Saturday, 02 July 2022 17:45

“እያሰባችሁ ነው ወይስ ብቅል እየፈጫችሁ?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


       “--እስቲ ወንበር ይበዛብኛል፣ ሙገሳ ይበዛብኛል፣ ጭብጨባ ይበዛብኛል፣ ገንዘብ ይበዛብኛል፣ ቤቱም መኪናውም ይበዛብኛል..አይነት ነገሮችን ማለት ልመዱ በልልኝ፡፡--”
                  
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰኔ የሚሉት ወር እንዴት ይዟችኋል! አሁንማ አንዱ ወር የሌላኛውን ወር ድንበር የገፋ ይመስል እየተቀላቀሉብን ተቸግረናል። ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ያለማጋነን ብዙዎቻችን የወጪው ወር መጨረሻ ቀናትና የገቢው ወር የመጀመሪያ ቀናት እየተምታቱብን ነው፡፡ (በነገራችን ላይ “ወጪው ወር” የሚለውን ‘ፓሺን’ የሌለበት – ቂ...ቂ...ቂ... – አባባል ትተን “ተሰናባቹ ወር” እንዳንል አሁን እኛ ‘በኦፊሴል’ የምንቀበለውም፣ ‘በኦፊሴል’ የምናሰናብተውም ወር የለም! አሀ...ወጪውም ያው! ገቢውም ያው! እኛ ታዲያ ለውጥ ለሌለው ነገር “ዌልካም” እና “ፌርዌል” እያልን ትንፋሻችንን መጨረስ አለብን እንዴ!)
“ስማ ያንን ነገር ከሰኔ አምስት ሳላሳልፍ እሰጥሀለሁ ብለኸኝ አልነበር እንዴ!”
“እኮ ምን አጣደፈህ! ሰኔ አምስት እሰጥሀለሁ።”
“አንተ ያምሀል እንዴ! ዛሬ እኮ ሰኔ ስምንት ነው፡፡”
“ምን ግንቦት አልቆ!” ቂ...ቂ..ቂ....
እናላችሁ... እንዲህ አይነት መልስ በአቆጣጠር በመደናገርም፣ በአቆጣጠር በማደናገርም ሊባል እንደሚችል ጥቆማ ቢጤ ለመስጠት ያህል ነው። (አንተ ወዳጅ፤ ያ ጊዜ እንኳን ለአሥራ አንድ ወር ነው ምናምን የተቀጠርከው፣ “ላቭ ኢዝ ብላይንድ” ነገር ተሳካ ወይስ አንደኛውን ፋይሉ ጠፋና አረፈው!)
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይሄን ሰሞን ቶሎ ቶሎ መምጣት ጀመርክ መሰለኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን ላድርግ ብለህ ነው! አንተ እንጂ ሌላ ምን መሄጃ አለኝ ብለህ ነው!
አንድዬ፡- ለነገሩ ምን ያህል እንደምናፍቅህ ስላወቅሁ ደስ ብሎኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ነው ወይስ ምድር ላይ የምትሸሸው ነገር ስላለ እኔ ዘንድ የምትመጣው ለመሸሸግ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ልሽሽ ከተባለ ሀገር ጥሎ የሚያስኬድ ስንትና ስንት ጉድ አለ መሰለህ! ስንትና ስንት ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል አይነት ነገር አለ መሰለህ! እንደውም አንድዬ አንዳንድ ጊዜ የሆነ ሲባጎ፣ ወይ ገመድ ነገር አንስቼ.....
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ! ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምነው እንዲህ ተቆጣኸኝ! ምን ባጠፋ ነው?
አንድዬ፡- ሁለተኛ እኔ ዘንድ ስትመጣ ሲባጎ፣ ገመድ ምናምን የሚባል ነገር እንዳታወራልኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አን... አንድዬ፣ እንደው ከብስጭቴ የተነሳ...
