Sunday, 10 July 2022 19:43

አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን መፍጠር ያስደስተኛል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የግል ሚዲያውን ለመታደግ የማስታወቂያ ህጉ መሻሻል አለበት

          አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው ይባላሉ። ሥራ ፈጣሪና ኢንቨስተር ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት “ናሁ“ ቴሌቪዥንን ጨምሮ የተለያዩ ኢንቨስትመንትና ኩባንያዎች  ባለቤት ናቸው፡፡ “ወደ 7 ገደማ ኩባንያዎችን ማቋቋም ችያለሁ፤ ህልሜም ሩጫዬም ገና ነው” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል ሪልስቴት፣ ሆቴልና አፓርትመንት፣ ሪዞርት፣ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ የግብርና ውጤቶች አስመጪና ላኪነት፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ  አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚገኙባቸው ይገልጻሉ፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ዛሬ በተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ስኬት ቢቀዳጁም በመንገዳቸው ብዙ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፤ከሃገር ቤት እስከ ሩቅ ምሥራቅ፡፡ ለመሆኑ ባለሃብቱ ከምን ተነስተው ነው ዛሬ ላይ የደረሱት? ምን ዓይነት ፈተናዎችን ተጋፍጠው በድል ተወጡ? የስኬት ምሥጢራቸው ምንድን ነው? የህይወትና የሥራ ፍልስፍናቸውስ? ሁሉንም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በስፋት አውግተውታል፡፡ እነሆ፡-


          እስቲ ስለ ትውልድዎና ዕድገትዎ ይንገሩን ?
እኔ ብዙም የተለየ ህይወት የለኝም፡፡ ቀለል አድርጌ ለመግለፅ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ የተወለድኩት ሰፈረ ሠላም አካባቢ ነው፡፡ ያደግሁት ደግሞ  ኦልድ ኤርፖርት፣ ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ ነው። እዚያው ያደኩበት አካባቢ ባለው ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ተማርኩ፡፡ ከዚያ ሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተግባረዕድ ተምሬ፣ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው፣ ከለውጡ በፊት ወደ ድሬድዋ ሄድኩ፡፡ ድሬድዋ ትንሽ ቆየሁና ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ።  አዲስ አበባ በስራ ላይ ትንሽ ቆይቼ ወደ ጃፓን ሄድኩ፡፡ ጃፓን እንደሄድኩ ቴክኒክ ት/ቤት ነው የገባሁት። ጎን ለጎን ለመኖር  ስራ መስራት እንዳለብኝ  ወስኜ፣ የጃፓንኛ  ቋንቋ ተምሬያለሁ፡፡ ከጃፓን በኋላ ደግሞ ወደ ቻይና ነው ያመራሁት፡፡ ቻይና ስደርስ እንግዲህ ጠቅልዬ ወደ ንግድ ዓለም ገባሁ ማለት ነው፡፡ በቻይና  ለዘጠኝ ዓመት በንግድ ስራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚያም በኛ ሚሊኒየም ላይ ሃገር ያቀረበልንን ጥሪ ተቀብዬ ወደ ኢትዮጵያ ገባሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ በተለያየ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ነው የተሰማራሁት፡፡ እንደገናም ወደ ትምህርት አለም ተመልሼ፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ተምሬያለሁ፡፡
አስተዳደግዎና የቤተሰብዎ ሁኔታ እንዴት ነበር?
