Print this page
Saturday, 13 August 2022 00:00

‘የቅሽምና ኤፒዴሚክ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

“እናላችሁ... ሁላችንም እኮ የምንናገረው ስለዛኛው ቀሺምነት፣ ስለዛኛው አይረቤነት፣ ስለዛኛው እርባነቢስነት ምናምን መሆኑ አያሳዝንም! ቦተሊካችንን ታዩት የለ...በቃ የዛኛውን ቡድን ቀሺምነት፣ የዛኛውን ቡድን ባለስውር አጀንዳነት፣ ምናምን ናፋቂነት...አይነት ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስለዛኛው ቅሽምና ማውራት፣ እኛ የተሻልን መሆናችንን ማሳያ አይደለም፡፡ --”
     
         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በአንድ ወቅት ተሳፋሪና ረዳት በዋጋ ሲከራከሩ፤ “መብትና ግዴታችሁ የሚታያችሁ ታክሲ ውስጥ ብቻ ነው እንዴ! ምነው ለዳቦ ጊዜ እንደዛ አትሆኑ!” አለ የተባለው ታክሲ አሽከርካሪ...አለ አይደል...ወይ የእኛ ነገር ትክት ብሎታል፣ ወይ ደግሞ የሆነ መብት አስጠባቂ ምናምን ሊያቋቁም አስቦ ቅስቀሳ መጀመሩ  ይሆናል፡፡ አሀ...“በምን አወቅህ?” ተብሎማ አይጠየቅም፡፡ ልክ ነዋ...ዘንድሮ እኮ ስለዛኛው ሰው ንግግር፣ ስለዛኛው ሰው ድርጊት፣ ስለዛኛው ድርጅት ምናምን የራስን ‘ውሳኔ’ በፈለጉት መንገድ መተርጎም በሽ ነው። እናም ደግሞ...ይሆናሉ ብለን ሳንጠረጥራቸው እየሆኑ ያሉ ነገሮች እየበዙብን ስለሆነ “ጠርጥር ከገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር፣” የምትልዋ አባባል በየአደባባዩ ትሰቀልልንማ! ለዘመኑ ልክከ ብላ የምትመች አሪፍ አባባል ነቻ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አሁን እዛ ፈረንጆቹ ሀገር ‘ትራንስሽናል ገቨርንመንት’ ነው ምናምን የሚል ነገር አቋቁመናል  አሉ የተባሉትን የ‘ኡበር ድራይቨሮች’፣ ጠርጥረን ነበር? ቂ...ቂ...ቂ... እናላችሁ... ዘንድሮ በሰው አነጋገር፣ ተናጋሪው ያላሰበውን የራስን ድምዳሜ መስጠት ሁላችን ‘መብታችን’ ያደርግነው ስለሆነ፣ ያ ባለ ታክሲ የሆነ ነገር አስቦ ነበር ማለት ነው ብንል፣ አይገርምም ለማለት ነው፡፡ የምር ግን እሱዬው እንዲህ የተናገረው፣ የሰው ነገር ምን ያህል ቢመረው ነው! ያው የዘንድሮ የሚኒባስ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ነገር እንዳለ ሆኖ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉን፣ አንዳችንን በሌላኛችን ላይ ሲጠቀጥቁን፣ መውረድ የምንፈልግበት ቦታ ሳይሆን እነሱ ያሰኛቸው ቦታ ወስደው ሲወረውሩን፣ መብታችንን እንዲያከብሩልን ካልጠየቅን፣ ማንን ልንጠይቅ ነው!
