Print this page
Saturday, 16 July 2022 18:20

“ኢትዮጵያዊ ግን ሀገሩ የት ነው?”

Written by  ቃልኪዳን ኃይሉ
Rate this item
(0 votes)

ከቤት ሰራተኛነት እስከ ክብርት ቆንስላነት
                           
               መግቢያ
እስከዳር ግርማይን የማውቃት እንደማንኛውም የኢትዮጵያን ኪነጥበብ በቅርበት እንደሚከታተል ሰው፤ በተዋናይነቷ፣ በፕሮዲውሰርነቷና በስክሪፕት ፀሐፊነቷ ነው፡፡ (ሞዴል እንደሆነችም አውቃለሁ።) “የጥቁር እንግዳ” እና “ሰውነቷ” በተሰኙ ፊልሞቿ ኮምጨጭ፣ ኮስተር፣ ጀገን… ያለ ገጸ ባህሪ ተላብሳ ነው የምትጫወተው፡፡ እኔ በግሌ ትንሽም ተዝናኖት የሌለው፤ አንዳንዴ “በዋልድባም ይዘፈን የለ?” ትንሽ ሳቅ ማለት፤ ትንሽ ፈገግ፤ ፈልጎ መቀለድ፤ ፈልጎም መጫወት የሚጎድላቸው (Humorless) ገጸ ባህሪዎች አይስቡኝም (ደግሞ መች በሳቀች የሚያስብል ፈገግታና ጥርስ ይዛ መሆኑ ይብስ ያናድዳል)፡፡
ብቻ እስከዳር ወክላ የምትጫወታቸው ገጸ ባህሪዎች የሚያልፉበትን ታሪክና የሕይወት ገጠመኝ ወድጄ የበዛ ኮስታራነቷ ትንሽ ይከብደኛል፡፡ ቢሆንም ሥራዎቿን አያቸዋለሁ፤ ጥራት፣ ቁምነገር፣ እውነትም ውበትም አለውና።
ይህች ተዋናይት “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚል መጽሐፍ እንዳወጣች ሰማሁ። ስለ መጽሐፉ ስሰማ አንዳንዶች የግል የሕይወት ታሪኳ (Autobiography) ነው ሲሉ፣ አንዳንዶችም ደግሞ የግል ማስታወሻዎቿ (Memoirs) ናቸው አሉ፡፡ የሕይወት ታሪኳንም ሆነ ማስታወሻዋን ለመጻፍ ትንሽ ብትቆይ ጥሩ ነው ብያለሁ፡፡ እንዲህ ያስባለኝ ምክንያት አብዬ መንግስቱ ናቸው፡፡ አብዬ መንግስቱ “መንግስቱ ለማ (ግለ ታሪክ)” በሚለው መጽሐፋቸው መንደርደሪያ ላይ፤ “ሰው ሃምሳ ዓመት ከሆነው በኋላ አንድ አይነት ግለ ታሪክን የያዘ (Autobiography) የሆነ ፅሑፍ ለተከታዩ ትውልድ ማቆየት እንዳለበት በመገንዘብ አንድ ጥሩ ደብተር ገዛሁ” ይላሉ፡፡ በዚህች ዓረፍተነገር የተነሳ ይመስለኛል፣ እስከዳር ምናለ ሃምሳ ቢያልፋት ብዬ አስቤ የነበረው፡፡ መልሼ ደግሞ “የአናን ማስታወሻ” ገና በአስራ ስድስት አመቷ ባትከትብልን ኖሮ፣ ያን ዘመን በምን እናውቀው ነበር? ብዬ ራሴን በራሴ አርሜያለሁ፡፡
ከምንም በላይ ግን የታዋቂው ፖለቲከኛ የአንዳርጋቸው ጽጌን “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” የሚለው መጽሐፉ ላይ (ይህም ግለ ታሪክ መጽሐፍ ነው) የከተበው ትዝ ብሎኝ፣ ኧረ ትጻፍ አስብሎኛል፡፡ ፖለቲከኛው አንዳርጋቸው በ1970ዎቹ መጨረሻና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንግሊዝ ሀገር “ውሊች” በምትባል መንደር የኮሌጅ ተማሪ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከክፍሉ ተማሪዎች ጋር በእድሜ ከአምስት አመትና ከዚያ በላይ፤ በሕይወት ገጠመኝ ደግሞ ከተማሪዎቹም አባትና አያትም ጭምር እበልጣለሁ ብሎ ስለሚያስብ ውሎው ከእሱ ከሚበልጡ አረጋውያን ጋር ነበር፡፡ በጊዜው አረጋውያኑ የአንዳርጋቸውን ወጣትነት አይተው እድሜውን ሲጠይቁት፤ “እርግጠኛ አይደለሁም ወደ ዘጠና ሳይጠጋኝ አልቀረሁም” ሲል ይመልሳል፡፡ አረጋውያን ወዳጆቹም፤ “አትቀልድ እውነተኛ እድሜህ ስንት ነው?” ሲሉት የወጣቱ ፖለቲከኛ መልስ፣ ቁጥሩን ሳይሆን የሕይወት ውጣ ውረዱን ነበር፡፡
በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሕይወቱ ከአዲስ አበባ እስከ አሲምባ ተራራ፤ ከቤት እስከ እስር ቤት፤ ከካርቱም እስከ ለንደን፤ በሞትና በሕይወት ባለ ቀጭን የሕይወት መሿለኪያ የተሽሎከለከውን፤ በመሀል ከተማ የተሳተፈበትን የባንክ ዝርፊያና ተኩስ፤ ከወባና ከተስቦ መትረፉን፤ እጁን ላለመስጠት ከሰባተኛ ፎቅ ራሱን ፈጥፍጦ ስላጠፋው የትግል ጓዱ፤ ምስጢር ላለማውጣት “ሳናይድ” ኪኒን ውጠው ራሳቸውን ስለሰዉ የዘመን አጋሮቹ፤ ስለ ትግራይ በርሃዎች… እያነሳ እድሜው በሃያዎቹ አጋማሽ ሳይሆን በመከራውና ባሳለፈው የተለያየ ገድል ዘጠና እንደሚያንሰው ይከራከራል፡፡
ይህን የሚሰሙ አረጋውያን ወዳጆቹ፤ “የሰውን ልጅ እድሜ በዚህ አይነት መንገድ ከሆነ የምትመለከተው፤ ታዲያ የእኛንስ እድሜ ስንት ሊሆን ነው?” ብለው ሲጠይቁት አንዳርጋቸው፤ “ቅድም አያቶቻችሁ፤ አያቶቻችሁ በተራመዱባቸው መንገዶችና ድንጋዮች ላይ አሁንም እየተራመዳችሁ ነው፡፡ በኖሩበት ቤት ውስጥ ትኖራላችሁ፡፡ የጠዋት ሻያችሁን እነሱ ሲያፈሉበት በነበረ ጀበና ታፈላላችሁ፡፡ እድሜ ከሰጣችሁ የነገውን ብቻ ሳይሆን የዛሬ ሃያ ዓመት ምን እንደምትሰሩ የታወቀ ነው… ለእኔ እናንተን የስልሳ አምስትና የሠባ ዓመት አረጋውያን አድርጎ ማየት ይቸግረኛል፡፡ ዕድሜያችሁ ምድር ፀሐይን በዞረችባቸው ዙሮች ቁጥር ሊለካ አይገባውም፡፡ የእናንተ አጠቃላይ የሕይወት ተሞክሮ የአንዷን ቀን የሕይወታችሁን ተመክሮ ድግግሞሽ ስለሆነች ዕድሜያችሁ ያችው አንድ ቀን ብቻ ናት” ሲል ይመልሳል፡፡
ስለዚህ በአብዬ መንግስቱ ስሌት ሰው ሃምሳን ስላለፈ ብቻ ሊጽፍ አይችልም፡፡ ቁምነገሩ ሃያውንም ሰላሳውንም እንዴት አሳለፈው ነው። በዚህ መንገድ ነው የእስከዳር ግርማይን “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚለውን መጽሐፍ ያነበብኩት፡፡ እውነትም የአንዲት የአርባ ምናምን አመት (ከብዙ የሀገራችን ሴት ተዋንያን በማይጠበቅ መልኩ እድሜዋን ስላመነች ነው የገለጽኩት) ቆንጅዬ፣ ሞዴል፣ ተዋናይ፣ አምባሳደር… ከቤተ ሰራተኝነት ተነስታ ተአምር በመሰለ ትጋት ሕይወቷን፣ ዕጣ ፈንታዋን በራሷ  የወሰነች ነች፡፡ ታሪኳን በፈቃዷና በጉልበቷ እንደ አዲስ የጻፈች እንስት ናት፡፡ መጽሐፍዋን  አስተማሪ፣ አስገራሚ፣ አስደንጋጭ… ድፍረትና ኃይል የበዛበት ግን ደስ በሚል ውብ ቋንቋ ተከሽኖ የቀረበ  ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
አንዳንዱ እንደው ዘመኑም ተመችቶት፤ ቤተሰብም አጋዥ ይሆንና ታሪክ ይሰራል። አንዳንዱም ከባዶ ተነስቶ ተፍጨርጭሮ የልቡ ባይደርስም ያቅሙን ይሞክራል፡፡ እንደ እስከዳር ከምንም ተነስቶ በብርታት፣ በትግል፣ በኃይል ታሪኩን በደማቁ ይጽፋል፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ ለደከሙት ብርታት፤ ለጀማሪዎች ስንቅ፤ ለበረቱት ልምድ ልውውጥ ነው፡፡ አስተማሪም አዝናኝም ነው፡፡ የእስከዳር “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” መጽሐፍ ግለ ታሪክ ወይስ ማስታወሻ?
