Sunday, 10 July 2022 19:20

የስነ ተዋልዶ ጤና በግጭት አካባቢ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹….ወሲባዊ ግንኙነት መቼ፣ ከማን ጋር፣ ለምን እና የት መፈጸም እንዳለበት እያንዳንዱ ሰው ትምህርት መውሰድ አለበት፡፡››
ምንጭ፡- የስነልቦና ባለሙያ እና በአዳማ የጋራ አገልግሎት መስጫ ማእከል አማካሪ
አቶ መኮንን በለጠ፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ህትመታችን በደሴ እና በአከባቢው በጦርነት ሳብያ ስለተፈጠረ የስነተዋልዶ ችግር እና ወሲባዊ ጥቃት መዳሰሳችን ይታወሳል።
በዚህ ህትመት ወሲባዊ ጥቃት በጦርነት ውስጥ ለምን ይዘወተራል? በተጠቂ እና በማህበረሰብ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖስ? እንደ ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? እንዲሁም እያንዳንዱ ግለሰብ መውሰድ የሚገባው የመፍትሄ አቅጣጫ ምን መሆን አለበት? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይዘን ቀርበናል። የስነልቦና ባለሙያ እና በአዳማ የጋራ መስጫ ማእከል አማካሪ የሆኑትን የአቶ መኮንን በለጠ ማብራሪያ ታነቡ ዘንድ ግብዣችን ነው።
በጦርነት ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች እንዲሁም ተሞክሮዎች አንደሚያሳዩት አስገድዶ መድፈር አንዱ የጦርነት ስልት ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው። አላማውም ልክ እንደ አንድ የጦር መሳሪያ ተተኩሶ ሰው እንደሚጎዳው የሰውን ሞራል እና ስብእና መጉዳት ነው። ይህም የአንድን ማህ በረሰብ ባህል፣ ስርአት፣ አመለካከት እና እምነት በማናጋት የሚያዋርድ ሲሆን በዚህም ሴቶች እና ህጻናት የጥቃቱ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል።
አቶ መኮንን ጨምረው እንዳብራሩት የጦር መሳሪያ ሰውን ይገድላል ወይም ያቆስላል ነገር ግን ወሲባዊ ጥቃት እጅግ ለከፋ የስነልቦና ቀውስ ይዳርጋል። የመጀመርያው የስነልቦና ቀውስ የሐይለ ስሜት መዛባት ሲሆን ለማያቋርጥ ጭንቀት የሚዳርግ ነው። እስከ የህይወት መጨረሻ ሊቆይ ይችላል። ሁለተኛው ደግሞ ፍርሀት ነው። ይህ ፍርሀት እየጨመረ ሲመጣ የደህንነት ዋስትና ማጣት ይከሰታል።
ከፍርሀት በመቀጠል የሚከሰተው ንዴት ነው። የንዴት መነሻ ተጠቂዎችን በማይመለከት መሳሪያ በታጠቁ ሰዎች መሀከል በተፈጠረ ጦርነት ምክንያት መፈጸሙ ነው። ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ በጥፋተኝነት ስሜት እራስን መውቀስ ይመጣል። በመጨረሻም ምንም እንዳልተፈጠረ በማሰብ ወደ ክህደት ማምራት ይከሰታል። ይህ አደገኛ የስሜት መናጋት በተወሰነ መልኩ ትውስታ በሚያገረሽበት ወቅት ወደ በቀል ስሜት የሚከት ይሆናል። በተጨማሪም ክስተቱ የተፈጸመበት ጊዜ ሲያልፍ የመርሳት እና የለሊት ቅዥት ችግር ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።
ከላይ የተጠቀሱት የስነልቦና ችግሮች ተደማምረው ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ወደ ሆነው የባህሪ ችግር ይሸጋገራል። የባህሪ ችግር ማለት ተጠቂዎች ባሉበት እድሜ እና አከባቢ መከወን የሚገ ባቸውን ሳይሆን በተቃራኒው ለህብረተሰቡ ጸር የሆነ ተግባር ሲከውኑ ነው።
በተጠቂዎች ህይወት ውስጥ የተጠራጣሪነት ስሜት ይገዝፋል። በአጠቃላይ ጾታዊ ወይም ወሲባዊ ህይወታቸው ሲቃወስም ይስተዋላል። አንዳንዶች ለበቀል ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ ሌሎች ደግሞ በጭራሽ ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም አይደለም መስማት አይፈልጉም። የስነልቦና ችግር የመጨረሻ ደረጃ ወደ ሆነው የአእምሮ መቃወስ የሚደርሱ ተጠቂዎች እራስን ወደማጥፋት ሀሳብ ያመራሉ። እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት ባመጣው የስነልቦና መቃወስ ችግር ብቻ ወሲብ የሚፈጽመው የሰውነት ክፍል ደንዝዞ[ፓራላይዝ ሆኖ] ከአገልግሎት ውጪ ሊሆን ይችላል እንደ አቶ መኮንን እማኝነት።
ከላይ የተዘረዘሩት የስነልቦና ችግሮች በሙሉ በተገቢው መንገድ ህክምና ከተደረገ የሚድኑ ናቸው። በተመሳስይ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በህግ አካላት ከለላ ማድረግ እና ጥቃት ፈጻሚው ተገቢውን ቅጣት አንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። ማህበረሰቡም ለመፍትሄው አካል በመሆን ድጋፍ በማድረግ ሊያግዛቸው ይገባል።
