Saturday, 13 October 2012 11:31

በኢትዮጵያ የአይሲቲ ግንዛቤና የግሉ ዘርፍ አላደጉም ሚዲያውና አይሲቲ ተራርቀዋል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(10 votes)

ወ/ሮ ያኔት ዓለሙ አዲስ አበባ ነው የተወለደችው - በ1969 ዓ.ም ነበር፡፡ ቸርቸል ጐዳና አካባቢ ያደገችው ወ/ሮ ያኔት፣ የተማረችውም ጥቁር አንበሳ ት/ቤት ነው፡፡ 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀች አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብታ በኦፊስ ማኔጅመንት በዲፕሎማ የተመረቀች ሲሆን ከማይክሮሊንክ ደግሞ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ በዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ወ/ሮ ያኔት “ሀ” ብላ ሥራ የጀመረችው ቢቲ በሚባል የእንጨት ሥራ ድርጅት ነው፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያን ክርስቲያን ቸርች ለተባለ የሃይማኖት ተቋም ለሴቶችና ወጣቶች የምክር አገልግሎት ለመስጠት ናይሮቢ - ኬንያ ሄደች፡፡ እዚያም አዲስ አበባና ናይሮቢ እየተመላለሰች ለሁለት ዓመት ከሠራች በኋላ፣ ግራፊክ ዲዛይን በሚሠራ አንድ ድርጅት ውስጥ በሂሳብ ሠራተኛነትና ጸሐፊነት ተቀጠረች፡፡ ከዚያም በፕሮግራም ማኔጀርነት፣ በረዳት ምክትል ማኔጀርነትና በክፍል ኃላፊነት አገልግላለች፡፡ የአዲስ አበባና የጀርመን ንግድ ም/ቤቶች ባቋቋሙት ፕሮጀክት ውስጥ ከከፍተኛ ኦፊስ ማናጀርነት እስከ ከፍተኛ ረዳት ፕሮጀክት ማኔጀርነት ሠርታለች፡፡

በአዲስ ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ ውስጥም በኮንሰልተንሲ አውትሪች ክፍል በማናጀርነት ሠርታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ መቀመጫው ናይሮቢ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ በሆነው የሃርድዌርና ሶፍትዌር ሶሉሽንስ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ቻናል ሴልስ ኢንኤብልመንት የኢትዮጵያ ተወካይ ሆና በማገልገል ላይ ናት፡፡ ከወ/ሮ ያኔት ጋር በሶፍትዌርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡

 

ሶፍትዌር ምንድነው?

እንዲህ ነው ብሎ በአንድ ቃል ለመግለጽ ያስቸግራል በአጠቃላይ ግን ኮምፒዩተሩ መሳሪያ (ሃርድዌር) እንዲሠራ የሚያደርጉ ትዕዛዞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሶፍትዌር እንደሚሠራው የሥራ ዓይነት በበርካታ ዘርፎች የሚከፈል ነው፡፡ ሁለቱ ዋነኛ የሶፍትዌር ክፍሎች ኦፕሬቲንግ ሲስተም (የኮምፒዩተሩን የአሠራር ሂደት የሚቆጣጠረው ሲስተም ሶፍትዌር) እና ሰዎች ኮምፒዩተር ሲጠቀሙ የሚገለገሉባቸውን በርካታ ተግባራት የሚቆጣጠረው አፕሊኬሽን ሶፍትዌር ናቸው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ የሶፍት ዌር ዴቨሎፕመንት በምን ደረጃ ይገኛል? በኢትዮጵያ እውቀቱ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች አልፈው በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ገበያዎች እየሠሩ ነው፡፡ ወደ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ዱባይ፣ ኳታር፣ … እየሄዱ የሚሠሩ ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ ያለው ችግር የእውቀት አይደለም፤ ያንን እውቀት የሚያስተግናድ ግንዛቤ ያለመኖር ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያን ብንወስድ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን (አይሲቲ) ሁሉም