ግለ ሕይወት ታሪክ ምንድነው?
ብዙዎቻችን ግለ ታሪክ (Autobiography)፣ የሕይወት ዘገባዎች (Diaries)፣ ከዜና መዋዕሎች (Chronicles)፣ ከግል ማስታወሻዎች (Memoirs) እና ትዝታዎች (Reminiscence) ከሚባሉ አጻጻፎች ጋር ያለው ምስስልና ልዩነት ላይ መምታታት አለብን፡፡
በተለይ ግለ ታሪክ (Autobiography) እና የሕይወት ዘገባዎች (Diaries) ከግል ማስታወሻዎች (Memoirs) እና ትዝታዎች (Reminiscence) ጋር ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ተመሳስሎሻቸው ጸሐፊዎቹ ከራሳቸው ሕይወት ተሞክሮ በማስታወስና ከማስታወሻቸው እያመሳከሩ የሚጻፉ  በመሆናቸው ነው፡፡ ይመሳሰላሉ ማለት ግን አንድ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ትዝታዎች (Reminiscence) ስንል ዛሬ ላይ ተቁሞ ትናንትን እያስታወሱ፣ ምንም የታሪክ ማስረጃ ሳያጣቅሱ፣ በራስ አዕምሮ ጓዳ ያለን ነገር አስታውሶ በመጻፍ ለንባብ ማብቃት ነው። ለዚህም ምሳሌ የመርስኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ “ካየሁት ከሰማሁት፤ የሃያኛው ክፍለዘመን መባቻ” እና የሐዲስ አለማየሁ “ትዝታ” ተጠቃሽ ነው፡፡ ግለ ማስታወሻዎች (Memoirs) ስንል ጸሐፊው በዘመኑ ቢነገር ፋይዳ አላቸው ከሚላቸው የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ መርጦ ለአንባቢ የሚያቀርብበት ልዩ ማስታወሻ ነው። “ሰበዝ”፣ “የታፋኙ ማስታወሻ”.. በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ማስታወሻዎች የሕይወት ዘገባዎችን (Diaries) መነሻ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ መገልበጥ አይችሉም፡፡ ጸሐፊው ለትውስታው ያለው ቅርርብ፣ ስሜትና ምልከታ ላይ ያተኩራል፡፡ አጻጻፉም እውነትን በልቦለዳዊ ተረክ የሚከተል አንዳንዴ የቃላት ምልልስን፣ መቼ እና የት የጨመረ ነው፡፡
ግለ ሕይወት ታሪክ ስንል ግን ትውስታንና የሕይወት ገጠመኞችን በመያዙ ከግለ ማስታወሻና ከትዝታ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ነገር ግን በጣም መደበኛ የአጻጻፍ ሥልትን የተከተለ፤ ማስረጃ የያዘ፤ እውነትነት የሞላው፤ የጸሐፊውን ከውልደት ፅሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የእድሜ ቅደም ተከተል ጠብቆ የሚቀርብ ነው። ግለ ታሪክ ዛሬ ላይ ተሁኖ ትናንት ማየት፣ ማስታወስ፣ አስታውሶም ለአንባቢ ማድረስ ስለሆነ፣ በዚህ መንገድ ውስጥ የትናንት ራስን ከዛሬ ማንነትና ብስለት ጋር እያወዳደሩ መታዘብ፣ መሄስ ያለበት የራስ የሆነ አሉታዊም አዎንታዊም ግምገማን ያካትታል፡፡ ከስሜት ይልቅ እውነትን፣ ማስረጃና መረጃን የያዘ ነው፡፡
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚለው የእስከዳር ግርማይ መጽሐፍ ከግለ ታሪክ (Autobiography) በላይ ወደ ግል ማስታወሻዎች (Memoires) ያደላ መጽሐፍ ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ቦታ ላይ የሕይወት ዘገባዎች (Diaries) ቀጥታ የተገለበጠ አለው። ከዚያ በተረፈ ሙሉው መጽሐፉ ግለ ማስታወሻዎች ሲሆን የጸሐፊዋ ብስል ዕይታና ምስል ከሳች ትረካ ተጨምሮበት ዐይናችን ከንባብ፤ አዕምሮዋችን ምስልን እየከሰተ ከጽሑፍ ጋር በሃሳብ እያነጎደ ከኮረም አሰብ፤ ከአሰብ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ ባህሬን፤ ከባህሬን ፈረንሳይ፤ ከፈረንሳይ ባህሬን ተመልሰን ከባህሬን ትኬት ቆርጠን አሜሪካ እንገባለን፡፡ ከባህሬን ዱባይ፣ ወይም ኢትዮጵያ…. የሻይ ጉዞዋ ነው ብዬ ነው ዝም ያልኩት፡፡ ጸሐፊዋ እስከዳር ከዚህ ሁሉ ጉዞና ውጣ ውረድ፤ ከዚህ ሁሉ ስኬትና ድል በኋላ “ባህሬንን አየነው ከእግር እስከራሱ፤ ፈረንሳይን አየነው ከእግር እስከራሱ ለካስ ደስ የሚለው ኢትዮጵያ ሲደርሱ” የምትል ይመስለኛል፡፡
