Print this page
Saturday, 06 August 2022 14:17

አስመራቂዋ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(3 votes)

      አዳራሽ ሙሉ ሕዝብ ቆሞ አጨበጨበለት።
እሷም ከቆመው ሕዝብ መሐል ናት። አታጨበጭብም። የአድናቆት ንፍገት አይደለም ያላስጨበጨባት። ከሁሉም በላይ ለእሷ ነው ቅርበቱ።  የእሱ ስኬት ከማንም በላይ እሷን ነው የሚያስፈነድቃት።
መጀመሪያ ነገር ማን ሆነና እሱን ለዚህ ወግ  ማዕረግ ያበቃው? እሷ አይደለችም እንዴ! እሷ ባትኖር በዚህች ቀን እዚህ መድረክ ላይ ወጥቶ ዋንጫ የሚቀበለው፣ ሕዝብ የሚያጨበጭብለት፣  ዩኒቨርስቲው በጉብዝናው ለክብር የሚያጨው ሌላውን ሰው አልነበረምን?
ከፍ ወዳለው መድረክ የወጣባት መሰላሉ ናት-ምዕራፍ ሙሉጌታ። ከትቢያው አንስታ የክብር ዙፋን ላይ ያስቀመጠችው ባለውለታው ናት። ይሄን የሚያቁት እሷና እሱ ብቻ ናቸው።
“እርግማን አለብኝ!” ብሎ በራሱ ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ድንገት ደርሳ የደገፈችው፣  ወደ ምርቃቱ የጠራችው ባውለታው ናት። ሦስት ዓመት ሙሉ ከራሷ ነፍጋ ለሱ በሰጠችባቸው እጆቿ ከሕዝቡ መሐል ቆማ ላጨበጨበችው የአድናቆት ንፍገት ኖሮባት አይደለም።  አዳራሹ በጭብጨባ ይናጋል።
እሱ “በእጅግ በጣም  ከፍተኛ ማዕረግ” በመመረቁ የተበረከተለትን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ይዞ ለሕዝብ ያሳያል። በዕለቱ የክብር እንግዳ አንገቱ ላይ የተንጠለጠለለትን ሜዳሊያ አሁንም አሁንም ይሰማል።
ሕዝቡ ያጨበጭባል። ቆሞ ያደንቀዋል። እሷ በህዝቡ ተውጣ ህዝቡን እያየች ትታዘባለች።
አዳራሽ ሙሉ ሕዝብ እየተጋፋ፣ ቁመቱን ለማርዘም እየሞከረ፣ አንዱ በአንዱ አናት ላይ እየተንጠራራ ያንን ባለ ክብር ተመራቂ ለማየት ይሽቀዳደማል። ሦስት ዓመት “የት ነህ?” ያላለውን ሰው ለክብር ሲበቃ “እንኳን ደስ አለህ” ይላል። ያጨበጭባል ህዝብ… በማያገባው።  ከፊቷ ያሉት ረጃጅሞች መድረኩን ሲጋርዱባት ትናደዳለች። “እስኪ ምን አጋፋችሁ” ትላለች- ከኋላዋ የከበቧትን አስመራቂዋ እየገላመጠች።
እስኪ ምን አጋፋቸው? ትርምሱን ምን አመጣው? እሱን ብሎ የሚጋፋው ይህ ሁሉ ሰው የት ነበረ በእነዚያ የተስፋ መቁረጥ ዓመታቱ?
እስኪ ዛሬ ምን አጋፋው?
