Saturday, 13 October 2012 14:08

ኧርያል ሻሮንና አያት አክራስ

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያውያን ዘወትር በረባ ባልረባው እየተጣሉ የሚናቆሩ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው አንድ የተለመደ አባባል አላቸው፡፡ እነሱኮ “አይጥና ድመት” ናቸው ይላሉ፡፡ በአለማችን ካሉ ሀገራት ሁሉ ነገረ ስራቸው ሁሉ የአይጥና የድመት የሆነ ለይታችሁ አውጡ ብትባሉ ከእስራኤልና ከፍልስጤም ሌላ ፈልጋችሁ ልታገኙ አትችሉም፡፡ ፍልስጤማውያን ያሲር አራፋትን የነፃነት ትግሉ አባት እያሉ ዛሬም ድረስ ይጠሩዋቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን ዕድሜያቸው ከማለቁ በፊት ታጋይ አራፋት የነፃና ሉአላዊት ፍልስጤም ባለቤት ያደርገናል ብለው ተስፋቸውን ሁሉ ጥለውባቸው ነበር፡፡ እስራኤል ከተመሠረተች በኋላ የአሁኗን እስራኤል እንድትሆን ጠፍጥፈው ካበጇት የጦር መሪዎችና ፖለቲከኞች ውስጥ ግንባር ቀደሙ እየሩሳሌም ተወልደው ያደጉት ይስሀቅ ራቢን ናቸው ይላሉ፡፡ የእኒህን ሰውም እስራኤላውያን ስለ እሳቸው የሚናገሩት ሁሉ ትክክል መሆኑን በሚገባና በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡


በእርግጥም ይስሀቅ ራቢን በህይወት የኖሩበት እያንዳንዱ አመት በታላቅ ታሪክ የተሞላ ገድለኛ እስራኤላዊ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ደረታቸው በፈፀሙት ልዩና አስደናቂ ጀብዱዎች በሜዳሊያ የተንቆጠቆጠ፣ እንኳን ሰው ሳር ቅጠሉ ሁሉ ቁጭ ብድግ እያለ ያረግድላቸዋል የተባሉ ዝነኛ ወታደራዊ መሪ ነበሩ፡፡ በፖለቲካው መስክም የእስራኤልን የሌበር ፓርቲንና እስራኤልን ራሷን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመምራት ከፍ ያለ ውጤት ለሀገራቸው ያስገኙ በሁለት እጅም እንኳ የማይነሱ ከባድ ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡
እናም ለበርካታ ጊዜያት የተቀመጡበትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን እንደገና በመጨበጥ በመሪነቱ መድረክ ላይ ብቅ ብለው የወቅቱ ዋነኛ ጉዳያቸው ከፍልስጤማውያን ጋር እርቅ መፍጠር መሆኑን ሲያስታውቁ፤ ከዚህ በፊት ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ አብዛኛው እስራኤል “እሰየው አበጀህ” ብሎ ሙሉ ድጋፉን ለግሶአቸው ነበር፡፡
ያኔ አብዛኛው እስራኤላዊ ሰላም የመምጫዋ እርግጠኛ ጊዜ እንደተቃረበ የእርግጠኝነት ስሜት ተሰምቷቸው በእጅጉ ደስ ተሰኝተው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያታቸው ሌላ ነገር ሳይሆን ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒሰትር ይስሀቅ ራቢን ብቻ ነበሩ፡፡ እስራኤላውያን ከማንም በበለጠ የሚያምኑትና ቃሉን በተግባር ይተረጉማል ብለው የሚተማመኑበት ፖለቲከኛና መሪ አለ ከተባለ ከጐልዳ ማየር ቀጥሎ ይስሀቅ ራቢን ናቸው፡፡
ይስሀቅ ራቢን በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ከእለታት ባንዱ ቀን ለወጠኑት የሰላም እቅድ ድጋፉን ሊገልጥና “አይዞህ ግፋበት” ሊላቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህዝባቸው በእየሩሳሌም የፂዮን አደባባይ ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ እርሳቸውም በዚህ ታሪካዊ ነው በተባለለት ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለተደረገላቸው ድጋፍ በምስጋና እጅ ለመንሳትና እግረመንገዳቸውንም ስለሰላሙ እቅዳቸው የበለጠ ለማብራራት በአደባባዩ ተገኙና ያሠቡትን ተናግረው ከደጋፊ ህዝባቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው የሰላም መዝሙር ዘመሩ፡፡
እጅ ለእጅ ተያይዞ ስለ ሰላም ከሚዘምረው የህዝብ ማዕበል ውስጥ ግን ልቡ በፍልስጤማውያን ጥላቻ አለቅጥ የተሞላ ፍልስጤማውያንን መፍጀት እንጂ እርቅ ብሎ ነገር እንዴት ይታሰባል እያለ በጠቅላይ ሚኒስትር ይስሀቅ ራቢን ላይ ቂም ቋጥሮ፣ ጥርሱን የነከሰባቸው አንድ እስራኤላዊ ወጣት ነበር፡፡ በዚህ ወጣት ልብ ውስጥ አለመጠን የሚንቀሳቀሰው የፍልስጤማውያን ጥላቻ መዝሙሩ ተዘምሮ እስኪያልቅ ድረስ እንኳ ፋታ አልሰጠውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ራቢን ወደቆሙበት መድረክ በማምራት ከተጠጋቸው በኋላ የታጠቀውን ሽጉጥ አውጥቶ አከታትሎ ተኮሰባቸው፡፡ ያ ታሪካዊ ቀን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እስከ ዛሬም ድረስ ተመዝግቦ የማያውቅ አዲስ ጥቁር ታሪክን መዘገበ፡፡ አንድ እስራኤላዊ መሪ በእስራኤላዊ ወገኑ እጅ በአደባባይ በጥይት ተደብድቦ ተገደለ፡፡
