Saturday, 30 July 2022 14:33

“ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ”

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(1 Vote)

   (ለዉጥ፣ ትዝታ፣ ምንምነት፣ ሞት …)
                            
            ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ (2012) በእሱባለዉ አበራ የተጻፈ ረዥም ልብወለድ ነዉ፡፡ ይኸ ሥራ እሱባለዉ በሳል ደራሲ (professional novelist) መሆኑን በተጨባጭ ያሳየበት ግሩም የፈጠራ ሥራ ነዉ፡፡ ደራሲዉ በዚህ ሥራ የተለያዩ የአጻጻፍ ቴክኒኮችን ማለትም ሕፅናዊነት (ይኸን የአማርኛ ቃል ያስተዋወቀዉ አዳም ረታ ነዉ) እና ትይዩ (parallel) (ይኸን የአጻጻፍ ቴክኒክ አዳም ረታ ሕማማትና በገና በተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች መድበሉ ዉስጥ በቀረበዉ ትይዩ በተሰኘ የአጭር ልብወለድ ሥራዉ ዉስጥ ከእሱባለዉ ቀደም ብሎ ሥራ ላይ አዉሎታል) ተግባራዊ አድርጓል። ሕፅናዊነት (intertextuality) ከድህረ ዘመናዊ የአጻጻፍ ይትባህሎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡  የሕፅናዊነት አጻጻፍ መገለጫ ቴክኒክ ቀድመዉ የተሠሩ የጥበብ ሥራዎችን በድርሰት ሥራ ዉስጥ መገልገል ነዉ (ካርተር፣ 2006፤ ኒኮል 2009)። የእሱባለዉ የምናብ ምርቶች የተንተራሷቸዉ የሌሎች ከያኒያን ነባር የጥበብ ሥራዎች (texts) ብዙ ናቸዉ፡፡ የገብረክርስቶስ ደስታ፣ የጸጋዬ ገብረመድኅን፣ የደበበ ሰይፉ፣ የቪንሰንት ቫን ጎ፣ የግርማ በየነ፣ የማሕሙድ አህመድ … ወዘተ ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ለዉጥን (flux) እና ትዝታን (reminiscence) ማዕከላዊ ጭብጥ አድርጎ በጥልቀት የፈከረ ግሩም ሥራ ነዉ፡፡ ልብወለዱ ከለዉጥ እና ትዝታ በተጨማሪ ዐቢይ የሜታፊዚክስ እና የግብረ ገብ ፍልስፍናዎችን (በሥነ ጽሑፍ እና በፍልስፍና መካከል ያለዉ መስመር ቀጭን ነዉና) ኀልዮን (existence)፣ ምንምነትን (nothingness)፣ ሞትን (death) እና ነፃ ፈቃድን (free will) እና ወሳኛዊነትን (determinism) የዳሰሰ ሥራ ነዉ፡፡
፩. ለዉጥ
በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ በእዚህ ተለዋጭ ፅንፈ-ዓለም (spaciotemporal world) ፀንቶ የሚዘልቅ ነገር የለም፣ ፍቅርም ቢሆን፣ ጓደኝነትም ቢሆን፣ ዉበትም ቢሆን (እሱባለዉ፣ 2012፡ ገጽ 109፤ ገጽ 124)፡፡ ምለዓተ-ዓለሙ ዉስጥ ያለ ነገር በጅምላ የለዉጥ ተገዥ ነዉ፡፡ ፍቅርም በወረት ይረታል፣ ወዳጅነትም ይቀዘቅዛል፣ ዉበትም እንደ ጧት