Sunday, 10 July 2022 19:24

ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአፍሪካ መቼ ነው?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ለ20ኛው ኬንያ፤ ጃፓንና ሲንጋፖር ይፎካከራሉ
                                               
              18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካዋ ኦሬጎን ከተማ ላይ ከሳምንት በኋላ እንደሚጀመር ይታወቃል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የሚያዘጋጀውን ሻምፒዮና በሃላፊነት ተቀብሎ ለማስተናገድ በሚካሄደው ዘመቻና የምርጫ ሂደት ላይ የኢትዮጵያ ተሳትፎ የሚያበረታታ አይደለም። በዓለም አትሌቲክስ በተለይም በሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ ብትሰለፍም የዓለም ሻምፒዮናውን በምድሯ ለማዘጋጀት ጥረት አለማድረጓ ያስቆጫል፡፡ በምድረ አሜሪካ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከሚካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ በ2023 እኤአ ላይ  በአውሮፓ አህጉር ላይ በሃንጋሪ መዲና  ቡዳፔስት 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ይካሄዳል፡፡ በ2025 እኤአ ላይ ደግሞ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አለ፡፡ የአፍሪካዋ ኬንያ፤ የደቡብ ኤሽያዎቹ ጃፓንና ሲንጋፖር ይህን መስተንግዶ ለመረከብ ፉክክር ውስጥ ናቸው፡፡  የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከኦሬጎን 2022 ጋር አያይዞ አሸናፊውን  አገር በይፋ የሚገለፅም ይሆናል፡፡ ስፖርት አድማስ በሻምፒዮናው አዘጋጅነት ዙርያ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ለማነቃቃት ይህን ልዩ ትንታኔ አቅርቧል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት...
አትሌቲክስ ከሰው ልጅ ጋር ከቆዩ ጥንታዊ ስፖርቶች አንዱ ነው፡፡ አትሌቲከስ በኦሎምፒክ መድረክ ቁጥር አንድ ስፖርትም ነው፡፡ በዓለም ዙርያ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ አትሌቶች በሩጫ፤ በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ከታላላቆቹ የዓለም ዋንጫና የኦሎምፒክ መድረኮች ተርታ የሚሰለፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት  ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በመጀመርያ ደረጃ ሻምፒዮናውን ማስተናገድ የሚፈልግ አገር የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የሚሰራበትን የግዜ ሰሌዳ በቅርበት መከታተል ይኖርበታል፡፡ 219  አገራትን በአባልነት የያዘው ማህበሩ ሻምፒዮናውን ለሚያዘጋጁ ጥሪ ያቀርባል። ይህን ተከትሎ አመልካች አገራት ዓለም አቀፉን ውድድር ለማስተናገድ ያሰቡበትን የስራ እቅዶች የሚገልፁ ደብዳቤዎች ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለተሟላ የሻምፒዮናው መስተንግዶ የሚያስቀምጣቸውን አስፈላጊ መመርያዎችና መስፈርቶች የሚገልፅ ሰነድ ያሰራጫል፡፡ ከዚህ በኋላም የዓለም ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ ያላቸውን ፍላጎት በደብዳቤ ያሳወቁ አገራትም አጠቃላይ የስራ እቅዳቸውን በተሟሉ ሰነዶች አጠናቅረው ያቀርባሉ፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ሻምፒዮናውን የሚያዘጋጅ ከተማ ለመምረጥ የአመልካች አገራትን በመጎብኘት የምርመራ ሪፖርት ያቀርባል፡፡  ሪፖርቱን የሚገመግመው ደግሞ የአለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ነው፡፡ በዘመናዊ ስታድዬምና ሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች፤ በትራንስፖርት አገልግሎት፤ በፀጥታና ደህንነት፤ በሆቴልና መስተንግዶ የቀረቡ መረጃዎችን አጣርቶ  ይመራመራል፡፡ የአመልካች አገራት መንግስታት ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው መስተንግዶ የሚሰጡትን ሙሉ ዋስትና ያረጋግጣል። በመጨረሻም አዘጋጁን የሚመርጥበት ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው አንድ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደብ ይጠይቃል፡፡  ከዚህ በጀት 33 በመቶው ሻምፒዮናውን ለሚያስተናግዱ የስፖርት መሰረተልማቶችና ሌሎች አገልግሎቶች ይውላል። 