ሰው ይጠቀማል፡፡ ገበሬዎች ሳይቀሩ ሞባይል አፕሊኬሽኖችን ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀማሉ፡፡ ሁሉም ሰው አይ ሲቲ ስለሚጠቀም ግንዛቤያቸው ትልቅ ነው፡፡ መንግሥትና ሕዝቡ ጥቅሙን ስለሚያውቁ ተደጋግፈው አሳድገውታል፡፡ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጀሪያ፣ … ሙያው ተጠቃሚ ስላለው በደንብ አድጓል፡፡ የማኅበረሰቦቹ የአይ ሲቲ እውቀት መዳበር ሙያው እንዲያድግ አድርጐታል፡፡ በዚችም አገር ሙያው ትልቅ በመሆኑ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶት፣ በዩኒቨርሲቲና በኮሌጆች ትምህርቱ እየተሰጠ ነው፡፡ ነገር ግን ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ይኼውም የግሉ ዘርፍ አላደገም ስለዚህ ተማሪዎች በት/ቤት ያገኙትን እውቀት፣ ወደ ሥራው ዓለም ገብተው በተግባር የሚለማመዱበት፣ እውቀታቸውን የሚያሻሽሉበትና የሚቀጥራቸው የግል ዘርፍ “የለም” ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ወጣቶች እንደ ድሮዎቹ በሁለትና ሦስት ሺህ ብር ደሞዝ አንድ ቦታ ረግተው የሚቀመጡ አይደሉም፡፡ሁኔታውም እንደዚያ እንዲሆኑ የሚፈቅድ አይደለም፡ የተሻለ ነገር፣ የተሻለ ኑሮና ሕይወት ይፈልጋሉ፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ የሚፈልጉትን  ነገር ማግኘት ስለማይችሉና በውጭ አገራት ፍላጐታቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ስለሚያውቁ አገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ እዚህ የሚቀሩትም ፍላጐት ተመሳሳይ ነው፡፡ በተማሩት ሙያ ጥሩ ገቢ አግኝተው ሕይወትና ኑሮአቸውን ማሻሻል ስለማይችሉ የተሻለ ገቢ ሊያስገኙላቸው በሚችሉ የተለያዩ መስኮች እየተዘዋወሩ ይሠራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ደግሞ ሙያው ሊሻሻል አይችልም፡፡ ይህን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?በዚህ ጉዳይ ላይ ሦስት ነጥቦች መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የግሉ ዘርፍ መጠናከር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአይቲ ዘርፍ በአገሪቷ ያሉት ከ10 እና 15 ዓመት በፊት የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ማደግና መጨመር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት ነገሮች ይታዩኛል፡፡ አንድ በዚያን ወቅት የተቋቋሙ ድርጅቶች በቂ ሥራ ማግኘት አለባቸው፡፡ ምን ማለት ነው፣ በአሁኑ ጊዜ በአይቲ ዘርፍ የሚወጡት ብዙ ጨረታዎች ዓለም አቀፍ ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የአገር ውስጡ አቅም የላቸውም በሚል ግንዛቤ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የእኛ አገር አይ.ሲቲ ሳያድግና ባለቤቶቹ ሳይጠቀሙ የውጭ ድርጅቶች እየመጡ የአገሪቷን አንጡራ ሀብት (ብር) ይዘው ይሄዳሉ ማለት ነው እላለሁ፡፡ ይህ አሠራር መቆም አለበት፡፡ ሁለተኛው በእንጀራዬ ላይ መቆም ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ተጠናክረው፤ አቅማቸውን አጐልብተው ከውጪዎቹ ጋር እኩል ተወዳድረው አሸንፈውና የተሻለ ነገር አቅርበው ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ አለባቸው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ሁለተኛው ነጥብ በግሉም ዘርፍ ሆነ በውጪው ተፎካካሪ የሆነ ብቁ ዜጋ ለመፍጠር መንግሥት በአሁኑ ወቅት በቲ ቪ.ኢ.