Saturday, 23 July 2022 14:34

“መንግስት ህይወቴን ይታደግ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  “እኔ ሟች ነኝ፤ እውነቱ ታውቆ ዓላማቸው እንዲከሽፍ እፈልጋለሁ”


          ባለፈው እሁድ ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከጅግጅጋ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አንድ የስልክ ጥሪ ይደርሳል። ግለሰቡ በስልክ ሲያወራ የተረበሸ ይመስላል። “እባካችሁ ህይወቴ አደጋ ላይ ነው፤ የሚመለከተው አካል ይታደገኝ ዘንድ ድምፅ ሁኑኝ” የሚል ተማጽኖ ነው። በእለቱም የመንግስት የፀጥታ አካላትን በቀላሉ አግኝተው የዚህን ሰው ህይወት ሊታደጉ ይችላሉ ላልናቸው ወገኖች የግለሰቡን የተማጽኖ ጥሪ አደረስን። የሶማሌ ክልል ብልፅግና
ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ ግለሰቡን አግኝተውት ነበር። “ነገር ግን የነገርኳቸውን ችግር ትኩረት ሰጥተው አልሰሙኝም፤ አልተከታተሉኝም” ይላል። “ጥቂት ደቂቃ ካነጋገሩኝ በኋላ ፖሊስ ኮሚሽኑ ያነጋግርሃል እኔም መልሼ አገኝሃለሁ” ብለውኝ፤ በዛው ቀሩ” የሚለው ግለሰቡ (ይሄን ያሉን ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2014) እስከ ትናንት አርብ ድረስ በአካልም በስልክም ያነጋገረኝ አካል የለም።” ብሏል ለአዲስ አድማስ።
   “ጭራሽ ህይወቴን ሊያጠፉ የሚከተሉኝ ግለሰቦች የተከራየሁበት መኖሪያ ቤቴ ድረስ በመምጣት ከቤት የምወጣበትን ጊዜ እየተጠባበቁ እየተከታተሉኝ ነው” ሲል ያለበትን ሁኔታ ገልጿል። ለመሆኑ ይህ ግለሰብ ማነው? ምንድን ነው የደረሰበት? ሰዎች ህይወቱን ሊያጠፉት የሚከታተሉት በምን ምክንያት ነው? ለእነኚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘትና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ዘንድ ይደርስ ዘንድ የአዲስ ያረጋል አያና ከተባለው ከዚህ ግለሰብ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ በስልክ አድርጓል። ስለጉዳዩ በማስረዳት ይጀምራል - ባ ለጉዳዩ።
                      ***
      እኔ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ ነኝ። የሰሜኑ ጦርነት አስጨናቂ በነበረበት ወቅት ላይ እነዚህን ሶስት ልጆች ተዋወቅኋቸው። በወቅቱ ልጆቹ ስራ ፈላጊ ነን ብለው ከወሎ ዩኒቨርስቲ የተመረቁበትን ሰርተፍኬት ይዘው ነበር። በጣም ምስኪን ሆነው የተቸገሩ መስለው ነው የቀረቡኝ። “የምንበላው የምንጠጣው የለንም ለስራ ፍለጋ ነው የመጣነው” እያሉ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ነው የሚያስተዋውቁት። በዚህ ሁኔታ ከቀረቡኝ በኋላ እኔ የተከራየሁበት ግቢ እነሱም ተከራዩ። ልክ እንደጓደኛ ሆንን፣ ጅግጅጋን ቀድሜ ስለማውቅ ብዙ ነገር ነበር ስለ ሶማሌ ክልል እና ጅግጅጋ የሚጠይቁኝ። እኔም በቀናነት ብዙ ነገር አጫውቻቸዋለሁ። በኋላ ግን ስረዳ ልጆቹ የገንዘብ ችግር የለባቸውም፤ ስራ ፈላጊም አይደሉም። እኔ የተከራየሁበት ግቢ ከተከራዩት ቤት በተጨማሪ ከተማው ውስጥ ሶስት ቤት ተከራይተዋል። አብዛኛውን ስልክ የሚደወልላቸው ከውጭ ሃገር ማለትም ከኬንያ፣ ከሱዳን ነው። በሌላ በኩል በጸጥታ ሃይሎች ብቻ የሚያዙ አይነት ሬድዮ መገናኛዎች ይዘዋል። ይሄን ባየሁ ጊዜ ተጠራጥሬ አውቄ እንዳላየሁ ሆኜ ተደብቄ መከታተል ጀመርኩ። ማታ ማታ ሁል ጊዜ ይደወልላቸዋል፤ ውጪ ላይ ወጥተው ነው የሚያወሩት እኔም እየተከታተልኩ አዳምጣቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ሃገሪቱ የከፋ ጦርነት ውስጥ ስለነበረች ነገሩን በደንብ ነበር ስከታተላቸው የነበረው። መጀመሪያ ላይ ከአንድ (ስሙ ከተጠቀሰ) ሰው ጋር ነበር የሚያወሩት። “በርቱ አይዟችሁ ስራችሁን ከጨረሳችሁ
ገንዘቡን እንልካለን” እያለ ነበር ሰውየው የሚያወራው። መልዕክቱን የሚቀበለው ደግሞ አሁን 2 ዓመት እስር የተፈረደበት ልጅ ነበር። እያንዳንዱን ወሬያቸውን ተደብቄ እሰማ ነበር። በእለቱ ያንን ካወሩ በኋላ ዘወር ሲል እኔን ይመለከታል፤ ሲደናገጥ “ግዴለህም እያንዳንዷን የምታወሩትን ሰምቻለሁ፣
ሁሉንም እ የተከታተልኩ ነ ው፤ አ ሁን ሁ ሉንም ነገር ካልነገርከኝ በቀጥታ ለፖሊስ እናገራለሁ” አልኩት። እሱም “አትናገር ሚስጥሩን ለመጠበቅ ቃል ግባልን፤ እንነግርሃለን” አለኝ። እኔም ቃል ገባሁለት፣ የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪም ስለሆንክ ለስራችን እንዳውም አንተም ታስፈልገናለህ አለኝ። እዚህ ባለሃብቶች ይደግፉናል፤ ከውጭም የሚረዱን ሰዎች አሉን፤ የምትፈልገው ነገር ይሆንልሃል አሉኝ። ስለዚህ መረጃውን ለማወቅ ስል ብቻ ቃል ገባሁላቸው።
      ምንድን ነው የነገሩህ መረጃ?
አሁን ረብሻና ጦርነት ስለሆነ የሱማሌ ክልል ተወላጆች በአማራ ክልል አድርገው ወደ ውጪ መሰደድ አቁመዋል። በፊት ወደ ጀርመን የሚሄዱት በመተማ በኩል ነበር። አሁን አቋርጠዋል። እኛ የድለላ ክፍያ የምናገኘው ጀርመን ሃገር ካለ ሰው ነው። ስለዚህ አንተ ሃገሩን ስለምታውቀው መሄድ የሚፈልጉ
ወጣቶችን “ወደ ጀርመን በነጻ እናሻግራችኋለን” እያልክ በሆነ መንገድ ካመጣህልን፣ እስከ 8 መቶ ሺህ ብር እንከፍልሃለን ይሉኛል።
   ከቻልክ 20ም 30ም አምጣ ግን ከ10 ሰው እንዳያንስ አሉኝ። በወቅቱ እኔ ያልኳቸው “እንዲህ በነጻ የምትልኩ ከሆነ፤ ለምን እኔን  አትልኩኝም” አልኳቸው። ሰውም እፈልጋለሁ አልኳቸው። ይሄን ጊዜ “ግዴለህም ላንተ አይሆንም” ብለው አንገራገሩ፤ በኋላም ዋናውን ሚስጥር ነገሩኝ፤ ልጆቹን ከመለመልናቸው በኋላ ጎንደር አካባቢ የሚቀበላቸው ሃይል አለ። የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሱማሌዎች ብቻ ነው የሚፈለጉት። ስደተኞቹ