እኔ ከነጋዴ ቤተሰብ አይደለም የመጣሁት፡፡ አባቴ ወታደር ነው፡፡ ለሃገሩ ሲሰራ የነበረ ሰው ነው፡፡ ስለ ንግድም ብዙ እውቀት አልነበረውም። እኔ ወደ ንግዱ የመግባት ፍላጎቱ ያደረብኝ በእናታችን ሞት ምክንያት ወደ ድሬድዋ በሄድኩበት አጋጣሚ፣ የንግድ እንቅስቃሴውን በመመልከቴ ነበር፡፡ ከድሬድዋ ወደ አዲስ አበባ  ስመለስም ባዶ እጄን ነበርኩ፡፡ እንደ ማንኛውም ወጣት አዲስ አበባ ላይ ስራ መፈለግ ነው የጀመርኩት፡፡ በወቅቱ ስለ አለም የተለያዩ ሚዲያዎችን አዳምጥ ነበር፡፡ ከዚያ በመነሳት ብዙ መስራት አለብኝ ብዬ አብዝቼ አስብ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ላይ በወቅቱ የቱሪስት  አስጎብኝና ጉዞ ድርጅት ውስጥ ለመስራት እፈልግ ነበር። በየቦታው መዞር ስለምፈልግ ያንን ስራ ነበር ሳፈላልግ የነበረው፡፡ ቀንቶኝ መጀመሪያ ያገኘሁት ሥራ  ሳፈላልግ የነበረው አይነት ነው። ነገር ግን ያንን ስራ ስሰራ  የነበረው ደመወዝ ተከፍሎኝ አልነበረም፡፡ ቀጣሪዬን “ግዴለህም በጣም ጠቀሚ ሠራተኛ እሆናለሁ” ብዬው ነበር የተቀጠርኩት፡፡

ሰውየው በሚዲያም ይታወቃል፡፡ ሞላ ዘገየ ይባላል፡፡ ስራውን ስጀምር ጠረጴዛና ወንበር አልተሰጠኝም። ብቃቴንም ማየት ስለሚፈልጉ እንዲሁ ነበር  የምሰራው፡፡ እንደ ኮሚሽን ሠራተኛ ስራ እያመጣሁ ነበር የምሠራው፡፡ በወቅቱ የ100 ሺህ ብር ስራ ካመጣሁ 10 ሺህ ብር ትሰጡኛላችሁ ስላቸው ስራውን ካመጣህ ምን ችግር አለው የሚል ነበር ምላሻቸው፡፡ በዚህ መልኩ ከተስማማን  በኋላ በመጀመሪያ ያሰብኩት ነገር በኢትዮጵያ ውጪ ስለመጓዝ ነበር፡፡ ያልተሞከረ ነገር መሞከር አሰብኩና ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ወደ ግብፅ ሃገር ሄደው እንዲጎበኙ እድል ማመቻቸት ጀመርኩ፡፡ አለቃዬ በሃሳቤ ተስማማ፡፡ እኔ በወቅቱ ስለ ግብፅ ከማንበብ ባሻገር ግብፅን በአካል አላውቃትም፡፡ መቼም የጉዞ አሰናጅ ሆኖ ወደ ግብፅ ለመሄድ ያሠበ ሰው ካለ፣ በመጀመሪያ  ስለ ሃገሪቱ ብዙ ማወቅ አለበት። እኔ ግን እንዲሁ በድፍረት አንድ የጉዞና የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጀሁ፡፡ ያንን ለህዝቡ ለማስተዋወቅ ማስታወቂያ ማስነገር ያስፈልግ ነበር፡፡ በወቅቱ ደግሞ በድርጅቱም ሆነ በኔ በኩል ያንን ማስታወቂያ ማስነገር የሚያስችል ገንዘብ አልነበረንም፡፡ በወቅቱ ያደረግሁት ቢኖር ከእህቴ የተሰጠችኝን አንድ ትንሽዬ መኪና ነበረችኝ፡፡ እሷን መኪና በ14 ሺህ ብር ሸጥኳትና አራት ሺህ ብር ለቴሌቪዥን ማስታወቂያ ከፈልኩኝ፡፡ ይሄን ሳደርግ ግን በወቅቱ ስራውን ለመስራት ካለኝ ጉጉት እንጂ ከቀጣሪዬ ጋር በወጉ እንኳ የስራ ቅጥር ውል አልነበረኝም፡፡ ያ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ሲተላለፍ አለቃዬ ቤቱ ቁጭ ብሎ ይመለከታል፡፡ “ፒርስ ትራቭል ኤጀንት ወደ ግብፅ ሃገር የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቷል” የሚል ማስታወቂያ ሲያይ ደነገጠ። አልነገርኩትም ነበር፡፡ ጠዋት ስንገናኝ ማን ነው ይህን ያደረገው አለኝ፤ እኔ ነኝ አልኩት፡፡ እንዴት ገንዘብ ከየት አመጣህ አለኝ፡፡ መኪናዬን ሸጬ አልኩት… እንዴ ሰው ባይመጣስ አለኝ… ግዴለህም ይመጣል አልኩት፡፡
ያኔ ይህን ያህል ሃላፊነት ለመውሰድ ለምን ፈለጉ?
ትልቁ ቁምነገር የስራው ፍላጎት ነበረኝ፤ ህይወትን  መለወጥ የሚቻለው ዋጋ ተከፍሎ ነው በሚለው አምን ነበር፡፡ ብዙ ሰው ያለውን አጥቶም ቢሆን አዲስ ነገር መሞከርን እንደ እብደት  ሊያየው ይችላል፡፡ እኔ ግን በህይወቴ ብዙ ውጣ ውረድን ያሳለፍኩ ስለሆንኩ ብዙ ነገር ተምሬአለሁና እንዲህ አይነቱን ውሳኔ አልፈራም፡፡ ያው ግን እንዳሰብነው ብዙ ሰው ግብፅን መጎብኘት ይፈልግ ነበርና፣ ቢሮአችን በሚመዘገቡ ሰዎች ተጨናነቀ፡፡ ካሰብነው በላይ ሰው ተመዝግቦ፣ የመጀመሪያውን ጉዞ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ አደረግን ማለት ነው። ግብጽን አላውቃትም ነበርና ከተጓዦች አንድ ቀን ቀድሜ ገብቼ በፍጥነት ያሉትን ነገሮች በሙሉ ተመለከትኩና እንግዶችን ደግሞ አስጎበኘሁ ማለት ነው፡፡ ያንን የጉዞ ፕሮግራም አዘጋጅተን ስንጨርስ ታዲያ 50 ሺህ ብር ትርፍ አገኘን፡፡ ያችን የሸጥናትን መኪና ተክቼ ለኩባንያውም የነበረበትን እዳ ከፈልኩ ማለት ነው፡፡ ከዚያም የኩባንያው መደበኛ ቅጥር ሆኜ በጉዞ አሠናጅነት፣ ለአንድ ለሁለት ዓመት ሠራሁኝ። እንግዲህ ትልቅ ገንዘብ እጄ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ  በዚህ አጋጣሚ ነበር የገባው። ከዚያ በኋላ ወደ ጃፓን ሃገር  ነው ያቀናሁት፡፡
ጃፓንን ለምን መረጧት? የተለየ ምክንያት ነበረዎት?
