Tuesday, 02 August 2022 00:00

“እውነትንና እውቀትን” የሚያከብር ትምህርት (በኢትዮጵያ የነበረ፤ ዛሬ የጠፋብን)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በየዘመኑና በየአካባቢው፣ በተለያየ ቅርፅና መልክ የተተረከላት ንግሥተ ሳባ፣ በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖታዊ መፃሕፍት ውስጥ የክብር ቦታ አግኝታለች።
የሰዎችን ቀልብ የሚገዙና የሚያዝናኑ ኪነጥበባዊ ጽሑፎችም፣ የንግሥተ ሳባን ትረካ በበርካታ አገራት በሰፊው አስተዋውቀዋል።
በእርግጥ፣ ትረካዎቹ ከየዘመኑ የፖለቲካ ልማዶችና ከሃይማኖታዊ ዝንባሌዎች ጋር እየተቆራኙ የተፃፉ በመሆናቸው፣ አንዱ ከሌላኛው ጋር መጣረሳቸው አልቀረም። እንዲያውም፣ በአንድ ትረካ ውስጥም፣ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሃሳቦች በርከት ብለው ቢገኙ አይገርምም።
እንዲያም ሆኖ፣  ሁሉም ትረካዎች በጋራ የሚገልፁልን አንድ ነገር አለ። ንግሥተ ሳባ፣ “እጅግ ጥበበኛና ባለፀጋ ንግሥት” እንደሆነች ትረካዎቹ ሁሉ ያለ ልዩነት ይመሰክሩላታል።
ክብረ ነገሥት የተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ፣ በንግሥት ሣባ ጥበብ ላይ ያተኮረውን ትረካ ለይተን ማውጣትና መመልከት እንችላለን።
የንግሥቲቱ ጥበብ ምን እንደሚመስል ከራሷ አንደበት መስማትና ማረጋገጥ አለብን። ከዚያ በፊት ግን፣ የተራኪውን ነጥቦች በአጭሩ እንይለት።
አንደኛ ነገር፣ ንግሥቲቱ በእውቀት የመጠቀች መሆኗን ተራኪው ይገልፃል።
ንግሥተ ሳባ፣ በረሃውንና ባሕሩን አቋርጣ ረዥም መንገድ የተጓዘችው፣ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብ በአካል ለማየት ነው። ሃሳቧ ግን፣ “ተጨማሪ እውቀትና ጥበብ ለማግኘት” ብቻ አይደለም። በቅድሚያ፣ ጥበበኛነቱን ማረጋገጥ አለባት።
በራሷ የምትተማመን ጥበበኛ ናትና፣ በእውቀትና በጥበብ ሁሉ ልትፈትነው ጭምር ነው የሄደችው። በዝና የሰማችውን የሰለሞን ጥበብ በአካል አይታ ለማረጋገጥ፣ ልኩንም ለማወቅ፣… ከባባድ ጥያቄዎችን ይዛ፣ “የእንቆቅልሽ ፈተና” አዘጋጅታ ነው ለጉዞ የተነሳችው!
