Saturday, 02 July 2022 17:58

“የመጽሐፍ ግምገማውን” እንገምግም!

Written by  ከተስፋዬ ሮበሌ (ዶክተር)
Rate this item
(7 votes)

 “--ዘመናዊው ሰው (የከተሜው ነዋሪ)፣ ደስታ ተክለ ወልድ፣ “ኸ”ን በሚጠቀሙበት መልክ ስለማይጠቀም ነው፡፡ በአጠቃላይ ጥያቄው የድምፀት ውክልና እንጂ፣ የሞክሼ ሆህያት ጒዳይ አይደለምና ወቀሳዎ መስመር ስቶአል፡፡ ስለዚህ ወቀሳዎ መጽሐፉ ማብራሪያ ባላቀረበለት፣ ነገር ግን እርስዎ ነው ብለው በተሳሳተ መንገድ ታሳቢ ባደረጉት ጒዳይ ላይ የቀረበ ነው፡፡ በአጠቃላይ እኔ ሞክሼ ሆህያት ይጠበቁ አልሁ እንጂ፣ በድምፀት ውክልና ጒዳይ ላይ አስተያየት አልሰጠሁም፡፡--”
        
             “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ፣ ግንቦት 20 ቀን፤ 2014 ዓ.ም፣ “ጥበብ” በሚለው ዐምዱ፣ በቅርቡ ታትሞ ለንባብ የቀረበውን— “ሆህያተ ጥበብ—ለጸሓፍያን፣ ለተርጓምያንና ለአርታዕያን” መጽሐፌን፣ በሚከተለው ርእስ ለግምገማ ዐቅርቦታል— “የመጽሐፍ ምልከታ—‘ሆህያተ ጥበብ’”፡፡
ሐያሲው ናይእግዚ ኅሩይ፣ የተባሉ ግለሰብ እንደ ሆኑ ተጠቅሶአል፡፡ ይህ ጽሑፍ የዚህን ግምገማ ቋንቋዊ፣ ምክንዮአዊና ፍትሓዊ መሠረት ይመረምራል፡፡ “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና” ሐያሲው መጽሐፌን አንብበው አስተያየታቸውን ስላጋሩ፣ ለቸርነታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አቶ ናይእግዚ ኅሩይ፣ ዕድሜና ጤና ይስጥዎ!
የአገራችን ሰው፣ “ፍርድ ለእግዚአብሔር ነው” እንደሚለው፣ አንባቢም የግራ ቀኙን ሙግት  አጢኖ፣ ሚዛናዊ ብያኔውን ይስጥ!       
ገምጋሚው መጽሐፉ፣ “አንፀባራቂ እንዳይኾን ያጠለሹ” የሚሏቸውን፣ “ዐሥር ስሕተቶች”1 ጠቅሰዋል፡፡ እርሳቸው ባስቀመጡት ቅደም ተከተል፣ ግምገማቸውን እንገመግመዋለን፡፡         
ሒስ አንድ:-
ሐያሲው፣ “የመጽሐፉ ችግር ከአርእስቱ ይጀምራል” ይላሉ፡፡ “ችግር” የሚሉትን ቀዳማይ ሕጸጽ ሲያብራሩ የመጽሐፉ ርእስ፣ “ሆህያተ ጥበብ” መባል አልነበረበትም፤ “ጥበበ ሆህያት” እንጂ ይሉናል፡፡ “ርግጠኛ ነኝ ደራሲው ማለት የፈለጉት፣ ‘የሆህያት [አጻጻፍ] ጥበብ’ ነው”። “ሆህያተ ጥበብ” መባሉ የመጽሐፉን ዐሳብ የሚወክል አይደለም፡፡ በዚህም የመጽሐፉ አሰያየም፣ ተሳስቶአል ባይ ናቸው፡፡ በርግጥ የአርእስት አሰያየሙ ስሕተት ነው?  በጭራሽ ስሕተት አይደለም!
ልጄ አትናቴዎስ ከቀናት በፊት፣ “ትክክለኛው የዐማርኛ ገለጻ፣ ‘እመጣለሁ’ ነው ወይስ፣ ‘እየመጣሁ ነው’ የሚለው ነው?” ሲል ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ “በሰዋስው አወቃቀር፣ ሁለቱም ዐረፍተ ነገሮች ትክክል ናቸው፡፡ ‘ማለት የፈለግኸው ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ግን፣ ‘የትኛው ገለጻ ተገቢ ነው?’ የሚለውን ምላሽ ይወስናል” አልሁ፡፡ ልክ እንደዚሁ፣ በሰዋስው አወቃቀር፣ “ሆህያተ ጥበብ” እንዲሁም፣ “ጥበበ ሆህያት” ማለት ይቻላል፡፡ ቃላቱን በሁለቱም መንገድ ማዛረፍ አንዳችም ሰዋስዋዊ ስሕተት የለበትም። ከአማራጭ አዘራረፎች መኻል፣ የትኛውን እንከተል የሚለውን አካሄድ የሚወስነው ግን፣ “መባል የተፈለገው (የታሰበው) ምንድን ነው?” እንዲሁም፣ “አጽንዖት እንዲያርፍበት የታሰበው ቃል የቱ ነው?” በሚሉ ሁለት መጠይቆች፣ የአዘራረፉ ዕጣ ፈንታ ይወሰናል፡፡ ገምጋሚው ሒሳቸውን ለማጽደቅ፣ “ርግጠኛ ነኝ ደራሲው ማለት የፈለጉት፣ ‘የሆህያት [አጻጻፍ] ጥበብ’ ነው” የሚል ዐረፍተ ነገር አስገብተዋል፡፡ በርግጥ፣ “ርግጠኛ” ናቸውን? እንግዲያው ሰዋስዋዊ ዐዋጁን አስቃኝቼ፣ ሙግቱን አስከትላለሁ፡፡    
ቃላትን እያዛረፉ መጠቀም በግእዝ ሰዋስው የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ ዐማርኛም ከግእዝ የወሰዳቸውን (የተዋሳቸውን) ቃላት፣ በዚህ መልክ እያዛረፈ ይገለገላል፡፡ አስረጅ:— “አምላከ ሰማይ” ማለት በቊሙ፣ “የሰማይ አምላክ” ማለት ነው፡፡ “እጀ ሰብዕ” ማለት በቊሙ፣ “የሰው እጅ” ማለት ነው፡፡ “ገብረ ክርስቶስ” ማለት በቊሙ፣ “የክርስቶስ ሥራ” ማለት ነው። በእነዚህ አስረጆች መሠረት፣ “ሰማይ”፣ “ሰብዕ” እና “ክርስቶስ” የሚሉት ቃላት፣ “ዘርፍ” የሚባሉ ሲሆን፣ “አምላክ”፣ “እጅ” እና “ግብር” ደግሞ፣ “ባለቤት” የሚል፣ ሰዋስዋዊ ስያሜ ተሰጥቶአቸዋል፡፡   
