Saturday, 30 July 2022 14:07

ሀቻምና ቅዳሜ…

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

  ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በአንደኛው ቃለ-ምልልሱ፣ ስለግጥም ቤት-ምት ዓይነቶች ሲያስረዳ፤
“ሀቻምና ቅዳሜ በክረምት ወራት
የጣሊያን ተወላጅ ቹሊ የሚሉት
ታታ ታታ ታታ ታታታ…” ያለውን ስሰማ፣ ይህ አሁን ያለው ትውልድ የደራሲ ከበደ ሚካኤልን “እሮሮ” የሚለውን  ግጥም ያውቀው  ይሆን? ብዬ በአጭሩ ልጽፍበት አሰብኩ።
እነሆ፡-
ደራሲ ከበደ ሚካኤል በልጅነታችን የጻፉልን “እሮሮ” የተሰኘ ግጥም (ኤፒክ ሊባል የሚችል) የዐንድን ህብረተሰብ በወራሪ ጠላት መጠቃት- በአካልም፣ በስነ-ልቡናም፣ በቅጡ ያስረዳናል። ስለ አንድ ቺሊ የሚባል የጣሊያን ተወላጅ ነው። ስለ ትምህርታዊነቱ ዛሬ  እዚህ እንጠቅሰዋለን።
“ሀቻምና ቅዳሜ በክረምት ወራት
የታሊያንን ተወላጅ ቹሊ የሚሉት
ልዩ ልዩ ወሬ ስንጨዋወት
በሰው ዘር መካከል ያለው ልዩነት
ብዙ ነው…”
እያለ እንዲህ ሲል አመጣ፡-
“ጣሊያን ባበሻ ላይ የበላይነቱን
የሚያሳይበትን ሰጥተናል” ዕውቀትን…
እያለ እጅግ አድርጎ ይመጻደቅ ነበር።
እስቲ አጠር አጠር አድርገን የተናገረውን እናስተውለው፡-
“እናንት አበሾች በታሪካችሁ ስትሞላቀቁ፣ የዋጋችሁን ልክ ለማወቅ ተስኗችኋል!” አለ።
ቀጠለ በግጥም፡-
“የምትመኩበት፣ ምን ይሆን ክብራችሁ
ባቡር አውቶሞቢል ስልክ ፈጠራችሁ?
ከመንፈስስ ጥበብ፣ ምን ፈለሰፋችሁ?”
ጥሩ አገር ይዛችሁ በከንቱ ስትኮሩ
ወይ አትሰሩበት ወይ ሰው አታሰሩ
ስንመለከተው የኑሯችሁ ቅጥ
ከእንስሶች አኗኗር ምን ያህል ሲበልጥ
አንደኛ ያለው ሕዝብ የሞላው ጥበብ
እንዳንተ ያለ የደከመውን
ዕውቀት ጦር መሳሪያም የጎደለውን
እንደ እንስሳት ሁሉ ፈጅቶ እያባረረ
ሰውንም ቤቱንም እየመነጠረ
ላየው ደስ የሚያሰኝ ለሰሪ እሚያኮራ
ለዓለም የሚጠቅም ብዙ ብዙ ሥራ።
እያከናወነ ይሰራበታል፤
የእናንተ ሙያ ግን ኧረ ወዴት አለ?
ምሳሌ ልንገርህ
የሚያገለግለኝ አብሮኝ የሚኖር
አለኝ የቀጠርኩት አንድ አበሻ አሽከር
… መሬት መሬት እንጂ ፊቴን እንዳያይ
አጥብቄ ከልክየው ተሸቆጥቁጦ ያድራል
ይሄንንም ትዕዛዝ ፈጽሞ ይኖራል።
ደግሞ ላበሻ ሰው ሰላምታ ስሰጥ
እጄን ዘርግቼለት እጁን መጨበጥ
ትልቅ ውርደት ሆኖ ስለሚታየኝ
መቼም አላረገው ለዚህ ኩሩ ነኝ።
ጣሊያኖች ደማችን የተቀደሰች ናት
የሚኬል አንጀሎ
የዳንት የማርኮኒ፣
የናጋሪ ባልዲ
የነሙሶሎኒ
የነጠረ ደም ነው ከወርቅም የጠራ
ሰርተናል ባለም ላይ ብዙ ትልቅ ሥራ
… አድዋ ድል ብንሆን
ዐርባ ዓመት ቆይተን
ይኸውና ዛሬ ተመልሰን መጥተን
አሸንፈናችሁ እንዲህ እያጠቃን
ደምን ለመበቀል ለመግዛትም በቃን
እያመነመነ ክፉ ድንቁርና
ስለገደላችሁ የማይተው ስንፍና
ብልሃት አይገኝም ምንም ቢመረመር
እናንተን ጨርሶ ከማጥፋት በተቀር።
ሰምቼ እንዳልሰማ በሆዴ እያረርሁ
የንዴቴ ብዛት መልስም አልመለስሁ።
ስቄ ካጠገቡ ተነስቼ ሄድኩ!
እያንገበገበ አንጀቴን ሲያጨሰው
እሮሮ አታሰማኝ ይላል ያገሬ ሰው።
የዲሞክራሲ መብትና ነጻነት ማስከበር፣ መደራጀ፣ ድርጅት ወይ ፓርቲ መፍጠር፣ ማህበራትን ማስተባበር ለረዥም ጊዜ በርካቶች የሞቱለትና የታገሉለት ፍሬ ነገር፣ አርቲስቶቻችን እነ እቴቴ በወር በወር የሚቀበሉት ጽዋ ለፖለቲካ አመራሮቻችን ጽኑ መርህ ሊሆን በተገባው ነበር።