ምን ይጠየቃል! ንግሥተ ሳባ፣ በብሩህ አእምሯና በምጡቅ ብቃትዋ እጅግ የላቀች፣ በራሷም የምትተማመን ጥበበኛ ንግሥት ናት።
ታዲያ፣ የንግሥተ ሳባ “የጥበብ ልህቀት”፣… ሁሌም ተጨማሪ እውቀት ለማግኘትና ለመማር ካላት ጉጉት ጋር የተጣመረ ነው። አይነጣጠሉም።
በራሷ መተማመኗም፣… ለእውነታ ከመታመንና ለእውቀት ካላት ፍቅር ጋር የተዋሐደ ነው። አይለያዩም። በሯሳ ትተማመናለች። ስህተትን ለማስተካከልም ቅንጣት አታመነታም።
“ፅኑ እምነት መያዝ” እና “የተሳሳቱ ሃሳቦችን ማስተካከል” እርስ በርስ እየተደጋገፉ እውነትን ይገነባሉ እንጂ አይጣሉም። እውነትም፣ የንግሥቲቱ ጥበብ የውሕደት ጥበብ ነው።
ንግሥተ ሳባ፣ የሥነ ምግባር መርሆችን ሁሉ የሚያዋሕድ አንድ ቃል መጠቀሟ አለምክንያት አይደለም። ለምን ቢባል፣…
ብዙ ስህተቶች፣ ጥፋቶችና ክፋቶች የሚመነጩት፣…
አንድን እውነት ከሌላ እውነት ጋር እያገናዘቡ ከማዋሐድ ይልቅ እየነጠሉ ለማጋጨት፣…
አንድን መልካም መርህ ከሌላ ተጓዳኝ መልካም መርህ ጋር እያጣመሩ ከመገንባት ይልቅ እየገነጠሉ እርስ በርስ ለማጣረስ ከሚደረግ ቀሽም ሙከራ ነው።
የንግሥተ ሳባ ጥበብ፣ እነዚህን  ጉድለቶች ያስወግዳል። Dogmatism እና Relativism ተብለው የሚታወቁ የአስተሳሰብ ቅኝቶች፣ ከአንድ ምንጭ የሚፈልቁ ስህተቶች መሆናቸውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። መነሻ አቋማቸው እንዲህ ይላል።
በአንድ በኩል “ፅኑ እምነትን መያዝ”፣ በሌላ በኩል ደግሞ “የሃሳብ ስህተቶችን ማስተካከል” እርስ በርስ ይጋጫሉ። ተስማምተው ሊዋሐዱ አይችሉም ባይ ናቸው። በዚህም ሳቢያ፣…
አንደኛው ጎራ፣ “ጭፍን እምነትን” አፅንቶ ለመያዝ ይመርጣል። Dogmatism ይሉታል። “ለእውነታ የማይበገሩ” መርሆችን በጭፍን ይቀበላል፤ ሰዎች ላይም ይጭንባቸዋል። በጭፍን እምነት የተቧደኑ ሰዎች፣ መግባቢያ ዘዴ ስለማይኖራቸው ለመጠፋፋት ይፎካከራሉ።
ሌላኛው ጎራ ደግሞ፣ “ሁሉም ሃሳቦች የዘፈቀደና የዘልማድ ሃሳቦች ስለሆኑ፣ እኩል ናቸው” ይላል። Relativism ይሉታል። እናም፣ ህሊና ቢስነትን፣ መርህ የለሽነትንና ሥርዓት አልበኝነትን የሚያበረታታ ይሆናል። አልያም፣ Post-modernism በሚሉት  ቅኝት ላይ እንደምናየው፣ ሰዎችን በዘር ወይም በብሔረሰብ ያቧድናል። በእድሜና በፆታም ጭምር።
የንግሥተ ሳባ ጥበብ፣ ከእነዚህ ስህተቶች የፀዳ ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ መድሃኒት ሊሆን የሚችል ጥበብ ነው። ከጭፍንነት ወይም ከቅዠት ለመገላገል፣ በእነዚሁም ሳቢያ ከሚመጡ የመደንዘዝ ወይም የመቅበዝበዝ መዘዞች ለመዳን ይረዳል።
“ትክክለኛ ሃሳቦችን በፅኑ እምነት መያዝ” እና “የተሳሳቱ ሃሳቦችን ለማስተካከል አለማመንታት”፣ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ይዋደዳሉ እንጂ አይጣሉም።
የግቢያችንን በር፣ በሁለት ስም “መግቢያ” እና “መውጫ” ብለን ብንጠራውም፣ በሁለት አቅጣጫ ብንጠቀምበትም፣ “አንድ በር” እንደሆነ ምን ያከራክራል?
