Saturday, 06 August 2022 12:36

“ባንኮች በሰነድ ቀሻቢዎች እየተጭበረበሩ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       አብዛኞቹ ባንኮች በ”ሰነድ ቀሻቢዎች” እየተጭበረበሩ ብድር ለማይገባቸው አካላት እየሰጡ ነው የሚሉት የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ጥላሁን ግርማ አንጎ፤ ለዚህም ምክንያቱ የበርካታ ባንኮች የብድር አፈቃቀድና አሰጣጥ የሃገሪቱን የፋይንስ ስርዓትና ደንብ የተከተለ አለመሆኑ ነው ይላሉ። በተጭበረበሩ ሰነዶች ለማይገባቸው አካላት ከባንኮች ብድር እየተሰጠ መሆኑ የሃገሪቱን ሃብት በአደገኛ ሁኔታ እንዲባክን ከማድረጉም ባሻገር፣ የማታ ማታ በአጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪውን የሚጎዳና የሃገሪቱን የፋይናንስ ስርዓትም የሚያቃውስ እንደሆነ ያስረዳሉ - ባለሙያው።
ከ15 ዓመት በላይ በባንክ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን የተመሰከረለት የሂሳብ አዋቂ (አካውንታት) ተቋም የሚመሩት አቶ ጥላሁን፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ለባንኮች እየቀረቡ ባሉ የተጭበረበሩ የብድር መጠየቂያ ሰነዶች ዙሪያ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል። ለመሆኑ የተጭበረበሩ የብድር መጠየቂያ ሰነዶች ምንድን ናቸው? ባንኮች እንዴት መከላከል ተሳናቸው? ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ማነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው? ባለሙያው በቃለ-ምልልሱ ያብራሩታል። እንደሚከተለው ይጀምራሉ፡-

           በፋይናንስ ስርዓቱ ላይ በጣም በርካታ የሚታዩኝ አደጋዎች አሉ፡፡ እኔም ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎችም እያስተዋልናቸው ያሉ አደገኛ አዝማሚያዎች አሉ። ለዚህ ነው በቀጥታ ተናግረን የሚሰማ ሲጠፋ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ደግሞ ይፋ ይሁንና ጉዳዩ ያሳስበናል የሚል አካል ይወያይበት በሚል ወደ ሚዲያ የመጣሁት፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዋጭነት ጥናት ተብለው የማይሆኑ ሠነዶች እየቀረቡ ባንኮች፣ ለተጭበረበረ የብድር ውል እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ አስፈላጊ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች - ለማይገባቸው ግለሰቦች በተጭበረበሩ የኦዲት ሪፖርቶች ብድር እየተሰጠ ነው፡፡ ባንኮች ራሳቸው እየተጭበረበሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። ይሄ አካሄድ በኋላ ላይ ልማድ ሆኖ ይሄድና የማይመለስበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስም ያሰጋኛል፡፡ እኔ አንደ አንድ የተመሰከረለት ኦዲተርና የቀድሞ የባንክ ባለሙያ የታዘብኳቸው ነገሮች፣ አዝማሚያቸው ጥሩ አይደለም፡፡
          ምንድን ነው የታዘቡት? ጉዳዩን በዝርዝር ቢያስረዱን?  
ከዚህ በፊት በራሴ መንገድ ችግሩን ላመለክት ሞክሬአለሁ፤ ግን ሰሚ አልተገኘም። ነገሩን በግልፅ ለማስቀመጥ አንድ ብድር ፈላጊ አካል ማሟላት ያለበትን ሳያሟላ ወይም በትክክል ሳያሟላ በተጭበረበሩ የአዋጭነት ጥናቶችና የኦዲት ሪፖርቶች ከባንኮች በስፋት ብድሮች እየተሠጡ ነው ያሉት። በብድር ማስያዣ የተበዳሪው ንብረት ግመታ ላይም በርካታ ማጭበርበሮች እየተፈፀሙ ነው፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ዋጋ የሚያወጣ ንብረት እያቀረቡ፣ ከፍተኛ ብድር የመውሰድ አካሄዶች በስፋት ይታያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ከ5 ሚሊዮን  ብር በላይ ለሚጠይቁ ብድሮች መሟላት ካለባቸው መስፈርቶች መካከል በተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች ምስክርነት የተሰጠባቸው የሂሳብ ስራ ሪፖርት (ኦዲት) ማቅረብ አንዱ ነው፡፡ ይሄ መመሪያ ነው እንግዲህ አሁን እየተጣሰና ለመጭበርበር እየተጋለጠ ያለው።
ማጭበርበሩ እንዴት ነው የሚከናወነው?
