Sunday, 10 July 2022 19:57

“ሐሰተኛው”ንና “የተጠላው እንዳልተጠላ”ን እንደ አንድ መጽሐፍ

Written by  በምግባር ሲራጅ
Rate this item
(5 votes)

ፈጣሪ በፍጡሩ የተከሰሰባቸው አንቀጾች በሁለቱ መጻሕፍት ውስጥ…
                                  
                   - በፈጣሪ መተው (Abandonment) እና ረሀብ  
በፈጣሪ መተው (Abandonment)
…የተፈጠርነው በግዴለሽነት፣ በእንዝህላልነትና በማናለብኝነት ተራድኦ እንደሆነ መቀበል ነፍስን እንደ ሻህላ የሚበላ እውነት ነው፡፡… (ገፅ 9፣ ሐሰተኛው)
… እግዚአብሄር የሰውን እጣ ፈንታ ለሰው ለራሱ ትቷል፡፡ ማዕበል ቢመታን፣ እሳት ቢነሳብን፣ ተስቦ መግቢያ ቢያሳጣን፣ ቸነፈር ቢንሰራፋብን… ለሰው ደራሹ ሰው ብቻ ነው። ግን ሰውን ለሰው የመተው ያህል አሰቃቂ የተፈጥሮ አደጋ በጭራሽ የለም፡፡… (ገፅ 128፣ ሐሰተኛው)
… ምድርን ራሷን በራሷ አዙሪት ውስጥ በመክተቱ ከእለት እለት፣ ብርሃንና ጨለማን ከማፈራረቅ እሽክርክሪት ራሱን ነፃ አወጣ፡፡ … (ገፅ 105 ሐሰተኛው)
… ወላጅ ልጁን አሳድጎ ለዓለም እንዲለቅ በእግዚአብሄርና በሰዎች መካከል እንዲሁ ይሆናል፡፡… (ገፅ 5፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… ፈጣሪ ርስቱን ለሰው ልጅ ትቷል፡፡ … (ገፅ 7፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… ለአዳምና ሄዋን ስህተት
   ሳይጠራ የመጣ
   ለእኛ መከራ ግን፣
 ጆሮውን ሳያዘነብል ቀረ፡፡… (ገፅ 34፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
በእኚህ ሁለት መጻሕፍት ውስጥ የተነሱ ፈጣሪ የፈጠራቸው ፍጡራን ላይ ፊቱን መመለሱን የሚወቅሱ የዴይዝም ፍልስፍና ተከታዮች ዝንባሌን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የዚህ ፍልስፍና ሀሳብ መምህራን እንደሚሉት፤ ፈጣሪ በፈጠራቸው ፍጡራን ሕይወት ጣልቃ እየገባ የሚያቀናው ጎዳና የለውም፡፡ ፈጥሮ ሲጨርስ ሄዷል የሚል ነው፡፡ God doesn’t interfere with the universe after it’s creation. ሌላው ይህን መሰል የዴይዝም አቀንቃኞች ሀሳብ የምናይበት ኢ-መዋቲነት የተሰኘው የሚላን ኩንዴራ ልብወለድ ነው፡፡ ... The creator loaded a detailed program into the computer and went away. That God created the world and them left it to a forsaken humanity trying to address him in an echoless void. …[Immortality, Milan Kundera]
አብዛኞቹ ከመጻሕፍቱ ውስጥ ለመሞገቻነት የሚወጡ ሀሳቦች እንግድነት የላቸውም፡፡ ነገር ግን፣ ደራሲው ባለው አቅም Supra-vistal መንጠራራትን ይፈቅድላቸዋል፡፡ ይህ ባህሪው፣ ጥያቄውን ወደ ራስ በማምጣት የራስ ማድረግ ያስችለዋል፡፡
ይህን በፈጣሪ የመተውን ጥያቄ የምናይበትን ሁለት ነጥብ ላንሳ፣ ፈጣሪን በሚታመነውና እሱን ተስፋ በሚያደርግ ሕዝብ ላይ ፊቱን ሲመልስ እና ፍጡራን የአምላክን ጣልቃ ገብነት ሳይፈልጉ ሲቀሩ፣ አልያም ሰው ለፈጣሪ ጀርባውን ሲሰጥ (turn away from God)፡፡
በኚህ ሁለት ምክንያቶች ፍጡር ከፈጣሪው ውጪ ሊኖር የሚገደድባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ የመጀመሪያውንና፣ አምላክ ፊቱን የመለሰበትን እንይ፣
…እግዚአብሔር እንዴት ላመኑት ሕዝቦች ሳይታመን ቀረ?… (ገፅ 7፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… በጎጇችን የነበረውን የእህል እንጥፍጣፊ