12 በመቶው ለሽልማት ገንዘብ የሚቆረጥ ነው፡፡ 10 በመቶው ለብሮድካስት ስራዎች እንደሚወጣ፤  ከ14 በመቶ በላይ ደግሞ ለአጠቃላይ የመስተንግዶ ተግባራት ይመደባል፡፡ የትኬት ሽያጭ ፤ የህክምናና የዶፒንግ ስራዎችን ለማከናወን ከበጀቱ  3 በመቶው የሚያዝ ሲሆን ቀሪው  11 በመቶም ለተጨማሪና ተያያዠ ወጭዎች የሚከፋፈል ይሆናል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማዘጋጀት በሚያዘው በጀት እስከ 30 ሺ ተመልካች የሚይዝና በኦሎምፒክ መስፈርት የተገነባ ዘመናዊ ስታድዬም  አስፈላጊ ነው። ከዋናው ስታድዬም  ሌላ አትሌቶችና ልዑካናቸው የሚከትሙባቸው ማረፊያዎች፤ ከውድድር በፊት በተጨማሪ የሚያሰለጥኑባቸው ሁለት የልምምድ ሜዳዎችን በተሟላ አቅም መገንባትም ይጠይቃል፡፡በሻምፒዮናው ወቅት በሆቴል ማረፊያ አገልግሎት ብቻ ከ11 እስከ 20 ምሽቶችን ቆይታ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ከ6600 በላይ የመኝታ ክፍሎች ነው፡፡
በ2023 ለሃንጋሪዋ ቡዳፔስት
በ2023 እኤአ ላይ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ ያመለከቱ አገራት ለምርጫው ውድድር ውስጥ የገቡት ከ4 ዓመታት በፊት ነው። በተለይ የአውሮፓዎቹ ከተሞች ቡዳፔስትና በርሚንግሃም መስተንግዶውን ለማግኘት እስከመጨረሻው ፉክክር አድርገዋል። የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔም 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታስተናግድ የተመረጠችው የሃንጋሪዋ መዲና ቡዳፔስት ናት፡፡ ቡዳፔስት ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት  እጅግ ዘመናዊ ስታድዬምና  የአትሌቲክስ ማዕከል ገንብታለች። ሻምፒዮናው በማስተናገድ በአገሪቱ ያለውን የአትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና የከተማዋን ገፅታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመገንባት ሰፊ እቅድ ይዘዋል፡፡ የቡዳፔስቱ 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2024 እኤአ ላይ የፈረንሳይ ከተማ ፓሪስ ለምታካሂደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ድምቀት እንደሚፈጥርም ተነግሯል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ካለፉት 17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ከ10 በላይ የሚሆኑትን የአውሮፓ ከተሞች እንዲያስተናግዱ አድርጓል። የዓለም ሻምፒዮናውን ካዘጋጁ የአውሮፓ አገራት ፊንላንድ፤ ጣሊያን፤ ጀርመን፤ ስዊድን፤ ግሪክ፤ ስፔንና ፈረንሳይ ይጠቀሳሉ፡፡
የደቡብ ኤስያዎቹ ጃፓንና ሲንጋፑር ለ2025
20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2025 እ.ኤ.አ ላይ ለማዘጋጀት ከመጀመርያው ፍላጎት የነበራቸው አራት አገራት ጃፓን፤ ኬንያ፤ ሲንጋፑርና ፖላንድ ነበሩ፡፡  የሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት  19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2023 እ.ኤ.አ ላይ እንድታስተናግድ ስትመረጥ ፖላንድ ከፉክክሩ ወጥታለች፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የማዘጋጀቱ ተራ ከአውሮፓ አህጉር እንደሚያልፍ በመታወቁ ነው፡፡ የአፍሪካ አህጉርን በመወከል ኬንያ እንዲሁም የኤሽያ አህጉርን በመወከል ጃፓንና ሲንጋፑር ለመስተንግዶው ፉክክራቸውን ቀጥለዋል።
