Saturday, 06 August 2022 11:27

የሰላም ድርድሩን የህወኃት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳያደናቅፉት ተሰግቷል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  • መንግስት ድርድሩን የትም፣ መቼም ያለቅድመ ሁኔታ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል
    •  የምዕራባውያኑ ልዑካን ቡድን ከመቀሌ መልስ በያዙት አቋም መንግስት ደስተኛ አይደለም
      •  የኬኒያ ምርጫ የሰላም ድርድሩ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበታል
             
              በፌደራል መንግስትና በህወኃት ታጣቂ ሃይሎች መካከል ሲካሄድ የቆየውንና ለሃያ  ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም  ያስችላል የሚል ተስፋ የተጣለበት የሰላም ድርድር፤ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በየጊዜው በሚያነሷቸው የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ሳቢያ ሊደናቀፍ ይችላል የሚል ስጋት አንዣቧል፡፡
ሰሞኑን ወደ መቀሌ ያመሩትና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሖመርና በአውሮፓ ልዩ መልዕክተኛ አኔታ ቬበር የተመራው የልዑካን ቡድን  የህወኃት ታጣቂ ሃይሎችን ፍላጎትና በቅድመ ሁኔታነት የሚደረድሯቸውን ጉዳዮች በማስፈፀም ተግባር ላይ ተጠምደዋል ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ወቅሷል፡፡
የፌደራሉ መንግስት ከሕወኃት ታጣቂ ሃይሎች ጋር ለሚደረገው ድርድር መዘጋጀቱንና ድርድሩ በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ጊዜ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መደረግ እንደሚችል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንት አማካሪው አምባሳድር ሬድዋን ሁሴን ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ በሰላም ድርድሩ ጉዳይ ላይ የሚነጋገር አንድ ቡድን  ወደ መቀሌ አምርቷል፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ቡድን ወደ መቀሌ አቅንቶ ለጦርነት ዘላቂ  መፍትሔ ለማስገኘት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የሚነጋገር ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ የተቋረጡ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮም፣ ባንክና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ለትግራይ ህዝብ እጅግ መሰረታዊና አስፈላጊ በመሆናቸው ሊለቀቁ እንደሚገባና እነዚህን ተቋርጠው የቆዩ መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን በፌደራሉ መንግስቱ ለሚላኩ ባለሙያዎች የደህነንት ዋስትና የሚሰጥ ደብዳቤ ከህወኃት ሊቀመንበር  ከዶ/ር ደብረ ፅዮን ገ/ሚካኤል፤ መቀበላቸውን ጠተቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በነዳጅ በጥሬ ገንዘብና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ የቆየው ክልከላም እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች የሰላም ድርድሩን በያዘበት ሁኔታ ላይ መንግስታቸው ደስተኛ አለመሆኑንና ዲፕሎማቶች ባልተገባ ተግባር ተጠምደው መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አምባሳደር ሬድን ሁሴን  በቲውተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እንደገለፁት ልዩ መልዕክተኞቹ ለሰላም ድርድሩ ጥረት ማድረግ ሲገባቸው፣ በሕወኃት ወገን የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት ጥረት በማድረግ ተግባር ላይ ተጠምደው ሰንብተዋል ሲሉ ተችተዋል።
ተቋርጠው የሚገኙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተመለከተ የመንግስት አቋም ግልፅ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ አገልግሎት ማስጀመር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ የሰላም ንግግር መጀመሩ ቀዳሚ ጉዳይ ነው  ብለዋል፡፡ የልዩ መልዕክተኞቹ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ትርክት አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሉ ያልተገደበ በረራና የጭነት መኪኖች ጉዞ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ጋር የሚያደርገው ድርድር የሚመራው በአፍሪካ ህብረት ብቻ ነው ሲሉ ቁርጥ ያለ የመንግስትን አቋም ያንፀባረቁት አምባሳደር ሬድዋን፤ ድርድሩ በየትኛውም ጊዜና ወቅት ሊደረግ እንደሚችል ዳግም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ የምዕራብ  አገራት ዲፕሎማቶቹን የመቀሌ ቆይታ ተከትሎ የህወኃቱ ቃል አቀባይ  አቶ ጌታቸው ረዳ ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፤ “ሰሞኑን ወደ ትግራይ  አቅንተው የነበሩት የአሜሪካና የአውሮፓ አምባሳደሮች ልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል የተቋረጡትን መሰረታዊ አገልግሎቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲጀምሩ ለማድረግ የቤት ስራ ወስደዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ከዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ጋር ባደረጉት ቆይታም “ለትግራይ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ የማቅረብና መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማስጀመሩ ጉዳይ እንደ ድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ሊታይ  አይገባም” ማለታቸውን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሊ ፊ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ፣ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም የታቀደው ድርድር በኬኒያ ምርጫ መጓተት ሳቢያ መዘግየቱን ጠቁመው፤ ድርድሩ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መግለፃቸው ተዘግቧል፡፡

Read 12705 times