Saturday, 30 July 2022 14:02

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ነገር

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሳውዲ አረቢያን ጎብኝተዋል፡፡ በሳውዲ አረቢያ የነበራቸው ቆይታ ሳውዲን የመጎብኘት ብቻ ሳይሆን፣የአረብ አገራት መሪዎችን ሳውዲ ላይ ሰብሰቦ ከእነሱ ጋራ በአካባቢያዊና በአለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የመምከር ነበር፡፡ በጉባኤው የሊቢያን፣ የየመንና፣ የሶሪያን ጉዳይ እንዲሁም አለም አቀፍ አሸባሪነትን አንስተው ተመካክረዋል።
ሳውዲ ድረስ ተጉዘው በጅዳው የአረብ አገራት  የመሪዎች ስብሰባ ላይ ከታደሙት አንዱ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ናቸው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባይደን እና የግብፁ ፕሬዚዳንት ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ተገናኝተውም በግል መክረዋል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል መቶ ዓመት ስለሞላው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው፣በመከላከያና በኢኮኖሚ ስላላቸው ትብብር፣ ግብፅ በአረቡ ዓለምና በእስራኤል መካከል ወዳጅነት ለመፍጠር ስለምትሰጠው ድጋፍ መክረዋል። ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብም  ጉዳይ አንዱ የመወያያ ርዕሳቸው  ነበር፡፡ በምክክሩ ላይ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ቢልንከን እና  የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሚ ሽኩሪ ተገኝተዋል፡፡
ከምክክሩ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫም፤ አሜሪካ የግብፅን የውሃ ዋስትና ማግኘት እንደምትደግፍ፣ለአካባቢው ሰላምና ብልፅግና አስተዋፅኦ በሚያደርግና የሁሉንም ወገኖች ጥቅም  በሚያስከብር መንገድ ችግሩ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ  እንደምትሻ ተመልክቷል፡፡
ግብጽና ሱዳን ላለመስማማት ተስማምተው፣ በታላቁ የሕዳሴ በግድብ ጉዳይ  ለአስራ አንድ ዓመት ተደራድረዋል። በግብፅና በሱዳን ኩርፊያ ይኸው ድርድር ከተቋረጠ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ድርድሩ የተቋረጠው በኢትዮጵያ ፈቃደኝነት ማጣት ሳይሆን፤ ግብጽና ሱዳን  ከኢትዮጵያ ጋር አሳሪና  አስገዳጅ ስምምነት ለማድረግ በመፈለጋቸው ነው፡፡ እነሱ አሳሪና አስገዳጅ ስምምነት የሚሉት እንዲይዝ የሚፈለገው ደግሞ የታላቁን የህዳሴ ግድብ እንቅስቃሴና አስተዳደርን (operation)  ጨምሮ ኢትዮጵያ ባሏት ወንዞች የሚኖራትን ተጠቃሚነት የሚያጠቃልል ነው።  
ወደ ግማሽ የሚጠጋው የኢትዮጵያ አካል የአባይ ገባር የሆኑ ወንዞች የሚመነጩበትና የሚፈሱበት አካባቢ ነው፡፡ ከሰሜን በሽሎ ተከዜን ብር፣ ተምጫና በለስ፤ ደቡብ ደዲሳ፣ ፊንጫ ጉደር፣ ሙገር፣ ወንጪ ባሮ፣ አኮቦና ጊሎ የተባሉት ትላልቅ ወንዞቻችን በዚህ አሳሪ ስምምነት ውስጥ ገብተው እንዲታሰሩ ይፈለጋል፡፡ ይሄ እነዚህን ወንዞች  ከመስኖ ጀምሮ ለልዩ ልዩ የልማት አገልግሎቶችት እንዳይውሉ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነው። ስለዚህም የግብፅንና የሱዳንን አሳሪ ስምምነት በሩቅ ማለት የግድ ነው፡፡
