Sunday, 10 July 2022 20:17

‘ሶፍት ፔፐር’ ከአሜሪካ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “እንግዲህ ነዳጅ ጭማሪው ተጀምሯል፡፡ እናማ... ጉዳችንን በመጪዎች ሳምንታት እናያለና! እንግዲህ ከባሰብን ውጭ ያሉ ወዳጆቻችንን እንደበፊቱ ስኒከር ላኩ፣ ምናምን ላኩ ማለት ትተን “ሶፍት ፔፐር ላኩልን፣” ማለት ሳንጀምር አንቀርም! ‘ሶፍት ፔፐር’ ከአሜሪካ! የጉድ ገንፎ እኮ አድሮ ብቻም ሳይሆን ሰንብቶም መፋጀቱ አይቀርም!”
          
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ወዳጆቻችሁን “አንተ ሰውዬ ዘለዓለም ዓለምህን እንዲህ ዘባተሎ መስለህ ሰውስ ምን ይላል! እስቲ አንዳንዴ እንደ ሰዉ ሽክ ብለህ ውጣ!” የምትሉ ሰዎች ምንም አይነት ‘ተግባራዊ ተሳትፎ’ የሌለበት ሀሳባችሁ ባይከፋም ጥያቄ አለን... ሰዋችን ሽክ ይላል እንዴ?! ነው ወይስ  ቡቲክ በር ላይ የሚደረደሩትን ሽክ ያሉ አሻንጉሊቶችን ማለታችሁ ነው? በእኛ ‘መዋያ’ አካባቢ  ብዙም ሽክታ ስለማናይ ነው፡፡ እናንተ የምታወሩት በታክሲም፣ በምንም ስታልፉ እንደ ኤግዚቢሽን ስለምታዩዋቸው ሰፈሮች ነው፡፡ እኛ ደግሞ... “ድራፍቱን አረፋ ሞልተሽ ያመጣሽው በእናንተ ቤት አራዳ መሆናችሁ ነው!” እያልን ቀውጢ ስለምንፈጥርበት ሰፈር ነው የምናወራው፡፡ (ለግንዛቤ...‘ቀውጢ’ ማለት ግርግር ረብሻ ምናምን ለማለት ነው እንጂ ምንም አይነት ቻይንኛ ቅኔ ምናምን የለበትም። ልጄ፣ ዘንድሮ በእያንዳንዷ ቃል ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ዘመን ነው!)
እናላችሁ ሽክ ማለት እኮ ቅድሚያ በርካታ ነገሮች ከሆኑ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ምንም ሰበካ ምናምን የለውም፡፡ አሀ...‘ሶፍት ፔፐር’ ከሀያ ብር በአንድ ጊዜ ሠላሳ አምስት ብር የገባበት ጊዜ ነው እኮ! ለመቆጠብ እንኳን ፈተና የሆነ ነገር፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...) ጋዜጣ ደግሞ እየተወደደ ነው፡፡ (ቢያስቅ ኖሮ በሳቅን ነበር!) የምር ግን ይገርማል፡፡ የምግቡ ዋጋ ሲጨምር ‘ሶፍት ፔፐር’ የአጠቃላይ ‘ፕሮሰሱ’ አካል ነው ተብሎ ነው እንዴ!
ስሙኝማ... አንዲት “ይቺ ብትለበስ ሰው ፊት ይህን ያህል አታሳጣም!” የሚባልላት ጃኬት አምስት ሺህ እየተጠየቀባት ሽክ ማለቱ ቀርቶብን ብርዱን በተከላከልን! (ማሳሰቢያ..ይህ ዋጋ ከነዳጅ ጭማሪው በፊት ነው፡፡ አሀ...ተከትሎ የሚመጣውን ለማወቅ ‘አዋቂ’ ቤት አያስፈልገንማ!)
እኔ የምለው... “አንዳንድ ጊዜ እስቲ እንደሰዉ ላይፍ ይኑርህ!” የሚሉት ነገር እኮ ከምክርነት ይልቅ በሞራል ላይ የተካሄደ የባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃት ነው! ሚሳይሉ ሀገር ያወድማል፤ “እንደ ሰዉ ላይፍ ይኑርህ!” አይነት ምክርም ሞራል ያወድማል፡፡ ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንዳንድ ወገኖቻችን ላይፍ የሚለውን ነገር የሚያዩበት ነገር አስቸጋሪ ነው። በዚህ ዘመንም ቢራ መጠጫው መጨበሻው ከተገኘ በቃ ላይፋችንን ስንቀጭ ሲባል ስትሰሙ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ እሺ፣ ፈረንካው ከጤፉም፣ ከዳቦውም ከተረፈ ይጠጣ፣ ይጨበስ፡፡ ግን ላይፍ የምንለውን ነገር በዛች ብቻ አጥብቦ ማየቱ አሪፍ አይደለም፡፡
“ስማ... ዊክኤንዱ እንዴት አለፈ?”