“የት ነበርክ?” ያላለ፣ “ከኔ ይቅር” ብሎ ጦም አድሮ ላቡን ለሱ ገብሮ ሳይሰለች የወር ክፍያውን ያልሸፈነ፣ ይሄው ለወግ ሲበቃ አጥር ሆኖ በዙሪያው ገጹን ከአይኖቿ ሸፈነ- ህዝቡ።
ትምህርቱን አስጀምራ፣ ከእሷ እንጂ ከእሱ ሳታጎድል ሌት ተቀን ሰርታ አስተምራ ለወግ ማዕረግ ስታበቃው “እንደግፍሽ” ያላላት፣ ፍሬዋን እንዳታይ ከለላት። ሕዝቡ ምን ነካው?... እቅፍ አበባ እንደያዘች ተረከዞቿን ትነቅላለች። በጆሮ ግንዳቸው አሾልካ ፍሬዋን ከመድረኩ ለማየት ግራ ቀኝ ትዋልላለች። ሕዝቡ ያናድዳታል። ሕዝቡ ያሳዝናታል። ይሄ ሞኝ ህዝብ ይህን ባለ ማዕረግ ወደ መድረኩ የጠራው ሰው፣ የዩኒቨርሲቲው ሬጅስራር ኃላፊ ይመስለዋል።
ሕዝብ ሲመስለው ያስቸግራል። እየገፈተረ፣ ከፊቷ እየተገተረ እንደዋዛ የወጣት ሴት ባለማዕረጉን ከጭንቀት ወደ ስኬት እንደጠራች አይጠረጥርም።
ይሄን የሚያውቀው እሱ ራሱ ብቻ ነው- የማዕረግ ተመራቂው እጮኛዋ። እሱ ሁሉንም ያውቃል። እንዴት ለዚህ እንዳበቃችው አይረሳም። ጭብጨባቸውን ጋብ አድርገው አንዲት ዕውነት እንዲናገር ፋታ ቢሰጡት፣ ምንም ሊል እንደሚችል ታውቃለች።
“ያችው ከመካከላችሁ! ፈጣሪ የሰጠኝ ሽልማቴ እሷ ናት… ምዕራፌ እሷ ናት ጀግናዋ ሴት! ሜዳሊያው ለሷ አንገት ነው የሚስማማው” ይል ነበር።
ሰው አድርጋዋለች- እጮኛው ምዕራፍ።
የምታገኛትን ደመወዝ እያብቃቃች እንደምንም አስተምራ አስመርቃለች። ለወግ አብቅታዋለች። የታጠፈ አንገቱን ቀና አድርጋ  ያው መድረኩ ላይ ሜዳሊያ አስጠልቃበታለች።
ብቻዋን ደፋ ቀና ብላ ሰው ያደረገችውን… እሱን… የማዕረግ ተመራቂውን ሮጣ ልታቅፈው ስትነሳ ግን ገርጋሪው ሰው በዛባት።
“እስኪ አሳልፉን” ስትል ደጋግማ ለምናለች።
አይሰሟትም። የሰሟትም በጎ አይመልሱላትም።
“አንቺ ብቻ ነሽ እንዴ ምታስመርቂው?” ብሏታል- አንዱ።
“እስ ረጋ በይ ምን ያንገበግብሻል!” ብሏታል ሌላው። ምነው ያ ረጋ በይ አላት? የማዕረግ ተመራቂው ያ የሴሚስተር ክፍያ ደርሶበት ከየትም ተበድራ ልትከፍልለት ስትጣደፍ ምነው ረጋ በይ አላላት?
ቸኩላለች እስክታቅፈው። አንገቱ ላይ ተጠምጥማ የሶስት ዓመት ልፋት ድካሟን ፍሬ መሳም አስቸኩሏታል።
የምረቃው ፕሮግራም ደግሞ ያለቅጥ ተንዛዛ። ምናለ ፈጠን ቢያደርጉት። ቸኩላ የምን እንዴ?... ጧት አይደለም መቸኮል የጀመረችው። የመመረቂያውን ቀን መናፈቅ ከጀመረች ቆይታለች። አደይ ሶስቴ አብባ ሶስቴ ረግፋለች። እንቅልፍ ባይኗ ሳይዞር አድራ ጧት ወደ አዳራሹ መጣች። እየሰጋች ነበር። ድንገተኛ ዝናብ ምረቃውን እንዳያስተጓለው። የፈራችው አልሆነም፡፤ የማለዳ ፀሐይ ደምቃ ወጣች።