በዚህ አግባብ፣ ዘርፉ ቅጽል፣ ባለቤቱ ደግሞ ስም ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አጽንዖት ልንሰጠው የምንፈልገውን ቃል ባለቤት፣ ከአጽንዖት ልናሸሸው የምንፈልገውን ቃል ዘርፍ አድርገን የምንቀምርበት አግባብ አለ። ይህ ደግሞ የአዘራረፍ ሁለተኛ ሕግ ነው፡፡ “ማዛረፍ ትርጒም ብቻ ሳይሆን፣ አጽንዖትንም ይከሥታል (ይጠቅሳል)” የሚባለው በዚህ አግባብ ነው፡፡ አስረጅ ላቅርብ:— “እደ ጥበብ” ስንል በቊሙ፣ “የጥበብ እጅ” ወይም “ጥበብ የተካነ (የለመደ) እጅ” ማለታችን ነው (በግእዝ “እድ” እጅ ነው)። ይህ፣ “ጥበብ” ለሚለው ቃል ትኲረት እንደ ተሰጠ ልብ ይሏል፡፡ “ጥበበ እድ” ስንል ግን በቊሙ፣ “የእጅ ጥበብ” ወይም፣ “በእጅ የሚሠራ (የሚከወን) ጥበብ” ማለታችን ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ትልቅ ቊም ነገር አለ፤ ይኸውም፣ “እደ ጥበብ” እንዲሁም “ጥበበ እድ” የሚሉት ሁለት የአዘራረፍ አካሄዶች፣ ትልቅ የሆነ የትርጒም ለውጥ የላቸውም፡፡ የመጀመሪያው “እድ” (እጅ) ላይ ትኲረት ሲያደርግ፣ ሁለተኛው ደግሞ “ጥበብ” ላይ ትኲረት አድርጓል፡፡ ይህን በውል ያላስተዋሉ አንዳንድ ሐያስያን፣ “‘ጥበበ እድ’ እንጂ፣ ‘እደ ጥበብ’ መባል የለበትም ነበር” የሚል ትችት ሲያቀርቡ ተደምጦአል፡፡ አበው፣ “ጥበበ እድ ትምህርት ቤት” ከሚለው ይልቅ፣ “እደ ጥበብ ትምህርት ቤት” ብለው ማዛረፋቸው፣ ስሕተት እንደ ሆነ የሚያስቡ አሉ። የነገሩን ምስጢር በውል የመረመረ (ጥራዝ ነጠቅነትን በጥራዝ ጠለቅነት የገራ)፣ ከዚህ ዐይነቱ አስተያየት ይቈጠባል፡፡ እንግዲያው ስለ አዘራረፍ ሥርዐት ያሉትን ሁለት መሠረታውያን ሕጎች በዚህ መልክ ከቃኘን፣ ሙግቱን ወደ ማስተንተን እንዝለቅ፡፡     
እንግዲያው መጽሐፉ፣ “ሆህያተ ጥበብ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ትኲረት ሊያደርግበት የፈለገውስ ነጥብ ምንድን ነው? የሚለውን ጒዳይ መመርመር ወሳኝ ነው፡፡ “ሆህያተ ጥበብ” የሚለውን የግእዝ አዘራረፍ፣ በዐማርኛው የዘርፍ አያያዥ መስተዋድድ ስናዋቅረው፣ “የጥበብ ሆህያት” ማለት ነው፡፡ “ጥበበ ሆህያት” ማለት ደግሞ፣ “የሆህያት ጥበብ” ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሆህያቱ በጥበብ መቀረጻቸውን፣ እንደ ትርፍ አንጀት ተቈርጠው ይጣሉ የሚለው ዐሳብ ስሕተት መሆኑን፣ በመጽሐፉ የቀረበውን ዐቢይ ጭብጥና ሙግት የሚያጸና ቅመራ ነው (ከገጽ 29 እስክ 45 ያለውን ክፍል ይመለከቷል)፤ ሁለተኛው አወቃቀር ግን፣ ሐያሲው በጽሑፋቸው በትክክል እንዳብራሩት (እንደ ገለጹት)፣ “የሆህያት [አጻጻፍ] ጥበብ” ማለት ነው፡፡ ይህ የእሳቸው አወቃቀር በአብዛኛው፣ የጽሑፍ አጻጻፍ (አጣጣል) ጥበብ ፈረንጆቹ፣ “penmanship” (the art or skill of writing by hand) የሚሉትን ዐሳብ የሚዳበል ነው፡፡ የእኔ መጽሐፍ፣ ሞክሼ ሆህያትን መጠበቅ የሚያስፈልገን ለምን እንደ ሆነ ሙግት የሚያቀርብ፣ ሞክሼ ሆህያትን እንዴት እንጠብቃለን ለሚለው ደግሞ አቅጣጫ የሚሰጥ፣ ሙግትንና ትምህርትን አዛንቈ የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው፡፡   
በዐጭሩ፣ መጽሐፉ ዐላማ አድርጎ የተነሣለትን ጭብጥና አጽንዖት እንዲሁም በመጽሐፉ የቀረበውን ሰፊ ሐተታ በውል ሳይመረምሩ፣ “ርግጠኛ ነኝ ጸሓፊው ለማለት የፈለገው” እንደዚህ ነው በሚል፣ ሙግትን ለማጽናት ብቻ መጽሐፉ ትኲረት ያላደረገበትን ዐሳብ ለማጽናት መሞከር ስሕተት ነው፡፡ የሙግቱ ድምዳሜ እነሆ:- የመጽሐፉን ጭብጥ የሚያጸናው፣ “ሆህያተ ጥበብ” እንጂ፣ “ጥበበ ሆህያት” አይደለም፡፡ ግልጽ ነው?
ሒስ ሁለት:-
ሐያሲው የመጽሐፉ ሁለተኛ ችግር ብለው ያቀረቡት፣ “የፊደል ግድፈትና ልውጠት” በመጽሐፉ ውስጥ፣ “በብዛት” መታየቱን ነው። እውነታቸውን ነው፣ በኅትመት ውጤቶች ውስጥ ስሕተትና ግድፈት ማየት ያታክታል፡፡ ቢቻል ጽሑፍ ሁሉ ጥልል ጥንፍፍ ባለ መልክ ተዘጋጅቶ ቢታተም፣ ትልቅ መታደል ነው፡፡ ይህን ተምኔት ለማሳካት፣ ወዳጆቼ በአርትዖቱ ሥራ ደቦ እንዲገቡ አድርጌአለሁ፡፡ በዚህም የችግሩ ብዛትና ስፋት በብዙ እንደ ቀነሰ አያጠራጥርም፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ስሕተት መታየቱ ግን አልቀረም። ፍጽምና የአካሄድ አቅጣጫ እንጂ፣ የሰብአውያን ሥራ መዳረሻ አይደለምና፡፡ በሥራዎቹ ሁሉ፣ “ፍጹም” የሚለውን ቅጽል በሙላት መጐናጸፍ የሚችለው፣ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ስሕተት፣ “በብዛት” መታየቱ፣ “ጽሑፍ ሽንፍላን እንደ ማጠብ ነው” የሚለውን የአበው አነጋገር፣ በአዎንታ የሚጠቅስ ነው፡፡ ሐያሲው፣ “በብዛት” ሲሉ ግን፣ አንጻራዊ ምልከታቸውን እንጂ፣ ስሕተትን፣ “ብዙ” እና “ጥቂት” ብሎ ለመፈረጅ የሚያበቃ፣ ነባራዊ መስፈርት ኖሮአቸው እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ግላዊ ዐዋጃቸውን ቀኖና (ነባራዊ መስፈሪያ) አድርገው ማቅረባቸው ግን ስሕተት ነው፡፡            