ጎንደር አካባቢ በተዘጋጀላቸው ቦታ ሲደርሱ በቪዲዮ እየተቀረጹ ይገደላሉ። በዚያ ሰአት አንደኛ ወሎ ውስጥ ያለው የመከላከያ ሰራዊት ወደዚያ ይሄዳል፤ ጅግጅጋ ላይ ደግሞ “ሄጎ” ፈጥሮት ከነበረው ረብሻ በላይ ይፈጠራል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የሶማሌ ኮንግረስ ሰዎች ናቸው። ውጪ ነው ያሉት። አሁን ፈጥነህ ልጆቹን ፈልግ፤ ይሄ ሲሆን ስልጣን በቅርቡ በእጃችን ይገባል አሉኝ። ወንድሞቻችን ሱዳን ውስጥ እየሰለጠኑ ነው፤ እዚህ ሱማሌ ውስጥም እየሰራን ነው አሉኝ። እኔ ይሄን መረጃ ይዤ በቀጥታ የሄድኩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ነው። ሁሉንም ነገር ነገርኳቸው። በወቅቱ የፖሊስ ኮሚሽኑ ለማጣራት ይረዳው ዘንድ፣  15 የፖሊስ አባላትን በሲቪል ልብስ ስደተኛ መስለው በኔ በኩል እንዲገናኟቸው አደረግን። በስልክ የምናወራውን ሁሉ የፖሊስ አባላቱ
እንዲሰሙ አድርገን ነበር። በኋላ ሰዓትና ቦታ ቀጠሮ ወስደን፣ በሲቪል ያሉት ፖሊሶች ስደተኛ መስለው ልጆቹን አገኟቸው።
በኋላም ስደተኛ መስለው በሲቪል ላሉት ፖሊሶች ስለ ጉዟቸው ሁሉ አስረድተዋቸው መንገድ ሊጀመር ሲል ነው ወንጀለኞቹ የተያዙት። ይህ የሆነው ማክሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር፤ በሶስተኛው ቀን ሃሙስ ቃል ትሰጣለህ ተብሎ ፖሊስ ጣቢያ ሄድኩ። በወቅቱ ቃሌን ልሰጥ ስል ፖሊሶች “ማለት ያለብህ ልጆቹ አስኮብላዮች ናቸው ብቻ ነው እንጂ፤ አማራ ክልል ሲደርሱ ይሄን ሊያደርጉ ነበረ የሚል ነገር መናገር የለብህም” አሉኝ። ከዚህ ውጪ የምትናገር ከሆነ “ባንተ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብህም ጭምር ዋጋ ትከፍላለህ” አሉኝ። እኔ ግን ለመርማሪው ሁሉንም ነገር ያስፈራሩኝን ጭምር ነበር የተናገርኩት። በኋላ በአንደኛው ቀን ታርጋ በሌለው “Force” ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ መጥተው፣ የማላውቃቸው ሰዎች ወደ ካራማራ ወሰዱኝና፤ “ቃልህን ያጠፍከው ለምንድን ነው? በል በህይወት አልመለስም ብለህ ደውል፤ ለቤተሰቦችህ” እያለ ከተሸከርካሪው አውርደውኝ ደበደቡኝ በኋላም በርቀት ሆነው ወደ እኔ ይተኩስ ነበር፤ ግን አልመቱኝም ሳቱኝ። ይህን የደረሰብኝንም ሁሉ ለፖሊስ ተናግሬያለሁ። ጥር 25 ቀን 2014 የምስክርነት ቃሌን ለፍ/ቤት ከሰጠሁ በኋላ ደግሞ በኔ ላይ ሌላ ውንጀላ ጀመሩ።
 ምንድን ነበር ውንጀላው? እኔ የማላውቃቸውን እነ ክርስቲያን ታደለን፣ ባለሃብቱ ወርቁ አይተነውን ስም እየጠቀሱ፤ “በሶማሌ ክልል የፋኖ አደራጅ ነው እያሰለጠነ ነው” ብለው ፎቶዬን በማህራዊ ሚዲያ ነበር የበተኑት። ይሄ ሁሉ ለሀገር የሚከፈል ነው ብዬ ችየው ተቀምጬ እያለ ነው፤ አሁን ሐምሌ ወር ከገባ በኋላ አንድ ጓደኛዬ መጥቶ “የባለፈው አንተ የደረስክበትን መረጃ አይነት ሰዎቹ አሁንም እየሰሩበት ነው” አለኝ። ይሄን ሲለኝ ጉዳዩ ለፖሊስ አሳወቅኩ። ያሉበትን ሆቴል ጭምር ነበር የነገርኳቸው። ፖሊሶች ግን ስታያቸው ደውልልን ነበር ያሉኝ። እኔ ለደህንነቴ አያሰጋኝም ማለት ነው? ፖሊስ ያገኘውን መረጃ ይዞ ስራውን እንዴት አይሰራም? ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ 12 የሶማሌ ወጣት ሴቶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ አገኘኋቸው፤ ከአንድ ሆቴል
