Monday, 01 August 2022 00:00

“አይቅርብኝ” - በንግሥት ሳባ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

ሥነ ምግባር ጠፍቶብን፣… በፖለቲካውም፣ በሌላው፣ በሌላውም፣… ክፉ የጭካኔ ተግባር በዝቷል።
አሳዛኙ ነገር፣ ለውንጀላ ከመሽቀዳደም፣ ወይም ይባስኑ የክፋት ፉክክር ላይ ከመጠመድ ውጭ፣ ሌላ ነገር ማሰብ አቅቶናል። ከሥነ ምግባር ርቀን ህሊናችን ስለተጋረደብን፣ መፍትሔ የማይታየን አቅመ ቢስ ሆነናል።
“ሥነ ምግባር ማለት፣ ራስን መጉዳት ነው” የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በጣም ጎድቶናል። መልካም ሥነ ምግባር፣… በሆነ መንገድ አንዳች ጉዳትና ጉድለት ማምጣት አለበት የሚል አስተሳሰብ ለምዶብናል።
ትክክለኛ የሥነ ምግባር ትምህርት፣… አዎ፣ ከባድ የሃላፊነት ሸክም ነው። መሆንም አለበት። መነሻውና መድረሻው፣ ምንጩና አላማው “የሕይወት ፍቅር” ነውና።
አሁን ግን በአናቱ ገለበጥነው። “ራስን ለመጉዳትና ለማዋረድ፣ ማገዶ ወይም ሚስኪን ለመሆን” የሚያዘጋጅ ወጥመድ አደረግነው። ከእውነት ብርሃን፣ ከስኬት መንገድ፣ ከተከበረ ሕይወት ተራርቀናል። ተጣልተናልም እንጂ!
ታዲያ፣ ወደ ሕሊና የሚመልሱና ብርሃን የሚሰጡ የሥነምግባር ትምህርቶች ሳይፈጠሩ ቀርተው አይደለም። በኢትዮጵያም በሌሎች አገራትም፣ ሥነ ምግባርን የሚያስተምሩ ጥበበኛ የንጋት ኮከቦች በየዘመኑ አልጠፉም።
ለዚያውም “ሕይወትን ለመማገድ” ሳይሆን፣ “ሕይወትን ለማለምለም” የሚያስችሉ መርሆችን የሚያስተምሩ ናቸው።
ብሩህ አእምሮ፤… “ለእውነታ የታመነ፣ እውቀትን ያከበረ”።
ትጉህ እጆች፤… “ሙያን የወደዱ፣ በረከትን የሚያፈሩ”።
ፅኑ የእኔነት ሰብዕና፤… “ለግል ማንነቱ ሃላፊነትን የጨበጠ፣ የሰውን ብቃት የሚያደንቅ”።
ማገዶነትን የሚሽሩ ትክክለኛ የሥነ ምግባር ሰዎች የተባረኩ ናቸው። ሰውን ለመማገድ አይፈልጉም። ማገዶ ለመሆንም አይፈቅዱም። ይልቁንስ፣ ለራሳቸው ይሆናሉ። ከራሳቸው አልፈውም፣ ለሌሎቻችንም ይተርፋሉ።
ተጨማሪ እውቀት ያመጣሉ። አዲስ የስራ እድል ይፈጥራሉ። የተሻለ የሕይወት አማራጭ ይከፍታሉ። በልግስናቸው ሰውን የማገዝ አቅምም ይኖራቸዋል።
አዋቂ ከሆኑ በሃሳብ ይረዱናል። ፍሬያማ ከሆኑ በኑሮ ያግዙናል። በሃላፊነት ስሜት የግል ማንነታቸውን ከገነቡ፣ አርአያ ይሆኑልናል፤ የመንፈስ ብርታት ያበረክቱልናል።
የንግሥተ ሳባ የሥነ ምግባር ትምህርት - በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ።
“ንግሥተ ሳባ”፣… ሁሉንም የሥነ ምግባር መርሆች በአንድነት አዋሕዳ፣ “ጥበብ” ብላ ትጠራዋለች።
እንደገናም፣ “ጥበብ” ማለት፣ ወደ ዋና ዋና መርሆች ሲፍታታ ምን ማለት እንደሆነ ታብራራለች።
ጥበብን ከልብ መሻትና እውቀትን ማበልፀግ፣…
ጥበብን በተግባር ለፍሬ ማብቃትና ኑሮን ማልማት፣…
ጥበበኛን ማክበርና የግል ማንነትን ማነፅ፣…
እንዲህ እያፍታታች ታስተምራለች።
ንግሥተ ሳባ፣ ጥበብን አሞግሳ አትጠግብም። ጥበብ፣… የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ ጣፋጭ ምግብ እንደሆነች ትገልፃለች። ኃይልና ውበትም ናት ትላለች።
ጥበብ፣ ሃሳብን ታስተካክላለች። ንግግርንም ታሳምራለች። ጥበብ፣ ከፀሐይ የደመቀች መተማመኛ ብርሃን ናት። አእምሮን ታነቃለች። እውነትንና ሐሰትን፣ ትክክልና ስህተትን፣ ጥሩንና መጥፎን ለይታ ታሳያለች። የጠራ እውቀትን ትገነባለች።