ገምጋሚው፣ “ስለ ቋንቋ ሊያውም ስለ ፊደል የሚያወራ መጽሐፍ ከአንድና ኹለት በላይ የትየባ ስሕተት ሊገኝበት ባልተገባ ነበር…ፍጽምናን ባልጠብቅም፣ ስሕተታቸው ግን በዐይነትም በቊጥርም በዛ” ሲሉ አማርረዋል፡፡ ስሕተት መታየቱ ዕዳ እንጂ፣ በረከት እንዳልሆነ ተስማምቻለሁ፡፡ ነገር ግን፣ “ከአንድና ኹለት በላይ የትየባ ስሕተት ሊገኝበት ባልተገባ ነበር” የሚለው ዐዋጃቸው፣ ከየት እንደ መጣ ወይም የትኛው የአርትዖት ቢሮ እንደ ቀነነው እንዲሁም እኛ በምን አግባብ ልንቀበለው እንደምንገደድ ቢነግሩን ጥሩ ነው፡፡   
ሐያሲው፣ መጽሐፉ እንዲገመገምበት ያስቀመጡት ይህ የፍጽምና ሕግ (ምንጩ በውል የማይታወቅ)፣ ለእርሳቸውም ጽሑፍ የቀኖና ዘንግ ሆኖ እንዲዳኛቸው መስማማት ይኖርባቸዋል፡፡ እኔ እንድተዳደርበት የተሰጠኝ ሕግ፣ ለእርሳቸው ሕግ ከመሆን ሊለዝብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የእኔ ጽሑፍ፣ “ስለ ቋንቋ ሊያውም ስለ ፊደል የሚያወራ መጽሐፍ” እንደ ሆነው ሁሉ፣ የእርሳቸውም መጣጥፍ፣ “በቋንቋና በፊደል ላይ” የተጻፈን መጽሐፍ የሚገመግም፣ የአርታዒ (የሐያሲ) ጽሑፍ ነውና (እንዲያውም ሕጉ በእርሳቸው ላይ ይበልጥ መክረር ያለበት ይመስላል)2፡፡ ምፀቱ ግን የእርሳቸውም ጽሑፍ፣ በእኔ መጽሐፍ ላይ ታይተዋል የተባሉት ሕጸጾች ሁሉ ታጭቀው መገኘታቸው ነው፡፡ ጥቂት አስረጅ እነሆ:— “እሻለሁ” ለማለት፣ “ሻለኹ”፤ “እንደ ተጻፈው” ለማለት፣ “እንደተጻፈው”፤ “ጐን” ለማለት “ጎን”፤ “እንደ ተማሩ” ለማለት፣ “እንደተማሩ”፤ “ቈርቈሮ” ለማለት፣ “ቆርቆሮ”፤ “በጒልህ” ለማለት “በጒልኅ”፤ “እንደ መረጡ” ለማለት፣ “እንደመረጡ”፤ “ዐሳብ” ለማለት “አሳብ”፤ “ምንድን ነው” ለማለት፣ “ምንድነው” ወዘተ ወዘተ፡፡ በአንድ መጣጥፍ ይህን ሁሉ ስሕተት ተሸክሞ፣ መጽሐፍን ያህል ሰፊ ሥራ፣ “ከአንድና ኹለት በላይ የትየባ ስሕተት ሊገኝበት ባልተገባ ነበር” የሚለው ሕግ፣ ልግጫ እንጂ ሕግ ሊሆን አይችልም፡፡
ወንድም ዓለም እርስዎ ሊያከብሩት ያልቻሉትን ሕግ፣ እኛ እንድናከብረው መጠበቅ ያለብዎት አይመስለኝም፡፡ ስሕተቱ ይስተካከል የሚሉ ከሆነ ግን፣ ወቀሳዎን ከሙሉ ልብ ተቀብያለሁ፡፡ በቀጣዩ ዕትም፣ ዐቅም በፈቀደ ሁሉ ተስተካክሎ እንዲታተም ይደረጋል፡፡ ሺሕ ጊዜ ተደጋግሞ ቢነበብ (ቢታረም) እንኳ፣ “ከአንድና ኹለት በላይ የትየባ ስሕተት ሊገኝበት ባልተገባ ነበር” የሚሉት ሕግ፣ ሊከበር የሚችል አይመስለኝም (ግምገማዎን እየገመገመ ያለውም ይህም ጽሑፍ፣ ብዙ ስሕተት እንዳለበት እሙን ነው)፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እርስዎም ሆኑ እኔ፣ በሞክሼ ሆህያትም ሆነ በሰዋስው ላይ ያለን ዕውቀት፣ “ከአንድና ኹለት በላይ” እንደ ሆነ እገምታለሁ። ስለዚህ የጽሑፍና የሞክሼ ሆህያቱን ስሕተት ብናርም እንኳ፣ የሰዋስው ዝርክርኩ በቶሎ የሚለቀን አይመስልም፡፡ በዐጭሩ የእኔ 205 ገጽ መጽሐፍም ሆነ፣ የእርስዎ 7 ገጽ መጣጥፍ፣ ለፍጽምና አብነት ሊሆን አልቻለም3፡፡ ቊም ነገሩ ልብዎ እንደ ደረሰ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡    
ሒስ ሦስት:-
“ሕጋዊ ስሞችን በሕገ ወጥነት ማስተካከል” የሚሉት ትችት ደግሞ ሦስተኛው ነው፡፡ ሰዎች እንዲሁም ተቋማት እንጠራበት የሚሉትን የሞክሼ ሆህያት አካሄድ መለወጥ ስሕተት ከመሆኑም በላይ፣ “በመደበኛው የትምህርት ዓለም እንዲኽ ያለው ጒዳይ ‘F’ እንደሚያሰጥ እንኳን ዶ/ር ተስፋዬ እኔም ዐውቃለኹ” የሚል ወቀሳ ቀርቦአል፡፡  
“ሀዲስ አለማየሁ” የሚለው መጠሪያ የግለሰቡ ሕጋዊ ስም መሆኑ እሙን ነው፡፡ “ስሙ ሕጋዊ ድጋፍና ጥበቃ አለው” ማለት፣ “ሞክሼ ሆህያቱም ሕጋዊ ድጋፍ ተሰጥቶአቸዋል” ማለት ነው እንዴ? የሕጉን ማዕቀፍ ከዐቅሙ በላይ የለጠጡት አይመስልዎትም? እሺ ሆህያቱ ሕጋዊ ድጋፍ አላቸው ብለን እናስብ፤ ግን የግለሰቡን ስም ለመጻፍ፣ በሕግ የተመዘገቡት ሆህያት የትኞቹ ይሆኑ? ለምሳሌ:— “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ፣ “ሀዲስ ዓለማየሁ” ብሎ ሲጽፍ፣ “ወንጀለኛው ዳኛ” እና “የልምዣት” ደግሞ፣ “ሀዲስ አለማየሁ” ብለው ጽፈዋል፡፡ የሕይወት ታሪካቸውን የሚተርከው መጽሐፍ ደግሞ፣ “ሐዲስ ዓለማየሁ የዘመናችን ቋሚ ምስክር” ሲል ጽፎአል፡፡ እንግዲያው ሕግ የመዘገበው፣ ጥበቃም የሚያደርግለት የቱን ይሆን? እርስዎ ይከበሩ እያሉ የሚጮኹላቸው ሞክሼ ሆህያት የትኞቹ ናቸው? “ሀዲስ አለማየሁ” የሚለውን ሕጋዊ ስያሜ፣ “ዐዲስ ዓለማየሁ” ብሎ ሞክሼ ሆህያቱን ማስተካከል፣ “‘እኔ ዐውቅልኻለኹ’ ማለትም አይደል?” ሲሉ ወቃሻዊ መጠይቅ ማቅረብዎ፣ የወቀሳዎ መሠረት ምን ይሆን?
