Saturday, 16 July 2022 18:03

ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ላይ የመንግስት አመራሮች እንዳሉበት ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(17 votes)

 • የመንግስት አመራሮች የጸጥታ አካላት ወደ ስፍራው እንዳይገቡ አድርገዋል ተብሏል
    • በጅንካ ከተማ ብቻ 144 የአማራ ተወላጆች ቤት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉ ተገልጿል
    • ለጥቃት አድራሾቹ ከመንግስት ካዝና አበል መከፈሉንም ሪፖርቱ አመልክቷልጥግ
              
             ባለፈው ሚያዚያ ወር በጎንደር በወራቤና በጂንካ አካባቢ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ተገለጸ። የፍትህ ሚኒስቴር ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ  ቢሮ ጋር በመተባበር ያካሄደውን የምርመራ ግኝት ይፋ አድርጓል።
በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋና በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ፣ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙልኢስ አብዲሳ በጋራ ስለ ለግኝቱ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኃላፊዎቹ በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ እንደገለጹት፤ በጎንደር ከተማ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም አንድ የእስልምና ሃይማኖት አባት ስርዓተ ቀብር ላይ የተፈጠረን ጊዜያዊ ግጭት መነሻ በማድረግ በተቀሰቀሰ ግጭት 20 ሰዎች ሲሞቱ፣ 100 ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በግችቱ አንድ መስጊድ ሙሉ በሙሉ ሲወድም፣ 8 መስጊዶች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። 2 መስጊዶች ላይም ቀላል ጉዳት ደርሷል።
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ 509 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመለከቱት ኃላፊዎቹ፤ የተደራጀው የምርመራ መዝገብ ለዐቃቤ ህግ መተላለፉን አመልክተዋል።
በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን ግጭት መነሻ በማድረግ፣ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ውስጥ በየተቀሰቀሰው ግጭትም 2 ሰዎች ሲሞቱ፣ 79 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። 4 የኦርቶዶክስና 3 የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ላይ ጉዳት ደርሷል። በ12 የግለሰቦች የንግድ ተቋማት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
በጂንካ ከተማ  ተፈጥሮ በነበረው ዘር ተኮር ጥቃትም የከተማው ከንቲባን ጨምሮ ሻንካ (ወጣት) የሚል ቡድን በማደራጀትና ቅስቀሳ በማድረግ፣ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በአማራ ተወላጆች ላይ መፈጸሙ ተገልጿል።
በዚህ ጥቃትም 1150 የአማራ ብሔር ተወላጆች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግ፤ 247 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት ወድሟል ተብሏል።
በጅንካ ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት በዞኑም በወረዳውም ያሉ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት መሆኑን ያመለከተው የምርመራው ግኝት ሪፖርት፤ “የዞን ጥያቄያችን ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደረገው የአማራው ተወላጅ ስለሆነ በቅድሚያ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ከአካባቢያችን ማስወገድ አለብን” የሚል ቅስቀሳ በመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ይደረግ ነበር ተብሏል። የጂንካ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ፣ የጂን ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ጅንካ ከተማ ፋይናንስ  ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የደቡብ  ኦሪ ወረዳ አስተዳደር፣ የጅንካ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በጥቃቱ ውስጥ መሳተፋቸውን ያመለከተው  የምርመራ ግኝት ሪፖርቱ ከመንግስት ፋይናንስ እየወጣ ለጥቃት ፈጻሚ ወጣቶቹ የወሎ አበል ይከፈል እንደነበርም አመልክቷል።
ፍትህ ሚኒስቴርና የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በጋራ ባደረጉት በዚሁ የምርመራ ግኝትም፤ የመንግስት አስተዳደር ላይ ያሉ ሰዎች በወንጀሉ ውስጥ በመሳተፍ ትልቅ  ሚና እንደነበረባቸው አረጋግጠናል ብለዋል።
በጅንካ ከተማ በተፈፀመው ዘር ተኮር ጥቃትም 144 የአማራ ተወላጆች ቤታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲቃጠል ሲደረግ፣ 46 ቤቶች ደግሞ በድንጋይና በተለያዩ ቁሳቁሶች ጉዳት እንዲደርስባቸው ተደርጓል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም አንድ መስጊድ ሲቃጠል፤ 232 የንግድ ድርጅቶች መዘረፋቸው ተጠቅሷል።
በወቅቱ የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ወደ አካባቢው ገብቶ የተፈጠረውን ችግር ለመከላከል እንዳይችል፣ “ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር የለም” በሚል አመራሮቹ የጸጥታ አካላት ወደ ስፍራው እንዳይገቡ አድርገዋልም ተብሏል።
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ 782 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።




Read 22471 times