ሃሳብን ማስተካከል፣ “እምነትን በትክክል ያፀናልናል” እንጂ አይሸረሽርብንም። የሃሳብ ስህተቶችን ማስተካከል የሚችል ሰው፣ በእውነታ ላይና በአእምሮው ላይ ጽኑ እምነት ይኖረዋል።
በሌላ በኩል፤ ትክክለኛ ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ፅኑ እምነት፣… ለእውነታ መታመን ነውና፣ የሃሳብ ስህተትን እንድናስተካከል ያበረታናል እንጂ፣ በጭፍንነት ከስህተት ጋር አስሮ አያስቀረንም።
ፅኑ እምነትና ሃሳብን የማስተካከል ዝግጁነት፣ እርስበርስ ይዋደዳሉ - በንግሥተ ሳባ ጥበብ።
ኋላቀር (Primitive) ድንዛዜ እና በዘመነኛ ቅዠት (Post-modernism) መሃል እየዋዠቅን እንዳንባክንም የንግሥቲቱ ጥበብ ያግዛል። የንግሥተ ሳባ ትምህርት ዘመናት የማይሽሩት ጥበብ ስለሆነ ዛሬም ኃያል ጉልበት አለው።
ሁለተኛ ነገር፣ ጥበበኛዋ ንግሥተ ሳባ፣ ፍሬያማና የተቃና መንገድን በብልኃት የምትጠርግ፣ ትጉህ የስራ ሰው እንደሆነች ተራኪው ይገልፃል።
እውቀት፣ እንዲሁ ያለ ፍሬ ባክኖ ወይም በከንቱ መክኖ እንዲቀር አትሻም። እውቀት ኃይል እንደሆነ ገብቷታል። “ጥበብ… ኃይል ትሆንልኛለች” ብላለች ንግሥተ ሳባ - የአገሯን ሰዎች ስታስተምር።
የእውቀት ኃያልነቱና መልካምነቱ ደግሞ ፍሬያማነቱ ነው። ትጉህ ሙያተኞች በየመስኩ እጅጉን የበዛ ሃብት እንዲፈጥሩና ኑሮን እንዲያለመልሙ፣… ንግሥተ ሳባ እንቅፋቶችን ታስወግዳለች። መንገዳቸውን ታቃናለች። በፅናት ትሰራለች።
ነገር ግን፣ “ሁሉንም ነገር የምሰራላችሁ እኔ ነኝ። የናንተ እረኛ ነኝ” የሚል ስህተት ውስጥ አልገባችም።
“የስራ ፍሬ ሁሉ በኔ ትዕዛዝ የሚገኝ ውጤት ነው” አትልም።
ይልቅስ፣ ሌሎች ሰዎች ሁሉ በየሙያቸው በጥበብ እንዲሰሩ ታበረታታለች።
የራሷን ድርሻ በትጋት ታከናውናለች። ሰዎች በሰላም ሰርተው ፍሬያማ እንዲሆኑ፣ ሕግና ሥርዓትን በጥበብ ታስከብራለች።
ጥበቧ ግን ከዚህም ያልፋል።
ሕግ ተከብሮ፣ የአገር ሰላም ተጠብቆ፣ ፍትሕ እንዲፈፀም እለት በእለት፣ የመንግሥትን ሃላፊነት ማከናወን፣ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ ለነገ የሚተርፍ፣ ለዘመናትና ለትውልዶች የሚበጅ ሌላ በረከት ደግሞ አለ።
መሠረቱ እየፀና፣ አወቃቀሩም እየተስተካከለ፣ ዘመናትን የሚሻገር፣ በሥልጣኔ ጎዳናም የሚራመድ፣ ጥሩ መነሻ ሊሆን የሚችል “ሥርዓትና ባሕል” ማደበር፣… በጣም ከባድ ስራ ነው። ብዙ መልካም ነገሮችን አዋሕዶ የማሰብ ጥበብ የሌለው ሰው፣ አይችለውም። አያስበውም እንጂ።
እውነትም ደግሞ፣ መልካም ሥርዓትን በመገንባት ጥበቧን ያሳየች ፈር-ቀዳጅ ንግሥት መሆኗን ተራኪው ይገልፅልናል። ሦስተኛ ነገር፣ በድንቅ ብቃቷና በልህቀቷ፣ ግርማዊ ክብርን፣ እንዲሁም የተቀደሰ ሰብዕናን የተቀዳጀች የውበት ንግሥት ናት።
ከጥበበኛ ሰዎች በረከት ለብዙዎች ይተርፋል። ከዘመን ዘመን ያፈራል። ከሁሉም በላይ ግን፣ ከአርአያነታቸው የምናተርፈው በረከት ይበልጣል።… ግን የውበት ነገርስ? እስቲ፣ እንደተለመደው አሳሳችና ቀሽም ጥያቄዎችን አደራርበን እናንሳበት።
የብቃት ልህቀቷንና ቅዱስ ሰብዕናዋን ብናደንቅ፣ ይሁን እሺ። ነገር ግን፣ ከዚህ ጋር አብሮ፣ “የውበት እመቤት፣ የግርማ ሞገስ ንግሥት” ብለን ለምን እናወራለን? ብቃትና ውበት ምና አገናኛቸው? ቅዱስ ሰብዕና ከቁመናና ከግርማ ሞገስ ጋር ምን ያዛምደዋል?