ብድር ጠያቂዎቹ ልክ የተመሰከረላቸው ኦዲተሮች የሚሰሩትን የሚመስል ሠነድ አዘጋጅተው የአንደኛውን የተመሰከረለት ኦዲተር ማህተምና ህጋዊ ሠነዶች ማረጋገጫ ፎርማሊቲዎችን በራሱ አስቀርጾ በመጠቀም ልክ የተመሰከረለት ኦዲተር ያረጋገጠው አስመስለው ማቅረብ አንደኛው የማጭበርበር  ስልት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክት ፋይናንስ ላይ ያለ ማጭበርበር ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ፕሮጀክት ፋይናንስ ብድር ሲጠየቅ በመጀመሪያ የአዋጭነት ጥናት ደንበኞች አስጠንተው ማቅረብ አለባቸው፡፡ ይህን ማጥናት የሚችለው ደግሞ ህጋዊነት (እውቅና ያለው) ባለሙያ ወይም ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በስተቀር ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ የአዋጭነት ጥናት በትክክለኛ ባለሙያና በትክክል መሰራታቸውን እየመረመሩ አይደለም። ለፎርማሊቲ ያህል ብቻ ይቀርባል፤ ነገር ግን በሚገባ ግለሰቡ ያቀረበው ሠነድ አይመረመርም፤ አይተነተንም። ይሔ በተጨባጭ ማስረጃ ያለው ነገር ነው። በርካቶቹ  በተጭበረበረ የአዋጭነት ጥናት ነው ብድር እየሠጡ ያሉት፡፡ ንግድ ባንክ ግን  እውነቱን ለመናገር በሚገባ ይመረምራል። ያን የአዋጭነት ጥናት አጥንቷል  የተባለው  አካል ጋ ጭምር ስልክ ደውለው ወይም በሌላ መንገድ አነጋግረው ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ነው በብድሩ ጥያቄ ላይ ምላሽ የሚሠጡት። ሌሎች ግን ይሄን እያደረጉ አይደለም፡፡
ለምንድን ነው ሌሎች ባንኮች  ሰነዶችን በሚገባ  የማይመረምሩት?
ብሄራዊ ባንክ መመሪያውን ሠጥቷቸዋል። የአዋጭነት ጥናት ማጥናት የሚችለው ፈቃድ ያለው አካል ነው ብሎ በግልጽ አስቀምጧል- መመሪያው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ለሌላ ፕሮጀክት የተሰራን ጥናት እንዳለ በመገልበጥ ወይም ትንሽ በማሻሻል ከዚያ የውሸት ማህተም በመምታት ለባንኮች ያቀርቡላቸዋል፡፡ ያንን ባንኮቹ ደግሞ በትኩረት አይፈትሹትም፡፡ ስለዚህ አዋጭ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች እነሱም አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ብድር እየሰጡ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ዞሮ ዞሮ ባንኮቹን ነው በመጀመሪያ የሚጎዳው። አዋጭ ላልሆኑ ፕሮጀክቶች የሠጡትን ገንዘብ በኋላ መልሶ ማግኘት ይከብዳቸዋል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ውስን የሆነውን የህዝብ ሃብት ለማይገባቸው ሰዎች እንዲውል ይደረጋል ማለት ነው፡፡
ይሄን መቆጣጠርና መከታተል ያለበት ማን ነው?
ብሔራዊ ባንክ ይህን መቆጣጠር አለበት፡፡ አንዳንዴ እኮ እዚያው ብድር ተጠያቂው ባንክ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች የአዋጭነት ጥናት ያጠናሉ። ራሳቸው ያጠኑትን ይገመግማሉ። ከዚያም ራሳቸው ብድሩን ይፈቅዳሉ። ራሳቸው  ፈጭተው አቡክተው ይጋግራሉ ማለት ነው። ይሄ ከመመሪያና አሠራር ውጭ ከመሆኑም በላይ ለባንኮች ደህንነትም አስጊ ነው፡፡ እነዚህ ሠዎች እየፈረዱ ያሉት በህዝብ ገንዘብ ላይ ነው። በዚያው ልክ የማጭበርበር ወንጀልም ነው። ባንኮቹም በቸልተኝነት ለዚህ መጭበረበር እየተጋለጡ ነው፡፡
ባንኮች ምን ማድረግ ይችላሉ?
እንዳልኩት በተጭበረበረ መንገድ የሚዘጋጁት ሠነዶች የሚጠቀሙት ማህተም የአንዱን የተፈቀደለት አጥኚ ኩባንያ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የባንኩ ማናጅመንት ብድሩን ከመፍቀዱ በፊት በሠነዱ አጥንተዋል ተብለው የተዘረዘሩ አካላት ጋር ደውለው በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ይሄ አድካሚ አይደለም፤ በቀላሉ ሊያደርጉት የሚችሉት ነው።
አሁን ደውለው አያረጋግጡም ማለት ነው?