ቲ ደረጃ የአይሲቲ የጥራት መመዘኛ እያዘጋጀ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ዲግሪ ይሄዳል፡፡ ለእኔ ትልቁ ሚና ሲ.ኦ.ሲ ማስፈተን ሳይሆን ለሲ.ኦ.ሲ ፈተና ብቁ የሚያደርግ ካሪኩሌም ማዘጋጀት ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ካሪኩሌም ያረጀ ነው፡፡ ለመሠረታዊ የአይሲቲ እውቀት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ያሉት የአይሲቲ ፕሮጀክቶች የሚፈልጉት ከዚህ የተሻለና የላቀ ነው፡፡  ስለዚህ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የ4 ዓመቱ ፕሮግራም በ2 ዓመት አልቆ፣ ተማሪው ተጨማሪና አስፈላጊ እውቀት እንዲያገኝ አሁን በአንድ ኮርስ የሚሰጡት እንደ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ አርክተክቸራል ዲዛይን፣ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣ ሶፍትዌር አናሊስስ፣ ዳታ ቤዝ ማኔጅመንት፣ ኔትዎርኪንግ … የመሳሰሉት ኮርሶች በስፋትና በጥልቀት መሰጠት አለባቸው እላለሁ፡፡ እኔ እንዲያውም አንድ ሰው በዲግሪ ደረጃ አይሲቲ ሲማር፣ በኋላ ሁሉንም ኮርሶች ዝም ብሎ ከማስተማር መሠረታዊ እውቀት ካገኘ በኋላ ደስ በሚለውና በሚፈልገው በአንዱ ዘርፍ ስፔሻላይዝ ቢያደርግ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ አሁን በኢንጂነሪንግ የተጀመረው አሠራር ደስ ይላል፡፡ መሠረታዊውን የኢንጂነሪንግ እውቀት ካገኘ በኋላ በሜካኒካል፣ በኤሌክትሪካል … ኢንጂነሪንግ ሲማር ይቆይና በመጨረሻው ዓመት ደግሞ ከተማረው ውስጥ በአንዷ ዘርፍ ስፔሻላይዝ ያደርጋል፡፡ የዚህ ዓይነት አሠራር በአይሲቲም ቢመጣ አንዱ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ሌላው በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በአርክትክቸራል ዲዛይን፣ በሲስተም አናሊስስ፣ በኔትዎርክ፣ … ስፔሻላይዝ ቢያደርጉ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአንዱ ዘርፍ ስፔሻላይዝ ማድረግ ሲ.ኦ.ሲ ሲፈተኑ በተማሩት አንድ ዘርፍ ስለሆነ የጥራት ደረጃቸውን ለማወቅ ይረዳል፡፡ አገሪቷም በየዘርፉ ያላትን የሰው ኃይል ማወቅ ያስችላታል፡፡ ኩባንያዎች ሁሉንም ይፈልጋሉ፡፡ ሁሉም ሰው ደግሞ እንደሚፈለገው ሁሉን መሆን ስለማይችል ስፔሻላይዜሽን ቢኖር  ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ የሚጠብቃቸውን ገበያ ያውቁታል ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው መሻሻል ያለበት ነገር ተማሪዎች በንድፈ - ሐሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲለማመዱ (ኢንተርንሺፕ) ወደ ግል ኩባንያዎች ሲላኩ፣ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው በሚፈለገው ደረጃ ልጆቹ እንዲለማመዱ የሚያደርጉት፡፡ አብዛኞቹ ግን ሁለቱን ወር ሙሉ በሚማሩት ሙያ ሳይሆን በሌላ በማንኛውም የተለያየ (በፀሐፊነት፣ በእንግዳ ተቀባይነት፣…) ሲያሠሩ ቆይተው በመጨረሻ ከመቶ 99 ሰጥተው ይልካሉ፡፡ ይህ ጥሩ አይሆንም፡፡ ሌላው ነጥብ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ነው “በቂ የተማረ የሰው ኃይል አልቀረበልኝም” በማለት ቅሬታ የሚያሰማው፡፡ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ግን መቅረጽ ያለበት ራሱ የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት 2 ወር፣ በሁለተኛው 2 ወር የተላከለትን ተለማማጅ ተማሪ በትክክል ቀርፆ ቢመልስ፣ ተማሪው በ4 ወሩ የመስሪያ ቤቱን አሠራርና ባህርይ በደንብ ስለሚረዳ፣ ተማሪው ሲመረቅ፣ ድርጅቱ አቅሙን ስለሚያውቅ ቢቀጥረው/ራት ሊጠቅሙት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ኢንተርንሺፕ መበረታታት አለበት፡፡ ከአገር ውስጥ ኢንተርፕነሮችና ከውጭ ከሚመጡ ዳያስፖራዎች በአይሲቲ ስኬታማና ውጤታማ የሆኑ ብዙ ፕሮግራመሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ ጊዜያቸውን ሰውተው ቢያንስ በአዲስ አበባ ወዳሉ አይ ሲ.