ባሕላዊ ፖለቲካዊና፣ ፖለቲካዊ ባህል የማይለየን ስርዓተ-ምሳሌያችን ነው። ቀጥሎ ደግሞ እላፊ ፖለቲካ ይመጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የእላፊ ድርጊቶች መኖራቸውና ማስቀጣታቸው አሌ አይባልም። ከአንበርብር ጎሹ ብንጀምር ወንጀሉ “አፍ-እላፊ” ይባላል። በጃንሆይ ጊዜ “ምላስ-እላፊ”  ፖለቲካዊ ኃይለ-ቃል ተጠቅሞ የአገር መሪን መንግስትን፣ ሊ/መንበርን፣ ባለ ጊዜን፣ መተቸት እግር-እላፊ
ከአገር መኮብለል
ጭን-እላፊ
የዘማች ሚሊሺያ ሚስት መድፍርና
ኪስ- እላፊ
ኪስ ማውለቅ፣ ከታክሲ፣ ከአውቶብስ ከእግር
ዐይን -እላፊ
የሰው ፍቅረኛ መጥቀስ፣ ማኳሸም፣ ማማለል
ባስ-እላፊ
የአውቶብስ ላይ “ቸወ”ዎች ሌብነት
አጥር-እላፊ
አጥር ዘሎ ጎረቤት ውሽማ
ሚስት-እላፊ፡-
የሰው ሚስት መድፈር
ፍቃድ-እላፊ፡-
ኮንትሮባድ
ልብ-እላፊ፡-
- ሳይገናኙ የሌላ  ሚስት  መውደድ መዋደድ
- ካገር ለመውጣት መዶለት
ይሄ ሁሉ እላፊ መኖሩ የሚጠቁመን እንግዲህ ከአገር ተነጥሎ የሚሄድ በርካታ ልብ ያላቸው አያሌ ወጣቶች- ወጣት ቢሉም የሕብረተሰቡ ትኩስና አምራች ኃይል መኖሩን ነው።
የሀገሪቱ የሰው ሃይል እየተመናመነ ከመሄዱ በተጨማሪ፣ በየጊዜው ቁጥሩ እያሻቀበ የሚወጣው የስራ-አጥ ቁጥር ሲታከልበት፣ “የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንደሚባለው ተረት ይሆናል ማለት ነው። አንድም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ “ለያዥ- ለጋራዥ ያስቸገረ” የሚያሰኘው ይሄ ይሄ ሰበብ ነው።
የትላልቅ አገሮች “ትልቁ አሳ ትንሹን አሳ መዋጡ” ያለና የነበረ ነው። ንድፈ-ሀሳቡ፤ የትናንሾቹ አገሮች መጎሻሸምና መናቆር በጎረቤቶች መካከል ሰላም እንዳይኖር፣ ከአገር አገር መፈናቀሉ እንዳያባራ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በየጊዜው መከሰት፣ “ከየባሰ-አታምጣ” የተሻለ መፍትሄ እንዳይኖረው አድርጎታል።
መሪዎቻችን ይህን እያዩ እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል፣ ባንልም ባለሙያዎቻችን ቢያንስ የወፍራም ደመወዛቸው ምንጭ ይሄው ችግር መሆኑን አውጠንጥነው፤ ከመሸሽ መጋፈጥን መርጠውና ከእኔ ምን አገባኝ አቋም ተላቅቀው ከአገራችን ገጣሚ ስላቅና ወግ መገላገል አለባቸው። ገጣሚው የሚለውን እንስማው፡-
“እኔ ምን አገባኝ”
እኔ ምን አገባኝ? የምትሉት ሀረግ
እሱ ነው ያረዳት አገሬን እንደ በግ
ብዬ ግጥም ልጽፍ ተነሳሁኝና
ምን አገባኝ ብዬ፣ ቁጭ አልኩ እንደገና!
ፈረንጅ አገር የተማረውም ኢትዮጵያዊ ወይ እንደ “አርአያ” (የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ድርሰት ገጸ-ባህሪ) አገሩን ለማገልገል ቆርጦ አልመጣ- እንዲያው ከባሕር ማዶ መፎከር ብቻ ፋይዳው ኢምንት ነው።
ገና ጥንት ጧት ዘፋኙ ታምራት ሞላ  (ነብሱን ይማረውና)፣ የሚሰማው አጣ እንጂ፣ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡-
“ፈረንጅ አገር ሄዶ፣ ተምሮ ሲመጣ
ትምህርቱን ሳይሰጠን፣ ነቀፌታው ጣጣ!
በወላጁ ዛተ ባገሩ ተረተ
ቢማር ተሳሳተ!”
ይሄ እንግዲህ ያውም በአብዛኛው የአንድ ዓመት ስኮላርሺፕ፣ ወደ አሜሪካ እየሄዱ የሚመጡ ተማሪዎች በነበሩ ሰዓት ነው!


Read 1351 times