Sunday, 10 July 2022 19:26

ብልፅግናን እከስሳለሁ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ እንደሚለው፣ እኔም አንድ ሰሞን “ኢህአዴግን እከስሳለሁ” እል ነበር። በእውነት እከስሳለሁም፡፡ ለምን? (ተነግሮ በማያልቅ ነገር!)
ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡
የቀድሞው ዘመናችንን ለማስታወስ ብንሞክር ከሰሜን እስከ ደቡብ የሚዘረጋ የጭቆና ብራና መዘርጋት ይሆንብናል፡፡ በርግጥ ለላንቲካ መጠቃቀስ እንችላለን፡፡ ብዙ ጊዜ እንዳወራነው፣ ለመናገርና ተዘዋውሮ ለመስራት የማትችልበት፣  በብሔርህ /በተለየ መልኩ የአንድ ብሔር አባላትና የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች - (ተዉ እንጂ እውነቷን እናውራ!)/ ተለይተው የሚቸገሩበት ዘመን ነበር፡፡
ነገሩ ሁሉ ግራ ሲሆንብህ ደግሞ ይህ ነገር መጥፎ ነው ብለህ መናገር ሀጢያት ነበር፡፡
ድሃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ማለት ነውር
ነበር፡፡
ኑሮ ተወደደ ስርቆት ተለመደ ማለት ያስቀጣ
ነበር፡፡
የሠው ልጅ ረከሰ እንባ እንደ ጎርፍ ፈሰሰ
ማለት ቀልደኛ ያስብል ነበር፡፡
ሶስቴ መብላት ቅንጦት ሆነ ማለት ፖለቲካ
ነበር፡፡
ኸረ ተው’ንጂ ...  በብዙ ምክንያት ኢህአዴግንማ በደንብ አድርጌ እከስሳለሁ፡፡
ለምን እንወሻሻለን? እስኪ ቅንጣት እውነት እናውራ፡፡ እንደሚሉን አጭር ጊዜ የሚቆይ ትውስታ ነው’ንዴ ያለን?
የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሚዲያዎች ለመሥማት አንሸማቀቅም ነበር ወይ? ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለፍርሃት ስለ መንግስት የሚያወራ ማን ነበር? ዲሾቻችን ከየጣራ ላይ አቅጣጫቸው እየታዩ አልተለቀሙም ነበር ወይ? ባለቤቶቹስ አልተንገላቱም? ወጣቶች ታስረው አልተገረፉም? በየጨለማ ቤቱ አልተሰቃዩም? ከፓርቲ አባል ውጪ የመንግስት  አገልግሎት አልተነፈግንም?
በተደራጀ መልኩ ጥቂቶች (በተለይ ከአንድ ዘር ነን የሚሉ) አልዘረፉም ነው የምትሉት?
ጥቂቶች ሆድ አደሮች ደግሞ ከየአቅጣጫው ተሠብስበው ከአደረጃጀቱ ስር ገብተው ሌላውን (የራሳችን የሚሉትን) ከጌቶቻቸው ጋር በመሆን አልዘረፉም? አልበደሉም? (እስካሁን የሚንደላቀቁብን አሉኮ!)
ምን እያላችሁ ነው?
በፈጠራ ታሪክ ጭምር (በነበረም ባልነበረም) አልተጋደልንም? ልብ ካደረግንና ቆመን ካሰብነውማ ከክፍለዘመን በፊት የተፈፀመ ታሪክ በምን ሒሳብ ነው የዛሬው ትውልድ መተላለቂያ የሚሆነው?
የማይገባ ነገርማ አለ፡፡ የእውቀት ማነስና ድንቁርና የሚባል በሽታ በስፋት አለብን፡፡ የደቦ አስተሳሰብ ተጣብቶናል፡፡ ብዙ ዩንቨርሲቲ ከፍተን የተማረ ደንቆሮ በስፋት አላመረትንም ነው የምትሉት? እየደነቆርን መመረቅማ ስናስበው  አስማት ነገር ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ በየኮብልስቶን ማምረቻው ድንጋዩ ድንጋይ ወቀረ እየተባልን ከራርመን ነበረ፡፡ ሰው ተምሮ ስራ ጠፋ፣ ስራ ሲሰጠውም አብዛኛው አያውቀውም አልንና ተባብለን ነበርኮ፡፡ ይሁንና አንዱን ትውልድ በጥላቻና በመሀይምነት ረሽነን ወደፊት ቀጥለናል፡፡ (መከራከር ካስፈለገ እንከራከራለን፡፡ ጥናትም ይሰራበትና ከሀሜት እንወጣለን፡፡) እስከዚያው አብዛኛውን እውነት ይዘን በገደምዳሜ እየደመደምን እናወራለን፡፡
ወቀሳና ክስ የሚያበዛ ሀሳባቸውን በመግለፃቸው  ጋዜጠኞች እየተሠደዱ፣ ጋዜጦች እንደ ቅጠል አልረገፉምን? /ግማሹ በራሱ ግማሹም በአፈናና በተደራጀ የማጥፋት ስራ እንደጨው ዘር ተበትነው አልነበረም?/
ጠንከር ብለው የሚታገሉ ሰዎች “ሳናጠፋህ ጥፋ” እየተባሉ አልተሰደዱም? ሰልፍ የወጡ በሰይፍ አልተቀጡም?
