Saturday, 30 July 2022 13:54

ልጅ አለመውለድ አለም አቀፍ ችግር ነው፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  በአለም አቀፍ ደረጃ ልጅ አለመውለድ ወደ 15% ለሚሆኑ ጥንዶች ወይንም 48.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ የትዳር አጋሮች ችግር ነው፡፡
‹‹….እግዚአብሔር ይመስገን የመካንነት ሕክምና ወደሀገራችን በመምጣቱ ልጄ የልጅ አባት ሆነልኝ….›› ያሉን አንድ አባት ናቸው፡፡ እኝህን አባት ያገኘናቸው በኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር ነው፡፡ ኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር የሚገኘው በሐምሊን ፊስቱላ አካብቢ ነው፡፡ ኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር የተሰኘው ክሊኒክ የመካንነት ሕክምና የሚሰጥበት ክሊኒክ ነው፡፡ ታካሚዎች ወደ ሐኪማቸው እስኪቀርቡ ድረስ ያለው መቆያ በመልካም የሶፋ ወንበሮች በጥሩ አቀማመጥ የተዋበ ስለሆነ ለህክምና የሚመጡ ሰዎች የሚያርፉበት አይመስልም። ለመዝናናት እንጂ፡፡ በእርግጥም ወደ ውስጥ ሲገቡ በቤቱ ውስጥ አንድም ሰው ያለ አይመስልም፡፡ በተረፈ ታካሚዎች ጥንድ ጥንድ ሆነው በእርጋታ ተቀምጠዋል። ፎቶግራፋቸውን የምትመለከቷቸውን ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽን ስናጠያይቅ በዚያውም ታካሚዎችን እየቃኘን ነበር፡፡
አንድ አባትና ጥንዶችን ያገኘነው፡፡ ልጃቸው ትዳር ከያዘ ወደ አራት እስኪሆነው ድረስ  ቢጠብቁ እርግዝና የለም፡፡ እሳቸው የሚኖሩት በእስራኤል እሱ በካናዳ ሚስትየው በአዲስ አበባ ነው፡፡ በሁዋላም አባትየው ከመጨነቃቸው ብዛት መረጃ ሲያሰባስቡ በኢትዮጵያ ሕክምናው መጀመሩን ሰሙ፡፡ ለልጃቸውም መረጃውን በመስጠት ወደ አዲስ አበባ እንዲገናኙ ቀጠሮ ያዙና ህክምናው በሚገኝበት ቦታ ቀረቡ፡፡ ልጅ ያለመውለድ ችግሩ ከወንድ ልጃቸው ስለነበር በዶ/ር ሙስጠፋ አማካኘነት ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት በላቦራቶሪ እገዛ ልጅ እንዲወልዱ ተደረገ፡፡ እነሆ ዛሬ የአንድ አመት ከሰባት ወር ወንድ ልጅ አባትና እናት ሆነዋል፡፡ አሁን በክሊኒኩ ያገኘናቸው ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ፈልገው ነው፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው እንደዚህ ያለ ክትትልና እርምጃ ሲወስዱ ማየት በጣም ያስደስታል፡፡ ቀደም ባለው ዘመን ቢሆን በአብዛኛው ቤተሰቦች ወይንም ጉዋደኞች ሴትዋ ናት መሃን በማለት ለማፋታት ጥረት ማድረግ ወይንም ወንድየው ከሌላ ሴት ልጅ ለመውለድ እንዲሞክር እና እቤት ያለችው እንድታሳድግ የመሳሰለ እርምጃ ነበር ሲወሰድ የሚታየው፡፡ ዛሬ ግን ሕክምናውም መጥቶአል፡፡ ቤተሰቦችም ተለውጠዋል ማለት ይቻላል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ መካንነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለዚህም መንስኤ ከሚሆኑ ነገሮች መካከል በተለያዩ ምክንያት መድሀኒትን መጠቀም ይገኝበታል፡፡ ከዚህ የተነሳም ከ5%-10% በየአመቱ ልጅ የመውለድ ችግር ሲጨምር ይታያል፡፡ እ.ኤ.አ በ1950 በአለም አቀፍ ደረጃ አንዲት ሴት 5/ልጅ ትወልዳለች ተብሎ የሚገመትበት እንደነበር የተባበሩት መንግስታት መረጃ ያሳያል፡፡
በኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር ተገኝተን መካንነትን አስወግዶ ጥንዶችን የልጅ እናትና አባት የማድረግ ተግባርን በሚመለከት ያነጋገርነው ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ የጽንስና ማህጸን እና የመካነት ሕክምና እስፔሻሊስትን ነው፡፡ ዶ/ር ሙስጠፋ እንደተናገሩት የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት ከሆኑ ጀምሮ የብዙ ጥንዶች ልጅ ያለማፍራት ጉዳይ በጣም ልባቸውን ይነካው የነበረ ሲሆን ቀላል የማይባሉ ታካሚዎችም ወደእሳቸው ጋር ይቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ መካንነት ጥንዶች በማህበራዊም ይሁን በስነልቡና የሚሰቃዩበት ሲሆን ይህ ችግር በምን መንገድ ይፈታል የሚለው ጥያቄ በውስጣቸው አድሮ ነበር፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ይህ የመካንነት ህክምና እንዲሰጥ መነሻ ሀሳብ ሲኖረው ጀምሮ በአደራጅነት ጭምር ከሌሎች የስራ ባልደረቦች ጋር በመሆን አገልግሎቱ እንዲጀምር የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡ ዶ/ር ሙስጠፋና የስራ ባልደረቦቻቸው ያንን ተቋም ለማቋ ቋም ከሰባት አመት ያላነሰ ጊዜ ውጣ ውረዶችን ካሳለፉ በሁዋላም እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2019 የፓውሎስ የመካንነት ክሊኒክ ስራ ጀምሮአል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ምቹ ክሊኒክ በሚል ስም በአዲስ አበባ በ22/አካባቢ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ይህ ክሊኒክ ብቻውን መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ስለማይታመን ሌሎች አማራጭ ክሊኒኮችንም በመክፈት ለመካንነት ሕክምና መስጠት ያስፈልጋል ከሚል ኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር መከፈቱንም ገልጸውልናል፡፡
ዶ/ር ሙስጠፋ ለበርካታ ጥንዶች ልጅ እንዲያቅፉ የበኩላቸውን የጣሩ የህክምና ባለሙያ መሆናቸውን በሳቸው የህክምና ክትትል ልጅ የወለዱ እድለኞች ገልጸውልናል፡፡
‹‹…ያናገርናት እናት በትዳር ላይ ለአራት አመታት ከቆየች በሁዋላ ከባለቤትዋ ጋር ትመካከራለች፡፡ ምን ይሻላል…. ልጅ መውለድ አልቻልንም፡፡ ባይሆን አንተ እንደምንም ልጅ ውለድ እባክህ ስለው …እኛ ኑሮአችንን በፍቅር መግፋት እንችላለን፡፡ የልጅ ጉዳይ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር አይደለም፡፡ ከመጣ ይምጣ" ካልመጣም ለዚህ ነገር መቆጨት የለብንም። እኔ አንችን አፈቅርሻለሁ፡፡ የቀረው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ሌላ ነገር ጣልቃ እያስገባሽ አታስቢ ብሎ ተቆጣኝ፡፡ እሺ ይሁን፡፡ ግን እስቲ እንታከም ስለው እሱን ፈቃደኛ ነኝ በማለቱ ምርመራ ማድረግ ጀመርን። ከዚያም ችግሩ ከእኔ ማህጸን ጋር በተያያዘ ሆኖ ተገኝ። ቀደም ሲል በማህጸኔ ሕመም ይሰማኝ ስለነበር ወደሕክምናው ስሔድ ብዙ እጢዎች ተገኙብኝ፡፡ እነሱን ለማውጣት በተሰራው ስራ ብዙ ጭረት ወይንም ጠባሳ በማህጸኔ ውስጥ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ምክንያትም ልጅ ለማርገዝ አልቻልኩም፡፡ ከዚያም ወደ መካንነት ክሊኒክ ሄድኩ፡፡ በተደረገልኝ ክትትልም ልጅ መውለድ በመቻሌ እነሆ የአስር ወር ልጅ ታቅፌአለሁ። ከእግዚአብሔር በታች ሐኪሜን በጣም አመሰግናለሁ። አሁን ጊዜው ሳይረፍድ ስለሁለተኛው ልጅ እያሰብኩ ነው ነበር ያለችን፡፡
ሌላዋ ያነጋገርናት እማኝ ትዳር በያዘች በአስራ ሁለተኛው አመት ልክ ትዳር በመሰረተችበት ሰኔ ወር ውስጥ ነበር ልጅዋን ያቀፈችው፡፡ ለ11 አመት ያህል በትዳር ስትቆይ ልጅን ብትመኘውም ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡ የማህጸን ቱቦው ዝግ እንደነበረም ገልጻለች፡፡ ለሶስት አመት ያህል ዶ/ር ሙስጠፋ ጋ ቀርባ ተስፋ ሳትቆርጥ ስትከታተል እንደነበር የገለጸች ሲሆን ያ የሆነበትም አንዱ ምክንያት የቅዱስ ጳውሎሱ የመካንነት መከላከያ ክሊኒክ ስራ እስኪጀምር ነበር፡፡ ልክ ክሊኒኩ ስራ ሲጀምር ህክምናዬን ቀጥዬ በላቦራቶሪው አንድ እንቁላል ብቻ እንደተሰራልኝና ወደ ማህጸኔ የሚገባው አንድ እንቁላል መሆኑ ነበር የተነገረኝ፡፡ ይሁን እግዚአብሔርን እለምናለሁ ብዬ በተስፋ በመጠበቄ በእግዚአብሔርና በዶ/ር ሙስጠፋ እርዳታ እነሆ የአንድ አመት ልጄን ታቅፌአለሁ ነበር ያለችን፡፡