ወደ ሌላ ሆቴል ነበር እየቀየሯቸው የነበረው። ያን ጊዜ መንገድ ላይ ድምጼን ከፍ አድርጌ እህቶቼ አማራ ክልል ስትደርሱ ሊገድሏችሁ ነው፤ እንዳትሄዱ ሊገድሏችሁ ነው እያልኩ ጮህኩ። በዚህ ጊዜ ነበር የያዙኝ። “ባንተ የተነሳ ብዙ ስቃይ ደርሶብናል። ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ አውጥተናል። አንደኛው ጓደኛችን ሁለት ዓመት እስር እንዲፈረድበት አስደርገሃል። ስለዚህ 3 መቶ ሺህ ብር ካሳ አምጣ አሉኝ። ከዚህ ባሻገር ገና ብዙ ዋጋ ትከፍላለህ” ብለው
ሽጉጥ ደቅነውብኝ፣ ቤቴ ድረስ አምጥተውኝ “ቀጥ ብለህ ያለህን ይዘህ ውጣ” አሉኝ። ሱቅ ለመክፈት ከጓደኞቼ ያሰባሰብኩትን 117 ሺህ ብር ወሰዱብኝ ። እንደገና “በቅርቡ ስልክ ገዝተሃል ብርድ ልብስም አዲስ ገዝተሃል አምጣ” አሉኝ። እሱንም ሰጠኋቸው። በዚህ አላበቁም? “እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 12 2014 ዓ.ም ያለህን ቀሪውን ብር ይዘህ ና ካላመጣህ ከዚያ በኋላ በህይወት አትኖርም” አሉኝ። ይኸው የሰጡኝ ጊዜ በማለቁ በበሬ ላይ እየተመላለሱ ና ውጣ እያሉኝ ነው። በዚህ ብቻ አላበቁም።
   በተለያዩ ሚዲያዎች ስማችንን አጥፍተሃል። ስለዚህ እየደወልክ ተሳስቼ ነው ብለህ ይቅርታ ጠይቅና ድምጹን ሪከርድ እያደረግህ አምጣ ብለውኝ እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ነበር ቀን የሰጡኝ። በዚህ መሃል ነው እንግዲህ ነፍሴን ትታደጉ ዘንድ ወደ እናንተ የደወልኩት። እስካሁን ግን ህይወቴን የታደገ የለም ትናንት (ረቡዕ) ማታ ታርጋ በሌላው ተሽከርካሪ መጥተው ነው አስፈራርተውኝ “ከእጃችን አታመልጥም፤ የተባልከውን ፈጥነህ አድርግ” ያሉኝ። ይሄን ጉዳይ ብዙ የመንግስት አካላት ያውቃሉ፤ ግን ቸልተኝነቱን ነው የመረጡት። በእውነት በጣም አዝኛለሁ፤ ከዚህ የበለጠ ምን ሊኖር ነው? ሰዎች ተገድለው ችግር ከተፈጠረ በኋላ ከመሯሯጥ ለምን አሁን ችግሩን አያስቀርም። እኔንስ ለምን ከለላ ሰጥተው ህይወቴን አይታደጉኝም? እሺ ይሁን እኔን ይግደሉኝ፤
ባለቤቴ ግን በእኔ ምክንያት ከአርብ ሐምሌ 8 ጀምሮ ከቤት መውጣት አቅቷት ረሃብ እየጎዳን ነው። ከዚያ በኋላ አሁን እስካወራሁህ ሁለት ቀን ብቻ ነው ትንሽ ነገር የቀመስነው። ቤታችን ባዶ ነው፤ ወጥተን የሚበላ ነገር እንኳ መግዛት አልቻልንም። ባዶ እጄን ነኝ፤ በዚያ ላይ ከቤት ከወጣሁ ይገድሉኛል።
ከተቻለ መንግስት ነፍሳችንን ይታደገን። እኔ እኮ ለሃገሬ ነው ግዴታዬን የተወጣሁት ወንጀለኛን በህይወቴ ተወራርጄ አሳልፌ ነው የሰጠሁት። ለዚህ ውለታዬ ምላሼ ሞት መሆን የለበትም። መንግስት እንዲያውቅ ህዝቡም እንዲረዳ አድርጉልኝ። ይሄ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው።
ልጆቹ ብዛታቸው ምን ያህል ነው?
