Monday, 08 August 2022 00:00

ሥነ-ምግባር የተላበሱ መሪዎችና ተቋማት ግንባታ!

Written by  ስንታየሁ ግርማ አይታገድ
Rate this item
(0 votes)

  ታዋቂው የስራ አመራር ምሁር ፒተር ድሩከር፤ ‘በእድገት ወደ ኋላ ከቀሩ ሀገራት ይልቅ በሥራ- አመራር የተበደሉ ይበዛሉ’ በሚለው አባባሉ በብዛት ይታወሳል፡፡ አባባሉ ለሀገር ወይንም ለድርጅት እድገትም ሆነ ውድቀት ወሳኙ የሰው ሀይል በተለይም መሪዎችና ተቋማት  መሆናቸውን ያሳያል፡፡
አስሞለጉ እና ሮቢንሰን why nations fail በሚለው መፅሐፋቸው፤ አንዳንድ ሀገራት መበልፀግ የቻሉት፤ ሌሎች ደግሞ በድህነት አረንቋ የተዘፈቁት በተፈጥሮ፣ በአየር ንብረት፣ በባህል ልዩነቶች ሳይሆን አካታች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርአት በመሪዎቻቸዉ መገንባት በመቻል ወይም ባለመቻላቸው ነው ይላሉ። በተፈጥሮ ሀብት፣ በአየር ንብረት፣ በባህል መመሳሰል ቢሆን ኖሮ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በተመሳሳይ እድገት ላይ በተገኙ ነበር፡፡ ለልዩነቱ መንስኤ በደቡብ ኮሪያ ፈጠራን የሚያበረታታ ኢኮኖሚና የባለስልጣን የበላይነት ሳይሆን የህግ የበላይነት የሰፈነበት አካታች የፖለቲካ ስርአት በመገንባቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባራዊ በመደረጉ ነዉ፡፡ የዚህን አይነት አካታች ስርአት ለመገንባት ደግሞ መሪዎች በተለይም ስነ-ምግባራዊ መሪዎች መኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለዉ፡፡ በስነ-ምግባር አርአያ  የሆኑ መሪዎች አካታች ስርአት ይገነባሉ፡፡ በስነ-ምግባር የዘቀጡ ባለስልጣናት ደግሞ አግላይ ስርአት በመገንባት፣ ሙስናን ባህል በማድረግ፣ ማህበራዊ ካፒታልን በመሸርሸር ሀገርን ወደ ውድቀት አዙሪት ይከታሉ፡፡
በዚህ አለም እንደ ሥነ-ምግባር በመጥፎም ሆነ በጥሩ ለሀገርም ሆነ ለተቋማት ወሳኝ ነገር የለም፡፡ በአለም ላይ ያደጉ እና የለሙ ሀገራት መሠረታቸው ስነ-ምግባር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በአለም በከፍተኛ ፍጥነት እድገት ያስመዘገቡ የሩቅ ምሥራቅ ኤስያ ሀገራት ደግሞ እድገታቸው ከህዝብ ብሔራዊ መግባባት ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ኮሪያ የመሳሰሉት ሀገራት ሌባ እንኳን ለክቶ የሚሠርቅበት ሀገር ነበሩ፡፡ ለምሣሌ ለኤክስፖርት በተዘጋጀ ምርትና አገልግሎት ላይ የጉምሩክ ሠራተኞች ስርቆት አይፈፅሙም ነበር፡፡ መሀንዲሶች በሚገነባው ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ መንገድ የራሳቸውን 1ዐ በመቶ ኮሚሽን ይጨምሩ እንጂ በጥራቱ፣ በጊዜውና በመጠኑ ላይ አይደራደሩም ነበር፡፡ ይህንን እስቲ ከእኛ አገር ሌቦች ጋር አወዳድሩት? ከዚህ በመነሣት ሥነ-ምግባር ሙስናን ለመከላከል ወይም ለመቀነስ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ ይሁንና በባህል ቢሆን ኖሮ፣ ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ተመሳሳይ እድገት ላይ በተገኙ ነበር፡፡ ጥሩ ባህልም የተቋማት ዉጤቶች ናቸዉ፡፡ ዋናዉ ሁሉንም በእኩል የሚያገለግሉ ተቋማት መገንባት ነዉ፡፡ ማህበረሰቡ ከማንኛውም የመንግሥት ተቋም ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ትክክለኛ አገልግሎት ይጠብቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ  “ደንበኛ ሁልጊዜ ትክከል ነው፣ ሉአላዊ ነው” የሚሉት አባባሎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ይሁንታ እያገኙ ነው፡፡ ደንበኛን ለማርካት የማይጥር ድርጅት፣ ተቋምና ሀገር እራሱን በገመድ አንቆ እንደ መግደል በሚታይበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡፡ ምክንያቱም ደንበኛን /ተገልጋይን/ የሚያማልሉ አገልግሎት ሰጪዎች እንደ አሸን እየፈሉና ድንበር የለሽ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው፡፡
ምንም እንኳን ማህበረሰቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ቢጠብቅም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ግን  በተቃራኒው ሥነ-ምግባራዊ እሴቶች በመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸሩ ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አገልግሎት አሠጣጥ መላሸቅ በዋነኝነት የሚገለፀው በሙስና መልክ ነው፡፡ ሙስና የህዝብ ስልጣንን ለግል ጥቅም ወይም ትርፍ ማዋል ነው፡፡
ሙስና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ በፖለቲካው መስክ ሙስና ለህግ የበላይነትና ለዲሞክራሲ ማበብ ትልቁ እንቅፋት ነው፡፡ ሙስና በተንሠራፋበት የሰዎች እንጂ የህግ የበላይነት የለም፡፡ የህግ የበላይነት  በሌለበት ሁኔታ ተቋማት አይገነቡም፡፡ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ ደግሞ አካታች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት አይመሠረትም፡፡ በተቋማት ያልታገዘ እድገትና ልማት ዘላቂነት አይኖረውም፡፡
የዳበረ የዲሞክራሲ ባህል ባላቸው ሀገራት ሣይቀር ሙስና፤ የመንግሥት ቢሮዎች፣ ተቋማት፣ መርሆዎች ላይ እምነት በማሣጣት የቅቡልነት ቀውስ ውስጥ ይከታል፡፡ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ደግሞ የበለጠ ጉዳት ያደርሳል። ሙስና በተንሠራፋበት ሁኔታ እና ቦታ ተጠያቂነት እና ልጓም ያለው የፖለቲካ አመራር ማስፈን አይቻልም፡፡
በኢኮኖሚው መስክ ሙስና የሀገር ሀብት እንዲወድም ያደርጋል፡፡ በአብዛኛው ውስን የሆነው የህዝብ ሀብት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው አነስተኛ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ግን እጅግ አስደናቂ እና መሰረታዊ ያልሆኑ አገልግሎቶች ላይ እንዲውል ያደርጋል (ለከፍተኛ ሙስና በር ስለሚከፍቱ)፡፡ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድና ውሃ ወደ ገጠር አካባቢ እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡ ከሁሉም የከፋው ደግሞ ውድድሩን በመገደብ የነፃ ገበያ እንዳይስፋፋ ያደርጋል፡፡ ኢንቨስትመንትም ያቀጭጫል፡፡
