Sunday, 10 July 2022 20:10

ይድረስ ለኦሮሞ ሕዝብና ለኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 የኦሮሞ ልሂቃን ዘር-ተኮር ጭፍጨፋን በአደባባይ ያውግዙ!”
                                  
              “በ2013 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ፣ በሕዝብ ድምጽ ወደ ስልጣን የመጣው ስድስተኛው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት (ጨፌው) እርስዎን ርዕሰ መስተዳድር፣ ወ/ሮ ሰአዳ አብዱራህማንን ዋና አፈ ጉባኤ አድርጎ መርጧል። እርስዎ ያቀረቧቸውን የክልላዊ መንግሥቱ የካቢኒ አባላትን ሹመትም አጽድቋል። አሁን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሥልጣንና ኃላፊነት ከእነ ሙሉ ተጠያቂነቱ በእርስዎና በሥራ ባልደረባዎች እጅ ገብቷል።… ዘር ተኮር ጥቃት በአማራ ላይ የፈጸሙ ሰዎች ወይም ቡድኖች ሕግ ፊት ቀርበው ከጥፋታቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት መቀበላቸውን ሰምቼ አላውቅም።…
“በኦሮሚያ ክልል በአማራ ላይ ዘር ተኮር ጥቃት መፈጸም የማያስከስስና የማያስወቅስ የወንጀል ድርጊት ሆኗል። ስለዚህ እያንዳንዱ ኦሮሞ በአጠገቡ የሚገኘውን ጎረቤቱን አማራውን በመጠበቅ እንዲተጋ፣ እንደ ምስራቅ ወለጋ አንገር ጉተን፣ እንደ አቢ ደንጎሮ ወዘተ ባሉ ቀበሌዎች ቋሚ ልዩ ሃይል ወይም ሚሊሺያ በመመደብ አማራውን ከጥቃት ይከላከሉ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።”
(ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ የተወሰደ፤ አዲስ አድማስ፤ መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም.)
ከላይ የቀረበው ከዘጠኝ ወር በፊት የተጻፈ ደብዳቤ “ሰሚ ያጣ ጩኸት” ነው የሆነው። ሰሚ ያጣ የምለው ከመሬት ተነስቼ፣ ያለ ምክንያት አይደለም። የኦሮሚያ ክልል ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ብዙ ጊዜ በዘራቸው አልፎ አልፎ በእምነታቸው የሚገደሉበት አካባቢ ሆኗል። ሰዎች አገር አማን ብለው ከቤታቸው ወጥተው ወደ አንድ አካባቢ ሲጓዙ ወይም ሲመለሱ መንገድ ላይ ሕይወታቸውን የሚያጡበት፣ ታፍነው አድራሻቸው የሚጠፋበት፣ ፈጣሪ አትሙት ያላቸው ደግሞ የተጠየቁትን ገንዘብ ለአፋኞቻቸው ሰጥተው ሕይወታቸውን የሚያተርፉበት ክልል ሆኗል።
ክልሉን እየመሩ ያሉት አቶ ሽመልስ አብዲሳና ካቢኔያቸው ይህን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት አልቻሉም። በወንጀል ፈጻሚነት የሚጠቀሰውን ኦነግ ሸኔን ከአረመኔያዊ ድርጊቱ ሊገቱት አልቻሉም። ንፁሃን ዜጎችን ከአሸባሪው ቡድን ጥቃት አልታደጓቸውም። አሁን አሁን ችግሩ ከምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ወጥቶ ወደ ሰሜንና ምዕራብ ሸዋም ገብቶ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በኦነግ ሸኔ ሰላማቸው እየደፈረሰ ነው።
ከሰኔ ወር መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ፣ ከቀደመው ሁኔታ እጅግ የከፋ ጥፋት በኦነግ ሸኔ እየተፈጸመ ነው። በምእራብ ወለጋ ግምቢ ወረዳ በሚገኙ ቶሌ ቀበሌና ሃዋን ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 በተባሉ አካባቢዎች፣ አማራዎች በዘራቸው እየተመረጡ በግፍ ተገድለዋል። የመንደር 20 እና 21 ሟቾች ቁጥር ከ400 በላይ መድረሱም እየተነገረ ነው። በዚህ ጊዜ ሁሉ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩም ሆኑ ካቢኔያቸው፣ ከዚህም አልፎ በታችኛው መዋቅር የሚገኙ የክልል መንግስቱ ባለስልጣናት፣ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ አለመቻላቸውን አረጋግጠናል - በየጊዜው ንፁሃን በግፍ እየተገደሉ ነውና።
ለዚህም ነው፣ በኦሮሚያ  ክልል በዘራቸው ግድያ የሚፈጸምባቸው ዜጎችን የክልሉ መንግስት ይታደጋቸው ዘንድ ከማሳሰብ ይልቅ፣ ወደ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ፊቴን ማዞር የመረጥኩት።
