Saturday, 30 July 2022 14:57

ሻንጣው!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

  ድሮ አስረኛ ክፍል ሳለን ነፍሰ ቀጭኑ የኬሚስትሪ መምህራችን እንዲህ ሲሉ ጠየቁን:-
“ውሃ ከምን እና ከምን ንጥረ ነገሮች ነው የተፈጠረው?” ብዙ ተማሪዎች ይህችን ቀላል ጥያቄ ለመመለስ ተቅለበለብን። መምህሩ ግን  ከሁሉም ተማሪ ይልቅ ትኩረታቸውን  ቦጋለ ላይ አድርገው እንዲመልስ አስገደዱት።
ቦጋለ ከእንቅልፉ የተነሳ ይመስል አይኑን አሻሽቶ ትንሽ ቆየና መምህሩ ጥያቄውን እንዲደግሙለት ጠየቃቸው። (በነገራችን ላይ የቦጋለ አባት ልጃቸው ትምህርት እንዳይገባው ተደግሞበታል ብለው ስለሚያስቡ፣ እሱን ይዘው ያልተንከራተቱበት  ጸበል አልነበረም። ኋላ ላይ ቢታክታቸው ጊዜ እርግፍ አድርገው ተውት! እርሱም ትምህርት አይንህን ላፈር ብሎ ማንበብና ማጥናቱን እርግፍ አድርጎ ተወው)
“እኛ የምንጠጣው ውሃ ከምንና ከምን ውህደት ተፈጠረ?” ብለው ጥያቄውን ደገሙለት።
“ውሃ ልማት እና ቀበሌ ተዋህደው በገጠሙት የቧንቧ መስመር ነው የተፈጠረው!” ብሎ ሲመልስ ያልደነገጠ ተማሪ አልነበረም። ሁላችንም እያሾፈ ነው ብለን በትኩረት አየነው። እሱ እቴ!
ልቡ ደጭ እንኳ አላለም! ሰው እንዴት ይህን የሚያክል ተራራ ስህተት ሰርቶ ትንሽ ሀፍረት እንኳ አይሸብበውም?
“ስ! ውይ ይቅርታ” አለን መልሶ… በቃ ኦክስጂንና ሀይድሮጅን ታውሰውት ነው ማለት ነው ብለን ማስተካከያውን በጉጉት መጠባበቅ ያዝን! ቦጋለ እጅ አውጥቶ መልሶ፣ የተሳሳተውን አውቆ ትክለኛ መልስ ከመለሰ፣ ዘጠነኛው ሺህ  አልፎ አስራ ዘጠነኛው ሺህ ገብቷል ማለት ነው በቃ! ቦጌ ጉጉታችን ላይ በረዶውን  ሲከለብስ፤
“ቅድም ተሳስቼ ነው መምህር! እህ ህ-- ውሀ ልማት እና ሰሜን ሸዋ ዞን በመተባበር ነው” ብሎ እርፍ አለው። ነፍሰ ቀጭኑ መምህራችን በንዴት ተነፋፍተው ነብር አከሉ! አለ አይደል ቤት ውስጥ ድመት ስትቆጣ እንዴት ነው ኩፍ የምትለው?
መምህራችን ኩፍ አሉ።
በስመአብ!
 አስተማሪ ሲናደድ ለካ እንደዚህ ነው?
ከአስተማሪም ሁሉ ደግሞ ኬሚስትሪ አስተማሪ ሲናደድ በጣም ያስፈራል። የሆነ ሰልፈሪክ አሲድ ከላብራቶሪ አንስተው ፊቱ ላይ የሚከለብሱበት ሁሉ መሰለን። የቦጋለና መምህራችን መጨረሻ የተዘጋው ዶሴ ሊሆን ነው ስንል ሰጋን!
“ተነስ!”
ቦጋለ ተነሳ። ደግሞ አነሳሱ እኮ እንደ ንጉስ ክቡር ዘበኛ ቀብረር ኮራ ብሎ ነው። ግዳይ የጣለ ጀግና የነብር ቆዳ ለብሶ ቢመጣ እንኳ መቼ ይሄን ያህል  ይጀነናል? ጅ---ንን--ን--ን ቅብርርርርርርርር--
ከሴክሽን አንደኛ  የሚወጣው ፍቅሩ የሚባለው ቸካይ ተማሪ እንኳ መምህር ሲያስነሳው አንገቱን ሰበር ያደርጋል እኮ!
ቦጌማ ጭራሽ ተንጠራራ… ደረቱን ነፋ!
“እነ ሚካኤል፣ እነ እዮብ፣ እነ አቤል-- ኢንጅነር ወይ ዶክተር ሲሆኑ ሻንጣ ተሸካሚያቸው እንደምትሆን አልጠራጠርም” ብለው ሞራሉ ላይ ቀዝቃዛ ውሃቸውን ከለበሱት። በቃ ቦጊሻ ሊተነፍስ ነው አልን!
ደግሞ እኮ እንደፈራነው ከወራት በኋላ ማትሪክን ወደቀ። እኛ ፈተናውን በጥሰን አለፍን።
እኛ አስራ ሁለተኛ ክፍል አልፈን ለዩኒቨርስቲ ስንዘጋጅ፣ ቦጋለ የሆነ ትምህርት እንደከረሜላ አሽጎ የሚሸጥ ኮሌጅ ዲፕሎማ መማር እንደጀመረ ሰማን። አውቶቡስ ተራ  አለመሄዱም የመምህሩ ትንቢት  እውን እንዳይሆን ስለሰጋ እንጂ የሱ መጨረሻ ከወያላነት ይዘላል ብሎ ማን ያስብ ነበር?
