኛ ጥያቄ ማንሳት አንድም ለቅድመ- ዝግጅቱ፣አንድም ለወቅታዊ ሂደቱ፣ ሁለትም ለፍሬያማ ውጤቱ ይበጀናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ከማንና ከማን ጋር ነው ስምምነት ላይ የደረስኩት? ለህዝብስ እንደምን ልግለጠው? ብሎ ማጤን ያባት ነው፡፡ አለበለዚያ “ከማይመስልህ ጋር መጋባት፣ አሳ ከዐብይ ጋር መብላት” የሚለው ተረት በእኛ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል!! ከዚህ ይሰውረን!!


Read 13950 times