እስራኤላዊው ጽንፈኛ ነፍስ ገዳይ ይጋል አሚር፤ የዚህ ጥቁር ታሪክ ባለቤት በመሆን በእስራኤል የፖለቲካ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ስሙን ለመጀመሪያ ጊዜ አስመዘገበ፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በከፍተኛ ደረጃ ተስፋቸውን ጥለውበት በነበረው የሰላም ዘንባባ ላይ ይጋል አሚር የጥፋት ቦንብ አጠመደበት፡፡
ከዚህ እጅግ አሳዛኝ ክስተት በኋላ የእስራኤልን የፖለቲካ መድረክ በዋናነት መቆጣጠር የቻሉት “ቡልዶዘር” በሚል የቅጽል ስም የሚጠሩት ኧርየል ሻሮን ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ዛሬ የት ነው ያሉት ብላችሁ አትጠይቁኝ፡፡
የሆኖ ሆኖ በእስራኤል የፖለቲካ መድረክ እንደ አርያል ሻሮን ያለ አወዛጋቢ ፖለቲከኛና መሪ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ኧርየል ሻሮን ከአስራ አራት አመታቸው ጀምሮ ለእስራኤል ነፃነት ነፍጥ አንስተው ተዋግተዋል፡፡ ለሃያ አምስት አመታት ካገለገሉበት የእስራኤል የመከላከያ ሰራዊት በጡረታ ሲገለሉ ማዕረጋቸው ሜጀር ጀነራል ደርሶ ነበር፡፡
የጦር መሪ እያሉ በ1956 ዓ.ም በተካሄደው የስዊዝ ጦርነት፣ በ1967 ዓ.ም በተካሄደው የስድስቱ ቀን ጦርነትና በ1973 ዓ.ም በተካሄደው የዮም ኪፑር ጦርነት ተሳትፈው ዛሬም ድረስ በአድናቆት የሚነገርላቸውን አንፀባራቂ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ከጦር ሃይሉ ጡረታ ከወጡ በኋላ በ1973 ዓ.ም የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) አባል ሆነው ሲመረጡ ዋነኛ የሰላም ስምምነት ደጋፊ ነበሩ፡፡ በ1981 ዓ.ም የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው እንደተሾሙ፣ ሀገራቸው እስራኤል ከበርካታ ሀገራት ጋር ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት እንድትመሠርት ማድረግ ችለዋል፡፡ የ”ሙዜ ዘመቻ” እየተባለ በሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራአሎችን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ በተካሄደው ዘመቻ፤ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን በሱዳን በረሃ ሲባዝኑ የነበሩትን በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ለተስፋይቱ ሀገራቸው እንዲበቁ አድርገዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ሁሉ ታዲያ ኧርያል ሻሮን ከውዝግብ ርቀው አያውቁም፡፡
የሰላም ስምምነቶችን በመደገፍ ይታወቁት የነበሩት ሰውዬ፤ የወግ አጥባቂው የሊኩድ ፓርቲ መሪ በመሆን በ2001 ዓ.ም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ስልጣን እንደጨበጡ ህዝባቸውም ሆነ መላው አለም አይቶት የማያውቀውን የተለየ ገጽታቸውን በግልጽ አሳዩ፡፡
ከሚመሩት የወግ አጥባቂው የሊኩድ ፓርቲ ውስጥ እጅግ ጽንፈኛ የሆነውን ሱድን በመምራት በአጐራባች የአረብ አገራት በተለይ ደግሞ በፍልስጤማውያኑ የአርነት ድርጅት ላይ እጅግ አክራሪ አቋም ይዘው ማራመድ ጀመሩ፡
“ኢንቲፋዳ” እየተባለ የሚታወቀውን የፍልስጤማውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴም መጠኑን እጅግ ያሳለፈ ሃይል በመጠቀም ሰጥ አደረጉት፡፡
በእስራኤል በወረራ በተያዙት የፍልስጤማውያን አካባቢዎች ላይም የእስራኤላውያን የመኖሪያ ሰፈሮች እንዲገነቡ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ፍልስጤማውያን ጠላቶችን በሀይል መደምሰስ እንጂ የሰላም ስምምነት ብሎ ነገር ፋይዳቢስ ነው ሲሉ በይፋ መግለጫ ሰጡ፡፡ እስራኤላውያን “ቡልዶዘር” የሚል ቅጽል ስም ያወጡላቸው ያለ ነገር እንዳልሆነም ለወዳጅም ሆነ ለጠላታቸው ግልጽ ሆነ፡፡ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በይስሀቅ ራቢን ጊዜ እጅግ ቅርብ ሆኖ ይታይ የነበረው ሰላም፣ በኧርያል ሻሮን አመራር እልፍ ክንድ ወደኋላ ተወረወረ፡፡ ኧርየል ሻሮንም የረገጡትን ሁሉ እየደረማመሱ መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡
እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ በመሆኗ ቅድስት ቦታነቷ ለእስራኤል ብቻ ከመሠላችሁ በእርግጥ ተሳስታችኋል፡፡ ፍልስጤማውያንም ወደፊት ለሚመሠርቷት ነፃና ሉአላዊት ፍልስጤም ዋና ከተማነት የመረጧት እቺኑ ኢየሩሳሌምን ነው፡፡ በቅዱስ ቦታነቷም ቢሆን ለፍልስጤማውያንም ሆነ ለመላው ሙስሊሞች ከመካና መዲና ቀጥሎ ያለች ቅዱስ ቦታቸው ነች፡፡ እናም የእየሩሳሌም ከተማ ነገር ልክ እንደ እስራኤላውያን ሁሉ ለፍልስጤማውያንም ተራና ቀልድ ነገር አይደለም፡፡
መላው ሙስሊሞች ከመካና መዲና ቀጥሎ ቅዱስ ነው የሚሉትና “አል አቅሳ” እያሉ የሚጠሩት ታላቅ መስጊድ የሚገኘው በሳኡዲ አረብ ሳይሆን በእየሩሳሌም ከተማ ነው፡
ቅዱሱ የአልአቅሳ መስጊድ ከሌሎች መስጊዶች ሁሉ የተለየ ባህርይ ተላብሷል፡፡ ይህ መስጊድ በየትኛውም የአለማችን ክፍል ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ የሙስሊሞች መስጊድ ብቻ አይደለም፡፡ በጀርባው በኩል ያለው ግማሽ ክፍሉ የአይሁዶች ቅዱስ ምኩራብ ነው፡፡ እናም በእየሩሳሌም የሚገኙ ሙስሊሞችና ይሁዲዎች የየራሳቸውን ሀይማኖታዊ ስነ ስርአት ለመፈፀም በአንድ ጊዜ መስጊድም ምኩራብም ወደ ሆነው ወደዚህ ቅዱስ ቦታ በአንድ በር ይገባሉ፡፡
ሙስሊም ፍልስጤማውያንም ሆነ ይሁዲ እስራኤላውያን ለበርካታ ዘመናት አንዳቸው አንዳቸውን አክብረው በዚህ ቅዱስ ሀይማኖታዊ ስፍራ የየራሳቸውን የሀይማኖት ስርአት እየፈፀሙ በሰላም ኖረዋል፡፡ 2000 አ.ም ግን ለእስራኤላውያንም ሆነ ለፍልስጤማውያን አስቸጋሪ አመት ነበር፡፡ በእስራኤል ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በኢንቲፋዳ አመጽ ለመግለጽ ነቅለው የወጡት ፍልስጤማውያን ወጣቶች፣ ከድንጋይ ውርወራ እስከ አውቶብስ ማፈንዳትና ሮኬት በመተኮስ በእስራኤላውያን ላይ የተቻላቸውን ያህል ሽብር በመልቀቅ ከፍ ያለ ጉዳት ሲያደርሱ እስራኤል በበኩሏ፣ ለፍልስጤማውያን የአመጽ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ወታደራዊ ሀይል በመጠቀም የአፀፋ መልስ ሰጠች፡፡ እስራኤል ከፍተኛ ወታደራዊ ሃይል ተጠቀመች የሚለው አባባል ምናልባት ትክክለኛውን ሁኔታ በግልጽ የማያሳይና አሳሳች ሊሆን ይችላል፡፡
በወቅቱ እስራኤል የወሰደችው ከፍተኛ ወታደራዊ እርምጃ ድንጋይ የሚወረውሩ ያመፁ ፍልስጤማውያን ወጣቶችን በአነጣጣሪ ተኳሾች መግደልና የመኖሪያ ሰፈሮቻቸውን ከፊቱ ዶዘር በተገጠመላት ታንክ መደረማመስ ነበር፡፡ እስራኤል በወሰደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ ከፍተኛ አለምአቀፋዊ ትችትና ወቀሳ ቢደርስባትም ከቁብ አልቆጠረችውም፡፡
ከወቀሳና ከትችት የተቆጠቡት ሀገራት ደግሞ የጀርመኖችን አባባል በመጥቀስ፤ ወታደራዊ እርምጃዋ የማታ ማታ ሊያስከትልባት የሚችለውን ዘላቂ ችግር በገደምዳሜ ለመጠቀም ሞክረው ነበር፡፡ ጀርመኖች “ከክፉ ስራው ያልታገታና ክፋቱን ያልገራ እርሱ የበለጠ ክፉ ነገርን በራሱ ላይ ይጋብዛል” ይላሉ፡፡ አባባሉን የተጠቀሙበት እስራኤል የራሷንም ክፉ ድርጊት በእርጋታ እንድትገመግምና የበለጠ አስቸጋሪ ሁኔታን በራሷ ላይ እንዲፈጠር ከማድረግ እንድትቆጠብ ለመምከር ነበር፡፡ ምክሩ ግን አልሰራም፡፡ ይልቁንም እስራኤል የተረዳችው ገልብጣ ነበር፡፡ ለእስራኤል የዚህ አባባል ትርጉም “ይህቺ ባቄላ ካደረች…” የሚለው ነበር፡፡ እናም አመፃቸውን ድንጋይ በመወርወር ለገለፁት ፍልስጤማውያን በጥይት መልስ ሰጠች፡፡
እስራኤል እንዲህ ድርጊቷ ማሳካት የቻለችው ከተሞችን ከፍልስጤማውያን አመጽ ለጊዜው ፋታ እንዲያገኙና ፀጥ ረጭ እንዲሉ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡
የጥይት እራት ከመሆንና በእስር ቤት ከመታጐር የተረፉት ፍልስጤማውያን ወጣቶች፤ ለጊዜው ድንጋይ ውርወራቸውን አቁመው በየቤታቸው አድበው ቢቀመጡም ልባቸው ግን ልክ እንደቀድሞው በአመጽና በነፃነት ትግል እንደነደደ ነበር፡፡ እናም እየተከታተሉ ከሚያልፉት ቀኖች በአንደኛው ምን አይነት አዲስ አመጽ ሊፈነዳ እንደሚችል ከተራ ግምት በቀር ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም ነበር፡፡
ሽቅብ እየወጣ ያለው ከፍተኛ ውጥረት ወላፈኑ የሁለቱን ደመኛ ህዝቦች ፊት መጋረፍ በጀመረበት የ2000 ዓ.ም የመስከረም ወር ላይ፣ ቡልዶዘሩ ኧርያል ሻሮን የትኞችም ወገን ያደርጉታል ብለው ያልገመቱትን ቀላል ነገር ግን እጅግ ጠንቀኛ ድርጊት ፈፀሙ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ በርካታ የግል ጠባቂዎቻቸውንና ወታደሮችን አስከትለው ካላጡት ቀን በአርብ ምድር ወደ አልአቅሳ መስጊድ በማምራት እጅግ በርካታ ፍልስጤማውያን የጁምአ ፀሎት ለማድረስ ተንበርክከው ባሉበት የመስገጃ ምንጣፋቸውን እየረገጡ ወደ አይሁዶች ምኩራብ ለማለፍ ሞከሩ፡፡