ጃፓን   የዓለም አትሌክስ ሻምፒዮናውን በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ለማስተናገድ ነው ያመለከተችው።  32ኛውን ኦሎምፒያድ በቶኪዮ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ስታድየም ተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ ስላነሳሳት ነው፡፡ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ የሆነበት  ስታድዬሙ ለሻምፒዮናው ከፍተኛ ድምቀት መፍጠር እንደሚችልም በበርካታ የዓለም አትሌቲክስ ባለሙያዎች ተመስክሯል፡፡ የዓለም አትሌቲክስን ከሚያግዙ አብይ ስፖንሰሮች መካከል ሶስቱ ማለትም ኤሲአይኤስ ፤ ሴኮና ቲዲኬን የጃፓን ኩባንያዎች መሆናቸውም መስተንግዶውን የምታገኝበት ተፅእኖ ሊፈጥርላት ይችላል፡፡ ጃፓን በ1991 እ.ኤ.አ ላይ በቶኪዮ እንዲሁም በ2007 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በኦሳካ ከተሞች ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን ለማዘጋጀት በቅታለች፡፡  
በኤሽያ አህጉር የምትገኘው ሌላዋ አገር ሲንጋፖርም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ተስፋ ያደረገችው  በ1.33 ቢሊዮን ዶላር የገነባችው ዘመናዊ ስታድዬም ስላላት ነው። የሲንጋፑር ስፖርት ሚኒስትር የአትሌቲክስን ስፖርት በመላው ኤሽያ ለማስፋፋት የያዘውን እቅድ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ትኩረት እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በደቡብ ኤስያ ከ600 ሚሊዮን በላይ ህዝብ መገኘቱ ለአትሌቲክስ ስፖርት እምቅ ሃይል መኖሩን ያመለክታል፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ግን አካባቢው ያለው ውጤት ደካማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ጃፓን ከፍተኛ አቅም ሊኖራት ይችላል፡፡ ሲንጋፖር ግን በዚህ ደረጃ አለምን ለማስተናገድ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት ባለሙያዎች አሰትያየት ሰጥተዋል፡፡ከቶኪዮና ከሲንጋፑር በፊት የኤሽያ አህጉር  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለ4 ጊዜያት  ማስተናገድ ችሏል፡፡ በ1991 እና በ2007 እኤአ የጃፓኖቹ ከተሞች ቶኪዮና ኦሳካ ፤ በ2011 እኤአ ላይ የደቡብ ኮርያዋ ዴጉ እንዲሁም በ2019 እኤአ ላይ የኳታሯ መዲና ዶሃ ናቸው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በአፍሪካ አህጉር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለማዘጋጀት እስከ መጨረሻው ፉክክር የዘለቀችው ኬንያ ብትሆንም ደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ ከጅምሩ ፍላጎታቸውን ገልፀው ነበር፡፡ የኬንያን አትሌቲክስ የሚያስተዳድረው ‹‹አትሌቲክስ ኬንያ›› 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በ2025 እኤአ ላይ ለማስተናገድ ሲነሳ በመጀመርያ ከአገሪቱ መንግስት ድጋፍና ይሁንታን አግኝቷል፡፡ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ‹‹ኬንያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በማስተናገድ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች። የዓለም የስፖርት ሻምፒዮናዎች መኖሪያ ምድር መሆኗ ለዚህ ጥረታችን ምክንያት ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው የኪሳራኒ ዘመናዊ ስታድዬም ተሟልቶ መገንባቱና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማስተናገድ ስኬታማ ተመክሮዎች ማግኘቱ  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማስተናገድ ጥያቄን በይፋ ለማቅረብ አስችሏል፡፡ በቻይና የተገነባው ዘመናዊ የአትሌቲክስ ስታድዬም በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠውን የዙር ውድድር በማዘጋጀት ተሳክቶለታል፡፡  በሌላ በኩል በ2017 እኤአ ላይ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ስር የሚካሄዱትን  Under-20 እና Under-18 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በማዘጋጀት የተገኙ ተመክሮዎችም ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡
አትሌቲክስ ኬንያ የአዘጋጅነት ማመልከቻውን እንዳስገባ ያስታወቀው  በኦክቶበር ወር 2021 እኤአ ላይ ነው፡፡ በወቅቱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሲናገሩ ኬንያ በአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር መድረኮች ታላላቅ አትሌቶችን የማፍራት ታሪኳን ከግምት ውስጥ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡ በአገሪቱ የአትሌቲክስ ስፖርት ልዩ መንፈስ መኖሩን ጠቅሰውም የዓለም ሻምፒዮናውን በማዘጋጀት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር የምትሆንበት እድል እንደሚሰጣት ተስፋ አደርጋለው ብለዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ  60 የዓለም ሻምፒዮኖችና 34 የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖችን ያፈራችው ኬንያ  በወንዶች 9 በሴቶች 8 የዓለም አትሌቲክስ ሪከርዶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
ኬንያ አፍሪካ ላይ በታሪክ የመጀመርያውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታስተናግድ በይፋ ድጋፋቸውን ከገለፁት መካከል ታላላቆቹ አትሌቶች ፖል ቴርጋት፤ ዴቪድ ሩዲሻ እና ካተሪን ንድሬባ ይጠቀሳሉ፡፡  የአፍሪካ አትሌቲክስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሃማድ ካልካባ የዓለም ሻምፒዮናውን በአፍሪካ አህጉር  ለመጀመርያ ጊዜ ለማካሄድ ኬንያ ሙሉ አቅም እንዳላት መስከረዋል፡፡ የአሜሪካው አትሌት ጀስቲን  ጋትሊን በበኩሉ በኪሳራኒ ስታድዬም የተካሄደ ውድድርን ከተሳተፈ በኋላ የዓለም ሻምፒዮናን  ኬንያ እንድታዘጋጅ መወሰኑ ታላቅ እድል መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ተራስ መቼ ይሆን...
የኢትዮጵያን ስፖርት የሚመሩ ተቋማት ከዚህ ዓለም አቀፋዊ የስፖርት ሁኔታ መማር አለባቸው። በአትሌቲክስ ዙርያ በተለይ ከኬንያ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ሰፊ ትምህርት በመቅሰም መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዘመናዊ ስታድዬሞችና የላቁ የስፖርት መሰረተልማቶች ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ለጥቅም ማዋል የአገርን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃና በጎ ገፅታን ለመገንባት እንደሚያግዝ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ስፖርቱን የሚደግፉ ኩባንያዎችና  ባለሃብቶችም ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እንዲካሄዱ መጓጓትና መደገፍ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ወደፊት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናግድ የምትፈልግ ከሆነ ከምትገነባቸው የስፖርት ልማቶች በሚመጥን ደረጃ ላይ የሚገኘው በአዲስ አበባ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቻይናዊ ኩባንያ ግንባታው ከ7 ዓመታት በፊት  የተጀመረው ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ   እስከ 60,000 ተመልካች እንደሚይዝ ይጠበቃል። የቅርጫት ኳስና ቮሊቦል ሜዳዎች እንዲሁም የኦሎምፒክ ደረጃን የሚያሟላ የመዋኛ ገንዳ እንዲሁም ሌሎች ዘመናዊ የስፖርት መሰረተልማቶችም ይኖሩታል።  ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣበትን የስታድዬሙን ግንባታ የሚያከናውነው የቻይናው ኩባንያ CSCEC በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በቻይና መንግስት የተደገፈውን አዲሱን የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት እና ለናሽናል ኦይል ኩባንያ (NOC) ዋና መሥሪያ ቤት ባለ 20 ፎቅ ሕንፃን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ግንባታዎችን ሰርቷል።  አዲሱን ባለ 46 ፎቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የገነባው ነው።
የዓለም ሻምፒዮና ትርፋማነትና በቀጣይ በ2027
