Saturday, 13 August 2022 00:00

ግራጫው ቀለም ለህንፃው ሳይሆን፤ ለአስተሳሰባችን!

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ - ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ አሜሪካ
Rate this item
(2 votes)

በዚያ ሰሞን  “የአዲስ አበባ ህንጻዎች አንድ አይነት ቀለም ይቀቡ” የሚል መመሪያ ወጣ ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያው ሁሉም ሲያሰራጨውና ሲያራግበው  ታዝቤ ነበር። ለህንጻዎቹ የተመረጠው ቀለም ደግሞ ‘ግራጫ’ እንደሆነም ጭምር ሲወራ ነው የሰነበተው። ከከተማዋ አስተዳደር ይህ መመሪያ በእርግጥ መተላለፉ ወይም አለመተላለፉ የዚህ ጽሁፍ አጀንዳ አይደለም፡፡ ይልቁንም ጽሁፌ የሚያጠነጥነው ‘ግራጫ’ በሚለው ቃል ዙሪያ ነው፡፡ ሁላችንም በአስተሳሰባችንና በአመለካከታችን ‘ምነው ግራጫው’ ላይ  ብንገናኝ ለማለት ቢከጅለኝ ነው፣ የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ለማድረግ የወደድኩት፡፡
ግራጫ ቀለም - በጥቁርና በነጭ መሀል ያለ፣ ሁለቱ የሚገናኙበት ጥላ ወይም ማዕከል አይነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከቶውንም በሰው አስተሳሰብ ቅድና ዘዬ ውስጥ - በተለይም ለአመራርና ለመሪዎች ክሂሎት፣ ‘ግራጫ’ መንገዱን ምረጡ የሚል አስተምህሮና ትንተና አለ፡፡
ከዚህ እንነሳ፡፡ ዓለማችን - ከቶውንም አስተሳሰባችን፣ በአብዛኛው - በጥቁርና በነጭ - በሰናይና በእኩይ የተከፈለች ናት፡፡ ባለንበት ቦታ - በደረስንበትም ስፍራ የምናያቸውን የምንሰማቸውን ኹነቶች (events) ስንተረጉም ወይም አስተያየት ለመስጠት ስንንደረደር፣ የምንመለከትበት መነጽርና የምንበይንበት ሚዛናችን፣ ‘በጥቁርና ነጭ’ ይመሰላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀድሞ በተጣባን አስተሳሰብ ወይም ቀድሞ በልቡናችን ይዞታውን በተከለ ሀሳብ ላይ ተንጠልጥለን እንቀራለን፡፡  ከሁለቱ ዋልታዎች ወይም ‘ጥቁርና ነጭ’ ከሚመስሉ አፈረጃጀቶች እንዳንወጣ የሚያደርጉን ሁነቶች ይበዛሉ፡፡ በዚህ የተነሳ እኛን ያልመሰለ ሁሉ ጠላት የሚል የአፈረጃጀት ወይም የአተያይ ስሌት ውስጥ እንደምንከላወስ ለማወቅ ቆም ብለን ራሳችንን ማጤን በቂ ነው፡፡  የተቃርኖው ሂደት በፈጠረው፣ እዚያና እዚህ በሚል የአመለካከት ቅድ ውስጥ አብልጠን እንዋኛለን። በፖለቲካ ልማዳችን በተለይ በ1960ዎቹ ከተማሪ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በወረስነው የአስተሳሰብ ግትርነትና ጭፍንነት፣ በአክራሪነት  ተቃኝተናል፡፡ ተራማጅና አድሃሪ በሚል የጦዘ ቅራኔ እርስበርስ ተጠፋፍተናል፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ ዛሬም ድረስ ከተመሳሳይ የፖለቲካ ቅኝት  አልወጣንም፡፡