እግዚአብሔርና ተአምሩን በመጠበቅ ጨረስን፡፡
ሀገር ምድሩ እግዚአብሔርን በመጠበቅ ጭር አለ፡፡… (ገፅ 46፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
በነኚህ ገፆች ውስጥ የእግዚአብሔርን አለመኖር በህዝቦቹ የጥበቃ ዘመን ልክ አስልቶ፣ ከፊሉ ጎኑ በቀቢፀ ተስፋ የተበላ ባሕረሐሳብ ይዘረጋል፡፡ የሕዝቡን በረሃብ ግዞት መያዝ፣ የእግዚአብሔርን ከሕዝቡ ጋር ያለመኖር ከሚረጋገጥባቸው ምልክቶች አንዱ አድርጎም ያቀርባል፡፡ ይህ፣ ፈጣሪ ፍጡሩን የመመገብና መንገድ የመምራት ግዴታ እንዳለበት የሚሰብከው ባለታሪክ፣ ሌላ ይዞት የሚመጣው ሀሳብ አለ፡፡ ተስፋ፡፡ ደራሲው፣ ኢትዮጵያውያን አምላካቸውን ተስፋ በማድረግ በመከራ ስለመፈተናቸው የሚቆጭበትንና የሚያነቃበትን የተግሳፅ በትር ነቅዕ ካሙ እንዲህ ይዛመደዋል፣ … Melancholy people have two reasons for being so; they don’t know or they hope. … [The myth of sisyphus] በፈጣሪ አስተዳደርና፣ በሰው ተገዢነት መካከል ኪናዊ መስተጋብር የሚፈጠርበት ፈር [Pattern] ተስፋ ነው፡፡ ሌላው፣ ሕዝቡ በአምላኩ ላይ ያለውን ተስፋ ሳይገድፍ ባለበት፣ አምላክ ያልታመነበትን ጉዳይ የሚከስበት ነጥብ፣ አላፊነት ያለመወጣት ችግርን [being Irrisponsible] በማንሳት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በፈጣሪ መተውን ተከትሎ፣ የሰው ልጅ በልጅነቱ የሚቀበለው ውርስ፣ ራሱን ይሆናል፡፡ ተስፋውንና አላፊነቱን በራሱ ስር በማስገዛት መኖር፣ አንድምታ የማያወጣለት ወንጌሉ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ እንዲህ ባለ፣ ፈጣሪ አላፊነቱን ባልተወጣበት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን ለሰው የሚበጀውን፣ ከራሱ ጋር ማድረግ የሚገባውን ስል ትውውቅ፣ የኅልውናዊነት አቀንቃኙ ጄን ፖል ሳርትሬ ያቀርባል፣
… Man is responsible for what he is. Thus, the first effect of existentialism is that it puts everyman in possession of him as he is, and places the entire responsibility for his existence squarely upon his own shoulders. … He will be what he makes of himself. Thus, there is no Human nature, because there is no God to have a conception of it. Man simply is. … [Existentialism and Humanism, Jean-Paul-Sartre]
መተው [abandonment] ስናነሳ በዋናነት አብረን የምናነሳው ነገር ቢኖር የእግዚአብሔርን አለመኖር ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው፣ የሰው ልጅ ሕይወቱን ከመለኮት ባለአደራነት ነጥቆ፣ በገዛ ራሱ አላፊነት ስር ሊያስገዛ መገባቱ የመሰንበቻ እጣው መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ፣ አላፊነቱን ባልተወጣ፣ ይልቁንም ሕዝቡን ትቶ ኮብልሏል ተብሎ በተከሰሰ ፈጣሪ ምትክ፣ የሰው ልጅ ላይ ተስፋ መጣል ያለውዴታ የሚቀርብ ጉዳይ መሆኑን እናያለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የዛሬው ሰው ለመጪው ዋስትና መሆኑን የፈረንሳዩ ባለቅኔ ፍራንሲስ ፖንጅ እንዲህ ሲል ፅፏል፤ Man is the future of man.