የጥያቄዎቹ መነሻ ምን እንደሆነ ይገባችኋል። ያው፣ መልካም ሥነ ምግባር፣… በሆነ መንገድ አንዳች ጉዳትና ጉድለት ማምጣት አለበት የሚል አስተሳሰብ ተጋብቶብናል። መልካም ነገሮችን እርስ በርስ ማቃረን እንጂ ማሟላትና ማዋሐድ “አልለመደብንም”። መልክና ቁመና፣ አላፊና ጠፊ ናቸው የሚል አባባል ይመጣብናል። እንዲህ ባናራክሳቸው እንኳ፣ እንደ ቁም ነገር እንዲቆጠሩ ግን አንጠብቅም። ከብቃት ልህቀትና ከቅዱስ ሰብዕና ጎን ለጎን፣ ስለ ውበትና ስለ ግርማ ሞገስ ከተተረከማ፣ አይዋጥልንም። ይከነክነናል።
ብቃትና ውበት ምና አገናኛቸው?
ባይጥመንም፣ ከንግሥተ ሳባ ልሕቀትና ጥበብ ጋር፣ ወደር የለሽ ውብ መልኳና ማራኪ ቁመናዋም፣ ብዙ ተወርቶላቸዋል። በእርግጥ፣ ስለ ቁንጅናዋ ስትጨነቅ ወይም ስትደክም አይታይም።
በመልኳና በቁመናዋ እጅግ የተዋበች መሆኗን በሚገልፅልን የንግሥተ ሳባ ትረካ፣ ራሷን ለማቆንጀት ምን እንደምታደርግ አይነግረንም። የመቆንጀት ጥረት ይቅርና ሙከራም አልተጠቀሰም።
ከተለመደው ጥንቃቄና ዝግጅት ውጭ የተለየ ነገር ባታደርግ ይሆናል። ደግሞም፣ ከመደበኛው በላይ የላቀና የደመቀ ውበት፣ በመቆነጃጀት ብቻ አይመጣም።
ይልቅስ፣ የውጭ ገፅታ፣ የውስጥ ማንነትን ያንፀባርቃል። ብሩህና ክቡር ማንነቷን ከውስጥ አውጥተው የሚመሰክሩ ናቸው - መልክና ቁመናዋ።
እንዲህ ሲባል ግን፣ የውስጥ ማንነትንና ሰብዕናን ለማሞገስ፣ ውጫዊውን መልክና ቁመናን አሳንሶ ለማሳየት አይደለም። መልካም ነገሮችን ማዋሐድ እንጂ፣ አንድን መልካም ነገር ለማድነቅ፣ ሌሎች ጥሩ ነገሮችን ማንቋሸሽ፣ የንግሥት ሳባ መንገድ አይደለም።
እንደ ንግግር አስቡት። አነጋገርን ለማሳመር መሞከር ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ የሃሳብን ትክክለኛነት ለመዘንጋት ወይም ለመሸወድ መሆን የለበትም። መልካም ነገሮችን ማጓደልና ማቃረን፣ የንግሥት ሳባ “ዘይቤ” (ስታይል) አይደለም።
ብንጠይቃት፣ “ሃሳባችንንም እናስተካክል፣ አነጋገራችንንም እናሳምር” የሚል መልስ ልትሰጠን ትችላለች።
ውስጣዊ እውቀትና ሃሳብን፣ ከውጫዊው የንግግር ለዛ ጋር አሳምሮ ማዋሐድ እየተቻለ፣ ለምን እናጣላቸዋለን? ማጣላት፣ ከአላዋቂነት የሚመጣ ጎደሎነት ነው፤ ወይም የስንፍና ስብራት።
እውቀትን ታፈቅራለች። ሃብት ማፍራትንም ትሻለች። ሁለቱን አስማምቶ ያሟላል - የንግሥተ ሳባ ጥበብ።
ለጥበበኛ  ሰው ያላት አድናቆትና አክብሮትም ሌላ ጥሩ ምሳሌ ነው። ጥበበኛን ስታፈቅር፣ የንግግሩን ቁምነገር ታደንቃለች። የአነጋገር ለዛውን ትወዳለች።
አንዱም እንዲቀርባት አትፈቅድም። ሁለቱንም ትፈልጋለች - እውቀቱንም አነጋገሩንም።
“ንግግር ያለ ጥበብ አይጨበጥም” ብላለች ንግሥቲቱ።
የጥበብ ትምህርትም ያለ ንግግር ለዛ አይሰምርም።
ማራኪ ውበትና ፅኑ ሰብዕናም፣ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ ይሄዳል። ጥበበኛን ማየት ትፈልጋለች። ሙያውና እውቀቱ ያስደንቃታል። መልኩና ቁመናው፣ አረማመዱና ግርማ ሞገሱም ይማርካታል። ደግሞስ ለምን ይቅርባት?