ሙስና በህብረተሰቡ ማህበራዊ ትስስር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከሁሉም በላይ ነው። ህብረተሰቡ በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ ያለውን እምነት ያቀጭጫል፡፡ በተቋማትና በፖለቲካ መርሆዎች ላይ ያለውን ተስፋ ያጨልማል፡፡ ይህ ደግሞ በዲሞክራሲ በተመረጡ መሪዎች ሳይቀር ህሊና-ቢስ በማድረግ የህዝቡን ሀብት ወደ ውጭ ሀገር እንዲያሸሹ ይረዳቸዋል፡፡ ጉቦ መጠየቅ እና መስጠት አፀያፊ ስነ-ምግባር መሆኑ ቀርቶ የተለመደ እና ቅቡልነት ያለው ባህርይ ያደርገዋል፡፡
ስነ-ምግባራዊ መሪ መገንባት ኢትዮጵያ አሁን ለተዘፈቀችበት ብልሹ አሰራርና የሙስና ማእበል ዋነኛው መፍትሄ ነው፡፡ መሪዎች ስነ-ምግባራዊ  ሲሆኑ ተከታዮቻቸዉ ስነ-ምግባራዊ ይሆናሉ፡፡ መሪዎቹ እና ተከታዮቻቸው ስነ-ምግባራዊ ባህል ይገነባሉ፡፡ እስቲ በቀጣይ ስነ-ምግባራዊ መሪ ምን እንደሆነ፣ የስነ-ምግባራዊ መሪ መርሆች፣ ስነ-ምግባራዊ ባህል  እንዴት እንደሚገነባ እንይ፡-
ስነ-ምግባራዊ (ግብረ-ገብ) መሪ
መሪ ማለት ተከታይ ያለው ሲሆን መደበኛ ስልጣን ይኑረውም አይኑረውም ተከታይ ካለው መሪ ነው፡፡
ስነ-ምግባራዊ (ግብረ-ገብ) መሪ የሚመራበት መርህ ያለው፣ ለመርሁ የታመነ ትክክል ያልሆነውን እየተወ ትክክል የሆነውን ለመተግበር የሚተጋ፣ እውነተኛና ፍትሀዊ የሆነውን ነገር በመስራት ለተከታዮቹ አርአያ የሚሆን ማለት ነው፡፡
አመራር ሲሆን የጋራ ጥቅምን የሚያራምድና የሚተገብር፣ በማንኛውም የህይወት መመዘኛ ተቀባይነት ያለውንና ተገቢ የሆነውን ነገር የሚፈፅም ነው፡፡
በማንኛውም ጊዜ ድርጊትና አመራሩ ሥነ-ምግባር የተላበሰ ሲሆን ሥነ-ምግባራዊ አመራር ይባላል፡፡ ስነ-ምግባራዊ ተቋምና መሪ ለመገንባት መርሆዎቹን መከተልና በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። በተዋቡና በተሰደሩ ቃላት ተቋማት አይገነቡም፡፡

የስነ-ምግባራዊ መሪዎች መርሆዎች
የስነ-ምግባራዊ መሪዎች መርሆዎች ከአርስቶትል ጀምሮ ያሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ መርሆዎች ጠቀሜታቸው በተለያዩ ዲሲፕሊን ውስጥ መወያያ መሆናቸው ነው፡፡ ሥነ-ምግባራዊ መሪ ለመፍጠር መሠረቶች ናቸው፡፡
ሥነ-ምግባራዊ መሪዎች ሌሎችን /ተከታዮቻቸውን/ ያከብራሉ፡፡ ሌሎችን ያገለግላሉ (The servant-leader is servant first)
“መሪ ማለት ተከታይ ያለው ማለት ነው። ተከታይ ሳይኖር መሪ መሆን አይቻልም፡፡ እውነተኛ ተከታይ ለማፍራት ደግሞ እውነተኛ አገልጋይ መሆንን ይጠይቃል”
ትክክለኛውን ውሳኔ ይወስናሉ - ይተገብራሉ
ሐቀኝነትን (honesty) እዉነትን መናገርን በተግባር ያስመሰክራሉ
ማህበረሰብ ይገነባሉ፣ ማህበራዊ ካፒታል ይገነባሉ
መሪዎች በቃላቸዉም ሆነ በድርጊታቸዉም አርአያ  ይሆናሉ፡፡
ሥነ-ምግባራዊ ድርጅት እንዴት ይገነባል?