ደራሲው፣ በፈጣሪ የመተው ጉዞ ውስጥ ሰዎች ስለሚያገኙት ነፃነትና ድሎት ሲያወራ፣ የስብከቱን ዋነኛ አላማ ይገልጣል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያንን ለኀሠሣ አምላክ ከማሰማራት ይልቅ፣ ከልባቸው የሚወጣበትን እቅድ በመንደፍ ላይ እንዲያተኩሩ ይገፋል፡፡ በዚህ ተገፍቶ የሚመጣው፣ የአምላክን ጣልቃ ገብነት ሳይፈልጉ ሲቀሩ ሰዎች ለፈጣሪ ጀርባቸውን የሚሰጡበት (turn away from God) አቋምን ነው፡፡
… ሰዎች ሲበረቱ እግዚአብሔር ያፈገፍጋል፡፡
ከህሊናቸው፣ ከመንፈሳቸው፣ ከነፍሳቸው ይወጣል፡፡
… ኢትዮጵያውን መቼ ይበረታሉ?        እግዚአብሔራቸው የሚያፈገፍግበት ቀኑ መቼ ነው?… (ገፅ 5-6፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… ኢትዮጵያ እንድትንቀሳቀስ ካስፈለገ የጽሞና ቅፅሯ ይፍረስ!  ጃንደረቦቿ ይንኳሰሱ፡፡
… ስለምን እምነታችሁን የተፈጥሮ ተፋሰስ መገደቢያ አደረጋችሁት? … (ገፅ 108፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚያነሳው፣ ኢትዮጵያውያንን ከአምላካቸው ጋር ያጣመራቸውን የእምነት ግድግዳ በማፍረስ፣ በምትኩ እንደታቆረ ውኃ የብስባሽና የአዋኪ ትንኝ ማደሪያነታቸው፣ የሚያንሸራሽሩበትን ቦይ በመቅደድ ለእንቅስቃሴ መዳርን ነው። በዚህ፣ ኢትዮጵያውያን ከአምላካቸው ጋር በተማማሉበት፣ ትካትና ፅናት በሚከፈልበት የእምነት ውል መሰረት፣ ዱኒያ ዳር ትይዛለች። ለዚህም እንደ መፍትሄ ከሚያቀርባቸው ነጥቦች ውስጥ ሁለቱ ዋንኞቹ ናቸው። የጽሞናን ቅፅር [Theosophy] ማፍረስና ጃንደረቦቿን [priests] ማንኳሰስ፡፡ ኦሾ፣ ከዚህ ጋር አያይዞ የኒቼን ‹‹እግዚአብሔር ሞቷል ሰውም አርነት ወጥቷል›› የሚለውን በሚያብራራበት መፅሐፉ፣ ከእግዚአብሔር ሞት ይልቅ የአይማኖት ስርዓቶች የሰው ልጅን እድገት ተጻራሪነት ያደምቃል፡፡ … The priest would manage to keep man in slavery. …  ሰውን ለሰው መተው የቅጣቶች ሁሉ ቅጣት እንደሆነ ሲገልፅ፣ በአንፃሩ፣ ፍጡር ካለፈጣሪው እገዛ ለመኖር የሚቸገር መሆኑን እናያለን፡፡ ሰው እርዳታውን የሚጠባበቅበት የትዕግስቱ ፅዋ ሲሞላ፣ ፊቱን ወደ ራሱ መመለሱ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ነው ከተስፋ ወደ አላፊነት የሚደረግ የለውጥ ሽግግር መልክ የሚከተው። በሽግግሩ ወቅት የሚነሱ የቁጣ፣ የተግሳፅና የልመና፣ የሚመስሉ መሪር የስንብት ቃላትን መስማት የለውጡ መምጫ ማሳያ ምልክቶች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በዚህ ርዕስ ዙሪያ መፅሐፉ የሚያነሳቸው ነጥቦች ከኑፋቄ በራቀ፣ እንደ እዮብ ያሉ፣ ከፈጣሪ መዋቀሻ (መካሰሻ) አንቀፆች የቆሙበት የፍርድ አደባባይ አድርጌ እቀበላቸዋለሁ፡፡ በሌላ አማርኛ (በጎጃምኛ አልያም በወሎኛ) አብሮን ያረጀ ሰይጣን ታግሎ መጣያ ጥበብ ከመንደፍ፣ ለውድቀት በታጨ መንፈስ ፈጣሪን ታግሎ መሸነፍ ወዳለበት ይገፈትራል፡፡ በዚህ ትግል መሃል ሰው ራሱን የሚያደረጅበትን ብስለት ከትግሉ ይማራል፡፡ ይህ ሀሳብ ያስታወሰኝን ካዛንታኪስ በሞንት አቶስ ገዳም ከመቃሪዮስ ጋር ያወሩትን አስታውሼ ወደ ሌላ ወደ ሌላ፣