እንዲህ ያለው የኧርያል ሻሮን ድርጊት ለእስራኤል የሚያስገኘው አንዳችም አይነት ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ድርጊቱ ተራና ቀሽም ጠብ አጫሪነት ነበር፡፡ እናም የፍስልጤማውያንን ትዕግስት በአጓጉል ሰአትና ሁኔታ የደረመሱት ቡልዶዘሩ ኧርያል ሻሮን፤ የፈለጉትን ጠብ ያገኙት የተፉት ምራቅ ሳይደርቅ ነበር፡፡ ፍልስጤማውያን በከፍተኛ ቁጣና ምሬት ሆ ብለው ተነሱ፡፡ ከአልአቅሳ መስጊድ የተቀሰቀሰው አመፃቸው በብርሃን ፍጥነት ድፍን እየሩሳሌም ከተማን ቁና አደረጋት፡ በአመፁ ጥቂት እስራኤላውያን ጉዳት ሲደርስባቸው በርካታ ፍልስጤማውያን ደግሞ በእስራኤል ወታደሮች ጥይት ወደቁ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን በአልአቅሳ መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳሉ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ሴቶችና ህፃናት ነገሩን እጅግ አሳዛኝና የከፋ እንዲሆን አደረገው፡፡
ይህን የከፋና አሳዛኝ ግጭት ሆን ብለው አስበውና አቅደው የፈጠሩት ኧርያል ሻሮን ስለሆኑ ተገቢውን ፍርድ ማግኘት አለባቸው በሚል የውግዘት ናዳ ቢወርድባቸውም ኧርያል ሻሮን እንደተለመደው ከቁምነገር አልጣፉትም ነበር፡፡ እንዲያውም ይባስ ብለው ፍልስጤማውያን አደብ ገዝተው ካልተቀመጡ የእስራኤል መንግስት ከዚህ የበለጠ ከረር ያለ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቁ፡፡ ለተከታታይ ቀናት በእስራኤል ቴሌቪዥን ብቅ እያሉም ይህንኑ ማስጠንቀቂያቸውን ሲሰጡ ሰነበቱ፡፡
ኧርያል ሻሮን ይህን ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ፍልስጤማውያኑ ያዳመጡት በከፍተኛ የረዳት ማጣትና የመጠቃት ስሜት ቆሽታቸው እርር ድብን እያለ ነበር፡፡
በተናጠልና በቡድን ሆነው አንዳንዶቹ ስሜታቸውን በማልቀስ ሲገልፁ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የአጆቻቸውን ቡጢ ጨብጠውና ወደ ሰማይ አንጋጠው በአምላካቸው ስም እየማሉ በእስራኤላውያን ላይ ለበቀል ይዝቱ ነበር፡፡ በእየሩሳሌም ነዋሪ በሆኑ ፍልስጤማውያን ዘንድ ታዋቂ ከሆኑት የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ውስጥ ግን ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ስሜቱን በግልጽ ያላወጣ አንድ ፍልስጤማዊ ጐልማሳ ይገኝ ነበር፡፡
በርካታ ፍልስጤማዊ የሃይማኖት መሪዎችና የፍልስጤም አርነት ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በአልአቅሳው እልቂት በቁጭትና በልቅሶ ሲነፋረቁና ለበቀል ሲዝቱ ፍልስጤማዊው ጐልማሳ ግን በግፍ የወደቁትን የወገኖቹን ደም እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚበቀል ወስኖ ነበር፡፡ የአልአቅሳ መስጊድ ግጭት ከተፈፀመ ከሶስት ወራት በኋላ ጐልማሳው በከፍተኛ ምስጢር የመለመላቸውን ፍልስጤማዊ ወጣቶች በምስጢር ወዳዘጋጀው የመሰብሰቢያ ቦታ ለምክክር ስብሰባ ጠራቸው፡፡
ፍልስጤማውያን ወጣቶቹም በተጠሩበት ቀንና ቦታ ተገኙ፡፡ ሁሉም በወገኖቻቸው እልቂት ቆሽታቸው የደበነ ልባቸው በከፍተኛ የበቀል ስሜት የነደደና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ ሲሉ ህይወታቸውን ለመሰዋት የቆረጡ ነበሩ፡፡ ሁሉም በወጣትነት እሳት የትግል መንፈስ ተሞልተው እሳት የሚተፉ ነበሩ፡፡
ስብሰባውን የጠራው ፍልስጤማዊ ጐልማሳ የተሰበሰቡበትን ዋና አላማ በአጭሩ አስረዳቸውና ፊታቸውን ትክ ብሎ እያየ “ጥያቄ አላችሁ?” በማለት ሃይልና የአዛዥነት ቃና ባለው ድምጽ ፈርጠም ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ሁሉም ጭንቅላታቸውን በማወዛወዝ ጥያቄ እንደሌላቸው ግልጽ አደረጉለት፡፡
ቀጠለና በተመሳሳይ ድምጽ “ለድርጅታችን መጠሪያ የሚሆን አሪፍ ስም ማውጣት የሚችል ከመካከላችሁ አለ?” አለና ጠየቃቸው፡፡ ሁሉም ያልጠበቁት አይነት ጥያቄ መሆኑን በሚያስታውቅ ሁኔታ እርስ በርሳቸው እየተያዩ ዝም አሉ፡፡
“ደህና፡፡ የድርጅታችን ስም የአልአቅሳ ብርጌድ ይባላል፡፡ እናንተም የመጀመሪያዎቹ የአልአቅሳ ብርጌድ አባላት ናችሁ፡፡” አላቸው ጐልማሳው ሰውዬ፡፡ ቀጠለና “የትግል ስልታችንን በተመለከተ ሁሉንም አይነት ዘዴዎችን እንጠቀማለን፡፡ በዋናነት ግን ምን አይነት ስልት ስንጠቀም የበለጠ ውጤታማ መሆን እንችላለን ትላላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ቀደም ብለው የተመካከሩበት ይመስል ሁሉም በአንድ ድምጽ “ጠላቶቻችንን በገፍ በማጥፋት ሰማዕት መሆን” አሉት፡፡ ጐልማሳው ፍልስጤማዊ ወጣቶቹ በሰጡት መልስ መርካቱንና መደሰቱን ለመግለጽ በአድናቆት ካጨበጨበላቸው በኋላ፣ ከሰጡት መልስ ላይ “እርም ጀነትን መውረስ” የሚል ቃል ጨመረበት፡፡