አንድዬ፡- በቃ ተናገርኩ፣ ሁለተኛ እኔ ፊት እንዲህ አይነት ቃል ከአፍህ ቢወጣ፣ በሬን ሁሉ ከርችሜ ይከፈትልኛል ብለህ ስትጮህ ውለህ ታድራለህ እንጂ፣ እንኩዋን እንዳሁኑ ወለል አድርጎ የሚከፍትልህ  ገርበብ የሚያደርግልህም አታገኝም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኔ ንዴትነትና ብስጭቴን አቃልላለሁ ብዬ መጥቼ ጭርሱን አንተንም አበሳጨሁህ! ይኸውልህ አንድዬ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን ሁሉ እንዲህ ሆኖልሀል፡፡ ምክክር እንደመፈለግ የራሳችንን ንዴትና ብስጭት ወደሌላ ማስተላለፍ ነው የምንፈልገው፡፡
አንድዬ፡- እንደው አንዳንዴ እኮ አንተና ምድር ያሉ ዘመዶችህ ሁሉ ግርም ትሉኛላችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደ እውነቱ በአሁኑ ጊዜ ራሳችን በገዛ ራሳችን እየተገረምን ነው፡፡
አንድዬ፡- እየው የተወደድከው፣ የተከበርከው፣ አቻ የማይገኝልህ ምስኪኑ ሀበሻ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ እሱ ሁሉ ይበዛብኛል!
አንድዬ፡- ጎሽ፣ ሌሎችም እንዳንተ ይበዛብኛል ማለት ቢለምዱ ጥሩ ነበር፡፡ እንደውም ምስኪኑ ሀበሻ ምድር ስትመለስ ምን ብለህ ንገራቸው መሰለህ... 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ብዬ ልንገራቸው አንድዬ?
አንድዬ፡- እስቲ ወንበር ይበዛብኛል፣ ሙገሳ ይበዛብኛል፣ ጭብጨባ ይበዛብኛል፣ ገንዘብ ይበዛብኛል፣ ቤቱም መኪናውም ይበዛብኛል..አይነት ነገሮችን ማለት ልመዱ በልልኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴት ሆኖ አንድዬ፣ እንዴት ሆኖ፡፡ እንደ እሱ ማለት ብንጀምርማ ምን መሰለህ አንድዬ፣ ማሰብ ጀምረናል ማለት ነው፡፡
አንድዬ፡- ወይንም ያለ ሥራ የተቀመጠውን ዋነኛ የሰውነት ክፍል ሥራ ላይ ማዋል ጀምራችኋል ማለት ነው፡፡ ስማ ይህን ወስደህ ንገርና ደግሞ “ድሮም እንደተውክን እናውቅ ነበር” እያሉ ጣታቸውን ሽቅብ እንዳይወዘውዙብኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደው አትታዘበኝና አሁንም እኮ ብዙዎች እንደዛ እያደረጉ ነው፡፡
አንድዬ፡-እሱን መች አጣሁት! አይ ደግሞ ቡድን ፈጥራችሁ በደቦ እንዳትዘምቱብኝ ብዬ ነው፡፡ ብቻ...ይልቅ አሁን ወደ ሌላ ነገር አትክተተኝ፡፡ ገጽታህ ላይ የሆነ ነገር እየታየኝ ነው፡፡ እያሰብኩ ነው በለኝና ደስ ይበለኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እያሰብኩ ነው፡፡
አንድዬ፡-ጎሽ! ጎሽ! ምስኪኑ ሀበሻ አንዳንዴ እንዲህ አስደስተኝ እንጂ! እኔ እኮ አንዳንዴ አንድታስቡብት የፈጠርኩት አካል ምኑን አበላሽቼ ይሆን አልንቀሳቀስ ያለው እያልኩ እጅ ሰባራነት ይሰማኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- እሺ በቃ አስደስተኸኛል፡፡ በል አሁን ስታስብ የነበረው እኔንም ይመለከት እንደሆነ አካፍለኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ቅድም የምትሸሸው ነገር ያልከው ትዝ ብሎኝ ነው። አንድዬ...አዎ ምን አስዋሸኝ፣ እየሸሸሁም ነው፡፡ አንድዬ፣ ብዙ ነገር እየሸሸሁ ነው፡፡ እያዳመጥክኝ ነው አንድዬ?
