Saturday, 06 August 2022 12:20

በኢ.እ.ፌ ምርጫ ፕሬዝዳንቱ ቢቀጥሉ፤ ለስራ አስፈፃሚው ግን...

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ነሐሴ 22 ላይ በባህርዳር ከተማ ይካሄዳል። የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  26 ለስራ አስፈጻሚና 3 ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ዝርዝርም አስታውቋል
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በሃላፊነት ለመምራት በሚካሄደው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነቱ የሚካሄደው የእጩዎች ፉክክር ያን ያህል አጓጊ አልሆነም፡፡ ለስራ አስፈፃሚ አባልነት በሚካሄደው ምርጫ ላይ  ግን እግር ኳሱን ወደ የላቀ ዘመናዊ የአስተዳደር ምዕራፍ የሚያሻግሩ እንደሚመረጡ የስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ አድርጓል፡፡ በፕሬዝዳንት መንበሩ ላይ ለመቀመጥ ሶስት እጩ ተወዳዳሪዎች  ቀርበዋል፡፡ ላለፉት 4 ዓመታት በሃላፊነቱ ላይ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከኦሮሚያ እግር ኳስ ፌደሬሽን፤ አቶ መላኩ ፈንቴ  ከአማራ እግር ኳስ ፌደሬሽን እንዲሁም አቶ ቶኩማ አለማየሁ ከድሬዳዋ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ናቸው፡፡ በስራ አስፈፃሚ አባልነት ለመወዳደር የቀረቡት ደግሞ 26 እጩዎች  ይሆናል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ለመምራት በሚከናወነው ሂደት አስመራጭ ኮሚቴውን የሚመሩት የፌዴሬሽኑ የህግ አማካሪ አቶ ሃይሉ ሞላ ናቸው፡፡ ኮሚቲያቸው የተለያዩ እግር ኳስ ፌደሬሽኖችን በመወከል በፕሬዝዳንትና ስራ አስፈፃሚ ምርጫው ላይ ለመሳተፍ የቀረቡት እጩዎችን የመወዳደር  ህጋዊ መብት አፅድቋል፡፡  ይህን ውሳኔ ተከትሎ የምርጫ አስፈጻሚው  የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ስራውን ጀምሯል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግና ብይኖችን በመስጠት እስከ ነሐሴ 6 በስራ ላይ የሚቆይ ይሆናል። ይግባኝ ኮሚቴው የመወዳደር መብቱ የተነፈጋቸውን አንዳንድ ተወካዮች የገለፀው ስራውን በጀመረበት ወቅት ነው። ከሀረሪ ውክልና የተነሳባቸው አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም ለሶስት የምርጫ ዘመን ተወዳድረው ለአራተኛ ጊዜ መወዳደር ህጉ ያልፈቀድላቸው አቶ አሊሚራህ መሀመድ ከአፋር የምርጫው ተሳትፎ ከተከለከሉት ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የምርጫ ህጉ በሚያዘው መሰረት ሶስቱ እጩዎች ከጋምቤላ በአምስት ክለቦች ያልተደገፈ መረጃ በማስገባታቸውና መመዘኛ ባለማሟላታቸው እንዲሁም ቢኒሻንጉል እጩዎችን አሟልቶ ባለማቅረቡ ከምርጫው ውጭ መሆናቸው በመግለጫው ጠቅሷል። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውን የሚያንቀሳቅሱት 3 አባላት  የስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አንበሳው እንየው፤ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድና ም/ል ፕሬዝዳንቱ  አቶ ብርሀኑ ከበደ እንዲሁም የወወክማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ጤናው ናቸው ፡፡
በምርጫ አስፈጻሚውና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በተከታታይ ከሰጧቸው መግለጫዎች በኋላ በሚቀጥሉት ሳምንታት የስፖርት ቤተሰቡ ትኩረት በአጠቃላይ ዘመቻውና የውድድር ሂደት ላይ ይሆናል፡፡ ባለፉት 4 ዓመታት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የሃላፊነት መንበር ካይ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ጅራ እግር ኳሱን  በተለያዩ ደረጃዎች ላለፉት 22 ዓመታት ማገልገላቸው ይታወቃል። በፕሬዝዳንት መንበሩ ላይ በቆዩባቸው ያለፉት አራት ዓመታትም ምስጉን ተግባራት ማከናወናቸውን ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ እግር ኳሱ በአቶ ኢሳያስ  ዘመን  በአፍሪካ ዋንጫ የብሄራዊ ቡድን ተሳትፎና በሌሎች አህጉራዊ ዋና ማጣርያ ውድድሮች የተመዘገቡ ስኬቶች፤ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሃለፊነት ቆይታ የተፈጠረው መረጋጋት፤  ከእግር ኳሱ አብይ ስፖንሰሮች ጋር ያለው ደህና ግንኙነት ከሊግ ካምፓኒና የክለቦች ገቢ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ያደጉ እንቅስቃሴዎች፤ ከሚዲያና ብሮድካስት ተያይዞ  የታዩ በጎ እርምጃዎች፤ በፅህፈት ቤት አሰራር የሚስተዋሉ መሻሻሎች ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህም በፕሬዝዳንት ምርጫው ጠቅላላ ጉባኤው ከሶስቱ እጩዎች የተሻለውን ለመሰየም የሚያዳግተው አይሆንም፡፡