ጥበብ፣ የጉዞ ግስጋሴና የኑሮ በረከት ናት። የሰዎችን ስራ ታሳልጣለች፤ ኃይልን ታጎለብታለች። የስራ ፍሬን ታበረክታለች፤ ኑሮን ታበለፅጋለች። የሙያ ባለቤት ታደርጋለች።
ጥበብ፣ ለነፍስ ደስታን፣ ለሕይወት ጣዕምን ትሰጣለች። አጥብቀው ከሚወዷት ጋር ትዋሃዳለች። “ጥበበኛ ማንነትን” ታንፃለች። ጥበበኛን ከልብ ለሚያፈቅሩም ንጹሕ መንፈስን ታቀዳጃለች።
የንግሥቲቱ የሥነ ምግባር ትምህርት፣ እንደ ግሩም ዋርካ ነው። ምድርን አጥብቆ ይይዛል፣ መሠረቱን ያፀናል። ሽቅብ ወደ ከፍታም ያድጋል። ልምላሜውን በየአቅጣጫው እየዘረጋ ወዲህና ወዲያ ቅርንጫፎቹን የሚያወዛወዝ  ዛፍ ብቻ አይደለም። አየሩን የሚዳስሱ አረንጓዴ ቅርንጫፎችን እንደ ጉልላት ወደ አንድ ሕያው ምሰሶ ሰብስቦ ያቀፈ አስተማማኝ ዛፍም ነው።
የተበታተነ ቅርንጫፍ ብቻ ወይም ነጠላ ግንድ ብቻ አይደለም።
የንግሥተ ሳባ ጥበብም፣ የቁርጥራጭ ሃሳቦችና የብጥስጣሽ መመሪያዎች ዝርዝር ብቻ አይደለም። በጥምረት የሚዋሐድ ትምህርት ነው።
ዝርዝር የሌለው ድፍን ትዕዛዝም አይደለም። በተግባር ወደ ኑሮ የሚመነዘር ትምህርት ነው።
እለታዊና ዘላለማዊ፣ ውስጣዊና ውጫዊ፣ ሃሳብና ተግባር፣ አእምሮና አካል፣ ሥነ ምግባርና ፍሬያማነት፣… ሁሉንም መልካም ነገሮች አስማምተን ሕይወትን በምልዓት ማጣጣም እንደምንችል ንግሥቲቱ ታስረዳለች።
ከዚህ አንፃር፣ ንግሥተ ሳባ፣ “አንድም መልካም ነገር እንዲቀርባት አትፈልግም” ብንል አልተሳሳትንም።
በእርግጥ፣ “አይቅርብኝ” የሚለውን ቃል፣ በተለመደው ስሜት ከተረጎምነው፣ ጥበብ ጎድሎን እንሳሳታለን።
በሁሉም የሙያ ዓይነቶች አንደኛ መሆን ማለት አይደለም። መልካም ነገሮችን በሙሉ፣ በአንዴ መስራትና ማሳካት፣ ማግኘትና ማሟላትም አይቻልም። ስለማይቻልም ነውኮ፣ ለእድሜ ልክ የሚያገለግል የሥነ ምግባር ትምህርትና ጥበብ አስፈላጊ የሚሆነው።
ይልቅስ፣ “መልካም ነገር አይቅርብኝ” ማለት፣…
በአንድ በኩል፣ የትኛውንም መልካም ነገር መጥላት ወይም ማጥላላት እንደማይገባን ለመምከር ነው።
በሌላ በኩልም፣ ሁልጊዜ መልካምነት እንዲበዛ መመኘት እንዳለብን ለማስተማር ነው።
“የእስከ ዛሬ መልካምነት ይበቃኛል፤ ተጨማሪ አልፈልግም” እንዴት ይባላል? ሕይወት በቃኝ እንደማለት ነው።
ይልቅስ፣ የዛሬ መልካምነት በነገ ሕይወታችን እየፀና፣… ደግሞም መልካምነት እየበረከተና እያማረበት እንዲቀጥል መመኘት አለብን። ማሰብና መትጋትም ጭምር።
“አይቅርብኝ” የሚለው አባባል፣ ይህን የመሰለ በጎ ትርጉም የሚኖረው፣ በንግሥተ ሳባ የጥበብ መንገድ ነው።
ጥበብንና እውቀት ከምን በላይ ታወድሳለች። ነገር ግን ጥበብን ለማወደስ፣ ዓለማዊ ኑሮን አታናንቅም። እውቀትን ለማክበር፣ ሃብትና ንብረትን አታዋርድም።
ውስጣዊ ሰብዕናን ለማድነቅና ቅንነትን ለማሞገስ፣ ውጫዊ ውበትን አታንቋሽሽም። ግርማ ሞገስን አታንኳስስም። መልክና ቁመናን አታጥላላም።
አንዱን መልካም ነገር ለመውደድ ሌሎች መልካም ነገሮችን ማንቋሸሽ፣ የጥበብ ጉድለት ነው። መልካም ነገሮችን ማዋሃድ ነው - ጥበብ።
የማንነት መርህ ከአኗኗር ጋር፣ የሃሳብ ቁም ነገር ከአነጋገር ለዛ ጋር አብረው እንዲዋሐዱ ትሻለች። ከመልካም ነገሮች፣ አንዱም እንዲቀርባት አትፈቅድም።
ጥረቷና ራዕይዋ፣ “መልካም ነገሮችን በምልዓት ማዋሐድ” ነው። የእውቀት፣ የትጋትና የሰብዕና መርሆችን ሁሉ ያቀፈ ነው፣ የንግሥተ ሳባ የሥነ ምግባር ትምህርት። እናም፣ “ጥበብ” ብላ ትጠራዋለች።

Read 2335 times