Saturday, 06 August 2022 11:57

እኛን የቸገረን የፖለቲካ ፓርቲ ነውን?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

   ሰሞኑን በከተማው ሲዘዋወሩ ከሰነበቱ ወሬዎች አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) እንደገና በምስረታ ሂደት ላይ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ድክመቶች ወይም ችግሮች አንዱ፣ የፈለጉ ሰዎች በፖለቲካ ፓርቲ እራሳቸውን እንዲያደራጁ አለመፍቀዱ፣ አልፎም የፓርቲ አሰራርና በፓርቲ አማካይነት የፖለቲካ ትግል ማድረግ እንዲለመድ አለማድረጉ ነው። እሱን አድርጎ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም ያኮረፉ ቡድኖች መሳሪያ እያነሱ ወደ ጫካ የሚገቡበትን መንገድ በዘጋ  ነበር።
የንጉሱ መንግስት ወድቆ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ በአንዳንዶች ዘንድ ትንሽ ቀደም ብሎ (እነሱ እንደሚናገሩት) በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች፣ እራሳቸውን ከተማሪ እንቅስቃሴ ወደ ፓርቲ እያሻገሩ ነበር። ኢሕአፓ፣ መኢሶን ወዘተ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
“ሕዝብ ተደራጅቶ ስልጣን ለመንጠቅ ሲነሳ እኛ የት ልንወድቅ ነው” ብለው የተጨነቁ የደርግ አባላት ራሳቸውን በፖለቲካ ፓርቲ የማሰባሰብ ስራ ጀመሩ። የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት አቋቋሙ። በዚህ ጽ/ቤት ሥር አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰባስበው ኢማሌድህ የተባለ የጋራ ግንባር ፈጠሩ። ከግንባሩ አባል ፓርቲዎች አንዱ ኮሎኔል መንግስቱን ጨምሮ ወታደሩን ያሰባሰበው አብዮታዊ ሰደድ ነበር። ሰደድ እየፈረጠመ ሲሄድ፣ ሌሎች እየኮሰመኑ - ለህልውናቸውም እያሰጋቸው መጣ። ከዚህ ጎን ለጎን የኮሎኔል መንግስቱ አምባገነንነትም እየተባባሰ እየሄደ ነበር። ሁኔታው ያላማራቸው የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) አባላት እራሳቸውን ከህብረቱ አገለሉ። “ፈረጠጡ” ተብለው መሪዎቻቸውና አባሎቻቸው እየታደኑ ተገደሉ። ከሞት የተረፉት ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። ከእነሱ ቀጥሎ ተረኛው የወዛደር  ሊግ ነበር። እሱም አበጠ ተብሎ ተደበደበ።
አንዳንድ እያለ ተቀናቃኞችን እየገደለና አንገት እያስደፋ የመጣው ደርግ፣ የሰራተኞችን ፓርቲ ለመመስረት የማደራጀት ስራ የሚሰራ፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሰፓአኮ) የተባለ ቢሮ አቋቋመ። የኢሰፓአኮ መቋቋም በፕሬዚዳንቱ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እንዳሻው አድራጊነት የተፈጸመ መሆኑን ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ምስክርነት ሰጥተውበታል። በኢሰፓ ምስረታ ጊዜ የሆነውም ይኸው ነው። የሆለታ ጦር መኮንኖች ማሰልጠኛ ተመራቂ የሆኑት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የአቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ወዛደር ሆነው፣ በወዛደርነት ቀርበው፣ ለኢሰፓ አንደኛ ጸሃፊነት መብቃታቸውን ማስታወስ ያንን ዘመን ለመታዘብ ይበጃል።
ኢሰፓ የመንግሥትንና የፓርቲን መዋቅር አደባልቆ አገር የመራ ድርጅት ሲሆን ዛሬም ድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥታዊ ስርዓት የተረፈ ችግር ጥሎ መሄዱ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው።
በመጨረሻው ዘመኑ ላይ ኢሰፓ አንድ መቶ ሰማኒያ ሶስት ሺህ አካባቢ አባላት እንደነበሩት ይገመታል። በገጠር የገበሬ ማህበር መሪዎች የድርጅቱ አባል ቢሆኑም ባይሆኑም ደርግ ኢሠፓ እየተባሉ በዚህ መከራ ተቀብለዋል። በከተማ የመንግስት ሰራተኞች በኢሰፓ ምክንያት እድገት ተነፍገዋል፤ ስራ ተከልክለዋል። ከፍ ያለ የሞራል ጉዳት እንዲደርስባቸውም ተደርጓል። በ1983 ሰኔ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ሰዎች ከሥራ የተባረሩት የኢሰፓ አባል ናችሁ ተብለው እንደነበርም የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለም።