ጣት የጠቆሙ ጣታቸው አልተቆረጠም? በዜጎች መካከል ግንብ አልገነባንም? የሚያገናኙ ድልድዮችን እያፈረስን የጥላቻ ሀውልት አላቆምንም? የተማሩትን እያባረርን ያልተማሩ ፖለቲከኞችን አልተከልንም? የተማረ ሳይሆን ፖለቲካ የተጠመቀ ነው የሚያስፈልገን እያልን መማርን ወደ በረዶ ቤት አልከተትንም? (ስለዚህ እውቀትን ይኸው ለዘመናት አቀዘቀዝነው!)
ኢህአዴግማ በደንብ መከሰስ አለበት፡፡ ነበረበትም፡፡
ዋናው ነገር ግን ለቅሷችንን አቁመን ከዚያስ ብለን ስንጠይቅ ነው፡፡ ኢህአዴግን የህዝብ ሰቆቃና እምባ ጠራርጎ ካባረረው በኋላስ? ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ አብዝቶ ማወደስ ለጥቆ ለመውቀስ ያስቸግራል፡፡
በብርሃን ማጣት በኢህአዴግ ጭለማ ውስጥ ብንኖርም፣ በብልፅግና ደግሞ ነገሩ ሁሉ ብርሃን ባለማየቱ ምክንያት እንደ ኢህአዴግ ሁሉ ብልፅግናንም እንከስ ዘንድ ማን ይከለክለናል? (ለነገሩስ አባትና ልጅ ናቸው ይባላሉ፡፡) እንግዲህስ የሚያሸማቅቅ ይሉኝታችንን ወዲያ ብለን መጮህ ይኖርብናል፡፡
እናም እኔ ብልፅግናን እከስሳለሁ!
ሲጀመር የመጣውን ሁሉ መጠራጠር የጤነኝነት ምልክት አይደለም በማለት ልባችንን ገርበብ አላደረግንለትም ወይ? የሚመጣው ምንም ይሁን ምን መጥፎው በመወገዱ ብቻ ተደስተናላ፡፡ ጤነኛ ህዝብ በመብዛቱም ተስፋችን እንደ ማለዳ ፀሀይ ብርሃን ፈንጥቆ ልባችንን ይሞቀን ዘንድ ልክ ነበር፡፡
አገራችን የጋራ ልትሆን፣ ጥላቻችንን ልናስወግድ ነበር፡፡ በተማሩና ዘረኝነትን በሚፀየፉ፣ ሀገርን ከባዶ ካዝና ተነስተው በመደጋገፍ ለሚያስጉዙ፣ ወደ ብርሃን ማማ ለሚያወጡንና ፍትህን ፍትህ ለሚያደርጉ እንደግፍ ዘንድ ግድ ይለንም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ሱስ ስትሆን ማየት አያስደስትም ነው የምትሉት? ዘረኝነትን መጠየፍ እቅዳችን አልነበረም? የተጣላን ማስታረቅና ሁሉን ማቀፍ ለምን አያስደስትም? ሰዎች ነፃ ሆነው ሳይሸማቀቁ የሚኖሩባት አገር አትናፍቅም? ስደት የሌለበት፣ ዘረፋና ገረፋ የጠፋበት አገር በደንብ ይናፍቃል፡፡
ቶማስ ሳንካራን የብርሃን ጭላንጭል አድርገን ስናደንቅ ስለኖርን፣ የራሳችን ቶማስ ሳንካራ ቢመጣ ብለን አላሰብንም’ንዴ? (ፀልየን ነበር ወዳጄ!) እናም የሚገርመው ራሱን ቶማስ ሣንካራን የሆነ መሪ ብቅ ማለቱ!