የአፍንጫና የጆሮ ቅርፅ፣ የዓይን ቀለም ወይም የፀጉር ዓይነት፣ የእግር ወይም የአንገት ርዝመት፣… ሁሉም ተመጣጥነውና ተስተካክለው ሲገኙ እሰዬው ነው። ጎላ ጎላ ማድረግ፣ ማሳመርና ማቆንጀትም፣ መልካም ነው። ግን፣ አእምሮንና የውስጥ ማንነትን ለመዘንጋት አይደለም። መሆን የለበትም እንጂ።
ያለ አእምሮ፣ ውጫዊው ውበት ባለበት አይቆይም፣ አይፈካም። በስንፍና ወይም በአላዋቂነት ምክንያት ይደበዝዛል። እየላላ እየጠመመ ይበላሻል። በአደጋ ወይም በሕመም ሳቢያ አእምሮ ላይ አንዳች ጉዳት ሲደርስ እንኳ፣ መልክና ቁመና፣ የፊት ቅርፅና አረማመድ እንደሚዛባ ጥያቄ የለውም።
ውጫዊና ውስጣዊ ገፅታዎች፣ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። እርስ በርስ እንዲቃረኑ ማድረግ ይቻላል። ግን ተገቢ አይደለም። እርስ በርስ እንዲዋደዱ ማድረግ ነው - ጥበብ። ንግሥቲቱ ይህን ታስተምራለች።
የንግሥተ ሳባ ማራኪ ውበትና ግርማ ሞገስ፣… የማንነቷን መልክ የውስጧን ቁመና የሚመሰክሩ ናቸው የተባለውም አለምክንያት አይደለም። እውነት ስለሆነ ነው። ንግሥቲቱ ከምታስተምረን ጥበበኛ የሥነ ምግባር መርህ ጋርም ይጣጣማል።
በአንድ በኩል፣ የግል ብቃትን፣ ጀግንነትንና የላቀ ራዕይን የራሷ በማድረግ፣ ልዕልናን ተቀዳጅታለች።
በሌላ በኩልም፣ የሌሎችንም ብቃት በማድነቅ፣ ጀግንነታቸውን በማሞገስ፣ የላቀ ራዕያቸውንም ከልብ በማፍቀር ጭምር የሥነ ምግባር መሪነቷን አስመስክራለች።
በአጭሩ፣... የተቀደሰ ሕይወትን በእውን አሳይታለች።
እንዲያም ሆኖ፣ በጥበብ ተራቅቄ፣ በእውቀት መጥቄ ጨርሻለሁ አላለችም። ከአገሯ አዋቂዎችና ጥበበኞች፣ እንዲሁም ከጎረቤትና ከባሕር ማዶ፣ ሁሌም እውቀትን ለመገብየት ትተጋለች። በዚህ መሃልም ነው፣ የንጉሥ ሰለሞንን የጥበብ ዝና የሰማችው፤ የተደነቀችው። ታዲያ እንዲሁ ዝናውን በመስማት ብቻ አይደለም።
ማስተዋልና መጠየቅ ባሕሪዋ ነው። ዝናውን ሰማች። የሰማችውን ያህል ጥያቄዎችን ታነሳለች። አማካሪዋ፣ በአካል ሄደው ያዩትንና የሰሙትን ይተርኩላታል። ታደምጣለች። ታሰላስላለች።
እንዲህ እንዲህ ነው፣ አድናቆቷ እየጨመረ የመጣው። ለመሄድም የተነሳችው።
ውሳኔዋን ለአማካሪዎቿና ለአገሯ አዋቂዎች ገለፀች። የወሰነችበትን ምክንያት አስረዳች። እንዲህም አለች።
“ነፍሴ ጥበብን ትሻለች። ልቤ እውቀትን ለመጨበጥ ታስሳለች።
በጥበብ ፍቅር ተማርኬያለሁ፣ በእውቀት አውታሮች ተይዣለሁ።
ጥበብ በምድር ላይ ከተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ ይበልጣልና።
ከሰማያት በታች፣ ከጥበብ ጋር የሚስተካከልስ ነገር ምን አለ?” በማለት ተናገረች ንግሥቲቱ።
በመቀጠልም፣
ጥበብ፣...