Kazantazkis:- do You still wrestle with the devil;
Fr, Makarios:- oh, no. I used to wrestle with him on the time,
But now I’ve grown old and the devil has grown old and
tired with me. So I live him alone, and he lives me alone
Kazantazkis:- then your life is easy now;
Fr, Makarios:- oh, no. life is much harder now, for now I wrestle with God.
Kazantazkis:- you wrestle with God and hope to win;
Fr, Makarios:- No. I wrestle with God and hope to lose.
[Report to Greco, Autobiography of Nikos Kazantazkis]
ረሀብ
… እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ማስራብ እንደ ዘዬ ይዞታል፡፡ … (ገፅ 27 ሐሰተኛው)
… እግዚአብሔር አስርቦ ከሚያፈላስፍ አጥግቦ ማስተኛት አይሻለውም ኖሯል? … (ገፅ 29 ሐሰተኛው)
… እምነታቸው ሲበሉ የማይወድ አዚም ነው፡፡ … (ገፅ 5፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… እትብታችሁን ከተቀበረበት የነቀሉ ረሀብና እግዚአብሔር አይደሉምን? … (ገፅ 11፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
… የእግዚአብሄርን ደጀን ረሃብን እመታለሁ፡፡ … (ገፅ 81፣ የተጠላው እንዳልተጠላ)
ከላይ ባለው፣ የፈጣሪ መተው በተነሳበት ጉዳይ ላይ፣ ሰውን ለራሱ በመተው ድንጋጌ ሥር ማለፍ ግድ የሚያስብሉ ነጥቦችን ዳስሻለሁ፡፡ በቀጣይ፣ በዚህ ብይን በመመራት ፈጣሪ በረሀብ የተከሰሰበትን ነጥብ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ አሁን ፈጣሪ የሚከሰስበት አንቀፅ ሁለት ሆኗል፣ አላፊነት ባለመወጣት (ፈጥሮ በመተው) እና ፍጡሩን በማስራብ፡፡ እኚህ ሁለት ክሶች ሰውን ለራሱ ሞግዚት የሚያደርጉበትን መግፍኤ ይለጥጣሉ፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ በትንቢት እግረሙቅ ታስሮ መማቀቂያ ጊዜን በመሻር፣ በድርጊት መዛለፊያ ቅጥ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህም ከሐሰተኛው ወደ የተጠላው ያንደረድረናል፡፡
ከላይ ባነሳኋቸው ምዕራፋት ውስጥ፣ እግዚአብሔር ሰውን ማስራቡና ለረሀብ አሳልፎ መስጠቱ፣ ከመተው ጋር አንድነት የሚያስነሳው ነው፡፡ እግዚአብሔር ለነኚህ ክሶች መልስ እንዲሰጥ የተጠበቀባቸው አዝማናት ስፍር፣ ክሱን ከኩርፊያ በዓቱ ይጎተጉቱታል፡፡ በዚህም ምክንያት የሐሰተኛው የተግሳፅ ቃል ወደ በትር ይለወጣል፡፡ በበትሩ ሊመቱት የተፈረደባቸው ደግሞ እግዚአብሔርና ረሀብ ሆነው ይቀርባሉ። በየተጠላው ውስጥ የተጠቀሰ፣ እግዚአብሔር ኢትዮጵያውያንን በመያዣነት እምነታቸውን የሚበዘብዝ አቋሙን የሚያሳየን ስንክሣር እነሆ፣ …ዝናብና ጠል፣ ከእርሱ እያሉ የሚከለክልና የሚነፍግ አምላክ በእርግጥ የእኛ ፈጣሪ ነው? ስንት ዘመንስ ዝናብና ጠልን መያዣ አድርጎ ይቀጥላል?  (ገፅ 92፣ የተጠላው…) ይህን የስንክሣር ሀሳብ የሚደግፍ የሳሙኤል ቤኬትን ኢንድ ጌም የተሰኘ ተውኔት ላይ ያለ መስመር እንይ፣ ... HAMM:- I’ll give you just enough to keep you from dying. You’ll be hungry all the time. የተጠላው እንዳልተጠላ፣ እግዚአብሔር የበረሃ ውኃ ዐይነት በቅምሻ እያባበለ ከኢትዮጵያውያን ጋር መጣመዱን ያሳየናል፡፡ በዚህ የመፅሐፉ የለውጥ ማቀንቀኛ አንድ እርምጃ በሆነው የወቀሳ ድርሳን ሥር፣ የማነሳው ሌላው የትዝብት እግረሙቅ፣ ኢትዮጵያውያን ከአምላካቸው ጋር የማይነጣጠሉበት ምክንያት ነው፡፡ …ፈጣሪ ለኢትዮጵውያን ወደ ኋላ እንተወው ዘንድ የማይቻለን የጉያ ጠላታችን አይደለምን? (ገፅ 8፣ የተጠላው…) ይህን ኢትዮጵያውያን ከፈጣሪያቸው፣ ፈጣሪያቸውም በሄድ መለስ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚመሩትን ገራገር ሕይወት የሚያጠብቅ ምሳሌ ላንሳ፣ ምሳሌው በዚሁ የሳሙኤል ቤኬት ኢንድ ጌም ላይ ያለ ምልልስ ነው፡፡
HAMM:- why do you stay with me?
CLOV:- why do you keep me?
HAMM:- there’s no one else.
CLOV:- there’s nowhere else.
ይህ አንዱን መሄጂያ በመንሳት፣ ሌላውን አብሮት የሚሆን ሰው በማሳጣት ላይ የተመረኮዘ አብሮነት መፍጠር፣ ፍጡር ከፈጣሪው ጋር የቆየበት ጥምረት እንደሆነ በመጻሕፍቱ እናያለን።
እኚህ መስፈንጠሪያዎችን በመርገጥ ወደ ዋናው ነጥብ ላምራ፡፡ ባለታሪኩ፣ ድርጊቱን የሚያስፈነጥርበትን ደጋን ወደ ረሀብ አነጣጥሯል፡፡ ቀስቱ ሄዶ የሚያርፍበት አካል ረሀብ ነው፡፡ ረሀብን ለመውጋት ሲነሳ፣ ረሀብን ምሽግ ያደረጉትን መውጋቱ የማይቀር ነው፡፡ ረሀብን ከመሸጉት መካከል አንዱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ረሀብ ድል በሚሆንበት የጦርነት ውሎ ደጀኑም አብሮ ድል መሆኑ የማይቀር ነው። ረሀብና እግዚአብሔርን ሊወጋ የተነሳው መሲህ፣ ባላንጣዎቹን የሚገጥምበት አካል ፈተናው ይሆንበታል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ሁለቱን ፊት ለፊት የሚገጥምበትን Medium ለይቶ ያወጣል። ረሀብን በባርነት በመግጠም፣ እግዚአብሔርን በቅጥሮቹና የሐይማኖት ጃንደረቦቹ ጋሻ የሆነውን ፍርሃት በመውጋት ነው፡፡ የዚህን መጽሐፍ የጦር ስትራቴጂ ደግፈው የሚሰለፉ ሌሎች ሁለት መጻሕፍት ላይ የተሰነዘሩ ሀሳቦችን እንይ፣
…religion is based, I think, primarily and mainly upon fear… fear is the parent of cruelty, and therefore it is no wonder if cruelty and religion have gone hand in hand. … [Why I am not a Christian, Bertrand Russell]
… the terror of society, which is the morals, the terror of God, which is the secret of religion- these are the two things that govern us. … [The picture of Dorian Gray, Oscar Wilde]