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” እንደ ግል ማስታወሻ
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚለው የእስከዳር ግርማይ የግል ማስታወሻ ማለት የአንዲት የፊልም ባለሙያ፣ ደራሲ፣ ፕሮዲውሰር፣ የክብር ቆንስላ የሕይወት ውጣ ውረድና ገጠመኝ ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንድፍታ ላውጋችሁ” ከተሰኘው መፅሐፍ ላይ ዲያቆን ብርሃኑ አድማሱ ከጻፉት ቀዳሚ ቃል ላይ የፕሮፌሰሩን ጽሁፍ ከዳሰሱበት ሦስት አእማድ ማለትም መራጭነት፣ አጓጊነት እና ሥዕላዊ አመላካችነት አንጻር እንየው፡፡
1.መራጭነት
ኤድዋርድ ቦለስ (Edward Bolles) የተባለ የሥነ ልቦናና የማስታወስ ክህሎት ማዳበር ባለሙያ ስለ ትውስታ እንዲህ ይላል፤ “We remember what we understand; we understand only what we pay attention to; we pay attention to what we want” (የተረዳነውን ነው የምናስታውሰው፤ ትኩረት የሰጠነውን ነው የምንረዳው፤ ትኩረት የምንሰጠው ደግሞ የምንፈልገውን ነው፡፡)
በኤድዋርድ አመክንዮ ስንንተራስ የሰው ልጅ የሚመዘነው በሚያተኩርበት ቁም ነገር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው የትኳሬው ውጤት ነው፡፡ ትኳሬያችን ያለንበት ዛሬን ያነብራል፡፡ እኛ ማለት የትኩረታችን፣ የማስታወሳችን እና የመረዳታችን አቅምና ፍላጎት ውጤት ነን፡፡
እስከዳር በሕይወት ዘመኗ ብዙ የምታስውሳቸው፤ በአዕምሮዋ ጓዳ ያሉ ብዙ የተከዘች የፈነጠዘችባቸው፤ የኮራች ያፈረችባቸው፤ ቅርም ደስም ያላት… መልካምም መጥፎም አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እነዚያን ሁሉ ግን እንዳልጻፈችልን እውነት ነው፡፡ በእሷ ምርጫ ውስጥ የእሷን የመምረጥ አቅም ስናነበው በምናገኘው እርካታና አዲስነት፤ ነገሩ አዲስ ባይሆን እንኳ አቀራረቡ አገላለጹ አዲስነት እንደመማለን፡፡ የጻፈቻቸው፤ የነገረችን ታሪክ ምርጥ ለመሆኑ ሴትነት፣ የፊልም ባለሙያነት፣ ዲዛይነርነት… ምን መምረጥ እንዳለባት ረድቷታል ብዬ አስባለሁ፡፡
ለምሳሌ መጽሐፏ ላይ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የምናውቀውን ኃይሌ ገ/ሥላሴን የገለጸችበት መንገድ በጣም ይለያል፡፡ “ኢትዮጵያ እኮ ልቧ የሚመታው ኃይሌ ውስጥ ነው” ትላለች፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ውስጥ ብዙዎቻችን ልብና አዕምሮ ውስጥ ያለው ኃይሌ ገ/ሥላሴ ተመሳሳይ ይመስለኛል፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን ኃይሌ ሌላ ነው፡፡ ኃይሌ ሯጭ ብቻ ሳይሆን መመኪያ፣ ማስፈራሪያ፣ መከታ… ወንድምም አባትም ነው፡፡ ለቤት ሳይሆን ለሰፈር፤ ለሰፈር ብቻ ሳይሆን ለሀገር፤ ለሀገርም ሳያንስ ለአህጉር የተረፈ፤ የሆነ የማይታይ ግን የሚያሳምን ባለ ሙሉ ማዕረግ ጄነራል ነው፡፡ ድሃ ተብለው ለሚሰደቡ ኢትዮጵያውያን፤ በቤተ ሰራተኛነት ብቻ ለሚያውቁን ለእነዛ፤ ኢትዮጵያዊ ሀኪም፣ የሕዋ ተመራማሪ፣ መሐንዲስ፣ አርቲስት፣ ከያኒ፣ ደራሲ… ለማያውቁ ለእነዛ፤ ኃይሌ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚንቀሳቀስ ሕያው ኢትዮጵያ ነው በማለት እስከዳር የኃይሌን አድባርነት ታሳየናለች፡፡
ለብዙዎቻችን ሯጩና ባለሃብቱ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ለእንደ እስከዳር አይነቱ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ኃይሌ ለእስከዳር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን  ለሚንቁ ሰዎች፣ ሀገራቸው ሄዶ ኢንቨስት የማድረግ አቅም ያለው ባለሃብት ነው፡፡ ኃይሌ ዓለም በአንድነት ተነስቶ ያጨበጨበለት፤ ነጮች እግርህ እንሳመው ብለው የሚንገበገቡለት… መሆኑን በመናገር ሲሮጥ ብቻ ሳይሆን ሩጫ አቁሞም የሀገሩን ልጆች ከመናቅ፣ ከመሰደብ ያዳነ፣ መመኪያ ታላቅ ወንድም፣ አባት ነው፤ በእስከዳር መጽሐፍ፡፡ እስከዳር የኃይሌን ውለታና አቅም በአንድ አረፍተነገር ስትገልጠው እንዲህ በማለት ነው፤ “ኃይሌ መጥፎ ገጽታችንን ማጥፊያ ዳስተራችን ስለሆነ እወደዋለሁ”፡፡
የራሱን ታሪክ የሚጽፍ ሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት ያለው፤ በሥራውም በትምህርት ዝግጅቱም ምልዑ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለ ትምህርት ዝግጅቷ “አልተማርኩም” በሚለው ምዕራፏ ላይ ማየት ይቻላል፡፡ እስከዳር አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ ትናገራለች፡፡ የባህሬን የክብር ቆንስል ሆና አገልግላለች፡፡ በቁንጅና ውድድር አንደኛ የወጣች፤ በዓለም አቀፍ ክንውኖች ማስታወቂያዎች ላይ የተሳተፈች፤ ሁለት ፊልም ላይ የተወነች፤ ፕሮዲውስ ያደረገች፤ አንዱን በድርሰት ያቀረበች ናት። በባህሬን የኮሚውኒቲ አመራር በመሆን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሌለበት ራሷ አምባሳደር ሆና ቤቷን እንደ ኤምባሲ ከፍታ ሀገሯን ያገለገለች ሴት ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህች እንስት ታሪክ መጻፉ ተገቢነት አለው፡፡
መጽሐፏ ላይ እንደምናነበው፤ በራሷ ተነሳሽነት ለወገኖቿ በተቻላት አቅም ቆማለች። በዚያ ውስጥ ከባዕዳን ወይም ከሀገሬው ባለቤቶች በላይ ኢትዮጵያውያን የኤምባሲው ሰራተኞች ራሳቸው፣ ከኢትዮጵያውያን ጉዳትና ችግር በላይ ስለ ሪፖርትና ቢሮክራሲ በጣም መጨነቃቸው ደም እያፈላ፤ በዚህ ስለ ደሞዝና ስለ ነገ ሹመት ሳይሆን ስለ ባንዲራውና ስለ ባንዲራው ስር ልጆች መፋለምን እናይበታለን። ለዚህም ነው ይህች እንስት አምባሳደር ሆና፣ በክብር ቆንስልነት የተሾመችው ያስባለኝ፡፡
2. አጓጊነት
አሜሪካዊው ጸሐፊ፣ አርታኢና መምህር ዊልያም ዚንሰር (William Zinsser) ስለ አጓጊነት እንዲህ ይላል፤ “Memoir… may look like a casual end even random calling up of bygone events. It’s a deliberate construction” (ማስታወሻ ሲጻፍ እንዲሁ እንደነገሩ ከትውስታ ማኅደር እየተፈተሸ የወጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ በእቅድ የተደረደረ ኩነት እንጂ፡፡)
ግለ ማስታወሻ ላይ አጓጊነት ማለት ግጭት ወይም ሴራ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ አንባቢን እያባበሉ ከመጀመሪያ ገጽ እስከ መጨረሻው እያዝናኑ፣ እያስገመቱ፣ እያጠየቁ፣ እያስደመሙ… የሚወስዱበት መጀመሪያ የጠየቁትን ጥያቄ እስከ መጨረሻው መልስ ሳይሰጡ መዝለቅ ነው፡፡ ታሪኩ ቢታወቅ እንኳ ከሚታወቀው እውነት ሌላ እውነት አለ ብሎ አንባቢው እንዲያምን ማስቻል፡፡ በዚህ ውስጥ ከ“ለምን” ይልቅ “እንዴት” የሚለው ጥያቄ ትልቅ ቦታ አለው፡፡