ብዙ ሰው ጃፓን ለምን ሄድክ? ይለኛል። እኔ ግን በወቅቱ አማራጭ አጥቼ ነው ጃፓን የሄድኩት፡፡ አውሮፓ፣አሜሪካ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም ነበርና ወደ ጃፓን ሄድኩ፡፡
በወቅቱ እዚህ ባለው  ስራዎ ስኬታማ ከነበሩ ለምን ስደትን መረጡ?
 አንደኛ በጣም ወጣት ነበርኩ፤ ሥራውም ያን ያህል የተፍታታ አልነበረም፡፡ እንደ እኔ አይነት ብዙ ፍላጎት ላለው ሰው ምቾት የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ከመሄዴ በፊት የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመስራት አየር መንገድን ጨምሮ ለማናገር ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ከልጅነቴም  የተነሳ ሊሆን ይችላል በሩን የከፈተልኝ በወቅቱ አልነበረም። ሁኔታዎች ከባድ ነበሩ፡፡ የለውጡ አካባቢም ስለነበር ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምን ወጥቼ አልሞክረውም ብዬ  ነው የወጣሁት፡፡
ጃፓን እንዴት ተቀበለችዎ?
የሚገርመው ጃፓኖች ጥሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች አይደሉም፡፡ የኔም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ያን ያህል አልነበረም፡፡ ጃፓንኛም አላውቅም፡፡ እዚያ የማውቀው ኢትዮጵያዊም አልነበረም፤ ገና ኤርፖርታቸው ስደርስ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን አካባቢ ነበር ማፈላለግ የጀመርኩት፡፡ እዚያ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ናቸው የነበሩት፡፡ ጃፓንን ቶሎ ለመልመድ አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንደው ባጭሩ ለመግለፅ አጋጣሚው በህይወት ውስጥ ፍዳ ያየሁበት ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ያ መከራ ግን አላቆመኝም፡፡ ከብዙ መቸገር በኋላ ስራ አገኘሁ፡፡ ያንን ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ በዚያው መላመዱ መጣ፡፡ እዚህ ላይ ባጫውትህ  ደስ የሚለኝ አንድ ገጠመኝ ነበረኝ፡፡ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ስሰራ እሳት ይነሳል፡፡ በኛ ሃገር እሳት ሲነሳ  የለመድነው ተሯሩጠን የመብራት ቆጣሪ ማጥፋት  ነው፡፡ እኔ ይሄንን ይዤ እዚያ ፋብሪካ ውስጥ እሳት ሲነሳ ሮጬ ባልቦላውን አጠፋሁት። እሳቱም ጠፋ፡፡ በወቅቱ በኔ ቤት የሚያሸልም ስራ የሠራሁ ነበር የመሰለኝ፤ ነገር ግን በማግስቱ ቢሮ  ተጠራሁና “ለምን ይሄን አደረግህ፤ በል ከእንግዲህ ላንተ የሚሆን ቦታ የለንም” ብለው ከስራ አሰናበቱኝ፡፡
ለምን?
ምክንያቱም ጃፓኖች በባህላቸው ለአለቆቻቸው ፍፁም ታዛዥ ናቸው፡፡ እነሱ ሳያዟቸው ምንም ነገር አያደርጉም፡፡ አዛዥ 5 በመቶ ቢሆን፣ ሌላው ጠቅላላ ታዛዥ ነው። አለቃ ያለውን ነገር መፈፀም ግዴታ ሲሆን ያላዘዘውን መፈፀም ወንጀል ነው፡፡ በዚያ የተነሳ ከሥራዬ ተሰናበትኩ፡፡  የዚያች ቀን መንገድ ላይ ስሄድ፤ “እኔ በህይወት ዘመኔ ጭራ ሳልሆን ራስ ሆኜ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ” እያልኩ ለራሴ እየነገርኩት ነበር፡፡ “ስለዚህ ያለቦታዬ ነበር የገባሁት፤ እግዚአብሔር አልፈቀደውም፤ ራሴ  የምመራውን ኩባንያ መመስረት አለብኝ” ብዬ ነው ያሰብኩት፡፡ ይሄን ሣስብ ግን ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ ጃፓን ውስጥ ደግሞ ሲሆን በጣም ከባድ ነው፡፡ ግን በጣም ብዙ ትግሎች አድርጌ ትንሽ ኩባንያ አቋቋምኩ፡፡ ምናልባት ጃፓን ሃገር የራሱን ኩባንያ ያቋቋመ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሳልሆን አልቀርም፡፡
ኩባንያው ምን የሚሰራ ነበር?