ዶ/ር ሙስጠፋ እንደሚሉት በዘርፉ ለህክምና የሚመጡት በርካታ ጥንዶች ናቸው፡፡ ፍላጎትን በየጊዜው ስንመለከተው ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገራችንም ሆነ በብዙ አካባቢዎች መካንነት የሴቶች ችግር ነው ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ነገር ግን የሴቶች ችግር ቢበልጥም የወንዱም የሴትዋም ችግር መሆኑን ለማወቅ በሚገባ መረጃ አለማግኘት በታካሚዎች ዘንድ ይታያል፡፡ መረጃው በትክክል በስፋት ለምን አልተሰራጨም ለሚለው አገልግሎቱን የሚሰጡት ክሊኒኮች በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው ከቅርብም ከሩቅም ለሚመጡ ታካሚዎች እንደልብ አገልግሎቱን ለማዳረስም ስለሚቸግር ይመስለኛል ነበር ያሉን፡፡ ስለዚህም መረጃው ለአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ባለመዳረሱ መካንነት ሊታከምና ሊድን የሚችል መሆኑን የሚያውቁት ጥቂት ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለን መረጃ መሰረት በቀን ከ5-7 የሚሆኑ ጥንዶች የIVF ማለትም እርግዝናውን በላቦራቶሪ እገዛ በማድረግ ማከናወን የሚያስፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ወደሐኪም ይቀርባሉ፡፡ በጳውሎስ ቅርንጫፍ ምቹ ክሊኒክም በየቀኑ ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ ጥንዶች ከ15-20 ይደርሳሉ፡፡ በእርግጥ ቀለል ያለውን ሕክምና የሚያደርጉም ብዙ ናቸው፡፡  ሆኖም ግን አሁንም በክሊኒኩ የቦታ እጥረት፤ የላቦራቶሪ ግብአት እጥረት፤ የሰለጠነ ሰው ኃይል እጥረት ስላለ በዚህም ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆ ኑን ዶ/ር ሙስጠፋ ገልጸዋል፡፡
ያነጋገርናቸው እናቶች እንደገለጹልን ከሆነ በአሁኑ ወቅት የትዳር አጋሮችም ሆኑ ቤተሰቦች ልጅ ባለመወለዱ ምክንያት ምንም ጫና የማያደርጉ እና አይዞሽ በማለት የሚያጽናኑ ናቸው፡፡ ይህ የጊዜውን መለወጥ እና በማይሆን ነገር ትዳርን ከማፍረስ ይልቅ በጋራ መፍትሔ መፈለግ የሚበጅ መሆኑ እንደታመነበት የሚጠቁም ነው፡፡ ዶ/ር ሙስጠፋም በእሳቸው እጅ ብቻ ወደ መቶ ያህል ጥንዶች ልጅ ማግኘታቸወን ገልጸዋል፡፡  
ጥንዶች ልጅ እንዲወልዱ የወንድና የሴት ዘር መኖር አለበት፡፡ የመራቢያ አካል በተለይም የሴትዋ ማህጸን ንጹህ መሆን አለበት፡፡ ማህጸን ላይ እጢ ካለ መወገድ አለበት፡፡ የዘር ፈሳሽ፤ በቱቦው አካባቢ የማይታወቁ ወይንም ባእድ የሆኑ ነገሮች ካሉ መወገድ አለባቸው፡፡ በተፈጥሮ በኩል ያሉ እውክታዎች በሙሉ ጽድት ብለው ነው IVF መሰራት ያለበት ብለዋል ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ፡፡ ይህን ለመስራት ከፍተኛ ወጪ እና ጊዜ፤ የአእምሮ ዝግጁነት፤ ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ ክፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በኢትዮ ፈርቲሊቲ ሴንተር የማህጸንና ዘር ፍሬ ዝግጅት ከተደረገ በሁዋላ አስፈላጊው የላቦራቶሪ ምርመራዎች ሁሉ ተካሂደው ወደ IVF ማለትም ልጅን በላቦራቶሪ ወደማፍራት አገልግሎት ይታለፋል ብለዋል ዶ/ር ሙስጠፋ፡፡ ጽንሱ በላራቦራቶሪ ከተዘጋጀ በሁዋላም ወደ እናቱ ማህጸን በመዛወር እንዲያድግ ይደረጋል እንደ ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እና የመካንነት ሕክምና እስፔሻ ሊስት ማብራሪያ ፡፡

Read 11331 times