ከዚህ የመጀመሪያ ስብሰባ በኋላ ለተከታታይ ስድስት ወራት ከሞላ ጐደል በየቀኑ እየተሰበሰቡ የሃይማኖትና የወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና በተለያዩ ምስጢራዊ ቦታዎች ሲወስዱ ከረሙ፡፡ ለአልአቅሳ ብርጌድ አባላት የተሠጠው ትምህርት የአጥፍቶ መጥፋት እርምጃ ለመውሰድ እንዳይፈሩ፣ ለእርምጃው ሀይማኖታዊ መልክና ዋጋ መስጠትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግም እንደ ሀማስና ሂዝቦላህ ከመሳሠሉት ፀረ ታጣቂ ቡድኖች የተለየ አድርጐአቸዋል፡፡ የሌሎቹ ድርጅቶች የርዕዮተ አለም መስመር መሰረት ያደረገው የሙስሊም ፋንዳሜንታሊዝምን ሲሆን የአልአቅሳ ብርጌድ ግን የፍልስጤም ብሔርተኝነትን ነበር፡፡
አስቸጋሪው የ2000 ዓ.ም አልቆ አዲሱ የ2001 ዓ.ም እንደተጀመረ ያ ፍልስጤማዊ ጐልማሳ አደባባይ ወጣና ለፍልስጤማውያን ነፃነት በአዲስ የትግል ስልት ጠላታቸውን እስራኤልን ፊት ለፊት ለመግጠም የተዘጋጀና “የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ” እየተባለ የሚጠራ አዲስ የፍልስጤም ታጣቂ የአርነት ድርጅት በእርሱ መሪነት መቋቋሙን ለወዳጅም ለጠላትም ይፋ አደረገ፡፡ መላው አለምም ይህ ፍልስጤማዊ ጐልማሳ ያሲር በዳዊ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ አወቀ፡፡
የ2001 ዓ.ም መገባደጃ ሲቃረብ በያሲር በዳዊ የሚመራው የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ የነፃነት ትግሉን በአዲስ ስልት አካሂዳለሁ ያለው የምሩን እንደሆነ አስመሠከረ፡፡ ወጣት አባላቶቹ ተገቢ ነው ባሉት ቦታ ሁሉ የአጥፍቶ ጠፊ የቦንብ ጥቃት በማድረስ እስራኤልን ልቧን አጠፋት፡፡ ከጥቃቱ መደጋገምና ቦታ አለመምረጥ የተነሳም መላ እስራኤላውያን በታሪካቸው ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ በራስ መተማመንና ጥበቃ በማጣት ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ወደቁ፡፡ የ2001 ዓመትን የተካው 2002 ዓ.ም የባሰውን አሳያቸው፡፡ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባላት በሚወስዱት የአጥፍቶ መጥፋት ተደጋጋሚ የቦንብ ጥቃት የተነሳ መላ እስራኤላውያን ወጥቶ በሰላም ለመግባት እርግጠኛ መሆን ባለመቻላቸው፣ ከቤታቸው ሲወጡ ቤተሠቦቻቸውን የምር ተሠናብተው እስከመውጣት ደረሱ፡፡
በዚህ የእስራኤላውያን ድርጊት መገረም የሚችል የያኔውን ሁኔታ በቅጥ መረዳት ያልቻለ ብቻ ነበር፡፡ ያኔ በእርግጥም ቤተሠቦቻቸውን ተሰናብተው እንደወጡ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባላት፣ የአጥፍቶ መጥፋት ቦንብ ሰለባ ሆነው የቀሩ በርካታ እስራኤላውያን ነበሩ፡፡
እስራኤል ሳታስበው በድንገት የመቀመጫ ላይ ቁስል የሆነባትን ይህን አዲስ ታጣቂ ቡድን አከርካሪውን ሰብራ ለማጥፋት እንደለመደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ሀይል ብትጠቀምም የተመኘችውን ውጤት በፍጥነት ማግኘት ሳይቻላት ቀረ፡፡ በአንፃሩ ያሲር በዳዊ አጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ጠላቶቻቸውን እስራኤላውያንን ጥለው የወደቁ አባላቶቹን “ጀነትን የወረሱ ተወዳጆቹ ሰማዕታት” በማለት ፎቶአቸውን በትልቅ ፖስተር ላይ እያተመ በየግድግዳው ላይ በመለጠፍ፣ ሌሎች ፍልስጤማውያን ወጣቶች የእነሱን አርአያ በመከተል የነፃነት ትግሉንና የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድን እንዲቀላቀሉ መቀስቀስ ጀመረ፡፡ ውጤቱም በእጅጉ የሚያስገርምና ተአምር የሚባል ነበር፡፡ እጅግ በርካታ የፍልስጤም ወጣቶች ብርጌዱን ለመቀላቀል በመጉረፋቸው፣ የያሲር በዳዊን ዋንኛ ስራ ከምልመላ የተረፉትን ወይንም በተለያየ ሁኔታ ብርጌዱን ለመቀላቀል ብቁ ሳይሆኑ የቀሩትን ወጣቶች እያግባባ ወደመጡበት መመለስ አደረጉት፡፡ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ መስራች መሪ የሆነው የያሲር በዳዊ ቅስቀሳ በእርግጥም የተለየና እጅግ ውጤታማ ነበር፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ፍልስጤማዊ ወጣቶች ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ጠላታቸውን በማጥፋት ለነፃነታቸው መታገል የፖለቲካም ሆነ የሀይማኖት ከፍ ያለ ዋጋ የሚያሰጥ ታላቅና የተቀደሰ ተግባር መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ ችሏል፡፡
