Saturday, 02 July 2022 19:55

“ሰለሞንን አልቀብረውም” ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ፀሐፊ ተውኔቱን፣ ደጉን፣ ሰው ወዳዱን፣ ተጫዋቹን ሰለሞን ዓለሙን ከእድሜዬ ከግማሽ በላዩን ያህል አውቀዋለሁ። በየጊዜው የምንደዋወልና በአካል የምንገናኝ አንሁን እንጂ ስንገናኝ ይበልጡን በእሱ ምክንያት ልብ የሚያሞቅ ወዳጅነት ይኖረናል። ሰለሞን መታመሙንና ወደ መጨረሻ ላይም ያለ ኦክስጂን የማይንቀሳቀስ መሆኑን አውቃለሁ። ችግር ላይ እንደነበረም አውቃለሁ። ግን ዛሬ ነገ ስል አልጠየቅኩትም። በአቅሜ ያህል እንኳ አልደረስኩለትም። ብዙ ጊዜውን በህክምና ያሳለፈ እንደመሆኑ ገንዘብም ይቸግረው ነበር። አልደገፍኩትም። ገንዘብ አጥቼ ወይም ወዳጅነታችን የማያሰጥ ሆኖ ሳይሆን ቸልተኛ ሆኜ ነበር።
የግንኙነት ስፋቱን ያህል ሰዎች እየሄዱ አይጠይቁትም ስለነበር እናቱ፤ “ደጉ ልጄ ምነው ወዳጅ ራቀው?" ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። እኔም እንዲህ እንዲያስቡ ካደረጓቸው ሰዎች መሀል አንዱ ነኝ። ወዳጄ ወድቆ ቤት ሲውል ለራሴ አድልቼ የምችለውን ያህል እንኳ ጊዜ አልሰጠሁትም። “እንዴት ያደርግሀል?" አላልኩትም። “ምን ይቸግርሀል?" አላልኩትም። “እስቲ ይቺን ያዛት ለአንዳንድ ነገር እንኳ ትሆንሀለች" እንኳ አላልኩትም። “አይዞህ ሰሌ” አላልኩትም። ሰው እንዳለው፣ ወዳጅ እንዳለው እንዲሰማው አላደረኩትም። እንደውም አደባባይ ተወጥቶ ቢለመንለት ያስፈልገው ይሆን ነበር፤ ምናልባት። እሱ ከችግሩ ጋር ሲሆን እንዲደረግለት ፈልጎ ይሆን ነበር፤ ምናልባት። ይህን ሁሉ ማድረግ ሲገባኝ አላደረኩም። ታዲያ የእኔ ቀብሩ ላይ መገኘት ጥቅሙ ምንድነው? ለማን ነው? ለምንድነው?
ሰለሞን ዛሬ የለም። ብሔድም ብቀርም አያየኝም። በሚያየኝ ሰዓት፣ ሰው በሚፈልግ ሰዓት፣ ደውሎ ሳይቀር ጠይቁኝ ባለ ሰዓት፣ ሰው በራበው ሰዓት፣ ወዳጅ በናፈቀው ሰዓት እኔ ከጎኑ አልተገኘሁም። ሁሉም ነገር ካለፈና ምንም ማድረግ በማልችል ሰዓት የሚያሳምም ፀፀት ተሰምቶኛል። ምንም ማድረግ አይቻልም። ይህን እንኳ ነግሬ ላገኘው አልችልም። ሄዷል። አምልጧል። በቃ ያ ደግ ሰው ሳጥን ውስጥ ገብቷል። አብቅቷል።
ቀብሩ ላይ የመገኘት አንዳች የሞራል ብቃት የለኝም። ብገኝና ለታይታ ባለቅስ፣ ባለቀ ሰዓት ቤቱ ተገኝቼ ወዳጅ ብሆን ራሴን ይበልጥ እታዘበዋለሁ። እጠላዋለሁ። በሕይወት ላይ፣ በእውነት ላይ የዘሞትኩ ያህል ይሰማኛል። እኔ ድራማ እጽፋለሁ እንጂ ድራማ የሆነ ሕይወት አልኖርም። ወንድሜን ድጋሚ አልክደውም። የመጀመሪያው ይበቃዋል።
ሰዋችሁ ሰው በፈለገ ሰዓት ዛሬ ከጎኑ ተገኙ። ነገ በማንም እጅ የለችም። ነገ ፀፀት ነው ያለው።
ወንድሜ ሰለሞን ዓለሙ ደህና ሁን። ነፍስህ በሰላም ትረፍ።
ከአዘጋጁ፡- አርቲስት ሰለሞን ዓለሙ ለረጅም አመታት የስኳር ህመምተኛ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በገጠመው ተያያዥ ህመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊቱን በተወለደ በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሰለሞን የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው፡፡ የቀብር ስነስርዓቱ  ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የሙያ ጓደኞቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአርቲስት ሰለሞን ዓለሙ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹና ለሙያ ጓደኞቹ ፈጣሪ መፅናናቱን እንዲሰጣቸው ይመኛል፡፡


Read 2310 times