መልካም ስም የአንድ ሀገር ወይም ድርጅት ስኬታማነትንና ውድቀትን ይወስናል፡፡ ለዚህም ነው የአለማችን ቁጥር ሶስት ቢሊየነር ዋረን ቡፌት፤ ‘ከምንም በላይ ለመልካም ስም /Reputation/ ከፍተኛ ትኩረት እሰጣለሁ’ ያሉት፡፡ መልካም ስምን ለመገንባት ብዙ አመታት ይፈጃል፤ ለማፍረስ ግን ጥቂት ሠኮንዶች ይበቃሉ፡፡ ለዚህም ነው ጠንቃቃ ድርጅቶች ለመልካም ስም ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጡት፡፡ መልካም ሥነ-ምግባር ጥሩ ስም እንደሚገነባ ሁሉ መጥፎ ምግባር የሠራተኞችን ሞራል ይጐዳል፣ ወጪን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ መልካም ሥነ-ምግባር ለመገንባት ተቋማት ትኩረት እየሰጡ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ስለ ሥነ-ምግባር ዲዛይን ይሠራሉ፡፡ ሥነ-ምግባራዊ ባህል ለመገንባት ለአራት ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ እነርሱም፡- (1) ግልፅ የሥነ-ምግባር እሴቶችን መቅረፅ እና መተግበር፣ (2) ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት፣ (3) ማበረታቻዎችን እና (4) ተቀጣይነት ያላቸውን ባህላዊ ልምዶችን መተግበር ናቸው፡፡ እነዚህ አራቱ የባህላዊ ልምዶች ምሰሶ በመባል ይታወቃሉ፡፡
ግልፅ የሥነ-ምግባር እሴቶች መቅረፅ እና መተግበር
እስትራቴጂዎችንና ተግባራትን በአግባቡ፣ በግልፅ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ በመቅረፅ በሁሉም ሠራተኞች ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአግባቡ የተቀረፀ ተልዕኮ ያስፈልጋል፡፡ ከመርሆዎች ጋር የተጣጣመ ተልዕኮ መቅረፅ ይገባል፡፡ የሚቀረፀው ተልዕኮ አጭር፣ ግልፅ፣ ስሜትን የሚያነሳሳና የሚያስተጋባ መሆን አለበት። ይሁንና የአብዛኞቹን ተቋማት ተልዕኮ በምናይበት ጊዜ በጣም ረጅም፣ ከሠራተኞች የዕለት ተዕለት ተግባራት ጋር ያልተቀናጀና ሠራተኞች ሊመሩባቸው የሚያስችሉ መነሻ አይደሉም፡፡ የተልዕኮ መግለጫዎች በወረቀት ላይ የሚቀመጡ ቃላቶች መሆን የለባቸውም። በቅጥር፣ በስንብት፣ በእድገት ወዘተ እንደ ፖሊስ ሆነው ማገልገል አለባቸው፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የሆነውን ፔንታጐን ተልዕኮን በምናይበት ወቅት ምን ያህል ግልፅ፣ አጭርና የሚያነሣሣ መሆኑን መንዘብ ይቻላል፡፡‘’Build the best product, cause no unnecessary harm, use business and implement solutions to the environmental crisis’’.
