Print this page
Sunday, 10 July 2022 19:56

የአዳም ረታ ፍልስፍና

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(1 Vote)

“A novel is never anything but a philosophy expressed in images.” -Albert Camus
                          
            አዳም ረታ ከሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን የምድራችን ታላላቅ ደራሲያን መካከል አንዱ ነዉ፡፡ ግራጫ ቃጭሎች (1997)፣ መረቅ (2006) እና የስንብት ቀለማት (2008) የደራሲዉ ዘመን አይሽሬ የረዥም ልብወለድ ሥራዎች (masterpiece) ናቸዉ፡፡ አዳም ግላዊ ፍልስፍናዉን በሥነ ጽሑፍ አማካኝነት የሚገልፅ ደራሲ ነዉ፡፡
ይኸ ጽሑፍ የአዳምን ግላዊ ፍልስፍናዎች (original philosophy) የሚፈክር ነዉ፡፡ እነዚህ ሁለት የአዳም ፍልስፍናዎች ከረሜላ እና ሸንኮራ ይሰኛሉ፡፡     
ከረሜላ
ከሰማይ የወረደ ፍርፍር እና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶች (2002) ከአዳም ድንቅ የአጭር ልብወለድ መድበሎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ በእዚህ መድበል ዉስጥ የቀረበዉ ከረሜሎች የተሰኘዉ አጭር ልብወለድ ከረሜላ የተሰኘዉ የደራሲዉ ፍልስፍና የተዳሰሰበት ግሩም ሥራ ነዉ፡፡ አዳም እንደሚነግረን የዚህ ልብወለድ ዐቢይ ጭብጥ በእየለቱ የምንገፋዉ ተመሳሳዩ ህልዉናችን የወለደዉ ስልቹነት ነዉ፡፡ ይኸ ልብወለድ ጥቂት ብቻ ለዉጦች በማድረግ ተደጋግሞ የተጻፈ ነዉ፡፡ ደራሲዉ ይኸን በማድረጉ ኋላ ላይ በሥራዉ መደምደሚያ ላይ ያቀረበዉ ፍልስፍና የሰመረ እንዲሆን ረድቶታል፡፡  
አዳም በእዚህ ሥራዉ የሚያሳየን የሰዉ ልጅ የመኖር ኩነኔ የምኞት ግዞተኛ አድርጐት በልማድ የሚጓዘዉ ጉዞ አዲስ መዳረሻ የሌለዉ ከንቱ ጉዞ የመሆኑን ሐቅ ነዉ፡፡ የከረሜሎቹ ዉክልና የሰዉ ልጅ ህልዉና ነዉ፡፡ እነዚህ ከረሜሎች፣ በቀለም የተለያዩ፣ ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸዉ፣ በተለያየ ልባስ የተጠቀለሉ እና በተለያዬ ቄንጥ የተሸመለሉ ናቸዉ። የከረሜሎቹ በመልክና በሽፋን መለያየትና በተለያየ ቄንጥ መሸምለል በእያንዳንዱ ዕለት የምንኖረዉ ፈርጀ ብዙ ህልዉና ተምሳሌት ነዉ። ይኸ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን በደምሳሳዉ ስናስበዉ አንዱ ከአንዱ የተለያየ ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣ ይኸ ሕይወት፣ ልክ በመልክና በሽፋን የተለያዩ ከረሜሎች ተራ በተራ ተገልጠዉ ሲቀመሱ ያላቸዉ ጣዕም ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ አዲስነት የሌለዉ ሕይወት ነዉ፡፡ አዳም እንዲህ ጽፏል፡-
ነገ የገና በዓል ዛሬ የገና ዋዜማ ነዉ፡፡ ከቢሮ ልወጣ ስል አንዲት ሴት የዋዜማን በዓል ከምሳ በኋላ ቢሮ ዉስጥ እንድናከብር ከረሜላ ገዝተህ ና አለችኝ (እስዋንም እንደ ከረሜላ አልፎ አልፎ የሚሰራት፣ ከአፏና ከአይኖቿ ዕፁብ ጣዕም የተንዠረገገ)፡፡ መልእክቷን እንዳልረሳዉ ምሳ ከመብላቴ በፊት አንድ ሱቅ ጐራ አልኩና የተለያየ ቀለም ያላቸዉ ከ30 የሚበልጡ ከረሜላዎች ገዛሁ፡፡ ከረሜላዎቹ ሞላሌ ቅርፅ አላቸዉ፡፡ መጠቅለያዎቹም አንዱ ከአንዱ የማይመሳሰል ዉብ አብረቅራቂ ወረቀቶች ናቸዉ፡፡ የተሸመለሉባቸዉም ቄንጦች ሶስት ዓይነት ነዉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱም ጫፎቻቸዉ የተጠመዘዙ፣ የሚቀጥሉት በሠፊዉ ጐናቸዉ በኩል የተጠመዘዙ ሲሆኑ፣ ሶስተኛዎቹ ደግሞ በአንድ ጠባብ ጐናቸዉ በኩል የተጠመዘዙ ናቸዉ፡፡ ጉንፋን ስላመመኝ አላማዬ ለምሳ ሾርባ ቢጤ /የበግ ሾርባ/ ልጠጣ ነበር፣ ግን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በምትኩ በቃሪያና የተጠበሰ የበግ ሥጋ በሚጥሚጣ ተምትሜ በላሁና ወደ ቢሮዬ መመለስ ጀመርኩ፡፡
የከረሜላዎቹ ልባስ በጣም ማራኪ ስለነበር አንጀቱና ጥርሱ ቢኖረኝ ሁሉንም ሳልበላቸዉ አልቀርም ነበር፡፡ ቢሮዬም ሳልደርስ አንዱን ከረሜላ ገልጬ አየሁት፡፡ ልክ ከዉጭ ከሽፋኑ እንደ ሚገመተዉ ወደ እንቁላል የሚጠጋ ሞላላ ቅርፅ አለዉ፡፡ እላዩ ላይ አንዳንድ ጉርብጥብጥ ምስል ነገሮች ተሰርተዉበታል፡፡ ትርጉማቸዉ አልገባኝም፡፡ ከረሜላዉን ወደ አፌ አስገብቼ መጥባት ጀመርኩ፡፡ ድዴን ጐረበጠኝ። አይመችም፡፡ ለመቆረጫጨም ፈልጌ ደጋግሜ በጥርሶቼ ከላይና ከታች ሆድቃዉን ተጫንኩት። በመጀመሪያ ትንሽ ታገለኝና ብዙም ሳይቆይ ተደረመሰ፡፡  ከዉስጡ እንደ ማር ሙሙት የሚል፣ እንደ አረቄ ሽታ ሰንፈጥ የሚያረግ ጣፋጭ ነገር አፌ ዉስጥ ፈሰሰ፡፡  ሽታዉ አደናብሮኝ ልተፋዉ ፈልጌ መጣፈጡ ግን ገታኝ፡፡ በቀስታ እየቆረጫጨምኩ እየሰባበርኩ እያባበልኩ እያንከላወስኩ ዋጥኩት፡፡ በአፌ ዉስጥ የነበረዉ የጥብስና የሚጥሚጣ ሽታ ጠፍቶ እንግዳ ነገር ተሰማኝ፡፡ ሌላ ከረሜላ አዉጥቼ ቆረጨምኩ፡፡ ያዉ ነዉ (አዳም፣ 2007: ገጽ 126)፡፡
የአዳም የከረሜላ ፍልስፍና አንኳር ሐሳብ (central thesis) እንዲህ የሚል ነዉ፡- የቱንም ያህል የሰዉ ልጅ ህልዉና በተለያየ ጎዳና ቢጓዝ፣ እንደ ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ጨዋታ በአሰልቺ የድግግሞሽ ዑደት የሚነጉድ ነዉ፡፡ ባለፈዉ፣ በዛሬዉና በመጪዉ ጊዜ መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ ሰዉ ይኸን ፈፅሞ ሊሸሽ የማይቻል ገሀድ ሲገነዘብ ነፍሱ የስልቹነትን ብሉኮ ትከናነባለች፡፡
2. ሸንኮራ
የሸንኮራ ፍልስፍና በአዳም ታላቅ የረዥም ልብወለድ ሥራ በሆነዉ መረቅ (2007) ዉስጥ የቀረበ ፍልስፍና ነዉ፡፡ የሸንኮራ ሁለቱ ዐቢይ ብልቶች አንጓና መለልታ ይሰኛሉ፡፡ የአንጓና መለልታ ተምሳሌትነት (metaphor) በሁለት ተቃራኒ ፅንፎች የተመሠረተዉ የሰዉ ልጅ ሕይወት ነዉ፡፡
አንጓ ለመበላት ከፍተኛ ጥረትና ድፍረት የሚጠይቀዉ እጅግ ጠንካራዉ የሸንኮራ ብልት ሲሆን፤ በተቃራኒዉ መለልታ ግን ለመበላት ምቹና ቀላል የሆነዉ ብልት ነዉ፡፡ እነዚህ ሁለት የሸንኮራ ብልቶች የሚወክሉት በህልዉናችን የሚፈራረቀዉን መከራ (adversity) እና ድል (triumph) ነዉ፡፡ አዳም እንደሚነግረን፣ የሸንኮራን ጠንካራዉን ብልት አንጓን መብላት በንፅፅር ለስላሳ የሆነዉን ብልት መለልታን እንደ መብላት የቀለለ ተግባር አይደለም፡፡ አንጓን መብላት በኑሮ የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በፅናትና በድፍረት ከመጋፈጥ ጋር ተመሳሳይ ነዉ (አዳም፣ 2002፡ ገጽ 43)፡፡
 አዳም በሸንኮራ ፍልስፍናዉ እንደሚነግረን፣ የሸንኮራን ጠንካራዉን ብልት አንጓን ቀድመን መብላታችን ኋላ ላይ የምንበላዉ መለልታ የበለጠ እንዲጥመን ያደርጋል (አዳም፣ 2002፣ ገጽ 45)፡፡ በህልዉናም እንዲሁ ነዉ፤ እጦትን የቀመሰ ብቻ ነዉ የማግኘትን ዋጋ የሚረዳዉ፣ የተገፋ ብቻ ነዉ የመፈቀርን ፀጋ የሚገነዘበዉ፡፡



Read 1346 times