Saturday, 23 July 2022 15:13

በትግራይ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ሲፒጄ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የትግራይ ባለስልጣናት ለሁለት ወራት ገደማ ያለአግባብ ያሰሯቸውን አምስት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲለቅና የፕሬስ ነጻነትን እንዲያከብሩ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም (ሲፒጄ) አሳሰበ።
ከፌደራል መንግስቱና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ሰርተዋ በሚል “ከጠላት ጋር በማበር” ክስ የቀረበባቸውና በእስር ላይ የሚገኙት የትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች፡- የሆኑትን ተሾመ ጠማለው፣ ምስግና ስዩም፣ ሃበን ሃለፎም፣ ኃይለሚካኤል ገሰሰ እና ዳዊት መኮንንን መሆናቸውን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ህወኃት በክልሉ ባደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ “ከጠላት ጋር ማበር” በዕድሜ ልክ ወይም በሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል መደንገጉን ሲፒጄ አመልክቷል።
በመቀሌ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልልን በተቆጣጠረበት ወቅት የትግራይ ቴሌቪዥንን ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
የህውኃት ሃይል ትግራይን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ ጋዜጠኞቹ ከስራቸው ታግደው ከቆዩ በኋላ በግንቦት ወር መጨረሻና ሰኔ ወር መጀመሪያ ከያሉበት መጥተው መታሰራቸውም ነው የተገለጸው። ለሁለት ወር ያህል ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ከቆዩት አምስት ጋዜጠኞች መካከል በሶስቱ ላይ “ከጠላት ጋር ማበር” የሚል ክስ እንደሚመሰረትባቸው አቃቤ ህግ መግለጹን የጠቆመው ሲፒጄ፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ፍ/ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት መጀመሩን
አመልክቷል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአምስቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ አስር የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አስታውቆ እንደነበር ያስታወሰው የተቋሙ መግለጫ፣ ከአምስቱ ጋዜጠኞች ውጭ የተቀሩት እስረኞች ያሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ቴሌቪዥን ሚዲያና ጋዜጠኞች በነጻነት የጋዜጠኝነት ተግባራትን ከማከናወን ይልቅ ሙሉ ለሙሉ የአንድ ቡድን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ብቻ እንደሆኑ የጠቆመው ሲፒጄ፤ የትግራይ ባስልጣናት የሚዲያውንና የጋዜጠኞቹን ነጻነት ሊያረጋግጡ ይገባል ብሏል። ስለ ጋዜጠኞቹ የእስር ሁኔታ ከትግራይ ቲቪና ከትግራይ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለትም ሲፒጄ አመልክቷል።

Read 21347 times