አናላችሁ... ያው እንግዲህ ‘ሰው ማስቀየም አንወድም’ አይደል! ስለዚህ ለባለታክሲው ተመጣጣኝ መልስ የሰጠው ያለ የለም መሰለኝ፡፡ (ስሙኝማ... እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ለምሳሌ “በዚህ ቦታ ለደረሰው ጥቃት ተመጣጠኝ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል...” ሲባል እንሰማለን፡፡ ግን ደግሞ ያ ነገር እንዳይደገም ነገርዬው ከተመጣጣኝ ትንሽ ከፍ ማለት የለበትም እንዴ!) አሀ ልክ ነዋ...ታች ታቹን ሳይለማመድ ላይ ሄዶ ጉብ ያለ ማንን አየና ነው! ደግሞስ በታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ያልተለማመድን የት ሄደን ልንለማመድ ነው? ከመሰላሉ ወደ ላይ እኮ መብቴ ነው ምናምን ማለት ሳንሞክረው ቀርተን እኮ አይደለም! ነገርዬው ግን...አለ አይደል... በል፣ በል እያለን እንደ ባለመብት ሊያደርገን ስንሞክር አኮ የሚገጥመንን የምናውቅ እኛ ነን፡፡  (ስሙኝማ... ሳይቸግራቸው ወይም አዲስ ስትራቴጂ ልጠቀም ብለው፣ ወይም ንዴታቸውን መቆጣጠር አዳግቷቸው የሆነ መሥሪያ ቤት መጉላላቱ ቢበዛባቸው፣ “እኔ'ኮ ታክስ ከፋይ ነኝ!” ሲሉ ተሳቀባቸው፣ የሚባሉት ዜጋ ሰው ታሪክ ትዝ ይላችኋል? አዎ..የእኛ ነገር እንደዛ አይነት ባለታክሲ ለመንገር ነው፡፡)  
እኔ የምለው...አለ አይደል....አንዳንድ ቦታዎች ፊት ለፊታቸው ቆማችሁ እያለም፣ ከመጤፍ ሳይቆጥሯችሁ ሲቀሩ፣ ማለትም ፊት ቢነሷችሁ አንድ ነገር ነው፣እኛን ገላምጦ ሶሊቲዬር ለመጫወት መሞከር እሱም አንድ ነገር ነው፡፡ (ስሙኝማ...እንትን መሥሪያ ቤት ያላችሁ እንትናዬዎች አሁንም ሶሊቲዬር ነው የምትጫወቱት? ጌም የሚሉት ነገር እንደ ጉድ ፈልቶና በነጻ እየተገኘ አሁንም ሶሊቲዬር! የወጣቶቹን አባባል ለመዋስ ያህል... “ኸረ ይደብራል!” ሀሳብ እናቅርብማ...“ሶሊቲዬር ስንጫወት ያዩ ደንበኞች፣ ለመሥሪያ ቤታችን ያላቸው ግምት በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እያለ ስለሆነ፣ ከጊዜው ጋር ለመራመድ የሀያ አራት ሰዓት ዋይፋይ ይግባልን! ብሎ ለአለቃ ማቅረብ አሪፍ አይመስላችሁም!)
እናላችሁ...በተገቢው መንገድ ማለገልገል ስንት ማሳያ እያለው...”ከፈለግህ ሂድና ለእከሌ ንገረው!” አይነት የቢሮ ፓትርዮቲዝም ከየትኛው ሀገር ተሞክሮ የተወሰደ ነው! እነሱ “እከሌ” ብለው የሆነ ስም ለጠሩት እናንተ ደግሞ አፋችሁ የተሰፋ ይመስል ክርችም ቢልም፣ የእኛዋ ጦቢያ ነችና “የሰው ዶሮ አለና ከአፍ ከአፍ የሚለቅም፣” ብላችሁ መሳቀቁ ቀላል መሰላችሁ! እና ባለ ሚኒባስ ስማኝማ... በታሪፍ እኛን ‘ክሬዚ’ ስታደርጉን፣ ስታጠቁን መብት መጠየቅ በእናንተ ካልተለማመድን የት እንሄዳለን! ከፍ ለማለትና እዛም ደረት ለመንፋት መሞከር እኮ ታች ተለማምደን ወደ ላይ መውጣት አለብና! መቼም... ተዘሎ ፕሬሚየር ሊግ አይገባ ነገር!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ይህች ሀገር አንድም አላላውስ ያላት ችግር መene መሰላችሁ...እርስ በእርስ መናናቅ። ሁልጊዜም እኛ አሪፍ፣ ሌላው ሁሉ ቀሺም አይነት ነገር ነው፡፡ እኔ የምለው...ምንም አሪፍ የሚባል ነገር ማሳየት ሳይቻል እንዴት ነው “የአሪፍነት ኮፒራይት  ለእኔ/ለእኛ ይገባል፣” ብሎ ነገር!  ምናምን ይሰጠኝ ብሎ ነገር!
አንዳንዴ ስታስቡት እኮ...አለ አይደል... በርሊን ውስጥ ያፈረሱትን ግንብ በሆነ ዘዴ እኛ ዘንድ አምጥተው የደነቀሩብን ነው የሚመስለው! እነሱ እኮ አይታመኑም!
እናላችሁ... ሁላችንም እኮ የምንናገረው ስለዛኛው ቀሺምነት፣ ስለዛኛው አይረቤነት፣ ስለዛኛው እርባነቢስነት ምናምን መሆኑ አያሳዝንም! ቦተሊካችንን ታዩት የለ...በቃ የዛኛው ቡድን ቀሺምነት፣ የዛኛውን ቡድን ባለስውር አጀንዳነት፣ ምናምን ናፋቂነት...አይነት ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስለዛኛው ቅሽምና ማውራት፣ እኛ የተሻልን መሆናችንን ማሳያ አይደለም፡፡
“ስማ ያ ጓደኛህ...ስለእሱ ሰዎች ሲያወሩልኝ ነበር፡፡”
“የትኛው ጓደኛዬ?”