በመጀመሪያ ያገለገሉ መኪናዎችን እየሰበሰብኩ እየጠጋገንኩ፣ ወደ ሌላ ሃገር እልክ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ ሌዘር ፕሪንተር ካርትሬጅ ማኑፋክቸር ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መማርና መስራት ጀመርኩ፡፡ በብዙ መከራ ፋብሪካ አቋቁሜ አሮጌ እቃዎችን መልሶ በማደስ ለሽያጭ ማቅረብ ጀመርኩ፡፡ እየሰራሁ በደንብ እያደግሁ መጣሁ፡፡ ነገር ግን ስራዬ ቢያድግም ለቤት ኪራይ፣ለሠራተኞች ደመወዝ፣ ለፋብሪካ ኪራይ ከፍዬ መኖር እቸገር ነበር፡፡ ስለዚህ  ለ12 ሰዓት ያህል በፋብሪካ ከሰራተኞቼ ጋር አብሬያቸው  እሰራና ሌሊት ደግሞ ሌላ ቦታ ተቀጥሬ እሰራ ነበር፡፡ 7 ዓመት ገደማ ጃፓን ስኖር  ከአራት ሰዓት በላይ ተኝቼ አላውቅም ነበር፡፡ ሌላ ጋ ተቀጥሬ ያመጣሁትን ገንዘብ ለሠራተኞቼ ደሞዝ እከፍል ነበር፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ እየሠራሁ፣ ኩባንያውም እያደገ ሲመጣ አንድ ቀን ከጃፓን መንግስት ኢምግሬሽን ቢሮ ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠራሁ፡፡ መልካም ነገር ይገጥመኛል ብዬ ነበር ወደ ቢሮው ያመራሁት፤ የጠበቀኝ ግን ሌላ ነገር ነበር፡፡ “ከኢትዮጵያ የመጣኸው በሌላ ቪዛ  ስለሆነ ኢንቨስተር ሆነህ እዚህ ፋብሪካ አቋቁመህ መስራት አትችልም፤ ስለዚህ ከሃገር ወጥተህ እንደገና የቢዝነስ ቪዛ ይዘህ መምጣት አለብህ!” ተባልኩ፡፡ ብከራከርም አልተቀበሉኝም፡፡ እዚያው ያለኝን ንብረት ትቼ 5 ሺህ ዶላር የማትሞላ ገንዘብ ይዤ፤ ከጃፓን ተባርሬ ወጣሁ፡፡ ያለምንም ክሊራንስ ባዶ እጄን ንብረቴን ጥዬ ነበር የወጣሁት፡፡ በወቅቱ ትራንዚት ያደረግኩት ታይላንድ ነበር፡፡ በዚያ ሰዓት ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፤ ቤተሰብ የሚያውቀው ፋብሪካ እንዳለኝ፣ ጥሩ ገቢ እንደማገኝ  ነው፡፡ ታዲያ ምን ይዤ ወደ ሃገር ቤት ልመለስ? ባጋጣሚ አየር መንገድ የሚሰራ አንድ ወዳጄን አገኘሁትና  የደረሰብኝን ሁሉ ነገርኩት፡፡ እኔ እና እሱ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ እያወራን ሳለ የምጓዝበት አውሮፕላን አመለጠኝ፡፡ ወዳጄ በደረሰብኝ ነገር  በጣም ስላዘነ አንድ ነገር መከረኝ፡፡ “ወደ ሆንግ ኮንግ ሄደህ ቪዛ ይዘህ ና” አለኝ፡፡ የ15 ቀን ቪዛ እንደሚሰጡ ነገረኝ። እኔም እንደተባልኩት አደረኩኝ፡፡ ወደ ሆንግ ኮንግ ሄጄ የ15 ቀን ቪዛ ይዤ  ተመለስኩ፡፡ ወደ ታይላንድ እንደተመለስኩኝ፣ እጄ ላይ በቀረችው 2 ሺህ ዶላር አንዳንድ ስራዎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከቱሪስቶች ጋር የተያያዙ ስራዎች ነበሩ፡፡ በ6 ወር ውስጥ ምንም በማላውቀው ሃገር እንደገና በእግሬ መቆም ጀመርኩ፡፡ በብዙ ትግል ሰው ሆንኩ፡፡ ነገር ግን ታይላንድ ብዙም እንደማያሳድገኝ ስላየሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ጀመረ ሲባል፣ እንደገና ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ቻይና ተሰድጄ ገባሁ፡፡ ቻይኖች እንግሊዘኛ አያውቁም፡፡ ትልቅ የቋንቋ ችግር ገጠመኝ፡፡ እንደአጋጣሚ አየር ማረፊያ ውስጥ ያገኘኋቸውን አረቦች ነበር እየተከተልኩ ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ እነሱ የሚሰሩትን የሚያደርጉትን ሁሉ በትኩረት እከታተል ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ነዴጋዎች ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር ስንቀሳቀስ ባጋጣሚ ለኢትዮጵያዊም ለአፍሪካዊም የሚሆን ሰፊ የስራ እድል  እንዳለ ተረዳሁ፡፡ በቃ ይሄ ሃገር የኔ የመጨረሻ ማረፊያዬ መሆን አለበት አልኩ። የኔ የቢዝነስ መነሻ ይሄ ሀገር ነው ብዬ አመንኩ። ወዲያው ትንሽዬ ቢሮ ነገር ተከራየሁ። ያቺን ቢሮ በተከራየሁ በአመቱ ሚሊዮን ብር እጄ ገባ።
የጀመሩት ሥራ ምን ነበር?