በርግጥ፣ “አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ” የሚለውን፣ “ዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ” ብሎ ሞክሼ ሆህያቱን ማረም፣ “F” ያስሰጣልን? አንድ ሰው፣ “ተስፋዬ” የሚለውን ስም፣ “ተሥፋዬ” ብሎ ሕጋዊ ሰነድ ላይ ቢጽፍ፣ “በሕግ የተመዘገበን ስም አሳስተሃል” ተብሎ በሕግ ሊያስጠይቅ ወይም ሐያሲው እንደሚሉት በትምህርት ተቋማት ውስጥ “F” ሊያከናንብ ይችላልን? ሞክሼ ሆህያት መጠበቅ የለባቸውም የሚለው ሕዝብ ይቅርና፣ መጠበቅ አለባቸው የሚለውም ሕዝብ፣ በዚህ ፍርደ ገምድል ሕግ እንዴት ሊስማማ ይችላል?
ሐያሲው ምክትል አርታዒ የሆኑበት፣ “ነገረ ክርስትና” መጽሔት፣ በቅርቡ ዐዲስ ዕትም ለንባብ ዐቅርቦአል፡፡ “ናይእግዚ ኅሩይ” ማለት ሲገባው፣ “ናይእግዚ ህሩይ” ምክትል አርታዒ ናቸው፣ የሚል ጽሑፍ በመጀመሪያው ገጽ ላይ ጽፎአል፡፡ ሞክሼ ሆህያትን መቀየር የሕግ ስሕትት እንዲሁም በትምህርት ተቋማት፣ “F” የሚያከናንብ ከሆነ፣ እርስዎ ራስዎ የራስዎን ስም፣ በራስዎ መጽሔት ላይ አሳስቶ በመጻፍ መቀመቅ ሊወርዱ፣ እንዲሁም “F” ሊልሱ ነው ማለት ነው፡፡ ሞት ባይቀድማቸው ኖሮ፣ “ሐዲስ ዓለማየሁም” የራሳቸውን ስም በዚህ መንገድ እየቀያየሩ መጻፋቸው፣ እርስዎ የገጠምዎት ኪሳራ ሁሉ፣ እርሳቸውም ገጥሞአቸው ነበርሳ? ስማችን ሕጋዊ መሠረት አለው ማለት፣ የምንጠቀምባቸውም ሆህያት ሕጋዊ ድጋፍ አላቸው ማለት በጭራሽ አይደለም፡፡ አንድ የሕግ ምሁር ይቅርና በቀለም የተሟሸ ማንኛውም ሌጣ ሰው፣ ይህን የአቶ ናይእግዚን ሒስ፣ በብዙ ፈገግታና በትልቅ ትንግርት እንደሚያነበው አልጠረጥርም፡፡
ልብ ይበሉ ይህ የእርስዎ ሙግት፣ በሥነ አመክንዮ መጻሕፍት ዳቦ አስቈርሶ ስም ያስወጣ የተፋልሶ ዐይነት ነው፡፡ “በትረ ጠንቋይ ተፋልሶ” (Accident Fallacy) በመባል ይታወቃል፡፡ “ሥነ አመክንዮ” በሚል ርእስ ያዘጋጀሁት መጽሐፍ፣ ይህን የተሳሳተ የሙግት ዐይነት በሚከተለው መልክ አስተዋውቆታል፣ “አጠቃላይ የሆነ ሕግ፣ ከጒዳዩ ጋር ተዛማጅነት ለሌለው ጒዳይ መርሖ እንዲሆን ሲገደድ፣ የሚከሠተውን ተፋልሶ አመልካች ነው፡፡ አጠቃላዩ ሕግ በግልጽም ሆነ በስውር ተሳቢ ተደርጎ፣ መርሖው በማይመለከተው ጒዳይ ላይ ተፈጻሚ እንዲደረግ ሲሞከር፣ የሚከሠት ስሑት ሙግት ነው” (ገጽ 312)፡፡  
ሒስ አራት:-
ሐያሲው ጠቃሽ አመልካች፣ “ን”ን አዛብቶ በመጻፍ ወቅሰዋል፡፡ ጥሩነቱ በሰዋስው ስሕተት የተወቀስሁበት በሁለት ወይም በሦስት ቦታ ብቻ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ከአንድ መጽሐፍ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ቦታ፣ ጠቃሽ አመልካች ተዛብቶ ቀርቦአል ብሎ ሒስ መሰንዘር፣ ሲበዛ ደቂቅ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ሐያሲው፣ የጠቃሽ አመልካች ጒዳይ ብዙ እንዳሳሰባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ላለፉት 31 ዓመታት በዚህ ረገድ እንከን አልባ ሥራ ማየት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፣ “ከ1983 ዓ.ም ወዲኽ በታተሙ ሥራዎች ላይ…የሞት መድኀኒት ነው ፈልገኽ አምጣ ብባል እንኳ፣ በዚኽ ረገድ ንጹሕ ኅትመት ማግኘት መቻሌ ያጠራጥረኛል (አላገኝም)”፡፡
ግነቱ (ኲሸቱ) ከገደብ ያለፈ ይመስላል! በርግጥ ግለሰቡ እንደሚሉት፣ ባለፉት 31 ዓመታት (ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ) በዐማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሔቶችን፣ መጻሕፍትን፣ ጥናታዊ ሰነዶችን  ወዘተ “ሁሉ” አንብበው ጨርሰዋል ማለት ነው? እርሳቸው ያላገናዘቡት፣ አንዳችም ጽሑፍ በአገር ውጭም ሆነ፣ በአገር ውስጥ አልታየም ማለት ነው? በዚህ ረገድ ከእርሳቸው አነጋገር ጋር የማይጣጣም አንድ ሰነድ እንኳ ቢገኝ፣ ጅምላ ፍረጃቸው በስሕተት እንደሚጠናቀቅ አስተውለውት ይሆን?  
ወደ ጠቃሽ አመልካቿ (“ን”) እንመለስ። የሰዋስው መጻሕፍት፣ ጠቃሽ አመልካች (ማለትም “ን”) ለገቢር አንቀጽ (ለአድራጊ ግሥ) ተገዥ የሚሆነውን ተሳቢ፣ አመልካች እንደ ሆነች ይገልጻሉ፡፡ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ “ያማርኛ ሰዋስው” በሚለው ስመ ጥር መጽሐፋቸው፣ በዚህ ረገድ የሚከተለውን አስረጅ ዐቅርበዋል:— “ልጆች ጨዋታን ይወዳሉ”4፡፡ “ውብሸት አንበሳን ገደለ፡፡ ከበደ የዱር አንበሳን ገደለ፡፡ ዠማነህ አሮጌ አንበሳን ገደለ”5፡፡ በዚህ ቦታ ልንጠይቀው የሚገባ ጥያቄ፣ በርግጥ የዐማርኛ ቋንቋ ባለቤት የሆነው ዘመናዊው ሰው፣ በእነዚህ ዐረፍተ ነገሮች ላይ፣ ጠቃሽ አመልካች ይጥላልን (ያኖራልን)? አይመስለኝም! የዐማርኛ ቋንቋ ሊቃውንት፣ ዘመነኛውን ሰዋስው በትክክል በማጥናት፣ በሰዋስው ላይ ክለሳ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ከምላቸው ሰዋስዋዊ ዐዋጆች መኻል፣ ይህ አንዱ መሆኑን፣ “ለሱታፌአዊ የዐማርኛ ጥናት ክፍል” ወዳጆቼ ገልጫለሁ፡፡   
ስለዚህ ጠቃሽ አመልካቿ የቱ ላይ ትውደቅ የሚለው ጒዳይ፣ እንደ ሰዋስው ስሕተት መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ በዚህ ረገድ ዘመነኞቹ ሊቃውንት የነገሩን አንዳችም ነገር የለም (ቢያንስ እኔ አላውቅም)፡፡ የቋንቋው ባለቤት የሆነ ዘመናዊው ሰው፣ ጠቃሽ አመልካችን በዚህ መንገድ እንደማይገለገል፣ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
ሒስ አምስት:-
በተራ ቊጥር አምስት ላይ ያሰፈሩት ትችት፣ ወቀሳውን የሚጀምረው በዚህ መልክ ነው፣ “በአንድ በኩል የሆህያት አጠቃቀማችን ሊስተካከል እንደሚገባ እየወተወቱ፣ በሌላ በኩል ራሳቸው ደራሲው ሆህያቱን ሙሉ ለሙሉ በትክክል አይገለገሉባቸውም…ለምሳሌ ‘ኸ’ና ዝርያዋን ሙሉ ለሙሉ አይጠቀሙም”፡፡
የ“ሆህያተ ጥበብ” መጽሐፌ ሞክሼ ሆህያት ይጠበቁ የሚል ሙግት ይዞ መቅረቡ ትክክል ነው፡፡ ሞክሼ ሆህያት ይጠበቁ የሚል፣ “ውትወታ” ማድረጌ ቅቡል ነው፡፡ ነገር ግን በወቀሳ ያቀረቡት፣ “ኸ” ሞክሼ ሆሄ አለው እንዴ? ከሌለው ወቀሳዎ በምን አግባብ ትክክል ሊሆን ይችላል?