አንድዬ፡-አይ ብቅል እየፈጨሁ ነው፡፡ ይልቅ ቀጥል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ በቃ ሰው እየሸሸሁ ነው፡፡ ለምን እንደሁ እንጃ ብቻ ከሰው ባልገናኝ፣ ከሰው ጋር ባልገጥም፣ በምንም ነገር ሰው አጠገብ ባልደርስ የምመኝበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ከሰዉ ሁሉ ሸሽተህ፣ ከሰው ሁሉ ተሸሽገህ ከማን ጋር ልትኖር ነው! ወደድክም ጠላህም ምድረ በዳም ሄድክ፣ ተራራ ወጣህ፣ ሸለቆ ወረድህ፣ ጫካ ገባህ፣ ራስህን የሆነ ቤት ውስጥ ቆለፍክ፣ ከሰው ጋር ነው የምትኖረው፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ፤ እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ውሎ አድሮ ማንንም ሳይሆን አንተኑ ነው የሚጎዳህ! ምስኪኑ ሀበሻ፣ እየሰማኸኝ ነው ወይስ እንደ እኔ ብቅል እየፈጨህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...ኸረ በደንብ እየሰማሁ ነው፡፡ ምን ላድርግ ግን አንድዬ፣ ምን ላድርግ?
አንድዬ፡- እኮ እንዲህ ያስመረሩህን ነገሮች ንገረኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የሰዉ ጠባይ አንድዬ፣ የሰዉ ጠባይ! ማናችን ምን እንደሆንን ግራ የሚገባ ዘመን እኮ ነው፡፡ ጥሩ ምግባር ያለው ሰው ነው ብዬ ስጠጋ፣ ትንሽ ቆይቶ እጅ እግር ያለው ዲያብሎስ  ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ እምነት የሚጣልበት ሰው ነው ብዬ ስጠጋ፣ እኔን ራሴን ከእነ ነፍሴ ከመሸጥ የማይመለስ የለየት ሞላጫ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ አጠፋሁ እንዴ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- እያወራህ አይደል እንዴ! ጥፋትን እዚህ ውስጥ ምን አመጣው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አይ አንድዬ፣ አንተ ፊት ሞላጫ የሚል ቃል መጠቀሜ...
አንድዬ፡- ተው እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ስንት ነገር ስትል ከርመህ ሞላጫ የምትል ቃል አሳሰበችህ! እንደውም መጣህልኝ፣ አየህ አንዱ ትልቁ ችግራችሁ ይኸው ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምኑ አንድዬ?
አንድዬ፡- ስንት ትልቅ፣ ትልቅ ጉዳዮች እያሉ፣ ስንት ጊዜ ልትሰጧቸው የሚገቡ ጉዳዮች እያሉ በፍሬ ከርስኪው ላይ ያዙን ልቀቁን ትላላችሁ፡፡ ስማኝ ምሰኪኑ ሀበሻ፣ አንዳንዴ ሀገራችሁን ምን እንደምታስመስሏት ታውቃለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አላውቅም አንድዬ፣ ምን እናስመስላታለን?
አንድዬ፡- በቃ ልክ የሆነ የቡና አሉባልታ የበዛባት ጎጆ፡፡ እንደው ምስኪኑ ሀበሻ፣ አይደክማችሁም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምኑ አንድዬ?
አንድዬ፡- ወሬ፤ ወሬ አይደክማችሁም!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ወሬ ማውራትማ...
አንድዬ፡- ቆይ፤ ቆየኝማ፡፡ ማውራቱን አይደለም እያልኩህ ያለሁት፡፡ ወሬ መፍጠር አይደክማችሁም! እንደው እንዲህ በየደቂቃው ወሬ መፍጠር እንደምትችሉ የሚጠቅም የሚጠቅመውን ሌላ ነገር ብትፍጥሩ እኮ ይሄኔ የማንም መዘባበቻ አትሆኑም ነበር፡፡ በል፣ ምስኪኑ ሀበሻ፤ ደግሞ ወደ ሌላ ርዕስ ልታስገባኝ ነው፡፡ ምድር ስትመለስ አንድ ጥያቄ አድርስልኝ፡፡ እያሰባችሁ ነው ወይስ ብቅል እየፈጫችሁ? ብሏል በልልኝ፡፡ በል በደህና ግባ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ! አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 748 times