ግን ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስንሆን ቦጋለ ቀበሌ ስራ አግኝቶ መግባቱ ተነገረን። ያኔ በሱ ሙድ ያልያዘ አልነበረም። እንደውም አንድ ቀን ፍቅሩ የሚባለው ቸካይ የነበረ ተማሪ ወደኔ ጠጋ ብሎ፤ “ቦጌ በዚህ ከመሬት አልሮ ማርስ የምትባል ፕላኔት ላይ እንኳ በማይገኝ ድድብናው ቀበሌ ስራ ማግኘቱም ተመስገን ነው” ብሎ ገለፈጠ። “ቦጋለ እኮ ቀን ስራ እንኳ ይበዛበታል። እንደ ህንዶች ሰባቴ  ቢፈጠር ሰባት ጊዜም ትምህርት አይገባውም” አለን ቀጥሎ።
ሁላችንም ጎበዝ ተብዬ ተማሪዎች ስንመረቅ ግን የነፍሰ ቀጭኑ ሰውዬ እርግማን ለቦጋለ ምርቃት ሆኖ እርፍ አለው።
የከተማችን አስተዳደር ተመራቂ ተማሪዎች ተደራጅታችሁ ኮብልስቶን አንጥፉ ምናምን ብሎ በስብሰባ ሰበብ ሲጀነጅን፣ ቦጌ ተከብሮ የከተማችን ከንቲባ ሆኖ ነበር።
ጭራሽ እዛ አመዳችን ቡን ባለ ተመራቂ ተማሪዎች ፊት ቀርቦ፣ ስለ ስራ ፈጠራ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠን።
 አቤት የምስሉ ፍጥነት! አቤት የንግግሩ ስድርነት! መጥበሻ ሆኖ የተማሪውን ልብ አቀለጠው። ከኔ ጎን ተቀምጣ የነበረችው ጸሐይ የምትባል ጓኛችን፣ ዛሬውኑ ጀበና እና ስኒ ገዝቼ ስራ ካልጀመርኩ በሚል ሀሳብ ጦዛ ብንን ብላ ጠፋች።
“ኢንጅነር ነን ዶክተር ነን ብላችሁ አትኮፈሱ፤ ጀበና ቡና ብታፈሉ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ሚካኤል እዮብ አቤል በኢንጅነሪንግ እና ዶክትሬት ተመርቃችሁ ሰፈር ለሰፈር ከምታውደለድሉ---ጀበና ቡና ብታፈሉ ምን ችግር አለው? ብሎ በምሳሌነት ጠቀሰን። እኔ እንዳስተማረን ሳይሆን  እንደ ሰደበን ቆጥሬው እሳት እንደነካው ላስቲክ ተኮራመትኩኝ።
አቤል፣ እዮብ፣ ሚኪ ምንም ጎበዝ ተማሪ ሆናችሁ ስታስጨንቁን ብትኖሩም፣ አሁን ግን መጨረሻችሁ እጣን እያጫጫሱ፣ አላፊ አግዳሚውን መካደም ነው ማለቱም አይደለ?
እዮቤ ጓደኛችን ፊቱ በርበሬ ሆኖ ቀላ!
አይ መንግስት የስራህን ይስጥህ፤ አንድ የተከበርኩ ዶክተርን ለመንደር ስኩፒኒ አሳልፈህ ትሰጠኝ ብሎ ክፉኛ ቆዘመ! እኔም አነጋገሩ ትንሽ ሸንቆጥ ስላደረገኝ፣ ከስብሰባው በኋላ ቦጋለን ለማናገር ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ተራመድኩኝ። ዛሬ ምንም ጉድ ይለይለታል!
በዛ ቢባል ከንቲባውን ገላመጥክ ተብዬ ብታሰርም አይደል? የልጅነት ጓደኛዬ ስለሆነ ትንሽ ራሮት ተሰምቶት፣ ከሳምንት በኋላ ራሱም ሊያስፈታኝ ይችላል የሚል ድፍረት አደረብኝ። ጀርባውን ተከትዬ ተጠጋሁት። በሰዓቱ ከየት መጣ ያልተባለ ጠባቂው በመዳፉ ጨብጦ አሽቀነጠረኝ። የጠባቂው መዳፍ ጎትቶ እዛው የተመረቅሁበት ዩኒቨርስቲ ግቢ ሊዶለኝ  ምን ቀረው? ቀና ብዬ  አየሁት! “ምን አጠፋሁ አለቃ?”
ፈርጣማው ጠባቂ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዲህ አለኝ፡-
“አንተ ምን አይነት ደፋር ነህ ባክህ? ክቡር ከንቲባችንን  ለመቅረብ አይደለም ሻንጣቸውን ለመሸከም ብትመጣ እንኳ ማስፈቀድ ነበረብህ”
(ከሚካኤል አስጨናቂ “ሸግዬ ሸጊቱ” የወግ መድበል የተወሰደ)


Read 1643 times