Saturday, 06 August 2022 11:51

“መዝገበ - አዕምሮ“ ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ከ1950ዎቹ ጋዜጠኛ ኃይሉ ልመንህ እስከ 2004ቱ ገድለ-ሚካኤል አበበ ድረስ ያሉትን 180 የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ታሪክ ያካተተው “መዝገበ - አዕምሮ“ የተሰኘ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በዛሬው  ዕለት ከ3 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር  ይመረቃል፡፡
በተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተዘጋጅቶ የታተመው መጽሐፉ፤ በ600 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን የመጽሐፉ  ርዕስ “መዝገበ - አዕምሮ”፣ ለእንግሊዝኛው ኢንሳይክሎፒዲያ የተፈጠረ አቻ ቃል ነው ተብሏል፡፡  
በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ከ15 ዓመታት በፊት የተቋቋመው ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን፤የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ  ማቅረብ  የጀመረው በሲዲ ነው -  ‹‹ታሪክን በሲዲ›› በሚል፡፡  
የመዝገበ-አእምሮ 180 ባለታሪኮች በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ፣ በአዊ፣ በሶማሊኛና በአረብኛ ቋንቋዎች የጋዜጠኝነትን ሙያ ያራመዱ ናቸው ተብሏል። ሁሉም ታሪካቸው የተነጻጸረው ከኖሩበትና ከሠሩበት ጊዜ እንዲሁም በጊዜው ከሠሩት ሥራ አኳያ እንጂ የቀደሙትን ከአሁኖቹ ጋር በማነጻጸር እንዳልሆነም ተመልክቷል፡፡   
“በዚህ መጽሐፍ ላይ የቀረቡት ሰዎች አብዛኛዎቹ ጋዜጠኛ ሆነው ሀገራቸውን ያገለገሉ፣ ጥቂቶቹ መገናኛ ብዙኃንን መስርተው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መነሻ ሥራቸው መገናኛ ብዙኃን ሆኖ በየመሥሪያ ቤቶች ጥሩ የተግባቦት ወይም የኮሙኒኬሸን ባለሙያ  ሆነው የሠሩ ወይም እየሠሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በግራፊክስና በቴክኒክ ዘርፍ የተካተቱ ናቸው፡፡“ ብሏል መጽሐፉን ያሳተመው ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባሰራጨው መግለጫ፡፡

Read 18016 times