ረሃብ፣ ኢትዮጵያውያንን በፈቃድ ባርነት ራሳቸውን በማጋዝ፣ የሚፈርጥ ምርቅዝ ቁስል ነው ይለናል ደራሲው፡፡ ይህን፣ በሐይማኖትና በሐይማኖት አባቶች እጅ ላይ ያለች ነፃነታችንን ዳግም ወደ እጃችን የምናገባበት መንገድ ነው፣ ባርነት፡፡ ይሄ ደራሲው በብርሀን ሞገስ የሚያመጣው የግዞት ዓለም፣ መነሻው ከሐይማኖት ባርነት የምንላቀቅበትን የፍርሃትን ክንብንብ የምንገልጥበት እንደሆነና፣ የነፃነትን ፋና የምናይበት ጎዳና፣ በባርነት የሚኬድ መሆኑን የተጠላው ላይ ያነሳል፡፡
…በፈረሰው ቤተ-እምነታችሁ ፈንታ ሰማይ ጠቀስ ጎተሮችን ገንቡ፡፡ …(ገፅ 77፣ የተጠላው…)
… ፈንጋዮቻችንን እንውለድ፣
   ባሪያ አሳዳሪዎቻችንን እንኮትኩት፣
   የነፃነት መውጫ ምዕራፎች ናቸውና፡፡…
… ባርነት የነፃነት ብቻ ሳይሆን
   የጌትነት መተላለፊያ ጨለማ ኮሪደር ነው፡፡
   ባርነት’ኮ ብርሀን ያረገዘ ጨለማ ነው… (ገፅ 136-7፣ የተጠላው…)
 ይህን የደራሲውን ሀሳብ የሚዛመደውን የኦሾን ሀሳብ ላንሳ፣
… Religiousness simply means a challenge to grow, a challenge for the seed to come to its ultimate peak of expression, to burst forth in thousands of followers and release the fragrance that was hidden in it. …
የሰውን ልጅ ከፍሬያማነት ተስፋው የሚያጨናግፉት (ዘሩን ቆልተው ከሚበሉ) መሰናከያዎች መካከል ሐይማኖት አንዱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህንንም በመውጋት፣ ሰውን በእምነቱ ስም ለታወረበት የቀቢፀ ተስፋ እርሻ፣ ሕይወቱን ከሚያስበዘብዝበት በማስጣል፣ ራሱን የራሱ ባሪያ ፈንጋይ ማድረግ ላይ ይሰራል፡፡ በዚህ የባርነት ትግሉ ለከርሥከው ምላሽ ከመስጠት በላቀ፣ የሚጎናፀፈው አርነት ስለመኖሩም ያትታል፡፡ ሌላው ይህንን አንቀፅ ሳነሳ፣ ረሀብና እግዚአብሄር ሲከሉ በአፀፋው ይገኛል ስለተባለው ነፃነትና ጥጋብ ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ከላይ በጥቂቱ የነካሁትን በማፍታታት ልጀምር፣
… የእግዚአብሔርን ሞት ስናውጅ መኖራችን ምክንያት አልባ ይሆንና ወደ ራሳችን በጠላትነት እንዞራለን፡፡… ምናልባትም የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ያበቃ ይሆናል፡፡… (ገፅ 100፣ 102)
የኒችን ሀሳብ በተለየ መንገድ የሚመለከተው ኦሾ ሌሎች እግዚአብሔር የሌላቸው ሀይማኖቶችን በመጥቀስ የሰው ልጅ ነፃነት ከእግዚአብሔር ሞት ጋር ሊነሳ አለመቻሉን ያትታል፡፡
… God and man’s freedom can’t coexist. Nietzsche was not aware that there are religions in the world which have no God- yet even in those religions man is not free. He was not aware of Buddhism, Jainism, Taoism, the most profound religions of all, for all these three religions. ...