አሁን ግን “ዝናብ  በሆነ፣ በቀዘቀዘ” ሳትል አትቀርም። ሙቀቱ የገዛችውን እቅፍ አበባ እያጠወለገው ነው። የፕላስቲክ አበባ ልትገዛለት ትችል ነበር። ሙት አበባ ለእሱ አይሆንም ብላ ተወችው። የተፈጥሮ አበባ ይዛ ጠበቀችው። ሙቀቱ ግን አበባውን አጠወለገው። በዚያ ላይ እየገፈታተሩ አበባውን ያጨማድዱባታል። መድረኩ ላይ ወጥታ ከነልምላሜው እንዳትሰጠው መንገዱን ይዘጉባታል።
ለዓመታት ነጠላውን ነበረ። አንገቱን ደፍቶ። ተስፋ ቆርጦ። ድንገት ተዋወቁና ተፋቀሩ። “ቀና በል” አለችው ምዕራፍ። አቅም አልነበረውም፣ አቅም ፈጠረችለት። ጦም እያደረች እየከፈለች አስተማረችው። ከዓመታት በኋላ ተመረቀ። መድረኩ ላይ ወጣ። እሷ ወደ መድረኩ መቅረብ አልቻለችም። እሱን ሕዝቡ ከቦታል። መንገዱን ዘግቶባታል።
የእናቶች አይን በእሱ ላይ ነው።
“አይ የኔ ጀግና” ይላሉ ልጃቸው በማዕረግ ያልተመረቀች አንድ እናት። እናቱ ቢሆኑ መመኘታቸውን ከፊታቸው ላይ ታነባለች።
የሚያውቀውም የማያውቀውም ፎቶ ሊያነሳው ይረባረባል። ከእሱ ጋር ፎቶ ለመነሳት ይጋፋል። እሷ ካሜራ የላትም። ተሸልሞ ከመድረኩ ሲወርድ ሁሉም እያቀፈ ደስታውን ይገልጽለት ጀመር። ከሱ ጋር ፎቶ ለመነሳት ወረፋው በዛ። ወረፋው ውስጥ ብዙ ሴቶች አሉ። እያቀፉ ሊስሙት የጓጉ። የሚያማምሩ። ፋሽን የለበሱ።
ከፊቷ የቆሙትን ረጅም ሽበታም ሰው ገፋ አድርጋ፣ ዝቅ ብላ ቀሚስ ጫማዎቿን አየች። የቆዩ ናቸው- ፋሽን ያልሆኑ። የሚያምር ቀሚስና ጫማ መግዛት ትችል ነበር። ደመወዟ ግን ከፍረኛዋ የኮሌጅ ክፍያ ሊተርፍ አልቻለም።
የምረቃ ፕሮግራሙ ተጠናቋል። ተመራቂዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይተቃቀፋሉ። በትርምሱ መሀል ፈለገችው። በብዙዎች ተውጧል። ብዙዎች ከበውታል።
ወረፋው በዝቷል።
ለዓመታት ነጠላውን የነበረው ሰው፣ ዛሬ በሰዎች ተከበበ። ሰዎች ተሻሙት። ከወዲያ ወዲህ እቅፍ አበባዋን ይዛ ፈለገችው። አበባዎቹ አንገታቸውን ደፍተዋል። የማዕረግ ተመራቂውን ህዝብ  ውጦ ሰውሮታል። እንባ ያቀረሩ አይኖቿ፣ አንገታቸውን የደፉትን የእቅፏ አበባዎች ያያሉ።
“በአዳራሹ ቀድሜ መገኘት ነበረብኝ” ብላ ጀመረች።
“የማይጠወልጉ የፕላስቲክ አበባዎችን መግዛት ነበረብኝ” ስትል ቀጠለች።
ቀና ብላ ዙሪያዋን ተመለከተች።
የሆነ ቦታ ተሰውሮ አይታያትም። ፈላጊዎቹ በዝተው ትርምሱ ውስጥ ተውጧል። የሆነ ቦታ በሰዎች ተከቦ ከአይኗ ተሰውሯል። ወረፋ በዝቶበታል። በቀላሉ አይገኝም። ተራ መጠበቅ አለባት።
“አስመረቅኩት” አለች።
ስላስመረቀችው ከእሷ ወጥቶ የብዙዎች ሆነ።
“አራቅኩት” አለች።
እንባዋ አመለጣት።
ከእንባዋ ጋር እሱም ሲያመልጣት ተሰማት።
(ከደራሲ አንተነህ ይግዛው “መልስ አዳኝ” አጭር ልብወለድ መድብል የተወሰደ)




Read 1045 times