Print this page
Saturday, 30 July 2022 14:45

የኢትዮጵያ ቡድን ከዓለም 2ኛ፤ ከአፍሪካ 1ኛ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


                "አትሌቶች ያስመዘገቡት  ታሪካዊ ድል በሃገራችን ሰላምና አንድነት ለማስፈን ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡" -  በርካታ ኢትዮጵያውያን
"ኢትዮጵያ ሁሌ አሸናፊ መሆኗን ያሳያል፤ ላዘኑና ለተከዙ ኢትዮጵያውያን ፈገግታን ያላብሳል" - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
"ኢትዮጵያን አስቀድማችሁ ከፊት ስላቆማችሁን ደስ ብሎናል" - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

          • ኦሬጎን ላይ 4 የወርቅ፤ 4 የብርና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎች
          • በሁሉም የዓለም ሻምፒዮናዎች 33 የወርቅ፤ 34 የብርና 28 የነሐስ በአጠቃላይ 95 ሜዳልያዎች ከዓለም 6ኛው ከፍተኛ ውጤት
          • 3 የዓለም ሪከርዶች፤ 13 የዓለም ሻምፒዮና ክብረወሰኖች ፤ 150 ሺ የስታድዬም ተመልካቾች ፤ 13.7 ሚሊዮን አሜሪካውያን ታዳሚዎች              በኦሬጎን22



            በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ቡድን  በልዩ ልዩ ሽልማቶችና ምስጋናዎች እየተንበሻበሸ ይገኛል፡፡ ቡድኑ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ ሃገር ቤት ሲመለስ  በአየር ማረፊያ ከተደረገለት ልዩ አቀባበል በኋላ በዋና ዋና የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመዘዋወርና  በመስቀል አደባባይ በመገኘት የከተማውን ህዝብ ደማቅ አቀባበልና ደስታ ተጋርቷል። የኢትዮጵያ መንግስት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች አካላት ለኢትዮጵያ ቡድን ልዩ ልዩ ሽልማቶችን እያበረከቱ ናቸው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያስመዘገቡት አዲስና ታሪካዊ ድል በሃገራችን ሰላምና አንድነት ለማስፈን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እየገለፁ ናቸው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በተለይ ከትግራይ የተገኙት አትሌቶች አንፀባራቂ ድል ማስመዝገባቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ስፖርት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አመልክቷል፡፡ አትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ አትሌት ጎይትኦም ገብረ ሥላሴና አትሌት ጎዳፍ ፀጋዬ የኢትዮጵያ ቡድን ከሰበሰባቸው 10 ሜዳልያዎች 3 የወርቅና 1 የብር  በድምሩ አራት  ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡ እነዚህ ጀግና አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ወደነበረበት ክብር እንዲመለስ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብና ብሔራዊ መዝሙራችን እንዲዘመር ማድረጋቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አስደስቷል፡፡  በአስደናቂ የቡድን ስራና ፕሮፌሽናሊዝም  ተምሳሌት ሆኖ የሚጠቀስ ገድል መፈፀማቸውም አኩርቶታል፡፡
ትናንት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ  ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት  ለኢትዮጵያ ቡድን የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና ልዩ የሽልማት መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡትና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ከ50 ሺህ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሽልማትም በየደረጃው ተበርክቷል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የቡድኑን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችውና በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ የተጎናፀፈችው ጉዳፍ ጸጋይ በልዩ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር፤ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውና በ5ሺ ሜትር አስደናቂ የቡድን ስራ በማሳየት አምስተኛ ደረጃ ያገኘችው ለተሰንበት ግደይ 2 ሚሊየን ብር ፤ በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች የወርቅ ሜዳልያ ላስገኙት  ታምራት ቶላና ጎይተቶም ገብረ ሥላሤ   ለእያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 750 ሺሕ ብር  ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሞስነት ገረመው በወንዶች ማራቶን እንዲሁም   ወርቅውሃ ጌታቸውና ለሜቻ ግርማ በ3 ሺሕ መሰናክል በተጎናፀፏቸው የብር ሜዳልያዎች እያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን ብር ተሸልመዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባሰሙት ንግግር አትሌቶች ለአገራቸው ያስገኙት ውጤት ኢትዮጵያ ሁሌ አሸናፊ መሆኗን የሚያሳይ፤ ላዘኑና ለተከዙ ኢትዮጵያውያን ፈገግታን የሚያላብስ ድል ነው ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ “አንድ ሆነን እንስራ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፍ” በሚል መሪ ቃል የምስጋና እና የክብር መስጠት መርሃ-ግብርን ያካሄደው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ነው። የከተማ አስተዳደሩ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ለተመዘገበው አዲስ ታሪክ ለኢትዮጵያ ቡድን  በጥቅሉ የ10 ሚሊዮን ብር  በጥሬ ገንዘብ የሸለመ ሲሆን፤ ለወርቅ ሜዳሊያ  500ካ/ሜ፣ ለብር ሜዳሊያ 350 ካ/ሜ እንዲሁም ለነሃስ ሜዳሊያ  250 ካ/ሜ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አበርክቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስነስርዓቱ ኢትዮጵያ የልጆቿ ገፅ መሆኗን ገልፀው ‹‹በድላችሁ ኢትዮጵያን ገፅታዋን ልታድሱ፥ ክብሯን በድል ልትገልጡ፥ ሰንደቃችሁን አትማችሁ ኢትዮጵያን አስቀድማችሁ ከፊት ስላቆማችሁን ደስ ብሎናል›› ሲሉም ተናግረዋል።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳልያ ሰንጠረዡ ላይ አዘጋጇ አሜሪካ 13 የወርቅ፤  9 የብርና 11 የነሐስ  በአጠቃላይ 33 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው፡፡ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ለመጨረስ የበቃችው ደግሞ 4 የወርቅ፤  4 የብርና 2 የነሐስ  በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ነው፡፡ ጃማይካና ኬንያ  በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎችን በተመሳሳይ ቢያሸንፉም   በሁለቱም ፆታዎች ማራቶንን  እንዲሁም በሴቶች በ10ሺና በ5ሺ ሜትር  ኢትዮጵያበወሰደችው አራት የወርቅ ሜዳልያዎች ከዓለም ሁለተኛውን ደረጃ ያሰጣት ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ አንደኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡  ጃማይካ 2 የወርቅ፤  7 የብርና 1 የነሐስ  በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎች፤ ኬንያ 2 የወርቅ፤  7 የብርና 1 የነሐስ  በአጠቃላይ 10 ሜዳልያዎች እንዲሁም  ቻይና 2 የወርቅ፤  1 የብርና 3 የነሐስ  በአጠቃላይ 6 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ከ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ኢትዮጵያ በምንግዜም ከፍተኛ የሜዳልያ ውጤት ከነበረችበት ሰባተኛ ደረጃ ወደ ስድስተኛ ከፍ ያለች ሲሆን፤ በተሳተፈችባቸው 16 ሻምፒዮናዎች 33 የወርቅ፤ 34 የብርና 28 የነሐስ   በአጠቃላይ  95 ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው 179 አገራትን የወከሉ ከ1700 በላይ አትሌቶችን ተሳትፈዋል፡፡  40 አገራት አንድና ከዚያም በላይ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ 29 አገራት የወርቅ ሜዳልያ ድል በማስመዝገባቸው በሻምፒዮናው ታሪክ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተፅፏል፡፡ በ2017 እኤአ ላይ  27 አገራት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኙበትን ታሪክ በማሻሻል ነው፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ሻምፒዮናው 3 የዓለም ሪከርዶች እንዲሁም  13 የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች የተገኙበትና  30 የዓመቱ ምርጥ የአትሌቲክስ ውጤቶች ስለተመዘገቡበት ስኬታማ እንደነበርም ተወስቷል፡፡
ኦሬጎን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሄይዋርድ ፊልድ   ለ10 ቀናት የተካሄዱትን የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች   ከ150 ሺ በላይ ተመልካቾች  ስታድዬም በመገኘት ተከታትለዋል፡፡ የዓለም አትሌቲከስ በአሜሪካ ኤንቢሲ ቲቪ ባገኘው ስርጭት ከ13.7 ሚሊዮን በላይ ታዳሚ ማግኘቱ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ እንደሆነም ታውቋል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሚጠቀምባቸው የሶሻል ሚዲያ አውታሮች ከ400 ሺ በላይ ተከታታዮችን ያገኘበት ደረጃ ላይ ሲደርስ፤ ከ7 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ሻምፒዮናውን በተለያየ መንገድ እንደታደሙ፤  ከ9.1 ሚሊዮን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች የዓለም አትሌቲክስ ማህበርን ዲጂታል ቻናሎችን እንደተጠቀሙና የዓለም ሻምፒዮናው ቪድዮች ከ41 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 11163 times