Sunday, 03 July 2022 00:00

ከታንኩ ፊት የሚቆም - ታንኩን ከመንዳት የሚታቀብ እና ታሪኩን የሚቀርጽ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ (ቤተሳይዳ -ምድረ አሜሪካ)
Rate this item
(1 Vote)

የናይጄሪያው ደራሲ ቺኑ አቺቤ ‘There was a Country’ በሚለው መጽሐፉ፣ በናይጄሪያ በኢግቦ የሚነገር አንድ ምሳሌያዊ አባባል ይጠቅሳሉ፡፡ ‘ዝናቡ የቱ ላይ እንደሚመታው ያላወቀ ሰው ገላውን የት እንዳደረቀ ሊናገር አይችልም’ ይላል፤ ምሳሌያዊ አባባሉ። በእኛም ዘንድ የችግሮቻችንን ሥረ-መሰረቱን፣ የተግዳሮታችንን ምንጩን በትክክል ያለማወቅ ችግር አለብን፡፡ ነፍሱን ይማረውና ጋዜጠኛው ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ፤ “ምን ነካን?” የሚል መጣጥፍ ከትቦ ነበር። አሁን ከምንገኝበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመን “ምን ነካን?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ ዝናቡ መቼ መምታት እንደጀመረን እንጠይቅ፡፡
እውነቱን እንነጋገር ካልን እኮ እኛ የጠፋነው - ለዛሬ ውስብስብ ችግርም የተዳረግነው - የምንኖርባትን መሬት - የተወለድንባትን - ያደግንባትን - የጎለመስንባትንና መልሰን ጥርኝ አፈሯ የምንሆንባትን ኢትዮጵያን - በጎሳ አጥረንና ከፋፍለን - የጋራ አገርነቷን ለመካድ የዳዳን ዕለት ነው፡፡
ያልተሰበረውን ሰብሮ እንጠግን የሚሉት ዘይቤ የሀገራችን የፖለቲካ ልማድ ከሆነ ብዙ ጊዜያትን አስቆጥሯል። ለማፍረስ የምንጣደፈውን ያህል ባፈረስነው ምትክ (አዲስ የምንፈጥረው ቀርቶ) አንዲት አጥቅ የሚያራምድ ዕቅድ እንደሌለን ዘመንና ታሪክ ታዝቦናል። ካፈረስን በኋላ ደግሞ ከፍርስራሹ አጠገብ ግራ ተጋብተን ቆመን፣ እርስ በርስ መወነጃጀላችን ይብሳል። መጋደላችንም ይከፋል፡፡ የፖለቲካ ወጋችን መነሻ ኢትዮጵያ የተባለች ቅድስት ሀገርን ውልና ቋጠሮዋን መፍታትና መበጠስ እንደሆነም መናገር የአደባባዩን በጆሮ ነው። ከሁሉም የሚከፋው ግን የቆምንበትን ምድር - ኢትዮጵያን - ክደን የተያያዝነው የእውር ድንብር ጉዟችን ነው፡፡ ዛሬ ፖለቲካ ብለን የምንደሰኩረው ከተዘፈቅንበት አሳፋሪ ድህነትና ኋላ ቀርነት የሚያወጣንን ሳይሆን እርስ በርስ የሚያጠፋፋንን የዘረኝነት መርዝ ነው፤ለዓመታት የሰለጠንበት ብቸኛ ሙያችን ይኸው ነው፡፡
 በአሁኑ ወቅት አገራችን እንድታቋርጠው የምናስገድዳት ወንዝ መመለሻ የሌለው እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ይሄ ዘመንና ትወልድ ያመጣው የወንዝ ማቋረጥ፣ የቄሳርን ሩቢኮንን የማቋረጥ አይነት ይመስላል። የሮማው ጁሊያስ ቄሳር ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ወደ ኋላ ላይመለስ ወታደሮቹን ይዞ ወንዙን ያቋረጠበት ታሪካዊ ምሳሌ ነው። መመለሻ የሌለው ወንዝ። አገራችንም ተመሳሳይ እጣፈንታ እንዳይገጥማት ያሰጋታል፡፡ በቅርቡ በወለጋ በዐማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከፊታችን የሚጠብቀንን አስፈሪ መንገድ አመልካች ነው፡፡   