ከፕሬዝዳንቱ ምርጫ ባሻገር ግን በስራ አስፈፃሚው አባላት ዙርያ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ድምፃቸውን መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በፌደሬሽኑ የሚከናወኑ የማርኬቲንግ፣ የህክምና፣ የቴክኒክ እና አስተዳደር ስራዎችን በብቃትና በእውቀት ሊሰሩ የሚችሉ አባካት ከቀረቡት እጩዎች ጎልተው እንዲወጡ  መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ነው። የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ  ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ይፋ ካደረጋቸው  እጩዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከእግር ኳስ ውጭ ልምድ ያላቸው መሆናቸው  ለማስተዋል ይቻላል፡፡ ስፖርቱን ከፖለቲካው አሰራር ለማላቀቅ አለመቻሉን ያመለከተ ዝርዝር ነው፡፡ ከስፖርቱ ጋር ባላቸው ልምድ ጎልቶ የወጣ ስም ቢኖር በስራ አስፈፃሚ ምርጫው ለመወዳደር ከአዲስ አበባ የተወከሉትየቀድሞ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አስራት  ሃይሌ ብቻ ናቸው፡፡ በሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገራት እየተለመደ የመጣው  በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስተዳደር ከስፖርቱ ጋር ቋሚ ትስስር ያላቸው፤ በሙያ ዘመን ያሳለፉ፤ በማርኬቲንግና በሚዲያ ስራዎች የሰሩና ስፖርቱን በመደገፍ የሚታወቁ እጩዎች በብዛት አለመኖራቸው የእጩዎች ዝርዝሩ ያሳብቃል፡፡
የምርጫው አስፈፃሚ ኮሚቴ በሚቀጥሉት ሳምንታት በምርጫ ዙርያ በይፋ ከሚያካሂዳቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ባሻገር ስለእጩዎች ግልፅ የሆኑ መረጃዎች የሚገኝባቸውን አሰራሮች መሞከር አለበት፡፡ የፕሬዝዳንትና ስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫውን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤው የሚወስን ቢሆንም ወደዚያ የሚያደርሰው ሂደት እንዲሟሟቅ ነው፡፡ ተወዳዳሪ እጩዎች ከእግር ኳሱ አስተዳደር ጋር ለመስራት በትምህርት፤ በልምድ፤ በሙያ ብቃት፤ የስራ ትጋት ያላቸው ዝግጁነት ለስፖርት ቤተሰቡ  በይፋ የሚገለፅበት መድረክ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ወደ ምርጫው በሚወስዱት ቀጣይ ሶስት ሳምንታት ለፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ለስራ አስፈፃሚ አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎች ለስፖርቱ ያላቸውን እቅድና ራእይ በግልፅ በሚያስቀምጡበት የምርጫ ዘመቻዎች መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ እግር ኳሱ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ካለው መለስተኛ መነቃቃት፤ በክለብ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው ኢኮኖሚ፤ ከብሮድካስት እና ከሚዲያ የሚያገኘውን ትኩረት ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ድባብ ያስፈልገዋል፡፡ በምርጫው ሂደት ላይ ጫና ይፈጥራል ተበሎ ከተሰጉ ሁኔታዎች አንዱ በመንግስትና ሌሎች አካላት ተፅእኖ መኖሩ መወሳቱ ነው፡፡ ምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፈው ሰሞን በሰጠው መግለጫ ይህን አይነቱን ተፅእኖ በአፋጣኝ በማሳወቅ መዋጋት እንደሚቻል አመልክቷል፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስሩ የሚሰባሰቡ የጉባኤው አባላትም በምርጫው ሂደት የሚመጡትን ፖከቲካዊ ንትርኮች ወደጎን በመተው በስፖርታዊና በእግር ኳሱ ህልውና ላይ ባተኮሩ አጀንዳዎች ውስጥ ሞቅ ያለ ውይይት አድርገው ድምፅ ወደ መስጠት እንዲገቡ ቀጣዮቹን ሳምንታት መጠቀም አለባቸው፡፡ ነሐሴ 22 ላይ የሚካሄደውን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ አስተዳደር ምርጫ ሊወሰን የሚገባው በተለያዩ ትንንሽ ፌደሬሽኖች የስልጣን ክፍፍል አይደለም። እግር ኳሱን ወደ ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ደረጃ ይዞ ለመውጣት በሚያስችል አቅም የሚገነባ አመራርን ለሃላፊነት የሚያበቃ ውሳኔ እንጅ። የምርጫው ውጤት በብሄራዊ ቡድን  ደረጃ ያሉ እንቅስቃሴዎች የሚያሻሽል ተስፋ የሚያለመልም፤ ከክለብ እግር ኳስ በተለይም ከሊግ ካምፓኒ በተያያዘ እያደገ የመጣው የገቢ ሁኔታ አጠናክሮ የሚያስቀጥል፤ በውድድር አካሄድና የብሮድካስት ስርጭት የታዩ መልካም ጅምሮችን የሚያፋፍም የአመራር ስብስብ ይጠበቃል፡፡  የኢትዮጵያ ስታድዬሞች የአፍሪካን ደረጃና መስፈርት ባለማሟላት የገጠማቸውን ፈታኝ ሁኔታን መፍትሄ በማስገኘት የሚሰራም አካል መመስረት ይኖርበታል፡፡  
በእግር ኳስ አካዳሚዎች፤ በስፖርት ትምህርትና የጤና መስኮች፤ በስፖርት ሚዲያ፤ ማርኬቲንግ፤ ብሮድካስቲንግና ትጥቆችና ቁሳቁሶች ምርት ላይ የሚሰማራ የስፖርት ኢንዱስትሪን ለመፍጠር ጥርጊያዎችን የሚያመቻች ስራ አስፈፃሚ የሚፈጥር እንዲሁም የስፖርት መሰረተልማቶችን በአግባቡ የሚጠቀምና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት ኢኮኖሚ የሚደግፍ ራእይ የሚያራምድም ስብስብ ማውጣት ይኖርበታል፡፡


Read 11873 times