በቻይና ፋብሪካዎችና በአፍሪካውያን ሸማቾች መካከል ትልቅ ክፍተት መኖሩን ተገንዝቤ ነበርና፣ ያንን ክፍተት መጠቀም ነው የጀመርኩት። በወቅቱ የቻይና ፋብሪካዎች በአፍሪካ አገራት ገበያ ይፈልጉ ነበር ። ይሄንን ስረዳ ቀርቤ እያናገርኩ በኮሚሽን ለብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት የገበያ እድሎችን የማመቻቸት ስራ ጀመርኩ። በኮሚሽን ስራ እንዲሁም በመርከብ የሚጫኑ እቃዎችን ሂደት የመከታተልና የማዘጋጀት ስራዎችን እሰራ ነበር። ይሄ ትልቅ ቢዝነስ ነበር። በወቅቱ ቻይናዎች እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ስላልነበሩ እኔ ያንን ክፍተት በመጠቀም ነው ጉድለታቸውን ስሞላ የነበረው። በዚህ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮን ብር ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን ዶላር ምን እንደሆነ ማየት ቻልኩ። እውነቱን ለመናገር ፈጣንና ጠንካራ ሰራተኛ ነበርኩ። በአፍሪካውያኑም በቻይናውያኑም እታመን ነበር። በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ስራ ኤጀንትነትን ወሰድኩ። በቀላሉ አየር መንገዳችንን በዚያ እያገዝኩ ለራሴም ገቢ አገኝ ነበር። እኔ በቢዝነስ አለም አዳዲስ ፈጠራዎች ናቸው የሚያስደስቱኝ። አሁንም ያሉት እነ “ካሽጎ” እና “ጉዞጎ” የኔ ናቸው። ፈጠራ ላይ በጣም መስራት እወዳለሁ። በትንሹ ጀምሬ ወዲያው ሌላ የቢዝነስ ፈጠራ ውስጥ ነው መግባት የምፈልገው። ቻይና ሳለሁ እንደ አልማዝ፣እንቁ፣ትልልቅ ብራንድ የሆኑ ሰዓቶችና፣ ጌጣጌጦች-- እንዴት ነው ከሃገር ሃገር የሚጓጓዙት የሚለውን ለራሴ ጠየኩና፤መቼም እነዚህ ንብረቶች እንደነ ዲኤች ኤል ባሉት ሊላክ አይችልም ብዬ ጉዳዩን ማጥናት ጀመርኩ። በኋላ ስገነዘብ እነዚህ ውድ እቃዎች ራሳቸውን ችለው የሚመላለሱበት መንገድ አልነበረም። ይሄን ክፍተት መሙላት አለብኝ ብዬ በኦንላይን የሚገበያዩ ውድ እቃዎችን የማጓጓዝ ስራ ጀመርኩ ማለት ነው። ያው የሚጓጓዘው እቃ ውድ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገውም የማጓጓዣ ገንዘብ ትልቅ ገንዘብ ነው የነበረው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ገንዘብ ሰራሁበት ማለት ነው። ያንን እየሰራሁ ሳለ ነው እንግዲህ በሚሊኒየሙ ጊዜ “ወደ ሀገር ግቡና ስሩ” ተብሎ ጥሪ ሲደረግ፣ ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ምን ገጠመዎት? በምን ሥራ ላይስ ተሰማሩ?