ሲጀመርማ፡- ስለ አገር ዘረፋና ስለ ባዶ ካዝና የተነገረን ልክ ነበር፡፡ ስለ ዘረኝነት የሠማነው የኖርንበትን ስለነበር ተቀብለንዋል፡፡ ስለ አድሎ፣ ስለ ሙስና፣ ስለ ድንቁርና፣ ስለ ስንፍና፣ ስለ ስደት፣ ስለ ርሀብ፣ ስለ ጦርነት፣ ስለ ዝሙት፣ ስለ እስር፣ ስለ ስቃይ ... ወዘተ ስለ ሁሉም የተነገረን የነበረ ነው፡፡ ልክ ነው፡፡ ለማጥፋት ቆርጠን ተነስተናል መባሉንም የደገፍነው ለዚሁ ነው፡፡ ምኞት ሁልጊዜም አይከፋም፡፡
ችግሩ መሬት መውረድ ላይ ነው፡፡ ብልፅግናንም የምከሰው ለዚሁ ነው፡፡ አሁን ባለን ነባራዊ ሁኔታ ከተወራው ምን ተፈፀመ? ምን ቀነሰ? ምንስ ጨመረ? የዶክተር ዐቢይን መንግስት በተባባሰው የተደራጀ ዘረፋ፣ ልብ በሚሰብረው ማንነት-ተኮር የንጹሐን ጭፍጨፋ፣ በተስፋፋው ሙስና፣ በተጠናከረው አፈና፣ በተደራጀው መዋቅራዊ የዘር ፖለቲካ እከስሰዋለሁ፡፡ ብልፅግናን አውርቶ ባለመስራት፣ በመጠላለፍ፣ በተንኮልና በንቅዘት እከስሰዋለሁ።
ይገባናል፤ ጠቅላያችን ሣንካራን ለመሆን  እየጣሩ ነው፡፡ ከላይ የዘረዘርናቸውን ሁሉ ለመስራት ቃል ገብተው የነበር ቢሆንም የፈፀሙት ግን ጥቂቱን ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ብዙዎቹን ሞክረዋል፡፡ ለዚህም ሳላደንቃቸው አላልፍም፡፡   
ለጊዜው ፓርቲያቸውን ብከሰውም እርሳቸው ግን እንዳጀማመራቸው እንዲያልቅላቸው እመኛለሁ፡፡ ወጣቱና ተስፈኛው፣ አዲሱ የአፍሪካ የዲሞክራሲ ፋና፣ የሰላም መልእክተኛ፣ ምርጡ መሪ ተብለው በቀሪ ህይወታቸው ተከብረው በህዝባቸው መሀል እንዲኖሩ እመኛለሁ፡፡ 
በርግጥ ጠቅላዩ ንግግራቸውን በተረት እያዋዙ ሰዎችን መጎንተል ጀምረዋል፡፡ (እሰይ ደግ አረጉ፤ በአህያና በጅብ ምሳሌ ካልተነገረው ለማይገባው ህዝብ ይላሉ ካድሬዎቹ።) ብልፅግናም አትውቀሱኝ “ዝምቤን እሽ አትበሉኝ” ብሏል፡፡ እናውቃለን ይህን ያህል ህዝብ ተጨፈጨፈ ስንላችሁ፣ በበለፀገው አለም እንኳ ከዚህ የበለጠ ያልቃል ትላላችሁ፣ ሰው እየታረደ ያለው በዘርና በሀይማኖት ነው ስንላችሁ፣ የዚህና የዚያ ዘር ጠል ተስፋፋ የሚል አጀንዳ ታመጣላችሁ፡፡ ኑሮ ተወደደ ስንል፣ አለም አቀፋዊ ነው ትሉና ታባብሳላችሁ። ነዳጅ ጨመረ ብለን ስንጮህ አሜሪካ በዚህ ዶላር፣ ኬኒያ በዚህ ሽልንግ ይሸጣል የሚል ዜና ትሰራላችሁ፡፡ አፈና እንዲቀር ታገልን ትሉና አፈናውን በግልፅ ታፋፍማላችሁ፡፡ ምን ተሻለ? ኸረ ህዝቡን ስሙት ግድ የለም!
እኔ ግን በርግጥ ብልፅግናን እከሳለሁ!
(የግርጌ ማሳሰቢያ (ግር ብሎት እሰይ ይበላችሁ ለሚል) ፡- ይህ ማለታችንና ብሶት መናገራችን የቀድሞው ይሻለን ነበር ማለት አይደለም፡፡ የያዝነው እንዲቀየር እንጥራለን እንጂ በቀድሞ ሲኦል መኖርስ አንመኝም። ኢህአዴግስ ምናባቱ ዳግመኛ ጥቅሻውንም አያሳየን፡፡ የኢህአዴግ ነፍስ (ነፍስ ካለው) በሰላም አትረፍ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ በቀረበው ጽሁፍ የተንጸባረቀው ሃሳብ የጸሃፊው ብቻ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

Read 2896 times