በመሠረቱ “ኸ”ን ከነጓዙ እጠቀማለሁ (“ኸ”ን አግድፎአል የሚለው ትችትዎ ስሕተት ነው)፤ ነገር ግን እርስዎና ደስታ ተክለ ወልድ በሚገለገሉበት አግባብ አልጠቀምባቸውም። ሞክሼ ሆህያት ይጠበቁ የሚሉ ድርጅቶችም (ለምሳሌ ዓለም ዐቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር) ደስታ ተክለ ወልድ “ኸ”ን በሚጠቀሙበት መልኩ አይጠቀሙም፡፡ ነባሩን (ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴን) ትርጒም ጨምሮ፣ በዐማርኛ ቋንቋ ታትመው የወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒሞች ሁሉ ይመለከቷል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ድምፀት እንጂ፣ የሞክሼ ሆህያት ጒዳይ አይደለም፡፡ ዘመናዊው ሰው (የከተሜው ነዋሪ)፣ ደስታ ተክለ ወልድ፣ “ኸ”ን በሚጠቀሙበት መልክ ስለማይጠቀም ነው፡፡ በአጠቃላይ ጥያቄው የድምፀት ውክልና እንጂ፣ የሞክሼ ሆህያት ጒዳይ አይደለምና ወቀሳዎ መስመር ስቶአል፡፡ ስለዚህ ወቀሳዎ መጽሐፉ ማብራሪያ ባላቀረበለት፣ ነገር ግን እርስዎ ነው ብለው በተሳሳተ መንገድ ታሳቢ ባደረጉት ጒዳይ ላይ የቀረበ ነው፡፡ በአጠቃላይ እኔ ሞክሼ ሆህያት ይጠበቁ አልሁ እንጂ፣ በድምፀት ውክልና ጒዳይ ላይ አስተያየት አልሰጠሁም፡፡ ሞክሼ ሆህያት መጠበቅ አለባቸው በሚል ጥብቅና የሚቆሙ ድርጅቶችም በ“ኸ” አጠቃቀም ላይ፣ ከደስታ ተክለ ወልድ የተለየ አቋም አላቸው፡፡ ምናልባት ደስታ ተክለ ወልድ ራሳቸው በዚህ ዘመን ቢኖሩ፣ የእነዚህን ድርጅቶች የድምፀት ውክልና ሙግት ከሙሉ ልብ የሚቀበሉ ይመስለኛል። በአጠቃላይ ወቀሳዎና ምሳሌዎ መስመር ስቶአል፡፡
ሒስ ስድስት:-
ሐያሲው በተራ ቊጥር ስድስት ላይ የሚተቹት፣ “‘ሞክሼ ሆህያትና ዋሕደ ድምፅ ፊደላትን ጠብቆ መጻፍ እንዴት ይቻላል?’ በሚለው ጒዳይ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ አላየሁም” ማለቴ ስሕተት እንደ ሆነ ይገልጻሉ። እኔ፣ “አላየሁም” ማለቴ፣ “የለም” ማለቴ ነው እንዴ? ያላየሁትን አየሁ ብዬ መጻፍ ነበረብኝን? በአንድ ርእሰ ጒዳይ ላይ ስንጽፍ፣ በተለያየ ምክንያት የመረጃ ውስንነት ሊገጥመን ይችላል። ሁሉን አሟጣችሁ ካልመረመራችሁ መጻፍ አትችሉም የሚል ሕግ በትምህርት ተቋማት መኖሩን፣ ቢያንስ እኔ አላውቅም። ካለ ሕጉ፣ የሰብአውያን የጊዜና የመረጃ ውስንነት ያገናዘበ አይደለምና ለመንግሥተ ሰማይ ጠብቀን ብናቆየው ሳይሻል አይቀርም፡፡ “እኔ አላውቅም” ወይም “እኔ አላየሁም” ማለት፣ ቢሆን በጨዋነት የሚያስመሰግን እንጂ፣ ለወቀሳ ሊዳርግ አይገባም፡፡
“ፈለግ ፈለግ ቢያደርጉ ያገኟቸው ነበር” ብለዋል፡፡ ለእርስዎ ፈልጎ ማግኘት ሊቀልዎ ወይም ያሉበት ቦታ ለዚህ መሰሉ ፍለጋ የተመቸ ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ቀላል ሆኖ ባለመገኘቱ፣ “እኔ አላውቅም” ወይም “እኔ አላየሁም” የሚሉ ቃታ ጠባቂ ቃላት መጠቀም መርጫለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለአንባብያን የጥርጣሬ መብት (benefit of the doubt) መስጠቴ፣ ቢሆን ሊያስመሰግነኝ እንጂ ሊያስወቅሰኝ አይገባም፡፡ በምንጽፍበት ነገር መረጃዎችን፣ “ሁሉ” ማመሳከር ይጠበቅብናል ወይም እናመሳክራለን ብሎ ማሰብ፣ ቢያንስ በእኔ መረዳት ስሕተት ነው፡፡
ሒስ ሰባት:-
ሐያሲው በሰባተኛ የመዘገቡት ሕጸጽ፣ “አላስፈላጊ ሐተታ” የሚሉትን ነው፡፡ ማብራሪያቸው እንደሚከተለው ይነበባል:— “ልንጽፍ ከተነሣንበት ጭብጥ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና የሌላቸውን ሐተታዎች ማስገባት አንባቢን ከማምታታትና እንዲከተሉልን ከምንፈልገው መስመር ከማውጣት ውጭ ጥቅም የላቸውም፡፡ ነቅሼ ላሳይ፡፡ ከገጽ 7-13፡፡ ስለ ትሕትና አስፈላጊነት የቀረበው ሐተታ ራሱን ችሎና ተፍታቶ ጥሩ መጣጥፍ ይወጣዋል፡፡ ለዚኽ መጽሐፍ ጭብጥ ግን ግንጥል ጌጥ ነው የኾነው”፡፡
በመጽሐፉ መግቢያ እንደ ተገለጸው፣ ለመጽሐፉ ውልደትና ልደት ምክንያት የሆነው፣ በአትላንታ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በርእሰ ጒዳዩ ላይ እንዳስተምር ግብዣ ማቅረቡ ነው፡፡ እኔ ዐማርኛን ኮሌጅ ገብቼ የተማርሁ ሰው አይደለሁም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የጉባኤው ታዳሚዎች ዐማርኛን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያጠኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የሚያውቀውን ይዞ እንዲመጣ በማሰብ ትምህርቱን፣ “ሱታፌአዊ የዐማርኛ ቋንቋ ጥናት” ብለነው ነበር፡፡ ሁሉም ያለውን እያዋጣ ሁሉም እንዲማማር፣ ትሕትና ትልቅ ቦታ እንዳለው በማሰቤ፣ ስለ ትሕትና ሰፊ ትምህርት ይዤ ቀርቤ ነበር፡፡  
ይህን ስለ ትሕትና የሚያወራ ጽሑፍ፣ ከመጽሐፉ ጋር እንዲታተም የወሰንሁት፣ መጽሐፉ የታተመበትን ዐውድ እንዲያስታውስ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር እንደማይገናኝ እሙን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፣ “አንባቢን ከማምታታትና እንዲከተሉልን ከምንፈልገው መስመር ከማውጣት ውጭ ጥቅም የላቸውም” የሚለው የሐያሲው ትችት፣ ፍጹም መስመር ስቶአል፡፡