በየፍልስጤማውያን ከተሞችና ሰፈሮች ግድግዳ ላይ የተለጠፈውን የብርጌዱን የተሰው አባላት ፎቶ፤ ፍልስጤማውያኑ እንኳን ከፍ ያሉት ወጣቶች ይቅርና ውሪዎቹ ህፃናትም የሚያዩዋቸው በከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር ነበር፡፡
እንደ ሌሎቹ የፍልስጤማውያን ከተሞች ሁሉ ከቤተልሄም ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ፈቅ ብላ በምትገኘው የቤት ጃላ ሰፈር ውስጥም በርካታ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ የተሰው አባላት ፎቶዎች በግድግዳው ላይ ተለጥፎ፣ የሰፈሩ ወጣቶች ሲወጡና ሲገቡ በአድናቆትና በፍቅር ያዩዋቸዋል፡፡
የሰማዕታቱን ፓስተር በተለይ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ሰብሰብ ብለው ለበርካታ ደቂቃዎች በፍቅር እያዩ፣ ሲያደንቁና እንደነሱ መሆንን ሲመኙ ከሚውሉት የቤት ጃላ ለጋ ወጣቶች መካከል እነ ሀምዛ፣ ዩሱፍ፣ አሊ፣ አሪፍ ነኢማ፣ ሁዳ ሁሴንና እህቱ አያት አክራስ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ከእነዚህ ወጣቶች ውስጥ ግን አያት አክራስ፤ የብርጌዱን ሰማዕታት ፓስተር ለደቂቃዎች የምታየው ከጓደኞቿ ላለመለየት በተለይ ደግሞ በፀረ ነፃነት ትግል እንዳትፈረጅ በመፍራት እንጂ ከልቧ ከመነጨ ስሜት ጨርሶ አልነበረም፡፡ ለሀገሯ ፍልስጤም ነፃነት የሚደረገውን ትግል ብትደግፍም የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ የሚከተለውን የአጥፍቶ መጥፋት የትግል ስልት ትክክለኛ ስልት ነው ብላ አትደግፍም ነበር፡፡ በተለይ አጥፍቶ በመጥፋት ሰማዕት መሆን ጀነትን ያወርሳል የሚለውን የያሲር በዳዊን ሀይማኖታዊ ስብከት ጨርሶ አትቀበልም ነበር፡፡
የአስራ ስድስት አመት ኮረዳ ለሆነችው ለአያት አክራስ፣ የያሲር በዳዊ ስብከት አባቷ ካስተማሯት የእስልምና ትምህርት የተለየ ሳይሆን ጨርሶ ተቃራኒ ነበር፡፡ አባቷ ደጋግመው እንዳስረዷት፤ ነፍሰ ገዳይ ሰው በምንም አይነት መንገድ ሀይማኖተኛ ሊሆን እንደማይችልና ገነትንም መውረስ እንደማይችል አጥብቃ ታምናለች፡፡ በእርሷ እምነት በአምላክ አምሳያ የተፈጠሩትን ንፁሀን ሠዎችን የሚገድል ሙስሊምም ሆነ የሌላ ሀይማኖት ተከታይ የሆነ ማናቸውም ሰው የአምላኩ አምሳያ የጠፋበት ነው፡፡
እናም ከሌሎቹ ጓደኞቿና ከወንድሞቿ በተቃራኒ ፖስተር ላይ ፎቶአቸው የተለጠፈውን የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባላት የምትቆጥራቸው እንደለየለት ሀጢያተኛና ወንጀለኛ እንጂ ገነትን መውረስ እንደሚችሉ ሰማዕታት አልነበረም፡፡
የአያት አክራስ ዋነኛ ህልሟና የህይወት ግቧ ትምህርትና ትምህርት ብቻ ነበር፡፡ በዚህ አፍላ የወጣትነት እድሜዋ፣ የእስራኤልን ወደርየለሽ ጭቆናና ግፍ ማሸነፍ የሚቻለው በከፍተኛ ደረጃ በመማርና በማወቅ ብቻ ነው ብላ ታምን ነበር፡፡ ይህንን እምነቷን አዘውትራ የምታጫውተው ታናሽ ወንድሟ ሁሴን በቀጥታ ባይቃወማትም “በወንዝ ውስጥ የምትኖር ከሆነ ከአዞው ጋር ተወዳጅ” የሚለውን የህንዳውያኑን አባባል በመጥቀስ ይሞግታት ነበር፡፡ እርሷ ግን ከዚህ አቋማ ለአፍታም እንኳ ሳታፈገፍግ እስከ ጥር ወር 2002 ዓ.ም ድረስ መዝለቅ ችላለች፡፡
ጥር 17 ቀን 2002 ዓ.ም ግን ለአያት አክራስ የተለየ ቀን ነበር፡፡ በዚህ ቀን የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባል የሆነ አንድ ወጣት ፍልስጤማዊ ሀደራ ከተማ ውስጥ የባትሚትዝባህ ሀይማኖታዊ ስነስርአት ይፈጽሙ በነበሩ እስራኤላውያን ላይ ለብሶት በነበረው ሰፊ ጃኬት ውስጥ የደበቀውንና በወገቡና በደረቱ ላይ የታጠቀውን ፈንጂ ድንገት አፈነዳባቸው፡፡ እርሱና በአብዛኛው የአንድ ቤተሠብ አባላት የሆነ ስድስት እስራኤላውያን በአጥፍቶ መጥፋት አደጋው ወዲያውኑ ተገደሉ፡፡
አደጋው እጅግ አስከፊ ነበር፡፡ የእስራኤል ፖሊስና የህክምና ቡድን አባላት የሟቾቹን አይሆኑ ሆኖ የተበጣጠሰ አካል በአንድ ጥቁር የፕላስቲክ ከረጢት ለማሰባሠብ ረዥም ጊዜ ወሰደባቸው፡፡ የእስራኤልና ሌሎች አለምአቀፍ የዜና አውታሮችም አሰቃቂውን ትዕይንት ለመላው አለም አዳረሱት፡፡
የዚህን አሳዛኝ ዜና የሰማችው አያት አክራስ፤ ሁሌም ተመሳሳይ ዜና ስትሰማ እንደምታደርገው ሁሉ ለማንም ሳትናገር በልቧ ድርጊቱን አወገዘች፡፡ “ሀጢያተኛ! ወንጀለኛ ነፍስ ገዳይ!” እያለች፡፡
በማግስቱ እንደ ወትሮዋ ከወንድሞቿና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ወደ ትምህርት ቤት አመራች፡፡ የጠበቃት ግን ለአመታት ትምህርቷን የተከታለችበትና የህልሟና የህይወት ግቧ የተመሠረተበት ያ የምትወደው ትምህርት ቤት ሳይሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህንፃ እንዳልሆነ ሆኖ የፈራረሰበት የፍርስራሽ ቁልል ነበር፡፡ አይኗን ማመን እያቃታት ለረዥም ሰአት ፈዛ ተመለከተችው፡፡ እንባዋ ግን ድንቡሽ ጉንጮቿን እያቋረጠ ያለማቋረጥ ይፈስ ነበር፡፡ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አጥፍቶ ጠፊዎች ዋነኛ የመመልመያ ቦታ ነው በሚል በግሬደር ያፈራረሱት የእስራኤል ወታደሮች ነበሩ - በበቀል ስሜት፡፡