መንግስት በይፋ ባይገልፅም፣ እራሳቸው ግብፆች ከሳተላይት አገኘነው ካሉት መረጃ ተነስተው፣ ምንም አይነት አሳሪና አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረግ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለሶስተኛ ጊዜ እየተሞላ መሆኑን እየተናገሩ ናቸው።  አልሞኒተር የተባለው  የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ይህንኑ ዘግቧል፡፡ ዘገባው በሁለተኛው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጊዜ አልፎ አልፎ በውሃ ተከበው የደሴትነት መልክ ይዘው የነበሩ ቦታዎች፤ አሁን በውኃ እየተዋጡ እየጠፉ ናቸው ሲልም ያብራራል፡፡
ኢትዮጵያ ፈቃደኛና ዝግጁ ብትሆንም፣ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ ወደ ነበረው ድርድር መመለስ ያልፈለጉት አጥብቀው  የጓጉለትን አስገዳጅና አሳሪ የሆነ ስምምነት ማግኘት እንደማይችሉ ስለ አመኑ ብቻ ሳይሆን፤ ስምምነት ኖረም አልኖረም አሁን እያገኙት ያለውን የውሃ መጠን እንደማያጡት  እርግጠኞች ስለሆኑም ነው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ሁለት ነገር ማንሳት አስፈላጊ ጉዳይ ይሆናል፡፡ አንደኛው ከኢትዮጵያ የሚወጡ ወንዞች አባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ፣ አኮቦና ጊሎ  ወዘተ ምን ያህል ዓመታዊ ፍሰት እንዳላቸው የሚያስረዳ መረጃ ኢትዮጵያ ያላት  አይመስለኝም፡፡ ሁልጊዜ ሲጠቀስ የምሰማው ከግብፅ የሚገኘው መረጃ ነው። ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በወንዞች መውጫ አካባቢ አመቺ ቦታ እየፈለገ፣ የራሱን የውሃ ፍሰት መለኪያ መትከል አለበት፡፡ ይህ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።
ክረምት በመጣ ቁጥር ህዝቡ በየአካባቢው ለችግኝ ተከላ  ይወጣል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እንደተተከለም ይታወቃል፡፡ የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ የፈወሳቸው ተብለው አንዳንድ አካባቢዎችም በማስረጃነት ይቀርባሉ።  በዶ/ር ዐቢይ ዘመነ መንግሥት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከል ከተጀመረ ደግሞ ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመቱ ነው፡፡ የሚተከለው ለዝና ሳይሆን በአካባቢ ላይ ለውጥ ለማምጣት ነው። የአካባቢው ለውጡ የህዝብም መጠን ለውጥ ብቻ ሳይሆን የወንዞችንም የፍሰት መጠን ይለውጣል፡፡  በየአካባቢው የጠፉ ምንጮች እንደገና መፍለቅ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው፡፡
አሁን ያለው የወንዞቻችን የፍሰት መጠን መጨመር ወይም ባለበት ለመቆየት መቻል በሁለቱም መንገድ በችግኝ ተከላ ላይ ያዋልነው ጊዜና ጉልበት ያስከተለው ውጤት መሆኑን መገንዘብ  ተገቢ ነው።
ስለዚሀም በዚህ መንገድ የተፈጠረው ወይም የተገኘው የውሃ ሃብት ተገምቶ ወደ ግብፅና ሱዳን ከሚሄደው  ውሃ ተቀንሶ መያዝ አለበት፤ ወይም ደግሞ ግብፅና ሱዳን እንዲከፍሉበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለሴቶ ከደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ ከ36 ሚሊዮን ዶላር በላይ የምታገኘው ከውሃ ሽያጭ መሆኑንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ የሞኝነት ዘመን ሊያበቃ ይገባል። የታላቁን ህዳሴ ግድብ ነገር  ከብዙ አቅጣጫ መመልከትም ያሻል።  
በነገራችን ላይ ዛፍ መትከል ለአፈር ጥበቃ ማገልግሉ የታወቀውን ያህል፤ የታጠበ አፈርን አጥልሎ በማስቀረት ደግሞ ሳርን የሚክል የለም። በወንዞችና በማሳዎች ዳርቻ ሳር ማልማትን ምነው ጉዳዬ የሚለው ወገን ጠፋ?!

Read 11976 times