የመሬት ላራሹ አዋጅ ከታወጀና መሬት ለገበሬው ከተከፋፈለ በኋላ የመሬት ባለቤት ወይም ባላባትነት የለም። የአማራ መንግስት ተደርጎ የሚቆጠረው የንጉሱ መንግስት ከተወገደ በኋላ የመጣው የደርግ ወታደራዊ መንግሥትም ሆነ የቀጠለው ሕውሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግስት አልፎም አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት፤ “የአማራ መንግሥታት”  አይደሉም። ዛሬም አማራ የኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን ተቆጣጥሮ እንደያዘ፣ በሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ እንደሆነ አድርጋችሁ የኦሮሞን ሕዝብ ስትቀሰቅሱ የኖራችሁ የኦሮሞ ልሂቃን ካድሬዎች ይሄ የንፁሃን ጭፍጨፋ የእናንተ የሥራ ውጤት መሆኑን ተረድታችሁ ከተመሳሳይ ድርጊት ትቆጠቡ ዘንድ በጥብቅ አሳስባለሁ።
በየትም ዓለም የሚገኙ አገሮች የተመሰሩት በጦርነት ነው። ያንን  ጦርነት የመሩ ሰዎች መኖራቸውም የሚታወቅ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ታሪክ ውጭ  ልትሆን አትችልም። የኢትዮጵያ መፍረስ የሚጎዳው አማራውን ብቻ ነው ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። የኢትዮጵያ መፍረስ የሚጎዳው አማራውን ብቻ ሳይሆን ኦሮሞውንም ሌላውንም ሕዝብ ነው። ስለዚህም አገር የሚያፈርስ ቅስቀሳና እንቅስቃሴ አቁማችሁ፣ መላ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን ለማሳደግ አንዲሰሩ በማነሳሳት የማይተካ ድርሻችሁን ታበረክቱ ዘንድም አደራ እላለሁ።
ኦነግም ሆነ ኦፌኮ ወይም ሌላ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ኦሮሞን አይወክልም። የኦሮሞ ሕዝብ ስብሰባ ተቀምጦ እከሌ የተባለ ድርጅት ይወክለኛል ብሎ ድምጽ ሰጥቶ አያውቅም። በትግሬውም፣ በአማራውም በሌላውም ሕዝብ ስም ተመሰረቱ  የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ  ተመሳሳይ ናቸው። የትኛውንም ህዝብ አይወክሉም። በተለይ ንፁሃን ዜጎችን (ህጻናት ሴቶችና አዛውንትን) በግፍ የሚጨፈጭፍ እንደ ሸኔ ያለ ቡድን፣ የኦሮሞን ህዝብ ሊወክል እንደማይችል ይታወቃል። ቡድኑ ግን ኦሮሞን እወክላለሁ እያለ  በስሙ እንደሚነግድ መካድ አይቻልም።  ከዚህ አንፃር፤  በቡድኑ የሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎችን በግልጽ ማውገዝ ከኦሮሞ ምሁራንና  ከኦሮሞ ፖለቲከኞች ይጠበቃል። ይህ ቁርጠኝነትን  የሚጠይቅ ትግል መጀመር ያለበት ደግሞ “አማራን በዘሩ መርጦ መግደል የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው!”  ብሎ በአደባባይ ከማውገዝ ነው።  ስለዚህ የኦሮሞ ልሂቃን ድርጊቱን በግልጽ አውግዙ።
ዛሬ በኦሮሚያ መሬት እየተገደለ ያለው አማራ አስገባሪ አይደለም። ረሃብ ከትውድ ቀዬው አፈናቅሎት በሰፈራ የገባ ተራ አርሶ አደር ነው። ወይም ደግሞ የቀን ስራ ፍለጋ ኦሮሚያ ክልል ገብቶ መኖሪያውን በዚያው ያደረገ ዜጋ ነው። እኒህን ንፁሃን መግደልና ማስገደል ፈጽሞ  ተገቢ አለመሆኑን ማሳወቅ፤ ድርጊቱም አንዳይፈጸም መከላከል የወቅቱ አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ሆኖ እንዲታይ አደራ እላለሁ።
ቀጣዩ አደራዬ ለኦሮሞ ሕዝብ ነው። ከምንም በላይ ሕዝብ ኃይልና ጉልበት እንዳለው አምናለሁ።  የኦሮሞ ተወላጆች የአማራ ወገኑን ከጅምላ ግድያ ለመታደግ ህይወታቸውን ሁሉ እስከመስጠት የደረሱትን ያህል፣ የጅምላ ግድያውን በጋራ በማውገዝ ከወገናችሁ የአማራ ህዝብ ጎን እንድትቆሙለት እማጸናለሁ።
በነገራችን ላይ የኦፌኮው ምክትል ሊቀመንበር አቶ  ጃዋር መሐመድ ሰሞኑን ከአሜሪካ ሆነው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “የአማራና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የአማራ ልዩ ኃይል ኦሮሚያ ክልል እንዲገባ  ተስማምተዋል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይሉ ወደ ኦሮሚያ መግባት ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ወደ ኦሮሚያ መግባት  እንደሌለበት ሁሉ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ወደ አማራ ክልል መግባት የለበትም፡፡ የአማራ ልዩ ኃይልን ወደ ኦሮሚያ መግባት የአማራ ወንድሞች ከእኛ ቀድመው መቃወም አለባቸው” ብለዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል የወገኖችን ህይወት ለመታደግ ወደ ኦሮሚያ ማቅናት የለበትም የሚሉት አቶ ጃዋር፣ ሰሞኑን ወለጋ ውስጥ በአማራዎች ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያ በአደባባይ ሲያወግዙ አልሰማናቸውም። የክልሉ መንግስት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ሲያሳስቡም አይታዩም። የአማራ ተወላጆችን ታዲያ ማን፣ እንዴት ይታደገው? ለአቶ ጃዋር የማቀርበው ጥያቄ ነው፡፡
ፈጣሪ የግፈኞችን እጅ ይያዝልን፡፡

Read 3358 times