ወሲባዊ ግንኙነት ሳይንስ እና ጥበብ ነው። ስለዚህ ግንኙነቱ ከማን ጋር፣ ለምን አላማ፣ መቼ እና የት መፈጸም እንዳለበት በሀይማኖት ተቋማት፣ በማህበራዊ ተቋማት እና በት/ቤቶች ግንዛቤ መሰጠት አለበት።  
ይህ ካልሆነ ግን ጥቃቱን ለማስቆም ሆነ ለመቀነስ ያዳግታል። በተጠቂዎች ላይም የሚደርሰው የስነልቦና ችግር ብቻ ሳይሆን በጭፍን ጥላቻ እና ፍረጃ ወደ ብቀላ ያመራል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የስነልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ መኮንን በለጠ እንደጠቀሱት በወሲባዊ ጥቃት ሳቢያ ለኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት ሌሎችን የበሽታው ተጋላጭ ማድረጋቸውን ነው።
በኢትዮጵያ በግጭት ሳቢያ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን በማህበረሰብ ደረጃ ጦርነቱ የሌለባቸው ቦታዎችንም ጨምሮ የአለመረጋጋት ስሜቶች ሲያንዣብቡ ይስተዋ ላል። ለዚህም የመጀመሪያው መፍትሄ እያንዳንዱ ግለሰብ ወደ እራሱ ተመልሶ ውስጡን አዳ ምጦ የአእምሮ ሰላምን ማንገስ አለበት። ሰላምን ለመፍጠር ፌደራል ፖሊስ ወይም መከላከያን ብቻ የሰላም ዋስትና ማድረግ አይገባም ብለዋል አቶ መኮንን።
የእራስን የውስጥ ሰላም ከማንገስ ቀጥሎ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ቤተሰብ ነው። ህብረተሰቡ ልጆችን በግልጽነት እና በምክንያት እያሳደገ መሆኑን ሊፈትሽ ይገባል። ማለትም ልጆች አንድን ጉዳይ እሺ ብለው ሲቀበሉም ሆነ በተቃራኒው እምቢታን ሲመልሱ ከምክንያት ጋር የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ በጥልቀት የሚያስብ ትውልድ ማፍራት ነው። በዚህም መረጃን በግርድፉ ሳያጣሩ ከመቀበል እና ስሜታዊ ከመሆን ይልቅ ምን፣ መቼ፣ የት፣ እንዴት፣ ማን እና ለምን የሚሉትን በማጤን ለመጓዝ ይረዳል።
አንድ ሰው ችግር ውስጥ ሲሆን ብስለት በተሞላበት ትእግስት፣ በውይይት፣ የምክክር አገልግ ሎት በመጠቀም እና ለሰው የማይቻል ነገር በፈጣሪ ይፈታል ብሎ በማመን ለመፍታት መሞ ከር ይገባዋል። ስለሆነም ችግሮች ሲፈጠሩ ልክ አሁን የሚታየውን ሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ትርምሶች ለመፍታት እውነተኛ ሰው መሆን ያስፈልጋል። ለዚህም መለኪያ ተብለው የተቀ መጡት 4 ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ ብለዋል አቶ መኮንን በለጠ የስነ ልቡና ባለሙያ። እነርሱም;
መንፈሳዊ እና ሀይማኖታዊ ህይወት; ከፍተኛ የሆነውን የሞራል እሴት ለማክበር፤ ስርአት እና ስሜት ያለው ህይወት ለመኖር፤ ለህሊና በማደር በጎ ምግባር ለመተግበር ፈሪሀ ፈጣሪ ያስፈልጋል። ነገር ግን ይህ ማለት ሀይማኖት የሌለው ወይም በፈጣሪ የማያምን ሰው በጎ ምግባር ከመስራት ይቆጥባል ማለት ኣይደለም። ዋናው ጉዳይ ምግባሩ ነው።   
የስሜት ልህቀት [ስሜትን መግዛት]; አብሮ በመኖር መልካም ነገሮችን ለማድረግ የሚያ ስችል ማንነት “ለእኛነት የሚያበቃ እኔነትን” መገንባት ይገባል። ስሜትን በመቆጣጠር እና የእኔነትን ስግብግብነት በማስወገድ ለመኖር ሌሎችን ማኖር እንዲሁም ሊሎችን ለማኖር እራስ መኖር እንደሚገባ አምኖ መተግበር ያስፈልጋል።
እውቀት፤ በመደበኛ ትምህርት የሚሰጠውን ትምህርት በአግባቡ ከመውሰድ ባለፈ የማህበረሰቡን ስርአት፤ ወግ ፤ልማድ እና ባህል በመውሰድ ጥሩውን መላመድ እንዲሁም ጎጂዎችን ማረም ሲቻል አዋቂ ያደርጋል። ማወቅን ከጥበብ ጋር አዛምዶ በመያዝ የሚተገበር ነው።
የአካል ብቃት፤ ሰው በስራ ላይ የሚያሳልፈው የጊዜ መጠን በትክክል እና ተገቢ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ሲደረግ ነው አካል ግልጋሎቱ በተገቢው መንገድ ሰርቷል የሚባለው።   
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ አብሮ መልካም ነገሮችን መተግበር እጅግ ያረካዋል። አብሮ መሞት ግን ሊቀፈው ይገባል። “አሁን በሀገሪቷ ላይ ያለው ነገር አብረን ተያይዘን እንሙት፤ ሀገሪቷን ባዶዋን እናስቀራት የሚል ይመስላል” ይህ የተሳሳተ ግንዘቤ መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል ይላሉ ባለሙያው።
በመጨረሻም ተያይዞ መጥፋት የማይቻል፤ የማይሞከር እና የማይታሰብ መሆኑን ሁላችንም ተገንዝበን አብሮ መልካም ነገሮችን ለመስራት ሰላማችንን በየግል አስፍነን እንኑር በማለት የስነልቦና ባለሙያ እና በአዳማ የጋራ መስጫ ማእከል አማካሪ አቶ መኮንን በለጠ መልእክታ ቸውን አስተላልፈዋል። 

Read 9659 times