ስለ ትሕትና የቀረበው ጽሑፍ ከጭብጡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም ማለት፣ “አንባቢን አይጠቅምም”፣ “አንባቢን ያምታታል”፣ “ከመስመር ያወጣል” ማለት በጭራሽ አይደለም፡፡ “አይጠቅምም” ማለት፣ “ይጐዳል”፣ “ያምታታል” ማለት ነው እንዴ? ብዙ የማይጠቅሙ ነገሮች አሉ፤ ይህ ማለት ይጐዳሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገሮችን እንዲሁም ምግባራዊ ብያኔዎችን ከመጥቀምና ከመጒዳት አንጻር ብቻ መመልከት ስሕተት ነው፡፡ የማይጠቅሙ በአንጻሩም የማይጐዱ ብዙ ነገሮች አሉና፡፡ የአገራችን ፖለቲከኞች፣ “ሰውን መግደል አይጠቅምም” ይላሉ፡፡ ይህ ስሕተት ነው፡፡ “ሰውን መግደል ይጐዳል” መባል ነው ያለበት፡፡ እንዲያውስ ከመግደል በላይ የሚጐዳ ምን ነገር አለ? ይህ በሥነ አመክንዮ ትምህርት፣ “የስሑት ቡአዴ ተፋልሶ” (False Dichotomy) በመባል ይታወቃል፡፡ “ሁለት አማራጮች ብቻ በመስጠት፣ ከሁለቱ መኻል አንዱን ብቻ ምረጥ ብሎ የሚያስገድድ የተፋልሶ ዐይነት ነው” (“ሥነ አመክንዮ” ገጽ 325)፡፡  
የመጽሐፉ ጸሓፊ በመሆኔ፣ ለመጽሐፉ ፅንሰትና ውልደት ምክንያት የሆኑ ነገሮች፣ በመጽሐፉ ውስጥ ተጠብቀው እንዲኖሩ የማድረግ ሙሉ መብት አለኝ፡፡ እነዚህን መረጃዎች አልፈልግም የሚል ሰው፣ እነዚህን ክፍሎች ያለማንበብ ሙሉ መብት አለው። በአጠቃላይ በመጽሐፉ ውስጥ ስለ ትሕትና የተጻፈው ጽሑፍ፣ ከጭብጡ ጋር ተዛማጅ አይደለም ማለት፣ “አንባቢን ይጐዳል”፣ “አንባቢን ያምታታል”፣ “አንባቢን ከመስመር ያወጣል” ማለት በጭራሽ አይደለም። ስለ ትሕትና የተባለው ነገር ቢሆን ይጠቅማል፤ ባይሆን ግን ጒዳት የለውም፡፡ አንባቢን “የሚጐዳበት”፣ አንባቢን “የሚያምታታበት”፣ “ከመስመር የሚያወጣበት” አንዳችም ምክንያት የለም፡፡  ግልጽ ነው?  
ሒስ ስምንት:-
ሐያሲው በስምንተኛ የመዘገቡት፣ “መሠረታዊ ቃሎችን አለመተርጐም” የሚሉትን ችግር ነው። ለዚህም በአብነት የጠቀሱት፣ “ሆሄ” የሚለው ቃል ምን ትርጒም እንደ ወከለ አልተነገረንም የሚል ነው፡፡
ቃላት የሚተረጐሙበት ዐቢይ ምክንያት፣ በመጽሐፉ ውስጥ ግልጋሎት ላይ የሚውሉት ወሳኝ ቃላት፣ አማራጭ ትርጒማቸው (range of meanings) ብዙ ሲሆን ወይም መጽሐፉ ቃላቱን ከመደበኛው አጠቃቀም በተለየ መንገድ ሊጠቀምበት ሲፈልግ ወይም ደግሞ አንዳንድ ተደራስያን የቃሉን ትርጒም አያውቁም ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ “ሆሄ” የሚለው ቃል አማራጭ ትርጒም አለው እንዴ? መጽሐፉ ቃሉን ከመደበኛው አጠቃቀም በተለየ መንገድ ተገልግሎበታል እንዴ? በርግጥ የመጽሐፉ ተደራስያን፣ “ሆሄ” የሚለውን ቃል አያውቁም እንዴ?
ሒስ ዘጠኝ:-
በዘጠነኛነት የሰፈረው ሒስ፣ በርካታ የግርጌ ማስታወሻዎች አልተሟሉም፣ አንዳንዴም ሕጉን ተከትለው አልተጠቀሱም የሚለው ነው፡፡ በዐማርኛ ተዘጋጅተው በአገር ውስጥ የታተሙ መጻሕፍትን፣ በዋቢ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥም ሆነ በኅዳግ መዘክር ላይ እንዴት እንጥቀስ የሚለው ጥያቄ እልባት ያገኘ አይመስለኝም። በፈረንጆቹ አካባቢ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት፣ እንመራበታለን የሚል የአጠቃቀስ ሥርዐት ይከተላሉ6፡፡    
በአገራችን ዐታሚ ድርጅቶችን እንደ አሳታሚ ድርጅት እየጠቀሱ የመጻፍ ስሕተት አለ፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ሮኆቦት ማተሚያ ቤት፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ ብራና ማተሚያ ቤት ወዘተ የምንላቸው፣ ማተሚያ ድርጅቶች እንጂ፣ ዐታሚ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ በእንግሊዝኛው ግን ከመጽሐፉ ስያሜ ቀጥለን የምንጽፈው፣ ዐሳታሚውን ድርጅትና የሚገኝበትን ቦታ ነው፡፡ ሥርዐተ ትእምርቶችንም በተመለከተ እያንዳንዱ ጸሓፊ የመሰለውን አካሄድ ሲከተል ነው የሚታየው፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ወጥ መመሪያ የለንም (ቢያንስ እኔ አላውቅም)፡፡  
ጸሓፍያን የቱንም አካሄድ ቢከተሉ፣ የመረጃ ምንጫቸውን መጥቀስ የግድ ይኖርባቸዋል። አጠቃቀሳቸውም ወጥ እንዲሆን ይጠበቃል። ሌላው ከተወሰነ ጸሓፊ ያገኘሁትን፣ ነገር ግን ከየትኛው መጽሐፍ እንዳገኘሁት ርግጠኛ ያልሆንሁበትን፣ ግለሰቡን ከጠቀስሁ፣ መጽሐፉንና ገጹን በትክክል ካልጠቀስህ ተሳስተሃል መባል ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ የኅዳግ መዘክሮችም ሆኑ መሰል ማመላከቻዎች ቀደማይ ግባቸው፣ ግለሰቡ ለጠቀሰው ምንጭ ተገቢውን ዋጋ እንደ ሰጠ እንዲሁም ስርቆተ መረጃ (plagiarization) እንዳላካሄደ ለማመልከት ነው፡፡
በሕግ ትምህርት፣ “የሕጉ መንፈስ” የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ሕግ ተግባራዊ እንዲደረግ የተፈለገበትን ምክንያት የሚያብራራ ነው፡፡ የኅዳግ መዘክር ያስፈለገበት ቀዳማይ ምክንያት፣ ስርቆተ መረጃ እንዳይኖር ጥበቃ ለማቈም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሥርዐተ ትእምርቱ በላይ፣ ዕውቅና መስጠቱ “የሕጉን መንፈስ” የተከተለ አይመስልዎትም?     