የፖለቲካ ባህላችን “ከእኛ ውጭ ትክክል - ከእኛ ሌላ እውነተኛ የለም” በሚል አደገኛ እሳቤ  ተበክሏል፡፡ ሀሳባችንን የሚቃወመን ሲገጥመን በሃሳብ  ከመሞገት ይልቅ ወደ ግጭት እናመራለን፤ ወደ መጠፋፋት እንገባለን። ተጻራሪ ወይም ተቀናቃኝ  እሳቤን የተቀበለ ወይም ያቀነቀነ ሰውን በተለያዩ ቅጽሎች ፈርጀን ለማጥፋት እንነሳለን፡፡ የአፈረጃጀታችን ማሽን በአግባቡ እንዲሰለጥን - ከረቂቅ ሀገራዊ - ብሔራዊ ስሜቶች ጋር በማቆራኘት ጋሻ ጃግሬ አጃቢ እንፈጥርበታለን፡፡ ባዶ ጠብመንጃ የሚሆኑንን፣ ያሻንን ቀልህ የምንተኩስባቸው ሰዎችንም እንመለምላለን፡፡
ግራጫ ሀሳብ እዚህ ላይ ነው የሚመጣው። በአንድ የህብረተሰብ ጉዞ ውስጥ የሀሳብ ብዝሃነትን ማጎልበት ለዕድገታችን ያሻናል ሲባል ብዙ ጊዜ ሰምተናል፡፡ የሀሳብ ሙግቶችና ፍጭቶችን ተቀብለን በመስማማትም - በልዩነትም የመቀጠል ባህልን የምናዳብረው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ግድ ይላል፡፡
የተሳሳተ አመለካከት እናት የሚባለውና በስነ ልቡናው ሳይንስ አዋቂዎች ዘንድ ‘ኮንፈርሜሽን ባያዝ’ የሚሉት አገላለጥ አለ፡፡ ለምሳሌ ‘የእኛ ሀገር ሰው ምቀኛ ነው’ ወይም ‘የእኛ ሀገር ሰው ቸር ነው’ በሚል ከወዲሁ የፈረጅነው አስተሳሰብ በውስጣችን ከሰረጸ ወይም ከኖረ የሚያጋጥመንን ሁሉ፣ በዚያ መነጽር የማየት አዚም አይነት ነው። ወይም አንድ ሹም “ይሄ ዘመቻ ይሠራል” ብሎ ያወጀውን ውሳኔ፣ አፈጻፀሙን ለመገምገም ሲነሳ “ዘመቻው ይሠራል’ ከሚል ነውና፣ ዓይኑ የሚማትረው - ልቡናው የሚያጤነው - “አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ወይም ድል በድል መሆኑን” ብቻ ይሆናል፡፡ እና በዚያ ሂደት የሚያያቸውን ‘ጥቃቅን’ የሚባሉ ግዙፍ ስህተቶችና ጉድለቶች እንደሌሉ አድርጎ የመመልከትና ራሱን የመሸፈን አዚም ውስጥ ይዘልቃል፡፡ እና ‘ዘመቻው ሰመረ’ ብቻ ዲስኩሩን ይቀጥላል፡፡
‹በመጀመሪያ በተለከፉበት ወይም ባገኙት እሳቤ ደንድኖ የመቀመጥ - አዳዲስ ኢንፎርሜሽን ወይም መረጃ የኛ ወገን ከምንለው ካልመጣ በቀር አልቀበልም ብሎ መፈጠም ያለጥርጥር ውስን የአስተሳሰብ አድማስን ይፈጥራል። በዛሬ ጊዜ ይህን ሰውኛ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ደካማ ጎንን የማህበራዊ መገናኛ ቴክኖሎጂያዊ ውጤቶቹ አዳብረውት የደራ ገበያ የሚያካሂዱበት ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት በዩቲዩብ’ የምንከፍታቸውና የምናያቸውን መረጃ በመሰብሰብ - ከዚያ ኩታ ገጠም የሆኑ ያንኑ ሀሳባችንን የሚያጠናክሩ ቪዲዮዎችንና ንግግሮችን ወይም መርሀ ግብሮችን በአከታታይ የቴክኖሎጂው ስሌት ይደረድርልናል፡፡ አዳዲስ ሀሳቦችንና ነባሩን የሚነቀንቁ ወይም የሚፈታተኑ አመለካከቶችን እንዳንሰማና እንዳናይ ያደርገናል፡፡  የማህበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚዎች ከሚወዱት ውጭ እንዳይወጡ - ሌሎች አመለካከቶችን እንዳያዩ በማድረግ ረገድ ሰፊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም ለማመልከት ነው፡፡ እና በተጠቃሚው ዝንባሌና ቀልቡ በወደደው ዙሪያ ማህበራዊው አውታሮች እየመገቡት አስተሳሰቡንም ከራሱ ስሌት እንዳይወጣ ገድበው ይይዙታል፡፡ ትርጓሜውም - አረዳዱም - ተግባቦቱም ከዚያ ከሚያውቀው ስሌት ሳይወጣ፣ በአንድ ሳጥን ውስጥ የሚከርም ያደርገዋል፡፡ ሌሎች ተቃራኒ እሳቤዎችን- አማራጮችን- አዳዲስ እውነታዎችን እንዳይመለከት ይገድቡታል፡፡
ዓለምን በሁለትዮሽ (binary) ብቻ ሰንጥሮ የማየት ዘይቤ እንዴት እንደምንመለከት የሚወስን ወይም ተፅዕኖ የሚያደርግ ህሊናዊ ሀይል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ዘይቤ ቀድሞ ከተያዘ አተያይ ወይም የአስተሳሰብ ሳጥን ውጭ ላለማየት ሰውን የሚገድብ ነው። ይህ አይነቱን የአስተሳሰብ አቅጣጫ ጨርሶ ከማሰብ ሂደታችን ውስጥ አውጥቶ ለመጣል ያስቸግራል፡፡ ለዚህ እንደ አንድ ማቃለያ ዘዴ ታዲያ ምሁራኑ ከሁለትዮሽ መድቦ ከማየት ውጭ ‘ግራጫ ማሰብ’ (thinking gray) የሚል አገላለጥ አላቸው፡፡ ስቲቨን ሳምፕል የተሰኙ (The Contrarian’s Guide to Leadership) በሚለው መጽሀፋቸው፣ ‘ግራጫ ስለማሰብ’ ያተቱበት፣ በተለይም ለመሪዎች የተናገሩበትን መጥቀስ ጉዳያችንን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ “አብዛኛዎቹ ሰዎች ፍርዳቸው ሁለትዮሽ እና ፈጣን ነው፡፡ ይኸውም ወዲያውኑ ነገሮችን ጥሩ ወይም መጥፎ፣ እውነት ወይም ሐሰት፣ ጥቁር ወይም ነጭ፣ ጓደኛ ወይም ጠላት ብለው ይፈርጃሉ። ይሁንና እውነተኛ ውጤታማ መሪ  በተግባሮቹ ላይ ብልህ ውሳኔ ለመውሰድ በመጀመሪያ በሁኔታው ውስጥ ያሉትን ግራጫ ጥላዎችን ለማየት መቻል ይጠበቅበታል፣” ይላሉ፡፡
‘ግራጫ ማሰብ’ በይዘቱ ወሳኝና ጠቃሚ ጉዳዮች ዙሪያ ፈጣንና የደመ ነፍስ ውሳኔ ማድረግን - ቀድሞ በተያዘ ውስን እሳቤ ተመርኩዞ፣ የመፍረድን ሂደት አይቀበልም። በሁሉም ወገን የሚመጡትን ጠቃሚ መረጃዎችን ማየትና ማመስኳትንም ይይዛል፡፡ “ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን በተመሳሳይ ጊዜ ይዞ ለመሥራት መቻል” እንደሚለው ነው፤ ስኮት ፊትዝጀራልድ፡፡ በሀሳቦች ዙሪያ ቶሎ መፍረድ ቀላልና የማያለፋ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜም በሴራ ትርክት የተያዘውን የአመለካከት ቅድና ዘይቤን ስለሚጋፋ፣ ብዙዎች ‘ከመንጋው’ የተገነጠለ ሀሳብን በተስፈንጣሪነትና ባሻቸው ዋሻ ከትተው ይዘምቱበታል፡፡ እዚህ ላይ ዋነኛ እምነቶችን ወይም መሰረታዊ መመሪያዎችን መለወጥ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ለመፍረድና ለመተርጎም ሀሳቦችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መመዘንና መመልከትን የሚያጎለብት ነው፡፡