“አሸወይና ነበር፡፡”
“አጅሬው ተመችቶህ ነበር ማለት ነው፡፡”
“መመቸት ብቻ! ስንጠጣ ስንጨብስ፣ ብቻ ምን አለፋህ ብርችንችን ስንል ነበር! ላይፋችንን ቀጨን ነው የምልህ!”
እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ...እኔ ምለው፣ በየቤቱ ያለውን የኢኮኖሚ ችግር ሁላችንም እንደየ ደረጃው ጓዳችንን ስለሚያንኳኳ እናውቀዋለን፡፡ አለ አይደል...ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚባለውን ብቻ ሳይሆን መካከለኛው ደረጃ የሚባለው ላይ ያለው ሁሉ ላይ ጫና እያሳደረ  ያለ ነው፡፡ እናላችሁ...በተወደደ መጠጥ ይህ ሁሉ ሰው የየመጠጫ ቤቱን ውስጥና ደጅ ሞልቶ እያማረጠ ሲገለብጥ የሚያመሸው፣ ገሚሱም ወፍ እስኪንጫጫ የሚያድረው በምን አይነት ተአምር እንደሆነ ግራ ግብት አይላችሁም!  ዋናው ጥያቄ “ለዚህ የሚያበቃውን ፈረንካ ከየት ነው የሚያገኘው?” ነው፡፡
ምቀኝነት?! ይህ የምቀኝነት ወይም ሌላው ደስ ሲለው ዓይናችን ስለሚቀላ ሳይሆን የኢኮኖሚ ትንታኔ ጉዳይ ነው፡፡ እኛማ...ለምን ይዋሻል፣  ያው የራሳችን “አዳም ስሚዝ” ምናምን የሚሉ ቅጥያዎች የሌሉበት ድምዳሜ ላይ መድረሳችን አልቀረም፡፡ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚዝናናው ከደሞዝ ባገኘው ገንዘብ መሰለህ! ልጄ፣ በብራይቡ ነው!” መባባላችንን መደበቅ ልክ አይሆንም፡፡ ምን መሰላችሁ... አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ እንደተፈለገው ‘የሚበተን ፈረንካ’ ላብ ያልፈሰሰበት ነው ይባል የለ! ብቻ የእኛን ‘ንድፈ ሀሳብ’ (ቂ...ቂ...ቂ...) ፉርሽ የሚያደርግ የባለሙያ ትንታኔ እስኪመጣ ደረስ እሷኑ ይዘን እናዘግማለን ለማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀች አንድ አጠር ያለች ቪዲዮ አለች።  በሆነ ግሮሰሪ ውስጥ ሲያዩት የልጆች አባት፣ የቤተሰብ ሀላፊ፣ “የተከበረ አባወራ የሚመስል ትከሻው የከበደ የሚባለው አይነት ሰው” እንዴት አዘናግቶ የሞባይል ቀፎ መንትፎ ሲሄድ የሚያሳይ ነው፡፡ ይገርማልም፣ ያስፈራልም። እንደዛ የሚመስል ሰው በዚህ አይነት ነገሮች ውስጥ ከገባ ማን፣ ከማን ጎን ሳይሳቀቁ መቀመጥ እንደሚቻል አስቡትማ!
እናላችሁ...እንግዲህ በዚህ ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ውጪ ለመመገብ ለሚገደዱ ወገኖቻችን ማዘን ግድ ነው፡፡ በየሆቴሉ ያለው የምግብ ዋጋ አጨማመር ጉድ የሚያሰኝ ነው። ደግሞ አቅማቸው አነስ ላለ ምናምን በሚል ነው መሰለኝ ብዙ ቦታዎች ‘ሙሉ’ እና ‘ግማሽ’ የሚባሉ ‘ዲሾች’ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የሙሉ አቅም ያለው በሁለት መቶ ሀምሳ ብር አንጀቱን ሲያርስ፣ የግማሽ አቅም ያለው ደግሞ በመቶ ሀያ አምስት አንጀቱን በግማሽ ያርስ ነበር፡፡  
ታዲያላችሁ... አሁን፣ አሁን ‘ግማሽ’ የሚሉትን ነገር እየተዉት ነው፡፡ እኛ ጭራሽ በእሩብና በአንድ አምስተኛ ወደ ደረጃችን ይወርዱልናል ስንል ግማሿንም የተዉአት... ምነው ግማሽ የሚያዘው የዓይኑ ቀለም አላማራቸውም እንዴ! ተዉ... ይሄ ቀን እንዲህ ሆኖ ዘለዓለሙን አይቀጥልም! ተዉ ግዴላችሁም...እንተሳሰብ! አይሆኑም የሚባሉ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ምድር ከፍ፣ ሰማይ ዝቅ ቢል ሊሆኑ አይችሉም የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ሊሆኑ በሚችሉባት ሀገር፣ ተዉ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ትዝብት ውስጥ አንገባባ!