ቲ የሚያስተምሩ ተቋማት እየሄዱ ፐብሊክ ሌክቸር ቢያደርጉ በጣም ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ፤ በዘርፉ የተሰማራው የግሉ ዘርፍ በጋራ በመሆን ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ቢፈጥሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኮምፒዩተር አክሰሰሪዎች ላይ መንግሥት የሚያዘጋጀው ኤግዚቢሽን አለ፡፡ አክሰሰሪዎች ጠቃሚ ቢሆኑም ለእኛ ሙያ አይደሉም፡፡ እኛ በአሁኑ ሰዓት በጣም የሚያስፈልገን ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጣውም ቢሆን አገር ውስጥ ባለው ካልተደገፈ ዋጋ የለውም፡፡ በአሁኑ ወቅት አይሲቲ የሚማር ተማሪ “ስመረቅ በሙያዬ ሥራ አገኛለሁ” የሚል ተስፋ የለውም፡፡ ነገር ግን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ተባብረውና ተጠናክረው የሶፍትዌር ጠቃሚነትን የሚያሳይ ዓመታዊ ኤግዚቢሽን ቢያቀርቡ ተማሪው “በአገሪቷ ውስጥ ምን እየተሠራ ነው? የእኔስ አቅም ምን ያህል ነው?” በማለት ራሱን ያይበታል፡፡ እንዲሁም “ስመረቅ በሙያዬ ሥራ አገኛለሁ” ማለት ተስፋ እንዲታየው፣ እንዲበረታና እንዲጠነክር ያደርገዋል፡፡የዚህ ነገር መዘጋጀት ሌላው ጥቅም ለግሉ ዘርፍ ነው - እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ፡፡ “እሱ እዚህ ደርሷል፤ እኔ ግን እዚህ ነኝ፡፡ ለምንድነው እሱ ጋ ያልደረስኩት?...” በማለት ራሳቸውን ጠይቀው ለማደግና ለመሻሻል ይረዳቸዋልና አውደ - ርዕዩ ቢዘጋጅ፤ ሙያው በኢትዮጵያም ያድጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስፔሻላይዜሽን ያልሽው በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ነገር ግን ከአገራችን ሁኔታ አንፃር ስናየው ተግባራዊ መሆን ይችላል?እኔ የሚታየኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ በሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ሳይሆን በሌላ ሥራ የተሰማራ ቢሮ፣ የአይቲ ሰው ሲፈልግ፣ ሁሉንም ነገር የሚሠራለትን ሰው ነው የሚቀጥረው፡፡ እንዲህ ዓይነት መ/ቤቶች ብዙ ጊዜ የሚፈልጉት ሶፍትዌር ዴቨሎፐር ወይም አርኪቴክት ዲዛይነር ሳይሆን ሶፍትዌር፣ ሃርድዌር፣ ዌብ ሳይት መቆጣጠር የሚችል ሰው ነው፡፡ ይህን ሥራ ለማከናወን ደግሞ በአራት ዓመት የሚማሩትን በሁለት ዓመት ተኩል ቢጨርሱ፣ በእነዚህ ቢሮዎች የሚፈለገውን ተግባር ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ ስፔሻላይዜሽን ያስፈልጋል ያልኩት ከዚህኛው የተለየና ጥልቅ እውቀት የሚፈልገውን ነው፡፡ ለምሳሌ በኔትዎርክ ስፔሻላይዝ ማድረግ የሚፈልግ ሰው ለዚያ ሙያ ብቁ የሚያደርጉ ኮርሶች አሉ፡፡ እነዚያን ኮርሶች በደንብ ቢከታተል ሲ ኦ.ሲ ያልፋል፣ ማይክሮሶፍትም፣ ሲስኮም ቢፈተን ያልፋል፡፡ ምክንያቱም ለኔትዎርክ የሚያስፈልገውን እውቀት ከት/ቤቱ ይዞ ስለወጣ እነዚህ ፈተናዎች አዲስ አይሆኑበትም፡፡ በሙያው ስፔሻላይዝ ለማድረግ ከት/ቤት ወጥቶ ብዙ ገንዘብ ከፍሎ መማር አይኖርበትም፡፡ ስፔሻላይዜሽን እንዳለ ሲያውቁ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ሲስኮ፣ የአይሲቲ ትምህርት ወደሚሰጡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እየሄደ ሲሲኮ አካዳሚክስ እያቋቋመ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሮች በሲስኮ በቂና አስፈላጊ እውቀት ኖሯቸው እንዲወጡ ተማሪዎችን ያበረታታል፡፡ በሌሎችም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በማይክሮሶፍት ኤ አስ ዲ (አርኪቴክቸር ሶፍትዌር ዲዛይን) ባለሙያ መሆን የሚፈልግ ሰው፣ ከተመረቀ በኋላ ብዙ ገንዘብ ከፍሎ ከሚማር ት/ቤት እያለ እነዚህ ኮርሶች ከመደበኛው ጋር ቢሰጡ በዚያ ዘርፍ ብቁ መሆኑን ለሚያረጋግጥለት ለፈተና ብቻ ይከፍላል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ብቃትና ማስረጃ ያለው ሰው ይኖራል ማለት ነው፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በአገራችን ኮምፒዩተር መጠቀም ባህል አልሆነም፡፡ ለዚህ ምን መደረግ አለበት?በዚህ ረገድ አንድ የሚታየኝ ነገር አለ፡፡ ኮምፒዩተር ወደ አገራችን ሲገባ እንደመጥፎና ጐጂ ነገር ነበር የታየው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ያ አመለካከትና ግንዛቤ አደጋ መሆኑ ቀርቶ ኮምፒዩተር ጠቃሚ መሆኑን ሕዝቡ ተገንዝቦታል፡፡ ይሁን እንጂ ያም ቢሆን ኮምፒተር የሚጠቀሙ ሰዎች በቂ እውቀት የላቸውም፡፡ መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች በእጅ ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ አንድ መ/ቤት ወይም ድርጅት ኮምፒዩተር የሚጠቀም ከሆነ፣ ብዙ ጊዜ ሁሉንም የኮምፒዩተር ሥራዎች እንዲሠራ አንድ ሰው ነው የሚቀጠረው፡፡ ያ ሰው፣ ጥገናውንና ሌሎችንም ሥራ እንዲያከናውን ይጠበቃል፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ሁሉንም ነገር መሆን አይችልም፡፡ ከዚህም አልፎ ያ ሰው እንደ አይቲ ባለሙያ ሳይሆን የማይመለከተውን ነገር እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ ያ ባለሙያ የመ/ቤቱ ጉዳይ ፈጻሚ ወይም ድርጅቱን ወክሎ ስብሰባ እንዲሳተፍ ተደርጐ አጋጥሞኛል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥትና ሚዲያው ተቀናጅተው መሥራት ያለባቸው ነገር ይታየኛል፡፡ ለምሳሌ፣ አዲስ አድማስ ስለ አይ ቲ ጥቅም፣ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ የሚያሳይ አምድ በየእትሙ ሊኖረው ይገባል እላለሁ፡፡ ሌሎችም ጋዜጦችና ሚዲያዎች እንደዚሁ፡፡ ኢቴቪ በአይ ቲ ዙሪያ አንድ ፕሮግራም አለው፡፡ ያንን ዝግጅት ወጣቶች እንጂ ትልልቅ ሰዎች አያዩትም፡፡ እዚህ ላይ እኔ ድክመት እንዳለ ይታየኛል፡፡ ይኼውም፣ ኢቴቪ ብዙ ሰው የሚያየው ሚዲያ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች ብቻ የሚያዩትና ለወጣቶች በሚመች ሰዓት ከሚያቀርቡ፣ የአይሲቲን ጥቅም ወይም የተለያዩ መ/ቤቶች ከደንበኞቻቸው ጋር በቀጥታ በመገናኘት (ኦቶሜትድ) በመሆናቸው ያገኙትን ጥቅምና ልምድ የሚለዋወጡበት ቶክሾው ዓይነት ተከታታይ ፕሮግራም ማድረግ ይችላል፡፡ ሬዲዮኖችም እንደዚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ሚዲያውና አይ ሲ.ቲ ስለተራራቁ ይህ ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአይ ቲ ዙሪያ የሚደረጉ ዝግጅቶች የሚዲያ ሽፋን አያገኙም፤ እንደዜናም አይታዩም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ “Application Challenge 4 Ethiopia” በሚል ርዕስ ቴክኖ ሞባይል ባዘጋጀው ውድድር ላሸነፉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ 1ኛ ለወጣው 50ሺ ብር፣ 2ኛ ለሆኑት ሁለት ተማሪዎች ለእያንዳንዱ 25ሺህ ብር በአጠቃላይ 50ሺህ ብር፣ 3ኛ ለሆኑት ሦስት ተማሪዎች ለእያንዳንዱ 15ሺህ ብር በአጠቃላይ 45 ሺህ ብር፣ ላስተማራቸው ዩኒቨርሲቲ ደግሞ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተሸለመውን ያህል፣ በአጠቃላይ 290ሺህ ብር ሸልሟል፡፡ ያንን ዜና በብዙ በጋዜጦች አላነበብኩም፣ በቲቪ አላየሁም፤ በሬዲዮ አልሰማሁም፡፡ ይህ የሚያሳየው አይ ሲ.