በእኛ ሀገር ሀሳቦችን እንደ ሀሳብ ወስዶ ከመወያየት ይልቅ ሀሳቡን ያመነጨውንና የሚያንጸባርቀውን ሰው ወይም የሀሳቡን ተሸካሚ ጨፍልቆ የመመልከት አተያይ ይበረታል፡። ሀሳብን መቀበል ወይም በጊዜ በማወቅ ሊለወጥ እንደሚቻል ያስረሳል፡፡ ለጠላትነት ስሜት ቅርብ መሆንን ያመጣል፡፡ እዚህ ላይ ቆም ብለን ከጥግና ጥግ ሆኖ የመመልከት አባዜን እንዴት ልናቃልል እንችላለን? የሚል ዘይቤያዊ ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ሰዎች በተለያዩ አመለካከቶች መዥጎርጎራቸው ለበጎ እንዲሆን - እንደሆነም ማሰብ የሚያስችል የአስተሳሰብ መሰረት እንዴት ልንፈጥር እንችላለን? የሚል ጥያቄ አለ። በሰዎች የአስተሳሰብ ፊና ውስጥ ዳርና ዳር የመቀመጥ - ጥቁርና ነጭ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ አደጋው የከፋ መሆኑን በራሳችን  ታሪክ አረጋግጠናል፡፡  
ሀሳብን ከተሸካሚው አለመነጠል - በተለይ ሀገራዊ ወይም የወል በሆኑ ጉዳዮች፣ በውጤቱ ሁላችንም ተጠቃሚ እንዳንሆን ዋነኛ እንቅፋት ይሆናል፡፡ አብሮ የመኖር ትስስርን ያፋልሳል፡፡ ማለቂያ የሌለው ክፍፍልን ይከስታል፡፡ ሁላችን አሸናፊ የምንሆንበትና የሁላችን ትክክለኝነትን ያለመፈለግ አደገኛ አመለካከትንም ያመጣል፡፡  
በሊባኖስ ተወላጁ ካህሊል ጊብራን የምትጠቀስ አንድ ምሳሌ አለች፡፡ አራት እንቁራሪቶች በወንዝ ዳር ላይ ተንሳፋፊ በሆነ ግንድ ላይ ተቀምጠዋል። በድንገት  የግንዱ ጉማጅ በጅረት ተጠርጎ እየተንሳፈፈ፣ ወደ ባህሩ ይገባል፡፡ እንቁራሪቶቹ ከላዩ ላይ ቆመው ይጓዛሉ፡፡ በዚህ ሳይገረሙ አልቀሩም። እናም በመጀመሪያ አንዱ እንቁራሪት፤ “ይህ በእውነት በጣም አስደናቂ ግንድ ነው። ግንዱ እኮ ህይወት እንዳለው ነው የሚንቀሳቀሰው፣” አለ። ሁለተኛው እንቁራሪት፤  “አይ ወዳጄ፣ ግንዱ ልክ እንደ ሌሎች እንጨቶች ነው፣ እናም አይንቀሳቀስም። የሚንቀሳቀሰው እኛን የተሸከመን ባሕሩ ነው።” አለ፡፡ ሦስተኛውም እንቁራሪት ቀጠለ፤ “የሚንቀሳቀሰው ግንዱም ሆነ ወንዙ አይደለም። እንቅስቃሴው በአስተሳሰባችን ውስጥ   ነው፣” አለ፡፡
ሦስቱ እንቁራሪቶች  ሙግት ገጠሙ፡፡ ብዙ ተጨቃጨቁ፡፡ ጭቅጭቁ እየበረታ ቢሄድም ሊስማሙ ግን አልቻሉም። ከዚያም ዝም ብሎ ሲያዳምጣቸው የቆየውን  አራተኛውን እንቁራሪት አስተያየቱን  ጠየቁት፡፡ አራተኛውም እንቁራሪት፤ “ሁላችሁም ትክክል ናችሁ፣” ብሎ ጀመረ፡፡ “የሚንቀሳቀሰው ግንዱም፣ ባህሩም፣ ሀሳባችንም ነው፣” አላቸው፡፡ ሦስቱ እንቁራሪቶች በየግላቸው  አሸናፊ ለመሆን ቋምጠው ነበርና በአስተያየቱ ተበሳጩ፡፡ ሁላቸውም ማሸነፋቸውን አልወደዱትም፡፡ ስለዚህም  ሦስቱ እንቁራሪቶች ተሰብስበው፣ አራተኛውን እንቁራሪት ከግንዱ ላይ ገፍትረው ከወንዙ ደፈቁት።
ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ውድድርና የፖለቲካ ሙግት ሳይኖር ሲቀር - ሁሉንም ጥቁርና ነጭ አድርጎ ለመመልከት ሲሞከር የሚፈጠረው ቀውስ፣ የእንቁራሪቶቹን ምሳሌ አይነት ነው፡፡ በእኛ ሀገር በራስ የሀሳብ ጥንካሬና ተጠየቅ ለማሳመን ከመሞከርና በሀሳብ ልዩነት ማህጸን ለመኖር ከመጣር ይልቅ፣ ሌሎችን በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ፣ የፖለቲካ ስሪቱ ዋነኛ መለያ ከሆነ ግማሽ ምዕተ ዓመት ተቆጥሯል፡፡  ሀሳቦችን በየራሳቸው ፋይዳና ዋጋ ከመመዘን ይልቅ የሌሎች ተፎካካሪ ሀሳቦች ማጣፊያ ለማድረግ ሲሞከር ሁሌም አደጋው  የከፋ ነው፡፡
በሀገራችን አማጽያኑና መንግሥት የሚፋለሙበት ወይም የሚጋደሉበት አንዲት የገበሬ መንደር ውስጥ የተከሰተ ነው፡፡ አማጽያኑ ታጣቂዎቻቸውን አሰልፈው የመንግሥትን ወታደር ተዋግተው  ከመንደሯ ያስወጣሉ። ከዚያም የአካባቢውን ሰው ሰብስበው፤ “እነሆ ከጨቋኙ ስርዓት ነፃ አወጣናችሁ። ለእናንተ አርነት ስንል ነው የምንዋጋው” ብለው በካድሬዎቻቸው ይሰብኳቸዋል፡፡ ጥቂት ቀናት ቆይቶ ደግሞ መንግሥት በተራው  ያለ የሌለ ሀይሉን ይዞ መጥቶ፣ አማጽያኑን ዋግቶ ያባርራል። እሱም በተራው፤ “ከእነዚያ ጸረ ህዝቦች... ነጻ አወጣናችሁ፡፡ እኛ ለሕዝቡ የቆምን ነን፣” ይላል፡፡ ይህን መሰል ዥዋዥዌ እዛች መንደር ውስጥ በየጊዜው እየተፈጸመ አርሶ አደሩ ክፉኛ  ተሰቃየ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን መንግሥት አሸንፎ  እንደተለመደው አርሶ አደሩ ተሰብስቦ  ካድሬዎቹ ይደሰኩራሉ፡፡ በመሀል ታዲያ አንድ አረጋዊ ገበሬ እጃቸውን ያነሳሉ - ሊናገሩ ተፈቀደላቸው፡፡ “እኛ የምንለው፤ እናንተም ስትመጡ እነርሱም ሲመጡ፣ ለእኛ ነጻነት ስትሉ እየሞታችሁ እንደሆነ ነው የምንሰማው፡፡ በእኛ ምክንያት እናንተም እነርሱም ከምትሞቱና ከምትጋደሉ፣ እኛም በመሀል ከምንሰቃይ፣ እኛን ጨርሱንና እናንተ ባይሆን ታርቃችሁ በሰላም ኑሩ፣” አሉ፤ይባላል፡፡
የሁለትዮሽ መጓተትና መጋደል - ሀሳብ የተሸከመን በሀይል የመደፍጠጥ አዚም ይዞት የሚሞተው - የሚጨርሰው - የሚያወድመው እጅግ የበዛ ነው፡፡ እስከዛሬ በዘለቀው የፖለቲካ ልዩነቶች ሽኩቻና ገመድ ጉተታ፣ በሀገራችን የደረሰው ኪሳራ በቀላል የሚገመት አይደለም። በእርስ በእርስ ጦርነት ትውልድ የተጠፋፋበት ታሪክ እጅግ በአስከፊነቱ የሚጠቀስ፣ አሁንም ያልተፈታ ችግር  መሆኑም መረሳት የለበትም። ለምንና ስለምን እንዲህ ሆንን? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡
ግራጫው ቀለም ለህንጻው ሳይሆን  ለአስተሳሰባችን ይሁንልን!!Read 972 times