ታዲያላችሁ...አንዳንድ የዋሀን ወዳጆቻችን “እንዲህ እኛን የማንችለውን ዋጋ እየቆለሉብን ጦማችንን አሳድረው እነሱ እንደው ምግቡ ይዋጥላቸዋል?” ይላሉ፡፡ ግራ ቢገባቸው ነው፡፡
“በካብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፣ በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፣ በምድር ላይ ብሠራ  እረኛው መከራ የት ውዬ የት አደር ብዬ!” የምትል ነገር አለች፡፡ ወፊቱ ነች አሉ እንዲህ ያለችው፡፡ የእኛም ነገር እንደዛ ይመስላል፡፡ ልክ ነዋ...ኑሮው በዚህ እንደምንም ዞረን አለፍነው ስንል በሌላ በኩል ወርድና ስፋቱን ጨምሮ ከች ይልላችኋል! እዚህ ቦታ ያሉትን እንቅፋቶች አልፈን ወደ ገላጣው ሜዳ ልንገባ ነው ስንል እዛኛው ቦታ ደግሞ ሙሉ በሬ ከእነዘር ማንዘሩ የሚያሰምጠው ኩሬ ከች ይልላችኋል! ይህኛውን ወንዝ አቋርጠን እፎይ ብለን ሳንጨርስ እዛኛው ቦታ ደግሞ አገር ብቻ ሳይሆን ሰማዩን ሊጋርድ ምንም የማይቀረው ጋራ ድንቅር! በቃ የችግር ሽክርክሪት!
በዚህ ላይ ደግሞ የብልጥ ሀገር ሆኖላችኋል፡፡ ኸረ ብልጥነት! ኸረ ብልጥነት! እኔ የምለው ይህ ሁሉ ብልጥነት እያለ እንዴት ነው በፕሬሚየር ሊግ ደረጃ የሞኝነት ሥራ የበዛው! የምር! አሁንማ ሞኝነት ‘እውቀት’ አይነት ነገር እየሆነ ማሳፈሩም ቀርቷል፡፡ ሰዉ ምን ነክቶታል! እንደው ሀገሩ ሁሉ ‘ወተቴ’ ነው ብሎ ማሰብ ከየት የተገኘ ልምድ ነው? (ለግንዛቤ...‘ወተቴ’ ማለት ሞኝ እንደማለት ነው እንጂ ምንም አይነት የእንትን ሰፈር ቅኔ የለበትም፡፡ “ደግሞ በተወደደ ወተት ምንድነው ብሶታችንን የሚቀሰቅስብን!” ብሎ ቅር የሚለው ወዳጅ እንዳይኖር ነው!)
ግለሰብ ብልጥ ይሆንባችኋል፤ ቡድን ብልጥ ይሆንባችኋል፤ ሚዲያ ብልጥ ይሆንባችኋል፣ ተቋም ብልጥ ይሆንባችኋል፡፡ አበሳ ነው እኮ፡፡
እናላችሁ...አለ አይደል... “አሁን እንዲህ አይነት የማይረባ ነገር ካሜራ ፊት ወጥቶ ሲናገር ትንሽ አይቀፈውም! በቃ... ‘ሰው ይታዘበኛል’ የሚባል ነገር ቀረ ማለት ነው!” የምንልባቸው ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገሮች እየሰማን፣ እያየን ነው፡፡ ጊዜው የመረጃ እንደሆነና ሰዉ መረጃ የሚያገኝባቸው በርካታ አማራጮች እንዳሉት መዘንጋት ራሱ የብልጥነት ምልክት አይደለም። ግን ደግሞላችሁ... በዛው ልክ በቀላሉ ‘ጉድ የምንሆን’ መአት ነን፡፡ በብልጥነት ስንት ሰው ፈረንካውን አስረክቦ አጨብጭቦ ቀርቷል! በብልጥነት ስንት ሰው ቤት ንብረቱን አጥቷል! በብልጥነት ስንት ሰው እንትናዬውን ዓይኑ እያየ አስነጥቋል! አዎ፣ “ብልጥ ጓደኛ የሰዎቹን የጋራዬ፣ የራሱን የብቻዬ” የሚሏት ነገር አለች፡፡ ጨዋታው እንዲህ ነው፡፡
እንግዲህ ነዳጅ ጭማሪው ተጀምሯል። እናማ... ጉዳችንን በመጪዎቹ ሳምንታት እናያለና! እንግዲህ ከባሰብን ውጭ ያሉ ወዳጆቻችንን እንደበፊቱ ስኒከር ላኩ፣ ምናምን ላኩ ማለት ትተን “ሶፍት ፔፐር ላኩልን፣” ማለት ሳንጀምር አንቀርም! ‘ሶፍት ፔፐር’ ከአሜሪካ! የጉድ ገንፎ እኮ አድሮ ብቻም ሳይሆን ሰንብቶም መፋጀቱ አይቀርም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1539 times