ጤዛ አመሻሽ ላይ የሚረግፍ ነዉ፡፡ የነገሮች በለዉጥ ቀመር ማለፍ ሊለፈፍ የሚገባዉ የረቀቀ እዉነት አይደለም፣ ለፋፊ ጠቢብ የማያሻዉ ፀሐይ የሞቀዉ አገር ያወቀዉ ተፈጥሯዊ ድንጋጌ ነዉ፡፡ ደራሲዉ ይኸን ነባር እዉነት ቀረብ ብለን እንድንፈትሽ ነፍሳችንን የኮረኮረበት መንገድ ግን ቱባ ነዉ፡፡ ቀጥሎ የቀረበዉ የዋናዉ ገጸባሕርይ ‘ገ’ እናት - ‘ር’፣  የዋናዋ ገጸባሕርይ ‘ዲ’ እናትና የ‘ዘ’ ሚስት- ‘ሰ’ እና የ‘ሰ’ ባልና የ‘ዲ’ አባት- ‘ዘ’ታሪክ ደራሲዉ ለዉጥን የተነተነበት ሐተታ ነዉ፦  
የተደፈርኩት ተወልጄ ባደግኩበት ቀዬ ነዉ። ማን ማን እንደሆኑ አዉቃለሁ፡፡ ሰባት የአገሬና የወንዜ ልጆች ናቸዉ፡፡ አብረን እየተጫወትን፣ ከብት እያገድን በጋራ አድገናል፡፡ ከአንድ ምንጭ ጠጥተናል፡፡ ልጆች ሳለን እንደ ወንድምና እኅት ነበርን፡፡ ከክፉ ነገር ጠብቀዉኛል፡፡ ሳለቅስ አባብለዉኛል፡፡ ስከፋ አስቀዉኛል፡፡ ከወደቅኩበት አንሥተዉኛል፡፡ ሁሉ ነገር እንዴት ይቀየራል? ትዝታችንን መካድ እንችላለን? ስናድግ አንዳችን ለአንዳችን ባዕድ እንሆናለን? እንዲተዉኝ የለመንኳቸዉ ስማቸዉን እየጠራሁ አይደለ? የማዉቀውን ሰዉ እንጂ የባዕድን ስም ከየት አመጣለሁ? በድንቁርና ታዉረዉ ባይገባቸዉም የደፈሩት እኅታቸዉን ነዉ፡፡ የተደፈርኩት በወንድሞቼ ነዉ፡፡ በማይደገመዉ ሕይወት ዉስጥ የተደፈረች ሴት ሆኜ እንዳልፍ ከጀርባዬ መክረዉብኛል (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 77-78)፡፡
‘ሰ’ እባላለሁ፡፡ የ‘ዲ’ እናትና የ‘ዘ’ ባለቤት ነኝ። በአሁን ሰዓት ትዳሬ እየፈረሰ ነዉ፡፡ በከባድ ጊዜና ስሜት ዉስጥ እያለፍኩ ነዉ፡፡ በአንድ ጣሪያ ሥር እየኖርን ቁርጡን አልተነጋገርንም። የሚያመዉ ‘ያ’ ነዉ፡፡ የምንለያይበት ቦታ ላይ እንደ ደረስን እኔም እርሱም እናዉቃለን፡፡ ‘ቻዉ ቻዉ’ ለመባባል ግን ተፈራርተናል፡፡ በአንድ አልጋ ላይ የምንተኛዉ በዕንጨት መነካት እንደ ሌለበት ቁስል አንዳችን ከአንዳችን ተራርቀን ነዉ፡፡ ሌላ ሴት ጋር ሄዷል፡፡ ጠልቶኛል። እስከ አሁን በአፉ አላለዉም፡፡ ድርጊቱ ግን ገላዬ ብቻ ሳይሆን ከገላዬ የሚወጣዉ ድምፄም እንዳረጀበት ከነገረኝ ቆይቷል፡፡ እንደ ድሮ ቀናቶቼ እንዴት እንዳለፉ አይጠይቀኝም፡፡ ከነጉድለቱ ላወራዉ ስሞክር አልችልም፡፡ ቀና መልስ አይሰጠኝም፡፡ ከባድ ቀን አሳልፎ ይሆናል ብዬ ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ ግን ከሌላ ሰዉ ጋር እንደ ልጀ ሲስቅ ሲጫወት አየዋለሁ፡፡ ቆይ ይህን ያህል ምን አድርጌዋለሁ? በመካከላችን ያለዉ ገደል በግልጽ እየሰፋ ነዉ፡፡ መጨረሻችን እንዳይከፋ በተቻለ መጠን እንድንነጋገር መንገድ እከፍትለታለሁ፡፡ የሚዘጋበት መንገድ አያጣም። ስለነበረን ትናንት ብዬ አለቅሳለሁ፡፡ የእንባ ብዛት ግን ያዘመመ ትዳራችንን ከመፍረስ አይመልሰዉም (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 97-98)፡፡