“ለልብ ደስታ፣ ለዓይን ፍንትው ያለ ደማቅ ብርሀን፣ ለእግር ግስጋሴ፣... ለደረትም ጋሻ፣ ለራስም መከታ፣ ለአንገትም ሃብል፣ ለወገብም ቀበቶ ናት” በማለት አወደሰች።
ደግማ ለማስረዳት፣ ከየፈርጁ ምሳሌዎችን ዘረዘረች።
ያለ ጥበብ፣… አገርና መንግስት፣ ሕግና ሥርዓት፣ አይቃናም።
ያለ ጥበብ ሃብትና ንብረት አይበረክትም።
ያለ ጥበብ፣ እግር በተራመደበት መሬት ላይ ፀንቶ መቆየት አይችልም።
ያለ ጥበብ፣ የአንደበት ንግግርም አይጨበጥም።… በማለት አስተማረች።
እውቀት የጎደላቸው ሰነፎች ከሚናገሩት ከንቱ ስብከት ጋር አነፃፅሩት። ንግሥተ ሳባ፣ “ጥበብ ብቻ ይኑረኝ፤ ሌላው ሁሉ ይቅርብኝ” አላለችም። እውቀትና ግንባታ፣ ሃሳብና ተግባር፣ የሥነ ምግባር መርህና የተባረከ ፍሬያማ ኑሮ እርስ በርስ የተጣመሩና የተዋሐዱ የሕይወት ገፅታዎች እንጂ፣ ተፃራሪዎች አይደሉም። ተፃራሪ ልናደርጋቸው እንደማይገባም ደጋግማ ትናገራለች።
“ጥበብ ለኔ... ስልጣኔና ኃይል ትሆንልኛለች። ጥበብ ለኔ፣ የተትረፈረፈ በረከት ትሆንልኛለች” ብላለች ንግሥቲቱ።
ይህም ብቻ አይደለም። ጥበብንና ብቃትን ማድነቅ፣ ጥበበኞችንና የብቃት ባለቤቶችን ከማድነቅ ጋር መዋሐድ እንዳለበት አስተምራለች። ታዲያ፣ የብቃት ሰዎችን ማክበር ማለት፣ ራስን ዝቅ ማድረግ ወይም ችሮታ እንደመስጠት አትቆጥረውም። አዎ፣ ጥበበኞች ክብር ይገባቸዋል። ነገር ግን፣ ጥበበኞችን ማክበር፣ “ለራስ ነው”። ጥበበኛን የወደደ፣ ጥበበኛ ማንነትን ለራሱ ይገነባል ብለለች ንግሥቲቱ።
“ጥበብን ማክበር፣ ጥበበኛውን ማክበር ነው።
ጥበብን ማፍቀር ጥበበኛውን ማፍቀር ነው።” አለች።
ጥበብን መሻትም ጥበበኛውን መሻት ስለሆነ፣ ለረዥም ጉዞ መነሳቷን አስረዳች።
የአገሬው ሰዎችም እንዲህ ሲሉ መለሱ።
“እመቤታችን ሆይ፣... ጥበብ እንኳ ሞልቶሻል። የጥበብ እመቤት በመሆንሽም ነው፣ ጥበብን ማፍቀርሽ” በማለት አድናቆታቸውን ገልፁላት።
እውነት ብለዋል። ጥበቧን ከልብ ተምረዋል።

Read 8084 times