እውነቱን ለመናገር በወቅቱ የነበረው ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ ተግዳሮት ነበር የገጠመኝ። እንደውም በሌሎች ዲያስፖራዎች ላይ ከደረሰው የከፋ እንግልት ነበር የገጠመኝ። ግን “ብረት በተቀጠቀጠ ቁጥር ይጠነክራል” እንደሚባለው፣ ፈተናዎች የበለጠ አጠንክረውኝ ነበር። እንደመጣሁ ሪል እስቴት ቢዝነስ ውስጥ ነበር የገባሁት፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ጉዳዬን ይዤ ወደ ቢሯቸው ስሄድ አያምኑኝም ነበር። በመጨረሻ ግን ኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ አካባቢ ሰው አልፈልግም ብሎ የተወውን ቦታ፣ ለምን ሄዶ አይሞክርም ተብሎ ቦታው ተሰጠኝ፡፡ እዚያ ጫካ ውስጥ መዋኛ ጭምር ያለው መኖሪያ ቤት  ሰራሁኝ። በወቅቱ ከሰው ርቆ ጫካ ውስጥ በመሆኑ አንዳንዱ እንደ እብድ ይቆጥረኝ ነበር። እዚህ ውስጥ ማነው መጥቶ የሚኖረው? እያሉ ያሾፉብኝ ነበር። ግን አላማና ራዕይ ስለነበረኝ  ስራውን ቀጠልኩበት፡፡ የተወሰኑ ቤቶች ሰራሁና ጨረስኩ። ግን በዚሁ መሃል ብዙ ፈተናዎች ነበሩብኝ። መንግስትን ያኔም እተች ነበር፤ ዛሬም ሲያጠፋ እናገራለሁ። በነዚያ ንግግሮቼ አልወደድም ነበር። በየስብሰባው የምናገራቸው ነገሮች ጥላቻን አትርፈውልኝ ነበር። በዚህም ብዙ ፈተና አይቻለሁ። በወቅቱ የፖለቲካው አባል መሆን ወይም የሆነ ዘር ውስጥ ማረፍ እንዳለብኝ ይነገረኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ አባቴም እናቴም የማን ዘር  እንደሆንኩኝ አልነገሩኝም። “ኢትዮጵያዊ ነህ” ብቻ ብለው ነው ያሳደጉኝ። ከኢትዮጵያዊነቴ ውጭ ሌላ የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ትናንትም ዛሬም የትኛውም ዘር ውስጥ መውደቅ አልችልም። በወቅቱ ለፖለቲካው የቀረበው ሰው በዘሩ ተመርጦ፣ ታክስ የማይከፍልበት፣ ሌላው ከሚገባው በላይ የሚከፍልበት፤ በዚህ ሰበብ ፍዳውን የሚበላበት ጊዜ ነበር። ሲያሻቸው የቅንጅት አባል ነህ ይሉኝም ነበር። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ከሃገር ስወጣ ጥሩ ነገር ያለ ሲመስለኝ፣ ደግሞ ስመለስ እንዲሁ ስባክን ነበር የቆየሁት። በጣም ያንገላቱኝ ነበር። በታክስ ሰበብ ብዙ ንብረቶቼ ተሸጠውብኝ  ወደ ነበርኩበት ቻይና ለመመለስ ተገድጄ ነበር። በኋላ አቶ ሃይለማርያም ሲመጡ ደግሞ ከ3 መቶ ሺህ ብር ያልበለጠ ካፒታል ይዤ መጣሁ፤ ግን በዚያ ካፒታል የጀመርኳቸውን ፕሮጀክቶች ጨርሼ ኢንቨስትመንቴን አስፋፍቼ፣ አሁን ላይ ከ7 ያላነሱ ኩባንያዎች አሉኝ ማለት ነው። ከ1250 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችለናል። በቴክኖሎጂው፣ በሚድያው፣ በሆቴል፣ በሪልስቴት፣ በሪዞርት፣ በኢምፖርት፣ በኤክስፖርቱ የቢዝነስ ዘርፎች ኩባንያዎች አሉን፡፡ አሁንም ደግሞ የበለጠ ለማደግ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን።
በሚድያው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?
እንግዲህ ወደ ሚድያው ስመጣ፣ በመጀመሪያ ከእነ አማረ አረጋዊ ጋር ሆነን አርትስ ቲቪን ማቋቋም ነበር የጀመርኩት፡፡ በኋላ እሱ ሲዘገይብኝ የራሴን ድርሻ ለሌላ ሰው ሸጥኩና ናሁ ቲቪን ገዛሁት። አገር እንድታድግ ከተፈለገ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ለውጥ ደግሞ ሚድያው ወሳኝ ሚና አለው ብዬ አምናለሁ። ሚድያ አራተኛ መንግስት ነው። ይሄ የሚሆነው ግን መንግስት ሲፈቅድና ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ ሲቻል ነው። በወቅቱ የለውጥ ስሜት በየአቅጣጫው የሚታይበት፣ ከፍተኛ ትግል ሲካሄድ የነበረበት ጊዜ ነበር። እኔም ለውጡን ከሚፈልጉት አንዱ ነበርኩ። በወቅቱ በተለይ በንግዱ አለም ያለን ሰዎች በእኩል አንስተናገድም ነበር። ከፍተኛ መድሎ ነበረብን። ስለዚህ ያ መለወጥ አለበት የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ። ኋላም ወደ መባቻው አካባቢ “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል በቴሌቪዥን ጣቢያው ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ  የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ችለናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪዝን ብሬክ ፊልምን “ሳቂ ሳንቃ” ወይም “እስር ቤቱን ሰብረህ ውጣ” በሚል ተርጉመን እናስተላልፍ ነበር። ያንን ያደረግነው ለውጡ ፈፅሞ መቆም የለበትም በሚል አቋም ነበር። ፊልሙንም ወቅቱን ጠብቀን አስበንበት ነበር ያቀረብነው። በወቅቱ የነበረው አማራጭም ለውጡን ወደፊት መግፋት ስለነበር በቁርጠኝነት ነው ትግል ስናደርግ የነበረው። ያኔ ወደ ኋላ ብንመለስ አይሆንም ነበር። ወጣቱ ድንጋይ ይዞ ክላሽ ፊት ቆሞ  ሲታገል ነበር። ያ ትግል ወደ ኋላ ፈፅሞ አይመለስም ነበር፡፡ እኛም ለውጡን ወደ  ኋላ እንዳይመለስ ነው በተለያየ ጥረት የደገፍነው።
የሚድያ ስራ ትርፋማ ነው እንዴ?  