‘ዘ’ እባላለሁ፡፡ የ‘ሰ’ ባልና የ‘ዲ’ አባት ነኝ። ለትዳሬ መፍረስ ተጠያቂዉ እኔ ነኝ፡፡ ይህን የምለዉ እየኮራሁም እያፈርኩም አይደለም። በርግጥ አዝናለሁ፡፡ ማለት ከድርጊቴ ይልቅ በዝምታዬ የቆሰለችዉ ቁስል ክፉኛ እንዳደማት ይገባኛል፡፡ ልቤ ቢቆርጥም በአፌ የደረስኩበትን ዉሳኔ ለመናገር ጊዜ ወስጃለሁ፡፡ ሳልሞክር ቀርቼ አይደለም፡፡ ‘እ… ’ እልና ግራ ተጋብቼ የጀመርኩትን ‘እእ’ታ ለመጨረስ ከእራሴ ጋር እታገላለሁ፡፡ የዉድቀቴን ታሪክ ከምን መጀመር እንዳለብኝ አላዉቅም፡፡ ነገር ግን ‘ሰ’ን ተራርቀን በነበረ ጊዜ ይበልጥ እወዳት እንደ ነበር አስታዉሳለሁ፡፡ ሳላዉቃት አፈቅራት ነበር፡፡ አይገርምም? በክንዴ ሳትገባ ትናፍቀኝ ነበር፡፡ ድምፇ ብርቄ ሳለ ልሰማት እጓጓ ነበር፡፡ እያወራሁት ያለሁት ስለመርታትና ስለመረታት አይደለም፡፡ አሁን ተቀራርበናል።ተጠጋግተናል። በአንድ ጣሪያ ሥር አድረናል፡፡ እጅግ በጣም ተላምደናል፡፡ ለገላዋ አዲስ አይደለሁም፡፡ ዉሎዋ እንዴት እንዳለፈ አዉቃለሁ፡፡ ከማን ጋር ምሳ እንደበላች፣ እነርሱ መሥሪያ ቤት ማን ወረኛ፣ ማን ጉረኛ፣ ማን ጅል፣ ማን ሰቆንቋና እንደሆነ አዉቃለሁ፡፡ የማልጠይቃትም ለዚያ ነዉ፡፡ ማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቀራረብን ቁጥር ስንራራቅ ይታየኛል፡፡ በፊት የነበረዉ የፍቅር እሳት አሁን በርዷል፡፡ እወዳታለሁ። ግን ዛሬም እርሷን ስለማፍቀሬ በልቤ እጠራጠራለሁ። ያረጀብኝ ገላዋ ሳይሆን እኔ ለእሷ ያለኝ ፍቅር ነዉ፡፡ መምኝ  መሰልቸት በዉስጤ እንደ ጉድ ይናጣል፡፡ ከዚያ መሰልቸት ዉስጥ እንደ እርጎ የሚወጣኝ ወፍራም ድብርት ብቻ ነዉ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 103-104)፡፡
ደራሲዉ እንደነገረን፣ ‘ዘ’ የተሰኘዉ ገጸ ባሕርይ የትዳር አጋሩንና የሴት ልጁን የ‘ዲ’ን እናት ‘ሰ’ን ሰልችቶ ጀርባዉን ሊሰጣት የበቃዉ ግለኝነቷን ሰዉታ ራሷን አሳልፋ በመስጠቷ ምክንያት ነዉ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 117)፡፡ ግለኝነት (egoism) በደራሲዉ የሚቀነቀን ሰናይ ምግባር (virtue) ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ፣ መስዋእትነት በደራሲዉ የተኮነነ እኩይ ተግባር (vice) ነዉ፡፡ የእሱባለዉ የግብረ ግብ ፍልስፍና እንደሚሰብከን፣ ከፍቅር አጋራችን ጋር እስከ ሞት አጣብቆ የሚያዘልቀን መግነጢስ ግለ አምልኮ ነዉ፡፡ ደራሲዉ ይኸን አቋሙን ያቀረበበት መንገድ አመክኖአዊና አሳማኝ (logically coherent and consistent) ነዉ፡፡ ከደራሲዉ ሐተታ ዉስጥ የሚከተሉትን ጥቂት መስመሮች እንመልከት፦