አንዳንዴ አጫጭር ልብ ወለድ ሲሆን አንዱ ካልሳበን ጥለነው ሌላኛውን ልናነብ እንችላለን። የእስከዳር ግርማይ መጽሐፍ የማስታወሻዎች ስብስብ እንደመሆኑ ከርዕስ ርዕስ ሁሉም ተያይዘውና ተሰናስለው የተቀመጡ አይደሉም፡፡ አንዱን ርዕስ አንብበን ቀጥሎ ያለውን የምናነበው ስለወደድነው ሳቢ ስለሆነ እንጂ፤ እንደ ልቦለድ በጣም ተያያዥ ስለሆነ፣ አንዱ ያንዱን ታሪክ ያን ያህል ስለሚያጎድል አይደለም፡፡
ባህሬን ለመሄድ ሁለት ሺህ ብር በማጣትና ብሩን ለማግኘት የተሄደበት ቤተሰብን የማስቸገር መንገድ፤ ብሩን መከልከል የፈጠረው መቃቃርና እስከ እለተ ሞት ድረስ የዘለቀ መኳረፍ የፈጠረው ቅያሜ አንጀት ይበላል (ወላጅ አባት የትኬት ብር ከከለከለ ታዲያ እንዴት ባህሬን ሄደች? ትዝታ ውስጥ ከለምን ይልቅ እንዴት ትልቅ ቦታ አለው።) ቅያሜው ከአባት ጋር ሲሆን ልብን ይሰብራል፡፡ እድሜ የሚያመጣው ብስለት፣ ሁሉም ወላጆች እንደሚሉት፣ “ወልደሽ እይው” እርግማን አቀፍ ምርቃት ያመጣውን ስክነት፣ በዛሬ መነጽር ነገን እያዩ በይቅርታ እንዳይሽሩት ሞት ሲቀድም ያማል፡፡ ዝም ያለ ፀፀት፡፡ እምባ ወደ ውስጥ ሲፈስ፡፡
ግን አባት ለምን ከለከለ ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ አባት እውነት አለው፡፡ አረብ ሀገር የሚሄዱ ሴቶች “አንድም ለግርድና፤ አልያ ለሽርሙጥና” ብሎ ስላመነ ነው፡፡ እስከዳር ደግሞ ትናንት ላይ ዛሬን አየች፡፡፡ አባት እዚህ ተማሪ አለ፡፡ እሷ እዛ ሄጄ ታሪክ እሰራለሁ አለች፡፡ አባት ስላልታየው ተቀያየሙ፡፡ አባት አይፈረድበትም፤ ልምዱና ገጠመኙ የነገረውን ነው ያደረገው፡፡ እሷም ያሰበችውን ከማሳካት ማንም አያቆመኝም አለች፡፡ ወጣትነት ልበሙሉነት፡፡ አባት ላይ ጎፈላች፡፡
እዚህ ላይ ቴዲ አፍሮና አባቱን ያስታውሰኛል። ቴዲ አፍሮ “ሙዚቃ ሕይወቴ” በሚለው ዘፈኑ ውስጥ ስለ አባቱና ስለ እሱ ጠብ ያወራል፡፡ የቴዲ አባት ካሳሁን ገርማሞ “ተው ልጄ ኪነት…. ከሀሁ ታረቅ” ይላል፡፡ ቴዲ ይመልሳል “በአንቺ ሆዬ ቃና ላላ ላላ… ልጁ ምን ያደርግን ክራሩን ያዘ”፡፡ የቴዲ አባት ካሳሁን ገርማሞ “ተማር” እንዳሉ እንደተቆጡ እንደመከሩ አረፉ፡፡ ቴዲ “ሙዚቃ ሕይወቴ” እንዳለ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ላይሻር ላይደለዝ ከላይ ከቁንጮው ላይ ተጻፈ፡፡ ጋሽ ካሳሁን ገርማሞ ይህን ክብርና ዝና በደንብ ሳያጣጥሙ አለፉ፡፡ ቴዲ ዛሬም “ቆመህ ካለህ አታምንምና ላባብልህ ዛሬ በክራሬ ቃና” ይላል፡፡ እስከዳር የቤት ሰራተኛ ሆና ሄደች፡፡ እመቤት ሆና ተመለሰች፡፡ አባት አረፉ፡፡ አሳዛኝ መተላለፍ፡፡
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” መጽሐፍ ላይ የግል ሳይሆን የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችን ታሪክ (በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ)፤ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት በሚደረግ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ እድልም፣ ብቃትም፣ ዘመንም፣ ችሎታም ፈቅዶ መሳተፍ፡፡ ተሳትፎም መሳካትን በጉጉት እናያለን፡፡
ሀገሬ ሸንተረሩ፣ አረንጓዴው ተራራው፤ ወንዝሽ ወንዛ ወንዙ፤ እንግዳ ተቀባይ፤ ፈሪሃ ፈጣሪ… የሚሉ ጅምላ ራስ ተኮር ማንቆለጳጰሶች በራሳችን ልጅ በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን ሳይኳል ሳይዳር ከነ ጉድፉ ይመዘናል፣ ይፈተሻል፣ ይለካል፣ ይቦካል፣ ይፈጫል፡፡ “ኢትዮጰያዊነት መልካምነት” “ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ” የሚሉት ደምሳሳ አባባሎች በተኖረ እውነት፤ በተፈተነ ኢትዮጵያዊነት፤ ከአመክንዮ እስከ ተግባር ይመዘናሉ፡፡ የሚዛኑ ውጤት በልባችን በአዕምሯችን በዝምታ ይቀመጣል፡፡ ምንም ትንፍሽ የለም፡፡ ፀጥ ብሎ!