ብዙ የሀገሬ ሰዎች አስጠንቅቀዋል። ጎምቱ የሀገር ህሊና የሚባሉት ዜጎች ተዉ ሲሉ ከርመዋል፡፡ ማስጠንቀቂያቸው ግን ጆሮ አላገኘም፡፡ ተዉ እያሉ በአደባባይ የጮኹ ሰሚ አጥተው፣ በምድረ በዳ እንደጮኸው ነቢይ ሆነው ብቻቸውን ቀርተዋል። ይባስ ብሎም ተወግዘዋል። ከግራም ከቀኝም ተጎትተው ተጥለዋል፡፡ ተንቀዋል። የጮኹትም ጩኸት - “ጮኸን ጮኸን እንዳልጮህን ሆንን” እንዳለው ቅዱስ መጽሐፍ አይነት ነው ተምሳሌቱ፡፡
በግሪክ አድባሬ ተረት ወይም ሚቶሎጂ ውስጥ ካሳንድራ የምትባል የትሮይ ንግሥት ነበረች። የአፖሎ አምላክ ወደፊት የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ የማወቅ ችሎታ ሰጥቷታል። ይሁንና በከተማይቱ የሚመጣውን ጥፋትና ምጽአት አይታ ብትናገርም - ትንቢቷን ለሰው ጆሮ ብታደርስም፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የሰሙትን ከልቡናቸው እንዳይከቱት ወይም ከቁብ እንዳይቆጥሩት በዚያው አምላክ ተረግማለች። እና እሷ ስትጮህ እሷ ስትናገር - ሰሚ አልባ ሆና በስተመጨረሻ የተነበየችው፣ ይመጣል ያለችው ምጽአት እርሷንም ጭምር ሰለባ አደረጋት። በእኛም ዘንድ ሁልጊዜም ሀገር መጻኢው እድሏ እንዳይከፋ፣ “ያልተሰበረን አትስብሩ፤ የተረጋጋውን አትናጡ” የሚሉና የሚያስጠነቅቁ ጠፍተው አያውቁም፡፡ ችግሩ ግንደ እንደ ካሳንድራ የሚሰማቸው የለም። እርግጥ ነው በመካከላችን መደማመጥ ጠፍቷል። የመጣውና የሚመጣው አደጋ ግን ሁላችንም ዘንድ ይደርሳል፡፡
“ተንኮለኛ ገደል በሬ ያሳልፋል - ዝንጀሮን
ይጠልፋል -
ጅል ያመጣው ነገር ለሁሉም ይተርፋል”
እንደሚባለው ያለ ነው። ከቆምንበት የጋራ መርከብ አንዱ ወለሉን ቢሸነቁርና ውሃ ቢገባበት - ብቻውን ተለይቶ የሚሰጥም የለም። ሁላችንም ነን ሰጣሚዎቹ።
እርግጥ ነው አሁን የምንገኘው መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ የጎሳ አደረጃጀትንና ክልልተኝነትን በፊታውራሪነት ተግብረውና በሀገሪቱ አዋቅረው የነበሩት ከስልጣኑ በከፊል ገሸሽ ተደርገው፣ ከእነርሱ ጓዳ ውስጥ የተገኙ የፖለቲካ መዘውሩን ከጨበጡ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የታሪክ ሂደት ሆኖ ጉዟችን ተጀምሯል፡፡
የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሚካኼል ጎርባቾቭን አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤
“ፕሬስትሮይካ ያሉት መንገድ ሶቪየት ህብረትን ለማደስ ያለው እድል ምን ያህል ነው?”
ጎርባቾቭም መለሱ፤ “ምን ምርጫ አለን? ከውቅያኖስ መሃል የተጣለ ሰው ወደዚህም ይሁን ወደዚያኛው ጫፍ ለመድረስ ከመዋኘት ውጭ ምን አማራጭ አለው?”