“ሂሳብ ክፍል አብሮህ የሚሠራው...”
“ማነው እሱ ጓደኛዬ ነው ያለህ?”
“አይ... ለተወሰነ ጊዜ አንድ ክፍል ስትሠሩ ስለኖራችሁ...”
“ሺህ ዓመት አብረን ብንሰራስ! ማነው አብሮ የሠራ ሁሉ ጓደኛ ነው ያለህ? ስማ እኔ ጓደኛ አጥቼ ነው እንዴ የእሱን አይነቱን የምሰበስብ!”
“እሺ፣ እሺ... በቃ ተሳስቼ ነው፡፡”
“ይቅርታ፣ ምን ነበር ልትል የነበረው?”
“ስለእሱ ሰዎች ሲያወሩልኝ ነበር ልልህ ፈልጌ ነበር...ተወው፡፡”
“ንገረኝ እንጂ ለምን እተወዋለሁ፡፡ እሱ ደግሞ ምን የሚወራ ነገር አለውና ነው!”
“እኔ እንግዲህ ያወሩልኝን ነው እየነገርኩህ ያለሁት፡፡ በጣም የሰቀለ ጉደኛ የሂሳብ አዋቂ ነው አሉ፡፡”
“አሉ! አሉ እንዴ! ጭራሽ ጉደኛ ሂሳብ አዋቂ ተባለና አረፈው፡፡ ስማ፣ የአሥር ድራፍት ሂሳብ አስቦ የአስራ አንደኛው የሚጠፋበት ነው የሂሳብ አዋቂ!”
“ታዲያ ያን ያህል ደካማ ከሆነ ከቢሮ ብቻ ሳይሆን፣ ከሄድኩዋርተርስ ሽልማት የተሰጠው ለምንድነው?”
“በዘመድ ነዋ! እኛ ገና ሲቀጠር ነው ባለዘመድ መሆኑን ያወቅነው፡፡ ስማ እሱ ብቻ አይደለም...እዛ መሥሪያ ቤት ከላይ እስከ ታች ምድረ ቀሺም የተሰበሰበበት አይደለም እንዴ! ደግሞ ጉደኛ ይባልልኛል!”
እንዲህ የሆንን ብዙዎች ነን ለማለት ያህል ነው፡፡ የምር ግን ምን መሰላችሁ...እንዲህ በችሎታም በምንም “እሱ ሰውዬ ሥራ ላይ ጎበዝ ነች፣” “እንዴት አይነት አሪፍ የአይ.ቲ. ሰው መሰለችህ!” የሚባሉ ሰዎችን ከፍ ዝቅ ማድረግ ብዙ ጊዜ የምመትሰሙት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ የሥራ ሰዓቱን ሁሉ በሥራ ላይ የሚያሳልፍና የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት ላይ ታች የሚለውም... “ሥራ ከተሠራ እንደ እሱ ነው፣” አይነት ነገር ከማለት ይልቅ ምን ብለው ጥሩ ነው...“እንዲህ የሚንቀዠቀዠው እኮ ለመታየት ብሎ ነው፡፡”  
በእንደዚህ አይነት ጊዜ ክርክር መቀጠል ዋጋ አይኖረውም፡፡ ምንም አይነት ማመሳከሪያ ብታመጡ በቃ ቀሺም ነው! ተቺው እኮ ካለበት ሳይንቀሳቀስ በር ጠባቂ ይመስል እዛቹ ቆሞ ሌላኛው ታታሪ ሦስተኛውን ዙር ጭማሪ ሲያገኝ የሆነ የሚነግረው ነገር አለ፡፡ ሁሉም እንዲህ የሚደረግለት በዘመድ ብቻ ነው ማለት ‘ፌይር’ አይሆንም፡፡ (ስሙኝማ ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በዘመድ ያስቀጠሩ፣ በዘመድ የቀጠሩና በዘመድ የተቀጠሩ ሁሉ ለአስራ አምስት ቀን የሆነ ቦታ ይቆለፍባቸው ቢባል...ስንት ዋን ፕላስ ምናምን ቪላ ሊደርሰን እንደሚችል አስቡትማ! (የክሎፕ ልጆች በቀደም ምነው ቀሸሙብንሳ! ቂ...ቂ...ቂ...)
ኸረ እባከችሁ “እኛ ብቻ አሪፎች” የሚል ነገር ተዉንማ፡፡ አሀ... ‘የቅሽምና ኤፒዴሚክ’ እያስመሰላችሁ አሳልፋችሁ አትስጡና! ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1526 times