3. ሥዕላዊነት
እውነት የትም አለ፤ ውበት ግን ይለያል። መረጃ የትም አለ፤ አቀራረብ ግን ይገዛል። ብዙ ሰው ብዙ እውነታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን እውነቱ ትርጉም የሚኖረው አቀራረቡ ላይ ነው። ግለ ታሪክ ዜና አይደለም፤ በእውነት ብቻ ሊታጨቅ አይችልም፡፡ ዘገባም አይደለም፤ አንድን ሁነት ብቻ ይዞ መቼና የቱን ነግሮን አያቆምም፡፡ የነገሩ እውነታነት ብቻ ሳይሆን አቀራረቡም አንባቢን መያዝ አለበት፡፡
እስከዳር ግርማይን በቴሌቪዥን ከምናያት ይልቅ መጽሐፉ ላይ ቁንጅናዋ በጣም ይጎላል። ጣልያን ሀገር ለስራ ሄዳ ጣልያናውያን “ቢሊሲማ፣ ቢሊሲማ” እና “ኦ… ኦ ማማ… ሚያ ቻው ቤላ! ቻው … ኢትዮጵያ ቻው!” የሚለው የሰውየው አገላለጽና አውዱ፣ በቁንጅና ውድድር አንደኛ ወጣሁ ከሚለው ዘገባ በላይ ውበትንና በውበት መደመመን ያሳያል፡፡
መጽሐፉ የእሷ እስከመሆኑ ድረስ ካፒቴኑም ነች፡፡ እኛ አንባብያን ተሳፋሪዎች፡፡ ግን የእኛ ጉዞ ከሌሎች ጉዞዎች በጣም የሚለየው በየትኛውም ሰዓትና ሁኔታ ከእሷ በረራ ውስጥ ለመውጣት ባለ ሙሉ ሥልጣን ነን፡፡ ስለዚህ የእሷ ማብረሪያ ቁልፎች ቃላት ይባላሉ፡፡ ቃላቶቿ ሊይዙን ይገባል፡፡ ከመያዝ አልፈው ሥዕል እየሰጡ እንደ ፊልም ልናያቸው፣ እያየናቸውም ሪሞት ሳናነሳ ሊያስጉዙን ይገባል፡፡ ይህንንም በደንብ ያየሁበት መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
አጻጻፏ ሥዕላዊ ብቻ ሳይሆን የፊልም ስክሪፕት ጸሐፊነቷም ጎልቶ ታይቶበታል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስል (video) ማለት “በጣም ፈጣን ተንቀሳቃሽ ፎቶ ነው” ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ ሰው በባህሪው ስልቹ ስለሆነ ችኮ የቆመ ጅብራ ነገር አይወድም፡፡ ጽሁፍ ሲሆን ደግሞ አንድ ነገር ላይ መልሶ መልሶ ሲሆን ማሰልቸቱ አይቀርም፡፡
በፊልም ውስጥ ትይዩ ትዕይንቶች ይኖራሉ። ባለታሪኮቹ ከዚህም ከዚያም ታሪካቸው ይታያል። ካስፈለገም በእነሱ ውስጥ ያለው ትዝታ (ፍላሽ ባክ) በካሜራና በኤዲቲንግ ታግዞ ዛሬ ላይ ትናንትን ዱሮን እናያለን፡፡ “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” ላይ እንዲህ ያለ ዛሬ ላይ ትናንትን፤ ትናንት ውስጥ ነገን ከትናንት ወዲያን በፈጣን ታሪኮች ታጅቦ እናያለን። በአንድ ታሪክ ውስጥ ሌላ ታሪክ እናነባለን፡፡ ሲያስፈልግ ወደ ኋላ መለስ ብለን ዱሮን፣ በጣም ዱሮን እናነባለን። በተለይ “ሪቮሊሽኒስቱ” ላይ ኮረም፣ አሰብ፣ አዲስ አበባ፣ ባህሬን… የኢህአዴግ ሥልጣን መቆጣጠር፣ ኢህአፓነት፣ ተስፋ፣ ሞት፣ ከሞት መነሳት፣ ዳግም ሞት ይፈራረቃሉ። በዚህ ውስጥ ልጅነት፣ ህልም፣ ጉጉት፣ ራዕይ… ሲፈራረቁ በምስል ተከስተው እናያለን፡፡
ማጠቃለያ