ፈፅሞ አይደለም። የህዝብ (መንግስት) ሚድያ ሲሆን የመንግስት በጀት ነው የሚጠቀመው፡፡ ያም ሆኖ ማስታወቂያውንም በብቸኝነት የያዙት እነሱው ናቸው። የግሉ ሚድያ በጀት የለውም፡፡ ማስታወቂያም አያገኝም። ታዲያ እንዴት ነው ውጤታማ የሚሆነው? የመንግስት በጀት የሚመደብላቸው ሚድያዎች፣ ማስታወቂያውንም በብቸኝነት በያዙበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። እኛ ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ስናነሳኮ የሳሙና ማስታወቂያ እንኳ ለማስነገር ደንበኞች ይፈራሉ። ታስፈርጀናለህ ይላሉ፡፡ ስለዚህ በሁሉም የሚጎዳው የግሉ ሚድያ ነው። በዚያው ልክ የመንግስት መስታወት የሚሆኑት ደግሞ ከመንግስት ይልቅ የግሉ ሚድያዎች ናቸው። የመንግስት ሚድያዎች እኔና አንተ በምንከፍለው ታክስ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ይህ ብቻ አይበቃቸውም፤ ማስታወቂያውን ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ያለውን ለብቻቸው ተቆጣጥረው ይይዛሉ። ጋዜጦች ዛሬ ላይ በመጥፋት ላይ ናቸው። መንግስት ታክስ እንዳይከፍሉ ማድረግ አልያም ወረቀት በነፃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። ትውልድ ያንብብ ይወቅ እያልን በሌላ ጎን ትውልድ እንዳያነብ የሚያደርጉ እክሎችን ማብዛቱ የሚደገፍ አይደለም። የማስታወቂያ ህጉ መስተካከልና ለሁሉም ፍትሀዊ መሆን አለበት። እኔ አሁን ናሁ ቲቪን በየወሩ ከሌላው ኩባንያ ገቢ ከ1 ሚሊዮን ብር  በላይ እየደጎምኩት ነው ያለው፡፡ ግን እስከ መቼ ይደጎማል? አንድ ቀን ይደክመንና ልንተወው እንችላለን። እኔ ግርም የሚለኝ ባለሃብቱም ትክክለኛ ድምፅ ሊሆነው የሚችለው የትኛው ሚድያ እንደሆነ አልገባውም። አንድ ችግር ቢደርስበት ድምፅ የሚሆነው እኮ የግል ሚዲያ ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ ሲዘጋ የሱም አንደበት እየተዘጋ መሆኑን አይረዳም፡፡ ጭራሽ አፉን የሚዘጋለት የመንግስት ሚዲያው ላይ ነው ሄዶ የሚያስተዋውቀው። ጉዳዩ የእውቀትም የግንዛቤም ችግር ነው። እኔ የፈለገ ቢመጣ የመንግስት ሚዲያ ላይ አላስተዋውቅም፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ የበለጠ ጉልበት ነው የምሰጣቸው፡፡ ጉልበት በተሰጣቸው ቁጥር ደግሞ መንግስት የበለጠ የፈለገውን እንዲያደርግ ዕድል እየሠጠኸው ነው የምትሄደው፡፡ መንግስትን መግራት ከፈለግህ የግል ሚዲያን ደግፍ አበርታ፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
በፈተናዎች መሃል አልፈው ለስኬት የበቁበት ምስጢር  ምንድን ነው?
ከሁሉም በላይ ምንም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም። ስወድቅ እልህ ይይዘኛል እንጂ በዚያው ተስፋ ቆርጬ አልቀርም፡፡ በተሻለ ጉልበት በድጋሜ እስክነሳ እንቅልፍ የለኝም። ሁልጊዜ የመሪ ሀሳብ እንጂ የተመሪነት መንፈስም ሀሳብም ፈፅሞ የለኝም። እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካሮች ነን፤ ሃሳባችን ትልቅ ነው። ትንሽ እንቅልፍ ቀንሰን በብዙ ማሰላሰል ከሰራን ምንም ነገር ማድረግ ይቻለናል። እኔ የተሸናፊነት ስሜት ፈፅሞ የለኝም። ስኬቴ እንጂ የዛሬው ስህተቴ አይታየኝም። ብዙ የመዝናናት ህይወት አላውቅም፤ ለኔ ህይወት ስራ ነው። ከመዝናናት በላይ የምመርጠው ቁጭ ብዬ ያሉ ክፍተቶችን ማጥናትን ነው፡፡ ወደ አንድ ቦታ ስሄድ ምን እድል አለ የሚለውን ነው ማየት የምፈልገው። ሁልጊዜ የማየው እድሎችን ነው። አንዱ ሲበላሽብኝ ወደ ሌላው አማራጭ ነው ምሄደው። የኔ ህይወት እረፍት የለውም፡፡ ዛሬም ትግል ላይ ነኝ። ገና ብዙ ማሳካት የምፈልጋቸው ነገሮች አሉኝ። ሲቀጠቅጠኝ የነበረው መንግስትም በኋላ ልፋቴንና ድካሜን አይቶ ሸልሞኛል። ለኔ ያ ቀን ልዩ ነበር፡፡  ለሁሉም ጊዜ አለው።
በእርስዎ  ህይወት ውስጥ ፈታኝ የሚሉት ጊዜ የቱ ነው?