ወንድሞቿና ጓደኞቿ ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ አያት አክራስ ግን ከትምህርት ቤቱ ፍራሽ ላይ ተቀምጣ ጀንበሯ እስክትጠልቅ ድረስ ስታለቅስ ቆየች፡፡ የማታ ማታ ግን በሀዘን ክፉኛ የተሠበረ ልቧን እንደያዘች እንባዋን በፀጥታ እያዘራች ወደ ቤቷ ሄደች፡፡ ጉድና ጅራት ወደ ኋላ ነው እንደሚባለው፣ እዚያም የጠበቃት እጅግ አሳዛኝ ነገር ነበር፡፡ ልክ ከሰፈሯ ስትደርስ ሰው ሁሉ ተሰብስቦ ሲጯጯህ አየች፡፡ አንዲት በመካከለኛ እድሜ ላይ የምትገኝ ሴትዮ ጥቁር ቀሚሷን እየቀደደችና ፊቷን እየጠፈጠፈች “ወዬ ልጄን! ልጄን አንጀቴን!” እያለች ትጮሀለች፡፡ ሶስት ሴቶች ደግም እጇንና አንገቷን እየያዙ ሊያረጋጉዋት ይሞክራሉ፡፡ ከምንጣፍ ላይ የተኛን አንድ ታዳጊ ልጅ ከበው ቆመዋል፡፡ በርካታ ቤቶች ደግሞ ፍርስርሳቸው ወጥቷል፡፡
አያት አክራስ ልቧ አለመጠን እየመታ ደረቷን የሚሠነጥቀው መሠላት፡፡ እየጮኸች የምታለቅሰው ሴትዮ፣ መልኳን በግልጽ ማየት ባትችልም እናቷ እንደሆነች ደመነፍሷ ነገራት፡፡ እናም በሩጫ ተፈተለከች፡፡ በእርግጥም እናቷ ነበረች፡፡ እናቷ ላይ ተጠምጥማ እሷም ጮክ ብላ ማልቀስ ጀመረች፡፡ “ልጄን አንጀቴን!” የሚለውን የእናቷን ለቅሶ እንደሰማችም የእናቷን አንገት ለቃ ክብብ ብለው ወደቆሙት ሰዎች አምርታ ከምንጣፉ ላይ በቁመቱ ዟ ብሎ የተኛውን ልጅ አየችው፡፡ ወንድሟ ሁሴን ነበር፡፡ ከግራ አይኑ ቅንድብ ላይ ጭንቅላቱ ተበስቷል፡፡ የለበሰው ነጭ ካናቴራና ሰማያዊ ጅንስ ሱሪው በደም ተጨማልቋል፡፡ ከሌሎች ፍልስጤማዊ ልጆች ጋር ድንጋይ በመወርወር ላይ እያሉ ነበር ከቅርብ ርቀት ላይ በእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ የፕላስቲክ ጥይት የተመታው፡፡ ወዲያውኑ ደግሞ ህይወቱን ለማትረፍ ደመነፍሱን ሲንደፋደፍ በግጭቱ የተጐዱትን ሰዎች ለመርዳት ይንቀሳቀስ የነበረ አንቡላንስ ገጨው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ህይወቱ አለፈ፡፡ አያት አክራስም የወንድሟን አስከሬን አቅፋ እሪ ብላ አለቀሰች፡፡ እናቷ፣ አባቷና ሌሎቹ የሰፈሩ ሰዎች የወንድሟን አስከሬን ደጅ ላይ አስተኝተው የሚያለቅሱት መኖሪያ ቤታቸው በእስራኤል ወታደሮች በግሬደር በመፈራረሱ እንደሆነ ስታውቅ ደግም ሀዘኑ የምትይዘውንና የምትሆነውን አሳጣት፡፡ ልቧ ለመጀመሪያ ጊዜ ቂም ቋጠረ፡፡ ቀልቧም በእስራኤላውያን ላይ ለበቀል ተነሳሳ፡፡ ከወንድሟ ቀብር በሁዋላ ያሉትን ቀናት መላው ቤተሰቧ በጐረቤት ቤት በመጠለል አሳለፈ፡፡ ትምህርት ቤቷ በመፈራረሱ ትምህርት ቆሞአል፡፡ አያት አክራስ በአንድ ጀንበር ብቻ ወንድሟን፣ መኖሪያ ቤቷንና ትምህርት ቤቷን በእስራኤል ወታደሮች የበቀል እርምጃ አጣች፡፡ እድሜዋን ሙሉ ስታልመውና የህይወቷ ግብ የነበረው ህልሟ ድንገት በኖ ሲጠፋ ታወቃት፡፡ ለጥልቀቱ ወደር የሌለው ሀዘንና ባዶነት ተሰማት፡፡
እናም አንድ ቀን ጧት ተነሳችና ታላላቅ ወንድሞቿና ጓደኞቿ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባላት ሀይማኖታዊ ትምህርት ይከታተሉበታል ብለው ወደአሳዩዋት አንድ አልባሌ ግን ሰፊ ግቢ አመራች፡፡ ሽማግሌው የግቢው ዘበኛ በሩን ከፍተው ካስገቧት በሁዋላ አንዲትም ቃል ሳይተነፍሱ፣ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ ቁርአን የሚያነብ ባለ ረዥም ጥቁር ጢማም ሰውዬ ዘንድ ወሰዷት፡፡ ጢማሙ ሰውየም እንዴትና ምን ፈልጋ እንደመጣች ጥቂት ጥያቄዎችን ካቀረበላት በኋላ የእሷ እድሜ እኩዮች የሚሆኑ አስራ አራት ወጣቶች መምህራቸውን ከበው የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት ወደሚከታተሉበት መጠኑ ሰፊ ወደሆነ ክፍል ውስጥ አስገባት፡፡ ቀጣዮቹን ሶስት ሳምንታትም በዚሁ ቤት ሀይማኖታዊ ትምህርት በመማር አሳለፈች፡፡
በአራተኛው ሳምንት የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ ሙሉ አባል በመሆን ወታደራዊ ስልጠና ወደሚሠጥበት ምስጢራዊ ቦታ ተላከች፡፡ የኢላማ ተኩስ ልምምድ ለማድረግ የመጀመሪያውን ጥይት ስትተኩስ፤ ልጅነቷ የዋህነቷና ሰላማዊ ሠውነቷ ሁሉ ከእርሷ ወጥቶ አብሮ ሲተኮስ ተማሰት፡፡ የድሮዋን አያት አክራስ በፀጥታ በሚወርደው እንባዋ ሸኘቻት፡፡ ሰላማዊው ልቧ ከፍተኛ ቂም ቋጥሮ ለበቀል አጣደፋት፡፡ አሁን የአያት አክራስ የቀን የሌሊት ህልም አንድ ብቻ ነው፡፡ በቀል፡፡ ባገኘችው አጋጣሚና መሳሪያ እስራኤላውያንን መግደል መቻል፡፡ በቃ፡፡ ይሄው ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ቀድሞ ታወግዛቸው የነበረውን የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አጥፍቶ ጠፊ ፖስተሮችን በከፍተኛ አድናቆትና የቅናት መንፈስ መመልከትና እንደነሱ ለመሆን መመኘት ጀመረች፡፡