አሜሪካዊው የግለ ታሪክ ጽሁፍ አብዮት አስነሺ የሚባለውና ደራሲው ጄሪ ዋክስለር (Jerry Waxler) እንዲህ ሲል ስለ ግል ማስታወሻ ጥቅም ይናገራል፤ “The more memoires I read, the more lessons I learn, first about the litrary from, second about other people, and third about myself” (ብዙ ማስታወሻዎችን ባነበብኩ ቁጥር ብዙ እማራለሁ፤ አንድም ስለ ሥነጽሑፍ፤ አንድም ስለ ሌሎች ሰዎች፣አንድም ስለ ራሴ፡፡)
“ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የሚለውን የእስከዳር ግርማይ የግል ማስታወሻን ሳነብ ስለ ራሷ መውጣትና መውረድ ብቻ አልነበረም እንዳውቅ ያደረገኝ፡፡ ይልቁንስ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ እህቶቻችንን የማይበትን መነጽርም ሙሉ ለሙሉ ቀይሮልኛል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በትንቢተ ሶፎንያስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 10 ላይ፤ “ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፤ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሶኛል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ እህቶቻችን መከራ እየበሉ በአድካሚ ሥራ የሚዳክሩት፣ እዚህ በአገራችን ለምንኖረው ኢትዮጵያውያን መሆኑን የተገነዘብኩበት መጽሐፍ ነው፡፡  
እስከዳር ውስጥ ብርታት፣ የዓላማ ጽናትና ጥንካሬን አይቻለሁ፡፡ ይህ ብርታት የሀገርን ምስል በሌሎች ዘንድ ለማስተካከልና ወደ መልካም ነገር ለመቀየር ተጠቅማበታለች፡፡
በሶፎንያስ የተነገረውን ትንቢት አንዱ ማሳያ አድርጌ ወስጄዋለሁ፡፡ በእሷ ውስጥ በመካከለኛው  ምሥራቅ ራስን ለመለወጥ፤ ቤተሰብን ለመርዳት፤ ሀገርን ለመወከል የሚታትሩትን እህቶቻችንን ያሳያል፡፡ አሁንም በዚያ ለሚገኙ እህቶቻችን ጥሩ ብርታትን የሚሰጥ ነው፡፡ በጥረት፣ በትዕግስት፣ በብርታት… ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት መሸጋገር እንደሚቻል የሚያሳይ ጥሩ ማስታወሻ ነው፡፡
የእስከዳርን የቋንቋ ውበት ተከትለን፤ የገባችበት ስንገባ፤ ሄደችበት ሀገር ስንሄድ፤ ያረፈችበት ስናርፍ፤ ያዘነችበት ስናዝን ቆይተናል። ኮስተር፣ ኮራ፣ ኮምጨጭ ብላ ፊልሞቿ ላይ የምትታየው እስከዳር፤ መጽሐፏ ላይ ፈታ ያለች ነች፡፡ ልክ ቃለ መጠይቆችዋ ላይ እንደምናያት።
“ኢትዮጵያዊ ማነው? ኢትዮጵያዊነትስ ምንድነው?” የሚለውን የሥልሳዎቹን ሐቲት ዛሬም እስከዳር ታነሳዋለች፡፡ በዘመናት ያልተመለሰ ጥያቄ፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ የመጣው የማንነት ጥያቄ፣ ዛሬ ላይ በስም ብቻ ከባድ መፈራረጅን ሲያመጣ እናያለን የግርማይ ተወልደመድህን ልጅ መሆን በጅምላ ሲያስፈርጅ እንታዘባለን፡፡ ከፍ ያለ ቦታ ላይ የሕዝብ አገልጋይ መሆንና ከሥርአቱ ጋር ያለው ቁርኝት? አገልጋይነትና ሥርአት ምንና ምን ናቸው? ሀገር ማገልገል ወይስ ጨቋኝ መንግስትን ማገልግል? ፈታኝ ጥያቄ፡፡ ወገን ያልተረዳው ግብ ግብ፡፡
“ኢትዮጵያዊ ግን ሀገሩ የት ነው?”

Read 11864 times