Print this page
Saturday, 23 July 2022 15:14

ዜጎች በግፍ የተጨፈጨፉበት የወለጋ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

  • ይህ በሴቶችና ህጻናት ላይ የተፈፀመ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን ሊጣራ ይገባዋል
     • "የፀጥታ ኃይሎች ከስፍራው የደረሱት ጥቃቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን ሰምቻለሁ"
                      
             ባለፈው ሰኔ ወር በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ከ400 በላይ የአማራ ተወላጅ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ አቅም ደካሞች በግፍ የተጨፈጨፉበት ሁኔታ በገለልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲጣራ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ፡፡
በአካባቢው በተፈፀመው ጥቃት ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉ ከዓይን ምስክሮችና በህይወት ከተረፉ ሰዎች መስማቱን የገለጸው ድርጅቱ፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ነግረውኛል ብሏል፡፡
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎቹ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ጥቃት መፈጸም እንደጀመሩና ገና የመጀመሪያዋ ጥይት እንደጮኸች ነዋሪዎች ለአካባቢው ባለስልጣናት ቢያሳውቁም “መንገዱ ተዘግቷል፤ ማለፊያ የለም” በሚል ምክንያት ወደ ስፍራው የደረሱት ታጣቂ ኃይሎቹ ከ400 በላይ ንጹኃን የአማራ ተወላጅ ህጻናትንና ሴቶችን በገፍ ከጨፈጨፉ በኋላ መሆኑን ነዋሪዎቹ አረጋግጠውልኛ ብሏል።
ጥቃት ፈፃሚዎቹ “የአማራ ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን እየመረጡ፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞችን ጨፍጭፈዋል፡፡ ብሏል የተቋሙ ሪፖርት፡፡
ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞች ነገሩኝ በማለት እንደገለፀው፤ በአንድ ስፍራ ብቻ ቁጥራቸው 42 የሚደርሱ ሰዎች በግፍ የተጨፈጨፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አዋቂ ወንድ ያለው አንድ ብቻ መሆኑን ሰምቻለሁ ብሏል፡፡ቀሪዎቹ ህፃናትና ሴቶች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ነግረውኛል ብሏል አምኒስቲ።
አንድ አባት 12 ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውን በጥቃቱ ማጣታቸውን ከራሳቸው ከጥቃቱ ሰለባ ሰምቼ አረጋግጫለሁ ያለው አምነስቲ፤ የአንድ ግለሰብ ቤት በውስጡ የሰባት ወር ነፍሰጡር ባለቤቱና ልጆቹ እያሉበት በእሳት እንዲጋይና ወደ ከሰልነት እንዲቀየር ተደርጓል ብሏል፡፡ ቤቱ ውስጥ እያሉ እንዲቃጠሉ የተደረጉት እናትና ልጆች ከሰል እስኪሆኑ ስለተቃጠሉ፣ እዛው እቤቱ ውስጥ እንዲቀበሩ መደረጉንም የዓይን እማኞች እንደነገሩት አምነስቲ አመልክቷል፡፡
በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥርን የተመለከተ ትክክለኛ መረጃ አለማግኘቱን የጠቆመው የሰብአዊ መብት ተቋሙ አንድ የአካባቢው ባለስልጣን 450 ሰዎች መገደላቸውን ነግረውኛል ብሏል፡፡ አጥቂዎቹ በለበሱት የደንብ ልብስ፣ በፀጉር አሰራራቸው በሚነገሩት ቋንቋ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን መለየት እንደቻሉ የዓይን እማኞች እንደተናገሩት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው ይህ በምዕራብ ወላጋ ዞን ገምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ የተፈጸመው አሰቃቂ የጅምላ ግድያ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ለሰዎች ህይወት ግድ እንደሌላቸው ማሳያ ነው ያለው መግለጫው የሴቶችና የህጻናት ህይወት የቀጠፈው ይህ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን በሚገባ ሊመረመር ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡

Read 21610 times