ቲ ትኩረት ስላላገኘ የዜና ሽፋን እንደማይሰጠው ነው፡፡ በአንድ ክልል በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ስብሰባ ቢካሄድ ሚዲያው ተሯሩጦ ያቀርበዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር ለአይ ሲ.ቲ.ም መኖር አለበት፡፡ ዘርፉ ሊያድግ የሚችለው በሚዲያ ነው፡፡ በየትኛውም የአገሪቷ ክፍል ያለው ሀብት የሚታወቀው በሚዲያ ነው፡፡ በዚህ በኩል ድክመት ስላለ መስተካከል አለበት እላለሁ፡፡ መንግሥትም ሚዲያውን ጠርቶና ትብብር በመፍጠር “ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ስንሠራ ለሕዝብ አስታውቁ፤ ንገሩ በማለት አስገዳጅ ሕግ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሌሎች አገሮች የሚዲያ ዘገባዎች ለሕዝቡ የሚደርሰው በጋዜጦች አይደለም፤ በቀጥታ (ኦንላይን) የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ነው፡፡ በርካታ የሆኑትን የጋዜጣ ገጾች የሚያገላብጥ የለም፡፡ እዚህ ግን የጋዜጣ አንባቢ ብዙ ስለሆነ፣ የአይ ሲቲ መልዕክት በጋዜጦችም መተላለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ኦንላይን የሚሰራጩትን መልዕክቶች የሚያስተላለፈው የአይ ቲ ባለሙያ የሆነ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ወደሚቀጥለው የሚዲያ ደረጃ ለመሸጋገር የአይሲቲ እውቀት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ በትብብር ዘርፉን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ያለው የአይ ሲቲ አጠቃቀም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር እንዴት ነው?በሌሎች አገሮች አንድ የመጀመሪያ ወይም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ብዙ ነገር ይሠራል - ልቀው ሄደዋል፡፡ በሌሎች አገሮች የአይ ሲ.ቲ ማዕከላት ብዙ ናቸው፡፡ ማንኛውም ወጣት ወደእነዚያ ማዕከላት ሄዶ ኮምፒዩተሩን በመክፈት ሐሳቡን ለሌሎች ያስተላልፋል፤ የሌሎችንም ሐሳብ ይቀበላል፡፡ እንደጌም ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኛ አገር ስሜት መግለጫ ቦታ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቢኖርም ሰው አያውቀውም፡፡ ሁለትና ሦስት ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚያ ቦታዎች በሚዲያው ድክመት የተነሳ፤ በጣም የሚፈልጋቸው ሰው ቆፍሮ ከሚያገኛቸው በስተቀር አብዛኛው ሰው በቀላሉ የሚያገኘው አይደሉም፡፡ በሌላው አገር ግን ወጣቶች እንደ ካፌ ሄደው ስሜትና ፍላጐታቸውን የሚገልፁባቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ሐሳብ ለመለዋወጥ የግድ የአይ ሲ.ቲ ባለሙያ መሆን አይጠበቅም፡፡ እዚህም የአካውንቲንግ ባለሙያ ሆነው ፕሮግራሚንግን በማንበብ የሚሠሩ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሀሳባቸውን የሚለዋወጡበትና የሚያዳብሩበት ስፍራ ቢያገኙ ምን ያህል ውጤታማ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩን እንደሚችሉ መገመት አያቅትም፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር ይህ ይጐድላል፡፡

Read 9929 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 13:41