የታህሳስ ወር 2002 ዓ.ም ሲቃረብ አያት አክራስ እንደሷው የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ አባል ከሆኑ ሶስት ወጣቶች ጋር ሆና የጁምአ ፀሎት ለማድረስ ወደ አልአቅሳ መስጊድ ሄደች፡፡ ለስግደት ከተሠበሠቡት ፍልስጤማውያን ጋር ተቀላቅላ፣ ሀሳቧንና ቀልቧን ሰብስባ “አላሁ አክበር” በማለት ለአምላኳ በግንባሯ ተደፍታ ሰገደች፡፡ “አላሁ አክበር! አላሁ አክበር” ፀሎቷን ማድረስ ቀጠለች፡፡
ፍልስጤማውያን ሙስሊሞች የአርብ ፀሎታቸውን ለማድረስ በቅዱሱ መስጊዳቸው ተንበርክከው ባሉበት ሰአት አንድ እስራኤላዊ ጐልማሳ የጥበቃ ማማውን አልፎ ወደ ሙስሊሞች መግቢያ በር አመራ፡፡ ከጥበቃ ማማው ላይ የነበረው እስራኤላዊ ወታደር ላቀረበለት ጥያቄ በእብራይስጥ ከመለሰለት በኋላ፣ በፈጣን እርምጃ ተራምዶ በሩን እንዳለፈ ለብሶት በነበረው ሹራብ ከልሎ ያነገተውን ኡዚ አውቶማቲክ ጠመንጃ በማውጣት ለፀሎት በተንበረከኩት ፍልስጤማውያን ላይ የእሩምታ ተኩስ ከፈተባቸው፡፡
ከአያት አክራስ በቀኝ በኩል አጠገቧ ስትሰግድ የነበረችው ሁሉም ነገሯ ወፍራም የሆነ ጠና ያለች ሴትዮ አንዴ ብቻ ቀጭን ድምጽ አሰምታ፣ ለስግደት በግንባሯ እንደተደፋች በዚያው ቀረች፡፡ ከማጅራቷ አካባቢ የሚፈሰው ትኩስ ደም ግማሽ ፊቷን እያለበሰ የመስገጃ ምንጣፏን ባንዴ አራሰው፡፡
አያት አክራስ ምን እንደተፈፀመ የተረዳችው ትንሽ ቆየት ብላ ነበር፡፡ ሰዎች በተኩሱ የተገደሉትን ሶስት ፍልስጤማውያን አስከሬኖችን ሲያነሱ፣ እሷ ከነበረችበት ቦታ እንኳ አልተነሳችም፡፡ “የአላህ! በቅዱሱ መስጊድ በስግደት ላይ እያለንም ይሁዲዎቹ ፈጁን፡፡” ከዚህም ከዚያም የዋይታና የምሬት ጩኸት ይሰማል፡፡ “ከይሁዲዎቹ ጥይት ሊያተርፈን የሚችል ቦታ ከእንግዲህ ምን ቀረን?” አያት አክራስ በከፍተኛ የመጠቃት ስሜት አሰበች፡፡ “ደህና! የመረጡት ይህ ከሆነማ ደህና!” በልቧ እየዛተች ወደ ተጠለሉበት የጐረቤት ቤት አመራች፡፡
መጋቢት 30 ቀን 2002 ዓ.ም በእየሩሳሌም ከተማ ጠርዝ ላይ የሚገኘው ሱፐርማርኬት እንደወትሮው ሁሉ የእለቱን ገበያውን እያከናወነ ነበር፡፡ ገበያተኞቹ ይገባሉ ይወጣሉ፡፡ ሁሉም ነገር የተረጋጋና ሰላማዊ ነበር፡፡ በዚህ መሀል አንዲት የአስራ ስድስት አመት ፍልስጤማዊ ወጣት ከእድሜዋና ከሠውነቷ ጋር አለመጣጣሙ በግልጽ የሚያስታውቅ ሠፊ ቀሚስና ጥቁር መነጽር አድርጋ ወደ ሱፐርማርኬቱ ገባች፡፡ ወዲያውኑም የሸቀጥ መያዥያ ጋሪ አፈፍ አድርጋ ያዘችና በሱፐርማርኬቱ ውስጥ ያለውን ገበያተኛ በአይኗ ማተረች፡፡ ከዚያም በርካታ ገበያተኞች ሰብሰብ ወዳሉበት አካባቢ ጋሪውን እየገፋች ተጠጋች፡፡ ከሶስት ደቂቃ በሁዋላም ሱፐርማርኬቱ በከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ተናወጠ፡፡ ሁለት እስራኤላውያን ወዲያውኑ ሲሞቱ ሀያ ሁለት የሚሆኑት ደግሞ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡ ከአንድ ሰአት በሁዋላ ደግሞ የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ ለጥቃቱ ሀላፊነቱን እንደሚወስድና ተመሳሳይ የአጥፍቶ መጥፋት አደጋ በእስራኤል ላይ ወደፊትም እንደሚፈጽም አስታወቀ፡፡ ይህን ካስታወቀ ከአርባ ሁለት ደቂቃ በሁዋላ ደግሞ ጥቃቱን ስላደረሰችው የብርጌዱ አባል የቪዲዮ ፊልም መረጃ አሰራጨ፡፡ ብርጌዱ ባሰራጨው የቪዲዮ ፊልም ውስጥ አንዲት ቆንጆ የአስራ ስድስት አመት ፍልስጤማዊ ወጣት ትታያለች፡፡ በንግግሯም በእስራኤላውያን ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቱን በማድረስ ራሷን የሰዋችው ለቅዱሱ የአልአቅሳ መስጊድ ስትል እንደሆነ ትገልፃለች፡፡ ይህች ወጣት አያት አክራስ ነበረች፡፡
የአልአቅሳ ሰማዕታት ብርጌድ ከሶስት ቀናት በሁዋላ የአያት አክራስን ፎቶ በፖስተር አትሞ በየግድግዳዎቹ ላይ ለጠፈው፡፡ የፍልስጤማውያን የነፃነት ትግል የታሪክ መጽሀፍም አያት አክራስን የአጥፍቶ መጥፋት አደጋ በማድረስ የተሠዋች ሶስተኛዋ ሴት ፍልስጤማዊ በማለት መዘገባት፡፡
የእስራኤል ወታደሮች የበቀል ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጠሉ፡፡ ፍልስጤማዊ ወጣቶችም “የሰማዕቷን” የአያት አክራስን ፖስተር እያዩ ማድነቃቸውንና የየራሳቸውን ተራ በጉጉት መጠበቃቸውን ቀጠሉ፡፡

Read 5482 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 14:26