… አንድን ሰዉ በሰብእናዉ ብርሃናዊነት በጣም ልትወጂዉ እንደምትችይ ሲገባሽ ያኔ መፍራት አለብሽ፡፡ ህልዉናሽ ራስሽን በማፍቀር ላይ ሳይሆን ሌላን ሰዉ በፍጹም ልብ ከመዉደድ ከተነሳ አደገኛ ነዉ፡፡ አየሽ… ቢያጠፋም ብርሃን–ብርሃን ነዉ፡፡ አምርረሽ መጥላት አትችይም፡፡ ካለ እርሱ ሕይወትሽ ጨለማ እንደሆነ እንዲሰማሽ የማድረግ ትልቅ አቅም አለዉ፡፡ ሂሂሂ… ብርሃንን መጥላት መቼ የዋዛ ሆኖ? እንደማፍቀሩ አይቀልም፡፡ ከባድ ሥራ ነዉ፡፡ ልብሽን ከመክፈትሽ በፊት ቅድሚያ ራስሽን ማፍቀር መማር አለብሽ፡፡ ያለበለዚያ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ ሆነሽ ቁጭ ነዉ፡፡ ሲበድሉሽ ለራስሽ አትቆሚም፡፡ ‘እሺ’ እንጂ ‘አይ’ አትዪም፡፡ ምርጫዎችሽና ሕልሞችሽ ይጨልማሉ፡፡ ብርሃንን ስለተጠጋሽ ብርሃንን አትሆኚም፡፡ በሌላ ሰዉ ማንነት አትደምቂም፡፡ የራስሽን ጌጥነት መፈለግ አለብሽ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 117)፡፡
፪. ትዝታ
ትዝታ ለዉጥን ተከትሎ የሚመጣ ግለ ታሪክ ነዉ፡፡ ይኸ ትዝታ የሚወለደዉ ከቁስ (inanimate objects) እና ከሌሎች ሰዎች (other self-consciousness beings) ጋር ካለን ጥብቅ ቁርኝት ነዉ፡፡ እሱባለዉ እንደሚነግርን፣ ትዝታ ትንሳኤዉ ዉስብስብ ነዉ፣ የትኛዉም ተራ ኩነት ትዝታን ሊከስት ይችላል፡፡ ታዲያ ይኸ ትዝታ ግለሰቦች ኩነቶችን የተረጎሙበትን ዉስብስብ መንገድ መሠረት ያደረገ በመሆኑ አሉታዊ ወይም አወንታዊ ገጠመኝ ሊሆን ይችላል፤ ኩነቶች በራሳቸዉ አልቦ እሴት (value nutral) ናቸዉና፡፡ ለኩነቶች ያለን ሥነ ልቡናዊ አተያይና ግብረ መልስ በከፊል አንፃራዊ ወይም ግላዊ ነዉ፡፡ እሱባለዉ እንደሚከተለዉ ጽፏል፦   ኸኸሀ   
ማንን በምን እናስታዉሳለን? የእንቅስቃሴዎች፣ የጠረኖች፣ የቀለማቶች፣ የድምፆች፣ የግዑዛን ቅርጾች ዉልብታ ጣፋጭ ወይም መራራ ትዝታን ይቀሰቅስብናል፡፡ ትዝታ ከየት እንደሚነሳ በዉል እንደማናዉቀዉ ነፋስ ነዉ፡፡ ሲደርስብን እንደ ስጥ እንበተናለን፣ እንተራመሳለን፣ እንረበሻለን፡፡ ለትዝታዎቻችን ያለን ስሜት እንደምናስታዉሰዉ ነገር ይወሰናል፡፡ ምናልባት እንፈግጋለን፣ እንኳሻለን፣ እንተክዛለን፣ እንናፍቃለን፣ እናለቅሳለን፣ እንቆጣለን፣ እንመረራለን፡፡ ያማረ ትላንት ለሌለዉ ሰዉ ትዝታ ምንድር ነዉ? የሚያጥወለዉል፣ እንቅልፍ የሚያሳጣ፣ ልብን የሚያከብድ፣ ኀዘን ላይ የሚጥል በሽታ አይደለምን? (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 13-14)፡፡
፫.  ኀልዮ
እሱባለዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ በስዉር (implicitly) እንደሚነግረን ኀልዮ (existence) ከሞት (death) አይሻልም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሰዉ በመኖር የሚያተርፈዉ አንዳች ቁም ነገር (ultimate goal or end) የለም፤ መኖር እንደ ሞት ሁሉ ግብ አልባ ጉዞ ነዉ። ይኸ የእሱባለዉ ፍልስፍና የሚግተን መራር እዉነት አስደንጋጭ ነዉ፣ ግን ደግሞ ፈፅሞ የማንሸሸዉ። የልብወለዱ ዋና ገጸባሕርይ ‘ገ’፣ ከዚህ መራር ሐቅ ጋር ፊት ለፊት በመላተሙ ምክንያት ነዉ ገና በወጣትነቱ የመሞት ፅኑ ፍላጎት በዉስጡ የተቀሰቀሰዉ፣ ሕይወት ከሞት የሚልቅ ዐቢይ ፋይዳ እንደሌለዉ በመገንዘቡ፡፡ እሱባለዉ እንዲህ ጽፏል፦ “ከተወለድኩበት ቀን አንስቶ በተሳሳተ ዓለም እንደ ተፈጠርኩ ይሰማኝ ነበር፡፡ የልጅነት ሕልሜ በወጣትነት መሞት ነበር”  (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 50)፡፡
፬. ምንምነት
ምንምነት የሰዉ ልጅ ቋሚ ተፈጥሮ ወይም ማንነት (enduring essence or identity) የለዉም (ፈጣሪ በህልዉና ባለመኖሩ ምክንያት) የሚል መልእክት ያለዉ የታዋቂዉ ኤግዚስቴንሻሊስት ፈላስፋ ዣን-ፖል ሳርተር ፌኖሜኖሎጂካል ኦንቶሎጅ ነዉ (ሳርተር፣ 1956፤ ካታላኖ፣ 1996፡ ገጽ 113)፡፡ የሰዉ ልጅ አብሮት የሚወለድ ቋሚ ተፈጥሮ ወይም ማንነት ከሌለዉ (lack of identity of consciousness with itself) ፍፁማዊ የሆነ የግብረ ገብ እሴት ሚዛንም (objective criterion of moral value) ሆነ ተፈጥሮአዊ የሆነ የህልዉና ትርጉም (inherent life meaning) የለም። የሕይወትን ትርጉም የምንፈጥረዉ እኛ እያንዳንዳችን ነን፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የሕይወትን ትርጉም የምንደርሰዉ እኛ እያንዳንዳችን ነን፡፡ ሕይወት በራሱ ትርጉም አልባ ነዉና። ወርቅ በራሱ ከድንጋይ የከበረ ተፈጥሮ ይዞ ወደ ኑባሬ አልመጣም፡፡ ወርቅ ከድንጋይ እንዲከብር ያደረገዉ የሰዉ ልጅ እሴት ነዉ፡፡ ሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም  (Existentalism Is a Humanism) በተሰኘ ታዋቂ ሥራዉ እንዲህ ጽፏል፦
In response, 1can say that I very much regret it should be so, but if I have eliminated God the Father, there has to be someone to invent values. Things must be accepted as they are. What is more, to say that we invent values means neither more nor less than this: life has no meaning a priori. Life itself is nothing until it is lived, it is we who give it meaning, and value is nothing more than the meaning that we give it (Sartre, 2007:51).  
በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ  እሱባለዉ የህልዉና ትርጉምን አስመልክቶ ሐተታዉን ያቀረበዉ እንደሚከተለዉ ነዉ፣
ሰዎች በሚያነቡት ምንባብ፣ በሚያዩት ቅርጽ፣ በሚያደምጡት ድምፀት ዉስጥ የማያቋርጥ የትርጉም ኀሰሳን ያደርጋሉ፡፡ ምክንያታዊትን ይጠይቃሉ፡፡ ሕይወት ላይ ግን ‘ለምን እንዲህ ሆነ? ለምን እንዲያ አልሆነም?’ ብለን መጠየቅ አንችልም፡፡ ከአልተመለሱልን ጥያቄዎች ጋር እንጓዛለን፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ የያዝነዉ ሕይወት እንጂ ተዉኔት አይደለም። የተሰጠን ቃለ ተዉኔት የለም፡፡ ወደዚህ ምድር ስንመጣ የሕይወትን ትርጉም የያዘ ክታብ በአንገታችን አሥረን አልተወለድንም (እሱባለዉ፣ 2012፡ ገጽ 25)፡፡  
፭. ሞት
ለእሱባለዉ፣ ሞት ዉሉ ያልተፈታ ምስጢር ነዉ፣ ይኸን እንቆቅልሽ አስመልክቶ ያለን ግንዛቤ (ኃይማኖቶች የሚያቀርቡትን ሀተታ ጨምሮ) አጥጋቢ አይደለም፡፡ ከሞት በኋላ የሰዉ ልጅ ነፍስ ዘላለማዊ ይሁን አይሁን በተጨባጭ ማስረጃ አልተረጋገጠም (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 7)። ይኸ የእሱባለዉ ሜታፊዚካዊ የነፍስ ፍካሬ (metaphysical analysis of the soul) የቁስ አካላዉያንን አተያይ የሚጋራ ነዉ፡፡ እሱባለዉ የሚከተለዉን ጽፏል፦
ከሞት በኋላ ያለዉን አጽናፍ አናዉቅም፡፡ እንዴት ያለ ነዉ? ምን አለ? ምንስ የለም? ሰዎች ስለሞት የጠረቁት ተስፋ ያደረጉትን ነገር እንጂ ያዩትን እዉነት አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ የሞት ፊቱ በዉል አይታወቅም፡፡ ከሕይወት በላይ ምሥጢራዊ ነዉ፡፡ እኛ ግን በሕይወትና በሞት መካከል ስለተዘረጋዉ ቀጭን ክር እንተርካለን፡፡ እንመላለሳለንም (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 7)፡፡
፮. ነፃ ፈቃድ እና ወሳኛዊነት
የሰዉ ልጅ ነፃ ፈቃድ አለዉ ወይስ የለዉም? የሚለዉ ሜታፊዚካዊ ጥያቄ የነፃ ፈቃድ እና የወሳኛዊነት አስተምህሮ አቀንቃኝ ፈላስፎችን ሁለት ጎራ ከፍሎ ከጥንት አንስቶ እስከ ዛሬዉ ዘመን ድረስ እንዳሟገተ የዘለቀ ዐቢይ የፍልስፍና ርእሰ ጉዳይ ነዉ፡፡  እንደ ታዋቂዉ የወሳኛዊነት ዐቢይ አቀንቃኝ ፈላስፋ ሄነሪ ደ’ ሆልባች እሳቤ፣ ዓለሙ ዉስጥ የሚከናወኑ ኩነቶች በሙሉ የምክንያትና ዉጤት ተፈጥሯዊ መርህ ተገዥ ናቸዉ፣ በመሆኑም ነፃ ፈቃድ ቅዠት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ምለዓተ-ዓለሙ ዉስጥ የሚካሄድ ነገር ሁሉ (የሰዉን ልጅ ተግባር ጨምሮ) በተፈጥሮ ሕግ የተወሰነ ነዉ፡፡ ታዋቂዉ የነፃ ፈቃድ ጠበቃ ፈረንሳዊዉ ፈላስፋ ዣን-ፖል ሳርተር እንደሚነግረን ደግሞ የሰዉ ልጅ ፍፁማዊ አርነትን የተጎናፀፈ ፍጡር ነዉ። ለሳርተር፣ ወሳኛዊነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም በተሰኘ ሥራዉ የሚከተለዉን ብሏል፦
For if it is true that existence precedes essence, we can never explain our actions by reference to a given and immutable human nature. In other words, there is no determinism-man is free, man is freedom. If, however, God does not exist, we will encounter no values or orders that can legitimize our conduct. Thus, we have neither behind us, nor before us, in the luminous realm of values, any means of justification or excuse. We are left alone and without excuse. That is what I mean when I say that man is condemned to be free: condemned, because he did not create himself, yet nonetheless free, because once cast into the world, he is responsible for everything he does. Existentialists do not believe in the power of passion. They will never regard a great passioil as a devastating torrent that inevitably conmpels man to commit certain acts and which, therefore, is an excuse. They think that man is responsible for his own passion (Sartre, 2007: 29).