ሶስት ናቸው። አንደኛው እስካሁን ያልተያዘም። አንደኛው ተለቋል፣ ሌላኛው ታስሯል። እነዚህ ዋናዎቹ ናቸው። ከነሱ ጋር ሌሎችም አሉ። የሚገርምህ እነዚህ ልጆች “የባንክ አካውንት የለንም” ይላሉ፤ ግን 8 ያህል ኤቲኤም ካርድ ይዘው ነው የ ሚንቀሳቀሱት። እኔ ሟች ነኝ፤ ግን ህዝብ ይወቅልኝ። ይሄን ህዝብ
አውቆ አላማቸውም እንዲከሽፍ እፈልጋለሁ። ህዝብ ሴራውን እንዲረዳ እፈልጋለሁ።
ማስታወሻ
በጉዳዩ ዙሪያ ከክልሉ መንግስት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ይበልጥ ለማጣራት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረግን ሲሆን አ ስቀድሞ ሊ ፈጸም ነበር የተባለውን ወንጀል ሲመረምሩ የነበሩ መርማሪ ፖሊስ የሞባይል ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። ግለሰቡ በቀጥታ መረጃውን በመጀመሪያ
ነግሬያቸዋለሁ ያሏቸው በወቅቱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር መሐመድ ያሬ ጋር ደውለን ስለጉዳዩ ስንጠይቃቸው፤ “ስለምትሉት ነገር አላውቅም” በማለት ስልኩን የዘጉት ሲሆን። ከዚያ በኋላም ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸው አይመልስም። ግለሰቡ “ህይወቴ አደጋ ላይ ነው” ብሎ ያቀረበውን አቤቱታ ለማጣራት መሞከራቸውን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት የሶማሌ ክልል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ሃላፊ ኮማንደር አብዱሃኪም በበኩላቸው ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጥቆማ ሰጥቶ እንደነበር መረዳታቸውን ጠቅሰው ስለጉዳዩ ግን በጥልቀት እንደማያውቁ አስረድተዋል። ግለሰቡ “ስጋት አለብኝ ላለውም “በፈለግህ ሰዓት ችግር ካለ ደውል” ብዬ ስልኬን ሰጥቼው ነበር። ነገር ግን ችግር እንዳጋጠመው ደውሎ አልነገረኝም፣ የአዕምሮ አለመረጋጋት ያጋጠመው ይመስለኛል” ብለዋል። በሌላ በኩል፤ ግለሰቡ ስሜና ፎቶግራፌ “የፋኖ አደራጅ” በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ተበትኖ ነበር ያለውን ጉዳይ አዲስ አድማስ ለማጣራት ባደረገው ሙከራ፤ በአንድ ብዙ ተከታዮች ባሉት ግለሰብ ገጽ ላይ Feb 19,2022 ከሙሉ ሃተታና ፎቶ ጋር የተሰራጨ መልዕክት እንዲሁም በሌሎቹ በርካታ ተከታዮች ባሏቸው ማህበራዊ ገጾች የአቶ ያረጋልን ፎቶግራፍ
በመጠቀም በጅግጅጋ የፋኖ አደረጃጀትን እየፈጠሩ መሆኑን በአሉታዊ መልኩ የሚገልጹ መልዕክቶች ስለመሰራጨታቸው ለመረዳት ተችሏል።

Read 13813 times