 የተገፉና የተንገላቱ ብዙ አባላቱ የድርጅቱን ዳግም ወደ ፖለቲካው እንቅስቃሴ መመለስ እንደሚፈልጉትና እንደሚወዱትም አምናለሁ። ይቅናችሁ ማለትም አይከበደኝም። ግን ግን ጥያቄዬ፣ የኢሰፓ መምጣት በሀገራችን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል? ነው፡፡ ቀደም ሲል ደርግ በኋላም ኢሰፓ በፖለቲካ ጉዳይ በተንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ባደረሱት ግድያ፣ ድብደባ፣ እስርና መንገላታት “ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቅ” የሚል አስተሳሰብ በሕዝቡ ዘንድ በማሳደሩ፣ በአገር ጉዳይ በራስ ፍላጎት ተነሳስቶ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማድረግ መብት መሆኑ ቀርቶ እንደ ሃጢያት እንዲቆጠር ማድረጉ ይታወሳል። ዛሬም ድረስ ብዙዎች ከፖለቲካው አንደራቁ በሀገራቸው ጉዳይ የዳር ተመልካች እንደሆኑ፣ በእነሱ መብትና ግዴታ ላይ ሌሎች ክፍሎች እንዲወስኑ ሆኗል። የኢሰፓ መመለስ ከዚህ ቆፈን ይገላግለን ይሆን? እኔ እንጃ፡፡
አንድ ሁለት ሶስት ተብለው የሚቆጠሩ ብዙ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፡፡ ማኅተም ይዘው እንደሚዞሩ እናውቃለን፡፡ ስም እንጂ ቢሮ የሌላቸው ብዙ ፓርቲዎች አሉን። አንዳንድ ፓርቲዎችም በአውሮፓና በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚያስገኝ ደብዳቤ ሲሸጡ እንደኖሩም ድብቅ አይደለም። “ከእኔ በላይ የሸጠው እሱ ነው” ብለው ሲካሰሱ የነበሩ የፓርቲ መሪዎችንም እናስታውሳለን። ኢሰፓ እንዲህ አይነቱን ነውር ተግባር ለማስፋፋት እንደማይመጣ ተስፋ አለኝ።
የፖለቲካ ድርጅቶችን በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ለመደገፍ የሚፈልጉና በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ገብተው ለመንቀሳቀስ የሚሹ በልዩ ልዩ የሥራ መስክና የመንግስት ኃላፊነት ላይ የተሰማሩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ግን በስራቸውና በህይወታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በመፍራት ፓርቲዎች ከደረሱበት ላለመድረስ ምለው ተገዝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ፣ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን በአውሮፓና በአሜሪካ ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በሚያገኙት ገንዘብ ላይ እንዲንጠለጠሉ አስገድዷቸዋል። በዚህም ሳቢያ ገንዘባቸውን የሚለግሱ ወገኖች ከፍለንበታል በሚል እምነት፣ የአገር ውስጡን ፖለቲካ እንዳሻቸው ሲቆጣጠሩትና ሲዘውሩት ቆይተዋል። እየዘወሩትም ይገኛሉ። ይህ ጥገኝነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአገራቸው፣ ግርማ ሞገሳቸውን እንዳሳጣቸው በግልጽ  መነገር ይኖርበታል። ሁኔታው ለመንግስትም ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም።
እንደሚታወቀው እጅግ የሚበዙበት የአገራችን  የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘርና በአካባቢ ላይ ያተኮሩ የብሔር ፓርቲዎች ናቸው። አይነታቸውና ቁጥራቸው መብዛቱ ብቻ ሳይሆን የሚያሳስበው በራሳቸው አካባቢ ከሚፈፀመው በጎም ሆነ ክፉ ነገር ውጭ የሌላውን በጎም ሆነ ክፉ ነገር ለመጋራት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህም እነሱንም ጭምር ደካማና አጋር የለሽ አድርጓቸዋል፡፡
ከዚህ አንጻር እኛን የቸገረን የፓርቲ ዓይነትና ብዛት ሳይሆን መንግስትና ገዢው ፓርቲ የሚያከብረውና የሚፈራው ፓርቲ አለመኖር ነው፡፡ እኛን የቸገረን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትና አመኔታ የተቀዳጀ ፓርቲ እጦት ነው፡፡ እኛ ያጣነው የሚለውና የሚናገረው  ብዙኃኑ ጆሮ ዘንድ የመድረስ አቅም ያለው ፓርቲ ነው፡፡ የቸገረን በሰበብ አስባቡ የተከፋፈለውን ህዝብ በጥበብና በብልሃት አንድ አድርጎ የሚመራ  ፓርቲ ነው፡፡



Read 2090 times