Saturday, 30 July 2022 13:28

ባለፉት 4 ዓመታት በኢትዮጵያ ከ25 ሺ በላይ ሰዎች በግጭት ሞተዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


           በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች የ17 ሺህ 701 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ 8 ሺህ 016 ሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉን አንድ አለማቀፍ ተቋም ጠቁሟል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው በግጭትና ሠላም ዙሪያ መረጃዎችን አሰባስቦ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ACLED በተባለ ድርጅት ስር የተደራጀው “የኢትዮጵያ ሠላም ምልከታ” (ኢፒኮ) የተሰኘው ተቋም ባወጣው የ4 ዓመት የኢትዮጵያ የሠላም ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ከመጋቢት 24 ቀን 2010 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በሃገሪቱ 3 ሺህ አንድ መቶ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡
በእነዚህ አራት ዓመታት ገደማ የነበሩ ግጭቶችንና የጠፋ የሠው ህይወትን በተመለከተ ድርጅቱ  በአመዛኙ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች፣ ከመንግስት ተቋማትና ከሰብአዊ መብቶች  ተሟጋቾች ይፋ የተደረጉ አሃዞችን በማገናዘብ መረጃውን ማደራጀቱን ጠቁሟል፡፡
በአስከፊ ደረጃ የሰው ህይወት እየቀጠፉ ካሉ ፖለቲካዊ ግጭቶች መካከል በኦሮሚያ የኦነግ ሸኔ እና  የመንግስት ሃይሎች ግጭትና የተኩስ ልውውጥ፣በአማራ ክልል እና አፋር ድንበር አካባቢ የሚፈጸሙ ግጭቶች፣ በአማራ እና ኦሮሚያ በተለያዩ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎች፡- በሸኔ እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ በደቡብ ክልል የተለይ በወረዳዎች የሚከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶችና ጥቃቶች፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በታጣቂዎቸ የሚፈጽማቸው ጥቃቶች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር የሚፈጽማቸው ጥቃቶች ተጠቅሰዋል።
ከሐምሌ 2 እስከ ሓምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ 22 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ተከስተው፣ የ190 ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው ይኸው ድርጅት ያመለከተው፡፡
በዚህ የአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ፣በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራ ክልል ሠሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶች ናቸው ለ190 ሠዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ብሏል- የድርጅቱ ሪፖርት፡፡

Read 11449 times