እንደ ኢ-አማኙ ሳርተር እሳቤ፣ ፈጣሪ ቀድሞ ያበጀልን ቋሚ ማንንት ባለመኖሩ (ለሳርተር ፈጣሪ በህልዉና እንደሌለ ያስታዉሱ) ምክንያት የሰዉ ልጅ ነፃ እንዲሆን ተረግሟል፡፡ ፈጣሪ ከሌለ የዕጣ ፈንታችን ተላሚነት ኃላፊነቱ የገዛ ጫንቃችን ላይ የወደቀ ይሆናል፡፡ ሳርተር ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስ በተሰኘ ሥራዉ የሚከተለዉን ጽፏል፦
… man being condemned to be free carries the weight of the whole world on his shoulders; he is responsible for the world and for himself as a way of being. We are taking the word ‘responsibility’ in its ordinary sense as ‘consciousness (of) being the incontestable author of an event or of an object.’ In this sense the responsibility of the for-itself is overwhelming since he is the one by whom it happens that there is a world; since he is also the one who makes himself be, then whatever may be the situation in which he finds himself, the for-itself must wholly assume this situation with its peculiar coefficient of adversity, even though it be insupportable. He must assume the situation with the proud consciousness of being the author of it, for the very worst disadvantages or the worst threats which can endanger my person have meaning only in and through my project; and it is on the ground of the engagement which I am that they appear (Sartre, 1956: 553–554).       
Human-reality is free because it is not enough. It is free because it is perpetually wrenched away from itself and because it has been separated by a nothingness from what it is and from what it will be. It is free, finally, because its present being is itself a nothingness in the form of the “reflection-reflecting.” Man is free because he is not himself but presence to himself. The being which is what it is can not be free. Freedom is precisely the nothingness which is made-to-be at the heart of man and which forces human–reality to make itself instead of to be. As we have seen, for human reality, to be is to choose oneself; nothing comes to it either from the outside or from within which it can receive or accept. Without any help whatsoever, it is entirely abandoned to the intolerable necessity of making itself be–down to the slightest detail (Sartre, 1956:440-441).
እሱባለዉ በበኩሉ ነፃ ፈቃድ ትርክት (illusion) ነዉ ይለናል፡፡ እንደ እሱባለዉ እሳቤ፣ እያንዳንዳችን የሌሎች ዉጫዊ አካላት ስሪት ነን፡፡ እሱባለዉ እንደሚከተለዉ ጽፏል፦
አንዳንዶች ከምግባረ እኩይነት ጋር ሌሎች ደግሞ ከሠናይነት ጋር ይወለዳሉ? ክፋትና ደግነት እንደ ነፍስ ይከፈላሉ? ታዲያ በመሐል የ ‘ነጻ ፈቃድ’ ነገር ወደ የት ይወድቃል? ለመልካምነት ወይም ለክፉነት ተላልፈን የተሰጠን ባሪያዎች ብንሆን ለድርጊታችን በምን ሒሳብ ኃላፊነትን እንወስዳለን? በእኛ ገላ ክፉና ደግ የሚሆነዉ በዉስጣችን ያለዉ ሌላ ባዕድ ‘እኛ’ ከሆነ… እኮ ማን ማንን ይኮንናል? ያወድሳልስ? በተፈጥሮዉ ክፉም ጥሩም የሚባል ሰዉ አለን? የምንበላሸዉ በገዛ ፈቃዳችንና ዙሪያችንን በከበበዉ የሰዎች ጥላ ጭምር አይደለምን? አሁን በያዝነዉ ባሕርይ ላይ ያዋጡ ሰዎች እልፍ ናቸዉ፡፡ ልቡና ‘የነገሮች’ ስብስብ ነዉ፡፡ የሕይወት ልምምድ በደግም በክፉም ይቀርጸናል (እሱባለዉ፣ 2012፡ ገጽ 59)፡፡
እንደ አጠቃላይ፣ እሱባለዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ የዳሰሳቸዉን ዐቢይ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳዮች ዋቢ በማድረግ የፈጠራ ሥራዉን ፍልስፍናዊ ልብወለድ ብሎ መፈረጅ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን የፈጠራ ሥራዉ ደረቅ ፍልስፍናዊ ስብከት ወይም ሐተታ ነዉ ማለት አይደለም፡፡ ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ነባር ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳዮች ኪነታዊ በሆነ መንገድ በአዲስ አተያይ (original interpretation) የቀረቡበት፣ የሥነ-ዉበት ይዘቱ (aesthetic content) የሠመረ አርኪ ሥራ ነዉ፡፡


Read 1136 times