እኛም እየቋረጥነው ያለው ወንዝ ወደ ኋላ መመለሻ የሌለው ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም እየዋኘን ራሳችንን ለማዳን ከመፍገምገም ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡
ምርጫችንም ይሁን አይሁን ሽግግር ያልነው አሻግሮን እንደሆነ - በዚህ ሽግግር ወደ ላይ ወጥተን ከመጀመሪያው ጉብታ ስንደርስ ያሉትን ፈተናዎች ለማለፍ የሚያስችል ዘዬና ዘዴ ኖሮን እንደሆነ እንፈተናለን፡፡ ከሁሉም በላይ የሽግግሩ ካፒቴን ወደየት እንደሚቀዝፍ - አሻግሮ የሚያየው - አልሞ የተነሳው ምንና ስለምን እንደሆነ እንጠይቃለን፡፡ በየአንጓውና በየመታጠፊያው ለሚገጥመው ተግዳሮት በሚሰጠው ምላሽም ይፈተናል፡፡ ይለካል። ዋኝተን የምንወጣበት ዳርቻ - ቀዝፍን የምንደርስበት ኬላ የት እንደሆነ እናሰላ - እናውቅ ዘንድ እንሻለን፡፡ ቃለ ነሲቡን ብቻ ሰምተን - የተዋቡ ቃላቱን ብቻ አድምጠን፣ ባሻው ይዞን ሲሄድ ይሁን ብለን፣ እግራችንን አንጥፈን፣ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም፡፡
የመጣንበት መንገድ ጎፃ ጎጽ ነው። አሁንም ማንገጫገጩን አልተወም፡፡ ‘የለውጥ ባህርይ’ ነው የተባለውንም ተቀብለን ብዙ ቆየን፡፡ አቅጣጫችንን ወደየት - የሚደረገውን ‘ለማን ጥቅም’ እያልን በመንገዳችን እንጠይቃለን። ስልጣን ላይ ለመውጣት በለስ የቀናቸው - አጋጣሚው የተገጣጠመላቸው - ዝመቱ ሲሉ ለማን ጥቅም? ተነሱ ብለው ሲጠሩን - ለምን ጥቅም? ብንል አይፈረድብንም። ጠመንጃቸው ሆነን ያሻችሁን ቀልህ ተኩሱብን ማለታችን - አንዳንዴ ሲያስከዳን አይተናል፡፡ አመኔታችን ሲሰበር ታዝበናል፡፡
አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ከመምጣቱ አስቀድሞ ነው አሉ - ኢህአዴግ ውስጥ በነበረ  ግምገማ ላይ አንድ ጥያቄ ተነሳ፡፡ አንዱ ተናጋሪ፤ “ኢህአዴግ ይህን ሁሉ ሥራ እየሠራ ለምንድን ነው የሚጠላው? ለምን ምንም ያልሠሩ ተቃዋሚዎች ይወደዳሉ?” ሲል ጠየቀና ራሱ መልስ ሰጠ፤ - “ኢህአዴግ - ‘ኢትዮጵያ’! ኢትዮጵያ’! ስለማይልና ስለ ኢትዮጵያ ስለማይናገር ነው” በማለት። በእርግጥም  የፖለቲካ ሰዎችና ድርጅቶች ሕዝብ ሊሰማ የሚፈልገውን በማሰማት ብቻ - አደንዝዘውና አፍዘው ለጊዜው ሊያወናብዱት፤ አመኔታውንም ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ቆይቶ ግን - ተግባር መለኪያ ሲሆን የታመነው ቃሉ ይሰፈራል፣ ይመዘናልም፡፡ ቃሉን ቀርጥፎ እንደበላ - ቃሉን እንደጠበቀ ሕዝብ የሚመሰክርበት ጊዜም አለ፡፡
ያለፍናቸውም ሆኑ እያለፍናቸው ያሉት ቅራኔዎችና ግጭቶች በተወሰኑ ጥቅመኞች መካከል የሚደረጉ መጓተቶች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜም፣ ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለሕዝብ አንዳችም ፋይዳ እንደሌለው ተሞክሯችን ምስክር ነው፡፡ ንጹሀን ዜጎች ሰለባ እየሆኑ - ግን ‘የመጣው ግርግርና ግድያ’ ለእናንተ የመጣ ነው የሚል ዜማ እያሰሙ ነው የኖሩት። በሀገራችን ስልጣን የሚቆናጠጡ ሀይሎች፣ የዛሬውንም ጨምሮ - የደረሰውን ችግር በግልጽ የመናገርና ሕዝቡን የማሳወቅ - እውነቱን ነግረውን ከጎናቸው የማሳለፍ ችግር አለባቸው። ጥፋቶቻቸውንና ስህተቶቻቸውን አምነው - ‘አጥፍተናል’ የሚል ራስን ተጠያቂ የማድረግ ብቃትም አሳይተውን አያውቁም። ይልቁንም የሁሉ ጥፋትና ስህተት ተጠያቂ የሚያደርጉትን አካል ወይም ቡድን፣ በዘመቻ በማውገዝ፣ ወደ ውጭ እንድንጠቁም ሊያደርጉን ይሞክራሉ። የእነዚህ ገዢዎቻችን ችግር የተናገርነውን ሁሉ ያለምንም ማንገራገር የሚቀበል ሕዝብ አለን ብለው ማመናቸው ወይም ማሰባቸው ነው፡፡ እውነቱ ግን ስህተትና ጥፋትን የሚደብቅ አገዛዝ - ደካማ መሆኑን ሕዝብ በውል ይረዳል፡፡
ብዙዎች በተደጋጋሚ የገለጹት ሀሳብ አለ፡፡ የመንግሥት ዋነኛና ቀዳሚ ሀላፊነት የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ዛሬ ግን የህዝብ ደህንነቱ ተናግቷል፡፡ የዜጎች ሕይወት በጠራራ ጸሀይ ይቀጠፋል። ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ‘እርምጃ ወሰድን’ የሚል መግለጫ ወይም ውግዘት ማውጣት ብቻውን ግን የሕዝብን ደህንነት አያረጋግጥም፡፡ አላረጋገጠለትም፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ህይወት በሚሰጠው ዋጋ ይመዘናል፡፡ ስንሞት ፊቱን የሚያዞርና ወሬ የሚቀይርልን እንዲሆን አንሻም፡፡
በዓለማችን የምንጠቅሳቸው ታሪካዊ መሪዎች፣ ከወገናቸው ጋር አብረው ቆመው ጥቃቱን ጥቃታቸው አድርገው - ለቅሶውን አልቅሰው የሚገኙ ናቸው፡፡ እውነተኛ መሪዎች እውነቱን ነግረውንና የወደቅንበትን ዋሻ አሳይተውን የመውጫውን መላ አብረውን የሚመክሩ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ የዜጎቻቸው ደህንነት ክፉኛ የሚያስጨንቃቸው፡፡     
በዚህ ጊዜ ታዲያ ሰሚም ኖረ አልኖረ፣ ተቀባይም ተገኘ አልተገኘ፤ “ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው” የሚል ደፋርም ያስፈልጋል። አንድ ታሪክ ልንገራችሁ። ከሠላሳ ዓመት በፊት የሆነ ነው፡፡ አንድ ተራ ሰው ነው። በእኛ ሀገር አጠራር ከአፍ የወደቀ  ጥሬ አይነት። በእጁ ከገበያ ይዞት የመጣው የላስቲክ ከረጢት አለ። በከተማው ዋና አውራ ጎዳና እየተጓዘ ነው። ስም አልባ የማይታወቅ ሰው። ከዚያ ሕዝብ ከሚተራመስበት ስፍራ ያ ሰው፣ በታሪክ በቁርጠኝነት እምቢኝ በማለት ምሳሌ ሆነ። ያ ሰው ከሰዎቹ መንጋ ተነጥሎ ከታንኩ ፊት ለፊት ቆመ። በቻይናው ቲነመን አደባባይ። ያንን ወቅት አስቡት። በዚያች እለት በዚያች ቅጽበት ከዚያ አውራ ጎዳና - ያ ሰው ምን ገፍቶት ምን አስቆመው? ያ ሰው ለዘለዓም የሚጠቀሰው ታንክ መርመስመሱን በቻይና ስላቆመ አይደለም። ግን አንድ ሰው ብዙዎችን ከእንቅልፋቸው አነቃ።
ካሸለቡበት ቀሰቀሰ። ታንኩን ያሽከረክር የነበረውንም አስቡት። ከቶ ስለምን ታንኩን ለማቆም ተገደደ? ያንዱ ሰው ቁርጠኝነት - የዚያ ሰው ከፊቱ መቆም ገታውን? የታንኩ አሽከርካሪ ወታደር የተልዕኮውን አላማ ከጥርጣሬ ከቶበትስ ይሆን? ሁለቱም አለፉ። የእነርሱን ምስል ያነሳው ፎቶግራፍ አንሺውስ? እነዚህ ሦስቱም ግለሰቦች በየራሳቸው ዛሬ የምንኖርበትን - ዛሬም የምንናገረውን ትርጉም እንድንጠይቅም ያደርጋሉ። ትውልድ የሚያሻው ከታንኩ ፊት የሚቆም - ታንኩን ከመንዳት የሚታቀብ - እና ታሪኩን የሚቀርጽ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 13507 times