Saturday, 06 August 2022 11:32

“ጦረኛ ትውልድ አገር አያቀናም”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  • የጠ/ሚኒስትሩ መጥፋት የፈጠረው ውዥንብርና “የሽግግር መንግስት” ጥድፊያ
     • በዘንድሮ በጀት ዓመት ከኤክስፖርት ከ10 ቢ. ዶላር በላይ ተገኝቷል
      • በቀጣዩ ዓመት በሌብነት ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል


                 የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድምጽ ለአንድ ወር ገደማ መጥፋቱ ውዥንብር ፈጥሮ ሰንብቷል- በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው። በእርግጥ በአሜሪካ ኦሪጋን ድል የተቀዳጀው የአትሌቲክስ ቡድናችን ወደ አገር ቤት መምጣትን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው የደስታና የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል- ብዙም ግን ውዥንብሩን አላጠፋውም።
“ጠ/ሚኒስትሩ ጤና ቢሆኑ ኖሮ በራሳቸው ቤተ-መንግስት ውስጥ በተዘጋጀው የአትሌቲክስ ቡድኑ የአቀባበልና የሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ይገኙ ነበር።” የሚል መላምት መቀንቀን ጀመረ።
ከሁሉም የሚገርመው ግን የጠ/ሚኒስትሩ ድምጽ ጠፋ ብለው በአገሪቱ የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠርና አገሪቱ በመሪ እጦት ወደ ቀውስ እንዳትገባ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም በአደባባይ ሃሳብ ያቀረቡ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መከሰታቸው ነው።
ይህንን ለአንድ ወር ገደማ የዘለቀውን ውዥንብር ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ደምስሰውታል- ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እመርታ ከታየበት መረጃ ጋር በመከሰት። ከሰሞኑ በ2014 ማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማና በ2015 የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ አቅጣጫ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በ2014 የበጀት ዓመት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የ6 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡም ተጠቁሟል።
“በማክሮ ኢንዲኬተርስ- በሁሉም- ከኢንፍሌሽን በስተቀር ያገኘነው እመርታ በእጅጉ ይበል የሚያሰኝ- የሚያኩራራ- ይበልጥ እንድንተጋ የሚያነሳሳ ነገር ነው።” ብለዋል- ጠ/ሚኒስትሩ ስለተመዘገበው ዕድገት ሲገለጹ።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በፓርላማ በተገኙበት ወቅት ከነበሩበት መንፈሳዊና አካላዊ ገጽታ በእጅጉ ተሽለውና በሃይልና በአዎንታዊ ስሜት ተሞልተው ነው የተስተዋሉት በሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ውይይት ወቅት። በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት መደሰታቸውም በገጽታቸው ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር።
“ዘንድሮ በኤክስፖርት ከ10.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው ያገኘነው፤ ከሸቀጦችና አገልግሎት ዘርፉ።  ከዳያስፖራ ከሚላከው (ረሚታንስ) እና የውጭ ቁጥተኛ ኢንቨስትመንት ሲጨመር ገቢው ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል። ለኢትዮጵያ ይህ ትልቅ አይደለም።
ኢትዮጵያ ከዚህ አምስት ስድስት እጥፍ ማደግ አለባት- ነገር ግን ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር በጣም ትልቅ እመርታ ነው፤ የማይጠበቅ እመርታ ነው።” ሲሉ በተገኘው ውጤት የተሰማቸውን እርካታ በቃላት ጭምር ገልጸውታል።
የላቀ ውጤት የተመዘገበው ደግሞ በኤክስፖርት መሆኑ ዘርፉ አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት ለመገንባት ሚናው ቀላል እንዳልሆነ ነው የተጠቆመው።