በፍፁም! ከንግድ ባንክና ከልማት ባንክ በስተቀር ሌሎቹ ይሄን እያረጋገጡ አይደለም። ለምሳሌ የኔ ድርጅት ያላጠናው የአዋጭነት ጥናት በኔ ድርጅት ስም ቀርቦ ልክ ብድሩ ሊሠጥ ሲል መረጃው ደርሶኛል። በኔ ስም ወንጀል እየተሰራ ነው ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ በኦዲት ሪፖርትም ድርጅቱ የሌለውን ትርፍ እንዳተረፈ አድርገው በመስራት አስተካክለው በአንድ በተፈቀደለት የሂሳብ አዋቂ ማህተምና የኩባንያ ስም ሠርተውት ለብድር መጠየቂያ ያቀርባሉ። እነዚህ በተጨባጭ በማስረጃ ላቀርባቸው የምችለው ጉዳዮችን ነው ያነሳሁልህ፡፡
በዚህ መንገድ በርካታ ባንኮች እየተጭበረበሩ ላልተገባ አሠራር እየተጋለጡ ነው፡፡ ችግሩን ደግሞ የበለጠ የሚያወሳስበው የባንክ ባለሙያዎች በዚህ ማጭበርበር ውስጥ እየተሳተፉ መሆኑ ነው፡፡ ከባንኩ ደሞዝ እየተከፈላቸው በሌላ በኩል ብድር ሊወስድ ለመጣ ደንበኛቸው ስለከፈላቸው ብቻ የማይሆን ጥናት እያቀረቡ፣ የኛን ማህተም እየተጠቀሙ ነው ማጭበረበሩን የሚሰሩት።
በተመሳሳይ ለኢንቨስትመንት ቢሮዎች የሚቀርቡ የፕሮጀክት ጥናቶችም እንዲሁ የተጭበረበሩ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ መሬት የሚጠየቅባቸው የፕሮጀክት ጥናቶች በተመሳሳይ እየተጭበረበሩ ነው፡፡ ይሄ አዝማሚያ በአጠቃላይ አደጋው የከፋ ነው፡፡
እኒህ ፈቃድ ሳይኖራቸው ጥናት አጠናን የሚሉ፣ በተጭበረበረ ማህተም የሚጠቀሙ አካላት፣ ሌላ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አለ፡፡ እነዚህ ህገ ወጥ አካላት ታክስ አይከፍሉም፤ ስለዚህ መንግስት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያጣ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ መፍትሄ ካላገኘ እንደ ሃገር በህጋዊነት ውስጥ የተከለለ ህገ ወጥነትን እያስፋፋ ነው የሚሄደው፡፡
ለዚህ መፍትሔ መስጠት የሚችል ህጋዊ አካል የለም አንዴ?
አለ! ግን አደጋውን በአግባቡ አልተረዱትም።  አብዛኞቹ ባንኮች ለብድር ማስያዣ የሚቀርቡ ንብረቶች ላይ ነው የሚያተኩሩት፡፡ ድርጅቱ ብድሩን ከወሰደ በኋላ ምን ያህል ጠቃሚ ፕሮጀክት ላይ አዋለው የሚለውን እምብዛም ከግምት ማስገባት አይፈልጉም፡፡ ድርጅቱ ገንዘቡን ባይመልስ ያስያዘውን ንብረት መሸጥ እንችላለን በሚለው አመለካከት ላይ ብቻ ነው የታጠሩት። በዚህ በኩል ደግሞ አንዳንዱ መሬት ላይ የሌለ ንብረት እንዳለው ተደርጎ ቀርቦም እነሱኑ (ባንኮቹን) ሜዳ ላይ ሊያስቀራቸው የሚችል አካሄድም እየተስተዋለ ነው፡፡ አጠቃላይ የብድሩ ስርዓቱ በማስያዣ የቀረቡ ንብረቶችን ተመልክቶ ብቻ የሚሰጥ እንጂ ፕሮጀክቱ ለሃገር ያለው ጥቅምና አዋጭነት ከሚዛን እየገባ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ አደጋው በግልፅ ሊታየው ይገባል፡፡ ለሁሉም ባንኮች ግልፅ መመሪያ ማስተላለፍ አለበት፡፡
ምን አይነት መመሪያ?
አንደኛ ለምታበድሩት ብድር ከመፍቀዳችሁ በፊት በትክክለኛ አካል የአዋጭነት ጥናት መሠራቱን አረጋግጡ፣ የሚል መመሪያ ማስተላለፍ አለበት። በትክክለኛ አማካሪ የአዋጭነት ጥናት መጠናቱን ለማረጋገጥም፣ አማካሪዎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው ከኢትዮጵያ ማናጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ትክክለኛ የአማካሪዎች ዝርዝር እንዲቀርብ ማዘዝ አለበት። የሃገር ውስጥ ገቢም ይሄ ጉዳይ ይመለከተዋል፡፡ ምክንያቱም ያልተገቡ ጥናቶች እየቀረቡ በየባንኩ  የሚሰገሰጉ ከሆነ፣ ማግኘት ያለበትን ገቢ እያጣ ነው የሚሄደው፡፡ ይሄ ለባንኮችም ለባንክ  ባለድርሻዎችም አጠቃላይ ለሃገርም እጅግ  አደገኛ የሆነ አካሄድ መሆኑን የሚመለከታቸው ሁሉ ከወዲሁ ተገንዝበው፣ አፋጣኝ ማስተካከያ ማድረግ አለባቸው፡፡


Read 1531 times