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፡፡  ከሻምፒዮናው በተገናኘ በሚደረጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አዘጋጅ አገርና ከተማው ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ። በአትሌቲክስ ስፖርት የሚከናወኑ ተግባራትን ከማነቃቃት በላይ የአገርን ገፅታ በመገንባትና በማስተዋወቅም ስኬታማ ለመሆን ይቻላል፡፡የዓለም ሻምፒዮናውን ትርፋማነት ለማመመልከት 16ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2017 እኤአ ላይ በማስተናገድ ከፍተኛ ስኬት ያገኘችውን የእንግሊዟ ለንደን ከተማ መጥቀስ ይቻላል። ለንደን በኦሎምፒክ ስታድዬሟ ለ10 ቀናት ባስተናገደችው ሻምፒዮና 900ሺ ተመልካቾችን ማግኘት ተችሏል፡፡ ከስታድዬም ውጭ በ10 ሺዎች የሚገመቱ የአትሌቲክስ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡ በጎዳና ላይ የሚካሄዱትን የማራቶንና የርምጃ ውድደሮች ከመከታተል ባሻገር ከሻምፒዮናው ጋር በተያያዘ በተካሄዱ ፌስቲቫሎችና ካርኒቫሎች ታድመዋል፡፡ በአጠቃላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከገቢ ጋር በተያያዘ ከ116 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማስገኘት የለንደን ኢኮኖሚን በከፍተኛ ደረጃ አነቃቅቷል፡፡
ከሳምንት በኋላ በሚጀመረው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዙርያ የሚወጡ ዘገባዎችም የኢኮኖሚ ጠቀሜታውን የሚያወሱ ናቸው፡፡ በኦሬጎን ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የሃይዋርድ ፊልድ ስታድዬም በግል ኢንቨስተሮች ከ270 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኖበት ተገንብቷል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ለሻምፒዮናው መስተንግዶ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዋጣቱም ይጠቀሳል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው በሚካሄድባቸው 10 ቀናት ውስጥ፣ ከመላው አለም የመጡ ተመልካቾች የአሜሪካን የተፈጥሮ ውበት ለማሳየት ፤ ህዝቡ ለስፖርት ያለውን ፍቅር ለማመልከት የዓለም ሻምፒዮናው ልዩ አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ከመላው ዓለም በኦሬጎን ከተማ የሚሰባሰቡት በሺዎች የሚቆጠሩ ብሮድካስተሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች ታሪካዊ ዘገባዎችን በመስራት አሜሪካን ያስተዋውቋታል፡፡ከ200 በላይ ሀገራትን የሚወክሉ 2,000  አትሌቶች አስደናቂ የውድድር ታሪካቸውን ለአለም አቀፍ ታዳሚዎች ያካፍላሉ። የዓለም ሻምፒዮናው በአለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች በህትመት፣ በማህበራዊ ሚዲያና በሺዎች የሚቆጠር ሰዓታትን በቲቪና በራድዮ ሽፋን ያገኛል፡፡ የኦሬጎን ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስፖርት ውድድር የማስተናገድ ብቃቷ  ብቻ ሳይሆን ለመኖሪያ፣ ለስራና ለመዝናኛ ምቹ ቦታ ሆና የዓለምን ህዝብ ትኩረት ልትስብ ትችላለች፡፡ ከ18ኛው የዓለም ሻምፒዮና ጋር በተያያዘ በሚፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ከ205 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይንቀሳቀስበታል፡፡ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኝዎችና ከሻምፒዮናው ጋር ተያይዘው በሚሰጡ አገልግሎቶች በ10 ቀናት ውስጥ ከ138 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለከተማዋ በወጭ መልክ ፈሰስ ይሆናል፡፡
21ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2027 እኤአ ላይ ለማዘጋጀት የዓለም አትሌቲክስ ማህበር አባል የሆኑ 219 አገራት እኩል እድል አላቸው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በመስከረም 2022 እኤአ ላይ የመስተንግዶ መመርያዎችና መስፈርቶችን የያዘ ሰነድ ያሰራጫል፡፡ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ የሚፈልጉ አገራት የመስተንግዶ እቅዳቸውን የያዘ ሰነድ ለማስገባት የሚችሉት  በጁላይ ወር  2023 እኤአ ላይ ሲሆን በዲሴምበር 2023 ላይ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር አዘጋጁን መርጦ ያስታውቃል፡፡

Read 10134 times