ሚዛናዊ ፍርድ
ብዙ ሰዎች ውሣኔ በሚወስኑበት ወቅት ሥነ-ምግባርን ግምት ውስጥ የማስገባት ችግር አለባቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ሥነ-ምግባራዊ ጉድለቶች ይከሰታሉ፡፡ የትኩረት ምንጭም ይሆናሉ፡፡ ለምሣሌ የቅርብ ዘመዳችንን ወይም ጓደኛችንን ስንቀጥር በሌሎች በማናውቃቸው ሰዎች ላይ የምናደርሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ አናስገባም፡፡ አዕምሯችን ያቀበለንን መልዕክት እንደወረደ ተግባር ላይ ስናውል ሚዛናዊ ፍርድ የመስጠት እድላችንን ያጠበዋል፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ፍርድ ስንሰጥ በምናውቃቻውና በማናውቃቸው መካከል ልዩነት ላለመፍጠር ቢያንስ ሁለት ጊዜ ማሰብ ይገባል፡፡
ማበረታቻዎች
ግልፅ ተልዕኮን ከመቅረፅ እና ከመተግበር እንዲሁም ሚዛናዊ ፍርድን ከመስጠት ጐን ለጐን መልካም ሥነ-ምግባር የተላበሱ ተቋማትን ለመፍጠር ማበረታቻዎችን ከሥነ-ምግባር ጋር ማያያዝ ይገባል፡፡ ውጤት የተመዘገበው ስነ-ምግባርን ተላብሶ አገልግሎት በመስጠት ወይም ባለመስጠት መሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኞች ሥነ-ምግባራዊ ስለሆኑ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ማበረታቻዎች የተለያዩ ዓይነቶች /ውጫዊ እና ውስጣዊ/ መሆን ይገባቸዋል፡፡
ከገንዘብ ማበረታቻ በተጨማሪ ሠራተኞች የሚያረካቸውን ሥራ በመስራት አዎንታዊ ተፅእኖ ማሣደርን፣ ክብር ማግኘትና መደነቅን ይፈልጋሉ፡፡ ይሁንና የሥነ-ምግባር አመራሮች ከፋይናንስ ውጭ ያሉ ማበረታቻዎችን ትኩረት ሲሰጧቸው አይታይም፡፡ ስለ እነዚህ ማበረታቻዎች የሚሠጡት ትኩረት አናሣ ነው። ይሁንና መልካም ሥነ-ምግባር ለተላበሱ ሠራተኞች እውቅና መስጠትና ማመስገን ይገባል፡፡ ተሸላሚዎችን የሚሠጣቸውን ሽልማት ለማህበራዊ አገልግሎት እንዲያውሉት ማድረግ የበለጠ ያበረታታቸዋል፡፡ ሥነ-ምግባራዊ ባህሪ ሥነ-ምግባራዊ ሥራ ብቻ እንዲሠሩ የሚያበረታታ ብቻ ሣይሆን ጥሩ ስሜትም እንዲሰማን የሚያደርግ ነው፡፡
ባህላዊ ልምዶች
በርካታ ከፍተኛ መሪዎች አስቀድሞ ለተጠቃቀሱት የሥነ-ምግባር መለያዎች ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና ለመካከለኛው አመራር ጥብቅ ሥነ-ምግባራዊ ስታንዳርድ መቅረፅን ችላ ይሉታል፡፡ በመካከለኛው አመራር የሚቀረፅ የሥነ-ምግባር ስታንዳርድ የሠራተኞችን ባህሪ በማነፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል። ጥሩ መርሆዎች ጥሩ ተከታይ ያፈራሉ፡፡ ሆኖም ሠራተኞች በሚዋሹ፣ በሚያታልሉ፣ በሚሠርቁ መካከለኛ አመራሮች የሚከበቡ ከሆኑ የሚዋሹ፣ የሚያታልሉና የሚሰርቁ የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡ ስነምግባራዊ ተቋም የሚገነባዉ በተግባር እንጂ በተዋቡና በተሰደሩ ቃላት  አይደለም፡፡
መርሆዎች ስነ-ምግባራዊ ባህልን በማበረታታት ጥሩ ሥራዎች ምን ምን እንደሆኑ ያሣውቃሉ፡፡ ስለዚህ የሥነ-ምግባር ምልክቶችን /Ethical beacons/ ተግባራዊ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ስነ-ምግባራዊ መሪዎችንና ድርጅቶችን ለመፍጠር ትኩረት በመስጠት ለሁላችንም የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይገባናል፡፡

Read 3855 times