ያለ ፈተና የሆነ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በህይወቴ የማልረሳቸው ከፍተኛ ዋጋ የከፈልኩበት የጃፓን ህይወቴ እና በመጨረሻ ከኢትዮጵያ ልሰደድ የነበርኩበት ጊዜያት ናቸው፡፡ እነዚህን በተለየ አነሳሁልህ እንጂ ብዙ ውጣ ውረዶች ናቸው በህይወቴ የገጠሙኝ፤ ግን እግዚአብሔር ቅን አምላክ ነው፡፡ እኔን በነዚያ እሳቶች ውስጥ እንዳልፍ አድርጎኛል። ዛሬ ለኔ ብዙ ነገር ብርቅ አይደለም፡፡ በ37 ዓመቴ ጥሩ ገቢ ኖሮኝ፣ አውሮፕላኖች ኖረውኝ፣ ብዙ ነገሮች አይቻለሁ፡፡ ለኔ በዓለም ላይ ምንም ነገር ብርቅ አይደለም፡፡ ያንን ህይወት እንዳልፍ ወይም እንዳውቅ ያደረገኝ ግን በብዙ የህይወት ውጣ ውረድ ማለፌ ነው፡፡ ስለ ረሃብ አውቃለሁ፤ ምክንያቱም ርቦኝ ያውቃል፡፡ ስለ ሃዘን ጭንቀት አውቃለሁ፤ ደርሰውብኝ አልቅሼ ስለማውቅ። የሰው ልጅ ቸገረኝ ሲል አውቃለሁ፤ እኔም ተቸግሬ ሰው ረድቶኝ ስለማውቅ፡፡  ያንን   አድርጌ ባላልፍ ኖሮ ዛሬ ቅልል ያለ ህይወት አይኖረኝም ነበር፡፡ በእግሬ ሄድኩኝ በመኪናም ምንም አይገደኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በእግሬ እሄዳለሁ፣ የትም  ቦታ  ከሰዎች ጋር ቁጭ ብዬ  የልቤን አውርቼ ወደ ቤቴ እገባለሁ፡፡ የሰውን ልጅ በገንዘቡ ባለው ሃብት ለክቼ አላውቅም፡፡ እንደዚያም እንዳደርግ አይምሮዬ አይፈቅድም፡፡ ፈጣሪዬንም ሁሌ አመሰግነዋለሁ፡፡ በብዙ ፈተና የተፈተንኩ ነኝ፤ ሰዎች ፈተና ሲገጥማቸው እኔም ያለፍኩበት ነውና በእጅጉ እረዳለሁ፡፡
የወደፊት ህልምና ራዕይዎ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ፣በዓለም ደረጃ ብዙ ነገር ለመስራት አስባለሁ፡፡ በአለም ደረጃ ታዋቂ ሊያደርገን የሚችል ነገር ሰርቻለሁ። ምቀኛው በዛበት እንጂ  “ካሽጎ” የኔ ፈጠራ ነው። ዛሬ አሜሪካኖች “ካሽጎ” ተግዳሮት ሆኖባቸው በጉልበት ኢትዮጵያ መጥተው አስቁመውታል። አለምን የሚለውጥ ቴክኖሎጂ ነበረን፡፡ “ካሽጎ” አለማቀፍ የገንዘብ ዝወውርን ያለ ደላላ የሚያሳልጥ፤ ኢትዮጵያ በየአመቱ በሌሎች የገንዘብ አዘዋዋሪዎች የምታጣውን 9 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ የሚያስጠብቅላት ነበር፡፡ ማንም ሰው በያዘው የእጅ ስልክ 10 ዶላር ልኮ፤ 10ሩም ዶላር በቀጥታ ለኢትዮጵያ የሚገባበት አሠራር ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሚሽን የሚያገኙ ሌሎች ካምፓኒዎች ተረባርበው አስቆሙት እንጂ በርካታ ጥቅም ያለው ነበር፡፡ አሁንም ተስፋ  የሚያስቆርጠን አይደለም፡፡ “ጉዞጎ” የኛ ነው፡፡ አሁን የ”ጉዞጎ” ሽያጭ ከ5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ አልፏል፡፡ በቀጣይ በቢሊዮን ይገባል፡፡ አሁን ወደ አሜሪካም እየወሰድነው ነው፡፡ አሜሪካን ሃገር “ጉዞጎ ኢንተርናሽናል” በሚል ተመዝግበን ልንገባ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት አሜሪካን ሃገር ይገባል፡፡ በዓለም መታወቂያችን የሆነ አገልግሎት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓለም ላይ ሁሉ መድረስና መስራት እፈልጋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ተኝቼ አላድርም፡፡ እኔ ብጀምረው ልጆቻችን ይጨርሱታል፡፡

Read 2034 times Last modified on Wednesday, 13 July 2022 08:30