ሒስ ዐሥር:-
ሥርዐተ ነጥብ ላይ የተሰጠው መረጃ፣ “እጅግ ቊንጽል” እንዲሁም በመጽሐፉ ውስጥ እነዚህ ትእምርቶች በወጥነት ግልጋሎት ላይ አልዋሉም የሚለው፣ የመጨረሻ ትችት ነው፡፡ ሐያሲው፣ “እጅግ ቊንጽል ነው” ብለው የጠቀሱት ብቸኛ ትእምርት እርሳቸው፣ “ታጣፊ ቅንፍ” [] ብለው የሚጠሩትን ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ካልሆነ በቀር ይህ ዐይነቱ፣ “ታጣፊ ቅንፍ” በዐማርኛ መጻሕፍት ላይ አይቼ አላውቅም፡፡ ሁሉን ጠቅሼ የቀረው ይህ ብቻ ከሆነ፣ “እጅግ ቊንጽል” ሊባል እንዴት ይችላል? ይህ ትእምርት በዐማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስም ተሰይሞለት፣ ሕግ ተደንግጐለት፣ ግልጋሎት ላይ ሲውል ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ቢኖር እንኳ ከተዘረዘሩት 16 ትእምርቶች መኻል አንድ መግደፉ፣ “እጅግ ቊንጽል” ሊባል እንዴት ይችላል?     
ማጠቃለያ:—
ለሐያሲው ወንድማዊ ምክር ማስተላለፍ በጐ መስሎ ታይቶኛል፡፡ የመጀመሪያው ምግባራዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሙያዊ ምክር ነው፡፡ በዚሁ ቅደም ተከተል ልሂድበት:—
አንደኛ፤ ሌላ ጊዜ ጠብ ጫሪ ቃላት አይጠቀሙ:—
- “ስለ ቋንቋ መጽሐፍ የሚጽፍ ሰው ግን መሠረታዊ የኾነ ዕውቀት እንዲኖረው ይጠበቃል”
“መሠረታዊ” ሲሉ ምን ማለትዎ ነው፣ እንኳን እኔ የስምንተኛ ክፍሏ ሴት ልጄ፣ “መሠረታዊ” ዕውቀት እንዳላት እሙን ነው፡፡ ይህ ገለጻዎ ወደ ጽርፈት ያጋደለ አይመስልዎትም?      
- “ስለማያውቁት ጒዳይ መጽሐፍ ባይጽፉና እንዳከበርኋቸው ቢቈዩልኝ እመርጥ ነበር”  
የማላውቀውን ጽፌ ከሆነ ስሕተቴን ነቅሰው በማውጣት የምማርበትን ማስረጃ ያቅርቡ። የእርስዎ ከበሬታ ከእኔ ማወቅና ያለማወቅ ጋር፣ መገናኘት ያለበት ግን አይመስለኝም፡፡ ሰው የሚከበረው በዕውቀቱ አይደለም፡፡ ሰው በመሆኑ እንጂ፡፡   
- “(ጠላታችኹ ክው ይበል) በድንጋጤ አፌን አስከፈቱኝ”፣ “እየቀፈፈኝም ቢኾን የጻፉት ይህ ነው”፣ “በእውነቱ ደፋር ናቸው”፣ “እንደለመዱት” ወዘተ
እነዚህ ቃላት ከአዎንታዊ አንድምታቸው ይልቅ፣ ስላቃዊ ጅራፋቸው ይበረታልና አይጠቀሙባቸው፡፡ ያቀረቡት ሙግትና ማስረጃ ሙሉ ለሙሉ ቅቡል ነው ቢባል እንኳ፣ ሰውን በዚህ መንገድ ማስተማር አዳጋች ነው። ሰው ተሳዳቢ ነው ከሚለው ሰው፣ ትምህርት መቅሰም ይቸግረዋል፡፡  
ስለቋንቋ ከሚሞግቱበት ጭብጥ ይልቅ፣ ሰውን መሳደብ ትልቅ ነውር እንደ ሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ አስረጅ ልስጥዎ፡፡ አንድ ሰው የሒሳብ ስሌቶችን ቢሳሳት ወይም የሰዋስው ሕጎችን ቢተላለፍ፣ ንስሓ መግባት ይቅርታ (መጠየቅ) አያስፈልገውም፡፡ ንስሓ በዋነኝነት ምግባራዊ ስሕተቶችን የሚመለከት ነውና። “አምላኬ ሆይ ሁለትና ሁለት ሰባት ነው ብዬ ዐስብ ነበር፣ ይህን ኀጢአቴን ይቅር በል” ወይም “ይህን የሰዋስው ሕግ አላውቅም ነበር፤ ጠቃሽ አመልካቿን ያለቦታ ጥያለሁና መተላለፌን ደምስስ” ማለት አያስፈልገውም፡፡ መሳደብ ግን በሃይማኖት አስተምህሮ ኀጢአት፣ በሥነ ምግባር ኢምግባራዊ ግብር፣ በሕግ ደግሞ ወንጀል ነው። እውነት ፍቅርን እንጂ፣ ስድብን አትሻምና ከዚህ አካሄድ ይራቁ፡፡ ከሥነ ጽሑፍ (ከሰዋስው) ስሕተት ይልቅ፣ ስድብ እጅግ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡
 ሁለተኛ፤ ሙያዊ ምክሬ የሚከተለው ነው። አንድ ጽሑፍ ወይም መጽሐፍ መገምገም ያለበት (ቢያንስ በዋነኝነት)፣ “የተጻፈለትን ዐቢይ ዐላማ ከዳር አድርሶአል ወይ?” ከሚለው ማጠንጠኛ አንጻር ነው (“ወደ ሰው ልብ ላደርሰው እፈልጋለሁ የሚለውን ቊም ነገር፣ በትክክል እንዲሁም ለአእምሮ ግቡዕ በሆነ መልክ አስተላልፎአቸዋል ወይ?” በሚለው ቀዳማይ ዐላማ ነው)፡፡ “ሆህያተ ጥበብ” የተጻፈበት ዐላማ የሚከተለው ነው:— (1) ሞክሼ ሆህያት ለምን እንደሚያስፈልጉ መሞገት፤ እንዲሁም አጠቃቀማቸውን ለተጠቃሚው ማስተዋወቅ። (2) ዋሕደ ድምፅ ፊደላትን ማስተዋወቅ እንዲሁም ግልጋሎታቸውን ማሳየት፡፡ (3) ፍንፅቅ ፊደላትን መቼና እንዴት እንደምንጠቀም ማብራራት፡፡ (4) በአበዛዝ ሂደት ውስጥ በስፋት የሚታዩትን ሰዋስዋዊ ችግሮች ማረም። ሐያሲው መጽሐፉን ከዚህ አንጻር መገምገም የነበረባቸው ይመስለኛል። በዚህ ጒዳይ ላይ ሁነኛ የሚባል አስተያት ሲሰጡ አንመለከትም።  ይልቁንም የመጽሐፉ ቀዳማይ ዐላማ ባልሆኑ ጥቃቅን ጒዳዮች ላይ ትኲረት አድርገዋል፡፡
የሐያሲው የዘረዘሯቸው ትችቶች ሁሉ ፍጹም ትክክል ናቸው ተብሎ ቢታሰብ እንኳ፣ የመጽሐፉ ቀዳማይ ዐላማ ጸንቶ መኖሩ አያወዛግብም፡፡ ሒሳቸው ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው፣ ምናልባትም ጥቃቅን በሚባሉ ጒዳዮች ላይ፣ ሙሉ ትኲረት አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ፣ ገምጋሚው መጽሐፉ፣ “አንፀባራቂ እንዳይኾን ያጠለሹ ዐሥር ስሕተቶች” ብለው የዘረዘሯቸው ነጥቦች፣ በተሳሳቱና ነባራዊ ባልሆኑ ሚዛኖች የተሰፈሩ በመሆናቸው ጸሓፊውም ሆነ ተደራስያን፣ የሐያሲውን ትችት ለመቀበል አይገደዱም፡፡ የሐያሲው ትችት፣ ከመጽሐፉ ቀዳማይ ዐላማ ጋር አንዳችም ግንኙነት ከሌለው ደግሞ፣ መጽሐፉ የቆመለትን ዐቢይ ዐላማ በትክክል አሳክቶአል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ፣ እርሳቸው ካሉት በተቃራኒ፣ መጽሐፉ አንዳችም ጽልመት ሳይጫነው፣ “አንፀባራቂ” ሆኗል7፡፡  
ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን!