ሌላው ሰው ነፃነቱን ሊያገኝበት በተማማለበት ነጥብ ላይ ሊገጥሙት የሚችሉ መሰናክሎች እንዳሉት የሚያሳየን ሐሰተኛው ላይ ያለ የናትራ ንግግር ትዝ ይላል፡፡
… አንተ ለጃክ ስጪው አላልከኝም? ፓስታውን ውጦ ውጦ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? የጣሊያን ነገር?
… ምን አደረገ?
… ሴት ተከትሎ ወደ ብቅ እንቅ፡፡ ከወንዶቹ ጋር እየተደባደበ ነው አሉ፡፡… (ገፅ 59፣ ሐሰተኛው)
በዚህ የናትራን ንግግር ውስጥ የምናየው አንኳር ጉዳይ፣ ሰው በነፃነቱ የሚገዛው አመፅ መኖር መቻሉን ነው፡፡ በዚህም የመጣ፣ ራሱን ለራሱ ማስገዛት የማይችልባቸው የነፃነት ፍኖቶቹን ጥያቄ ውስጥ ይከቱበታል፡፡ ይህን መሰል የናትራን ንግግር ላይ የተመረኮዘ ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ ኦሾ እንዲህ ይላል፣
… It is not right to call it freedom- It’s licentiousness. It is not freedom because it does not carry any responsibility, any consciousness.
... It is possible your freedom may take you lower than your slavery, because the slavery had a certain discipline, it had a certain morality, and it had a certain principles.
በዚህ ስር ኦሾ እስከ ባርነት ልንሄድለት የምንገደድለት ነፃነት ይዞት ስለሚመጣው ውጤት መጠይቅ ያቆማል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በሐሰተኛው ላይ፣ ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወትን በመመኘት የሚያንኳስሷትን ምድራዊ ሕይወት፣ በመመመርኮዝ የመጨረሻውን ጦር ረድ ሠርዌ ላይ ሲወረወር የሚሳየንን ገፅ ገልጬ ላጠቃልል።
… ጥጋብ ፀጋ እግዚአብሔርን ይገፋል፡፡ …
… ነፍሴ ሆይ በዚህ ልትጠግቢ በወዲያኛው ልትራቢ ትወጃለሽ? …(ገፅ 72-113፣ ሐሰተኛው)
በሐሰተኛው ላይ ስትባክን የኖረች የባሕርያት ሕይወት፣ በመጨረሻም ፈጣሪን ከስፍራው አሽሽቶ በምትኩ ጎተራ የሚገነባበትን ጥበብ የምታስተምርበት የስብከት ሰገነት ላይ ትወጣለች፡፡ በመጨረሻም፣ (እንደ መውጫ) ሁለቱ ዓለማት፣ ረሀብን መካከል አድርገው፣ የአምላካቸውን ኅልውና ለድርድር የሚያቀርቡትን  አቋም፣ በከፊል ለሐሰተኛው መሲህ በሚያዘነብል ግን ፈፅሞ ባልተኮሳተረ ግጥሙ Pindar  የሚዘምረውን ተከትዬ እያሸበሸብኩ ልውጣ፣
…we must seek from the gods
What is suitable for mortal minds.
Knowing what is at our feet,
And what kind of lot we have.
So do not, my soul, be eger for immortal life.
***
“--ረሃብ፣ ኢትዮጵያውያንን በፈቃድ ባርነት ራሳቸውን በማጋዝ፣ የሚፈርጥ ምርቅዝ ቁስል ነው ይለናል ደራሲው፡፡ ይህን፣ በሐይማኖትና በሐይማኖት አባቶች እጅ ላይ ያለች ነፃነታችንን ዳግም ወደ እጃችን የምናገባበት መንገድ ነው፣ ባርነት፡፡
ይሄ ደራሲው በብርሀን ሞገስ የሚያመጣው የግዞት ዓለም፣ መነሻው ከሐይማኖት ባርነት የምንላቀቅበትን የፍርሃትን ክንብንብ የምንገልጥበት እንደሆነና፣ የነፃነትን ፋና የምናይበት ጎዳና፣ በባርነት የሚኬድ መሆኑን የተጠላው ላይ ያነሳል፡፡ --”

Read 1152 times