“ኤክስፖርት ላይ ያልተሳካለት ኢኮኖሚ በብዙ ምክንያት ማደግ አይችልም። ምንም እንኳን የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ብዙ ቢሆኑም፤ ዋናው ግን የኛ ቡድን የራሱን ስራና ውጤት መገምገም ያለበት በኤክስፖርት ምን አመጣሁ ብሎ ነው፤ እሱ ሲስተካከል ብዙዎቹን የምናያቸውን አመላካቾች (ኢንዲኬተርስ) የማስተካከል አቅም አለው።” ሲሉ አብራርተዋል-ጠ/ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዕድገትና ብልጽግና ትገሰግስ ዘንድ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኘው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝቧ ዕምቅ አቅም መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ሁለት ችግሮች እንደሚስተዋሉ አልሸሸጉም።
“አንደኛው፤ በከፍተኛ ደረጃ እርዳታ የሚጠብቅና የልመና ባህሪ የተለማመደ ትውልድ እየፈጠርን መሆኑ ነው፤ ይህ ለብልጽግና ጠር ነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ “ሰርቶና ደክሞ ለውጥ የሚያመጣ ሃይል ነው መፈጠር ያለበት እንጂ ቁጭ ብሎ በሰበብ አስባቡ ችግር እየተናገረ መረዳት የሚያስብ ኃይል አደገኛ ነው።” ብለዋል።
ሁለተኛው የሚያስፈራውና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ደግሞ፤ ጦረኛ ህብረተሰብ (Warrior Society) እየተፈጠረ እንዳይመጣ ነው ይላሉ።
“እንደ ትውልድ-እንደ ህዝብ ውጊያን በጣም የሚያፈቅር ስለ ውጊያ የሚያወራ ስለ ውጊያ የሚያስብ ህጻናት ሆነው ዱላን እንደ ክላሽ የሚሰሩ ዓይነት ትውልድ ከፈጠርን ኪሳራ ነው፤ የውጊያ ትውልድ ልማት አያመጣም። መማር- መፍጠር- መስራት የሚል ትውልድ ነው አገር የሚያቀናው እንጂ ጦረኛ ትውልድ አይደለም።” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ አመራር ሆነው፣ ፓርቲ ሆነው፣ ክልል እየመሩ ህብረተሰቡን በሙሉ- ህጻን ሽማግሌውን- ለውጊያ የሚያሰለጥኑ- የሚያዘጋጁ- የሚያስታጥቁ አካላትን በተመለከተ የዛሬው ሳይሆን የነገው ነው የሚያሳስበኝ ይላሉ-ጠ/ሚኒስትሩ።
“ህብረተሰቡን በሙሉ ጦረኛ ካደረግህ ልማት አይመጣም፤ ለማኝና ጦረኛ ትውልድ አገር ሊያቀና አይችልም፤ ይሄ ብዙ ልንሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።” ሲሉ ምክርም ማሳሰቢያም ሰጥተዋል፤ ዶ/ር ዐቢይ።
ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ሌብነት መሆኑን ጠቁመዋል። “ሌብነት፤ ጌጥ-ልምምድ- ምንም ነውር የሌለበት ጉዳይ እየሆነ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ማንም ሰው ምንም ሳይሰጋ እንደፈለገ የሚሰርቅበትና ገንዘብ የሚሰበስብበት ሁኔታ ጥፋት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“በአንድ በኩል እናለማለን፤ በአንድ በኩል ይፈርሳል፤ በግብርና ያመጣነው እመርታ በጣም ትልቅ ነው፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ቢሮክራት ለመታወቂያና መንጃ ፈቃድ ብር የሚቀበል ከሆነ ዋጋ የለውም። ህዝብ የምናስመርር ከሆነ ዋጋ የለውም። ኢንፍሌሽንን (ግሽበትን) ብናስተካክል ሌብነት ካለ ዋጋ የለውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ጠንከር ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።” ብለዋል።
በዚህ ብቻ ግን አላበቁም። በመጪው ዓመት አንድ ጠንካራ ስራ የሚያስፈልገን በዚህ ጉዳይ ላይ ነው፤ ሌብነት ልምምድ  ሆኖ መቀጠል የለበትም ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ከማክሮ ኢኮኖሚ ገምጋሚ ቡድኑ ጋር የተሰበሰቡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ዘንድሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እመርታ አምጥተናል። ይህን በጋራ ማክበር ስለሚያስፈልግ ነው። ሁለተኛው ለቀጣዩ ዓመት ከዘንድሮውም ትንሽ የተለጠጠ ዕቅድ አቅደናል።   ይህንን ለማሳካት ደግሞ የዘንድሮውን ማክበርና  ለሚቀጥለው መዘጋጀት ስለሚፈልግ  በጋራ እንድንዘጋጅ ነው።” ብለዋል። ቡድኑንም ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እመርታ በማመስገን፤ ለቀጣዩ ሥራ እንዲተጉ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከጠ/ሚኒስትሩ መጥፋትና ከተፈጠረው ውዥንብር ጋር በተገናኘ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ ተቆርቋሪ ዜጎች፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለረዥም ጊዜ ድምጻቸውን ማጥፋታቸው ውዥንብር ለሚነዙ ወገኖች ዕድል ስለሚከፍት፣ በየጊዜው የሚገኙበትን ሁኔታ ለህዝባቸው በማሳወቅ፣ ሀገርና ህዝብን ከአላስፈላጊ ሽብርና ውዥንብር ቢያድኑ መልካም ነው ብለዋል።Read 13555 times