የኅዳግ መዘክሮች
(Endnotes)
ሐያሲው፣ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር ተዛማጅነት የሌላቸው፣ እንደየሰዉ ፍላጎት በሚወሰኑ የጣዕማና (free variation) ምርጫዎች ላይ ሁሉ፣ ትችት ሰንዝረዋል፡፡ አብዛኞቹ ትችቶች ለመጽሐፉ ቀዳማይ ዐላማ፣ አንዳችም እውናዊ ረብ የሌላቸው ስለሆኑ፣ እንዳላየ ዐልፌአቸዋለሁ፡፡ ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ:— የኮይኔ ግሪክን አነባበብ፣ ከዘመናዊ ግሪክ አነባበብ ጋር በመቀየጥ፣ ትችት ሊያቀርቡ ሞክረዋል፡፡ እውነታው እርሳቸው እንዳሉት ቢሆን እንኳ፣ ከመጽሐፉ ጭብጥ ጋር፣ በአገርም በዘመድም አይገናኝምና፣ እግረ መንገድ ዘው ባለ ደቂቅ ዐሳብ ትችት የሚሰነዝርን የሐያሲ አስተያየት ችላ ብሎ ማለፍ፣ ቢያንስ ጊዜ ለሌለው ለእንደኔ ዐይነቱ ባተሌ ተገቢ  ይመስለኛል፡፡ አስረጅ መጨመር ካስፈለገ፣ ቅኔን ከምንጨታዊ ሙግት አካሄድ ጋር አመሳክረው፣ ለመተንተን መሞከራቸው የችግሩ ሌላ ናሙና ነው፡፡ እነሆ፣ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ቅኔ፣ በሌጣው ተርጒመሃል የሚል ወቀሳ ዐቅርበዋል፡፡ (ሲጀመር ያስቀመጡት የምንጨታዊ ሥነ አመክንዮ መርሖ ስሕተት ነው:— “የመጀመሪያዎቹ ኹለት ዐረፍተ ነገሮች እውነት ከኾኑ፣ መደምደሚያውም እውነት ይኾናል” የሚለው ዐዋጃቸው፣ ለሥነ አመክንዮ ሕግ ስሕተት ነው፡፡ ምንጨታዊ ሙግት፣ የሙግት ነጥቦች ትክክል ሆነው፣ ድምዳሜው ስሕተት የሚሆንበት አግባብ አለና)፣ ሐያሲው የሚሉት ትክክል ከሆነ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ፣ ንጉሥ ኀይለ ሥላሴን  በቅኔ ዘልፈዋል (ተሳድበዋል) ማለት ነው። በውኑ በታላላቅ የቅኔ ሊቃውንት የተከበቡት ንጉሥ፣ በስድብ ተሞልጨው፣ በዝምታ ዐልፈዋል ብሎ ማሰብ ሲበዛ አዳጋች ነው፡፡ ተሳዳቢውስ ይህ ዐይነቱን ድፍረት ከየት ሊያገኘው ቻለ? የወቅቱ ሥርዐት ንጉሥን በዚህ መጠን የማዋረድ መብት የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ለመጽሐፉ ጭብጥ አንዳችም እርባና ስለሌለው፣ የአጸፋ ሙግት አላዋቀርሁም፤ የሙግታቸውን ከንቱነት ለማሳየት ጥረት አላደረግሁም፡፡ በእነዚህና እነዚህን በመሰሉ ጒዳዮች ላይ፣ አንባብያን የራሳቸውን ብያኔ ይስጡ፡፡
2  ፈረንጆች፣ “The principle cuts both ways” እንደሚሉት ነው፡፡ እንዲያውም፣ “This principle cuts the other way more” ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የሕጉ አመንጪ እርሳቸው ናቸውና፡፡    
3 በማጣቀሻነት ደጋግመን የምንጠቅሳቸው የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንዲሁም የደስታ ተክለ ወልድ መዛግብተ ቃላት እንኳ፣ በርካታ የጸሓፊ ስሕተት እንዳለባቸው አስተውለው ይሆን? በትልቅ ጥንቃቄ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም ሥራዎች እንኳ፣ እጅግ ብዙ ስሕተት ታይቶባቸዋል፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚና አርታዒ በዚህ ረገድ ያለኝን ተሞክሮ ባጫውትዎ በርግጥ ጽሑፍ፣ “ሽንፍላን እንደ ማጠብ ነው” የሚለውን ቊም ነገር፣ ይበልጥ ይገነዘቡታል ብዬ ዐስባለሁ፡፡   
4.  ገጽ 70፡፡
5.  ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 39፡፡
6. ለምሳሌ:— Kate L. Turabian, A Manual for Writers.  Chicago Manual of Style. MLA Handbook.
7. የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ረቂቅ አንብበው፣ አስተያየት የሰጡኝን እንዲሁም በትየባ ወቅት የተከሠቱ ስሕተቶችን በማስተካከል ያገዙኝን ባልንጀሮቼን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ እኅት ሳባ በየነ፣ ወንድም መኮንን አዳሙ፣ መጋቢ ዮሐንስ መሐመድ፣ ወንድም አንዱዓለም ገበየሁ፣ ወንድም ወርቁ ኤጄሬ፣ ዶክተር ግርማ በቀለ፣ ወንድም ቊምላቸው ፋንታሁን፣ ወንድም ሳሙኤል በየነ፣ ወንድም ፍቃደ ጥላሁን እስጢፋኖስ፣ ወንድም ፍቅሩ በፍርዱ፣ዶክተር ዮሴፍ መንግሥቱ፣ ወንድም መሐመድ ረሻድ፣ እኅት ዮዲት ኀይሉ፡፡  

Read 810 times