Tuesday, 16 August 2022 19:59

ይድረስ ለብልጽግና ፓርቲ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(11 votes)

 የወሎ ህዝብ በአማራ ክልል ስር በመሆኑ ምን አተረፈ? ወሎ ክልል ቢሆንስ?
         

     በቅድሚያ የአክብሮት ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህንን ርእሰ ጉዳይ በተለይ ለብልጽግና ፓርቲ “ይድረስ” ማለቴ፣ የኢህአዴግ ወራሴ መንግስት በመሆን “የገዢነትን” መንበር የተረከበና ባለፉት 30 ዓመታት የነበሩትን ጥፋቶችም ሆነ ልማቶች አብሮ የወረሰ በመሆኑ፣ በእነዚህ ዓመታት የጎደሉ ነገሮችን የማስተካከልና የህዝብን የዓመታት ጥያቄዎች የመመለስ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሆነ እንዲታወቅ እሻለሁ።
በዚህ ማስታወሻ ትኩረት የማደርግበት ዋና ጉዳይ፣ በቀድሞው አጠራር “ወሎ ክፍለ ሀገር” ይባል የነበረውን አካባቢ በተመለከተ ይሆናል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ከአካባቢው ከተለየሁ ከ30 ዓመታት በላይ የተቆጠሩ ቢሆንም፤ በዚሁ ክፍለ ሀገር ተወልጄ ያደግኩ፣ ትምህርቴንም የተማርኩ በመሆኑና ዘር ማንዘሬ እዚያው የሚኖር በመሆኑ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚያ አካባቢ መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር ይመለከተኛል ብዬ በማሰብ ነው፣ ይህቺን ጭንቀት የወለዳት ማስታወሻ ለመክተብ ብዕሬን ያነሳሁት፡፡
ታሪካዊ ዳራ
የኢንተርኔት ባህረ-ጥበብ (ኢንሳይክሎፔዲያ) የሆነው ዊኪፔዲያ ወሎን እንዲህ ይገልጻታል፡- “ወሎ በሰሜን ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ታሪካዊ አውራጃ እና ክፍለ ሀገር ሲሆን ዋና ከተማው ደሴ ነው። ከ1700 ዓ.ም በፊት ከፊል የወሎ አካል የነበረው አካባቢ ስሙ “ቤተ-አምሓራ” ይባል ነበር፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተውን የኦሮሞ ስደት ተከትሎ፣ “ቤተ-አምሓራ” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እና ከቤተ-አምሓራ በሰሜንም በምስራቅም ያሉ አካባቢዎች በአንድ ላይ ተጠቃለው “ወሎ” በሚባል ሰፊ ግዛት ውስጥ ተካተቱ፡፡ የወሎየነት ስያሜና ማንነትም ከዚህ ዘመን ጀምሮ እውን ሆነ፡፡ … የወሎ ድንበር በየዘመኑ የመስፋትና የመጥበብ ሁኔታዎች የሚታይበት ሲሆን፤ በአንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች እስከ አሰብና አውሣ ድረስ ይሰፋ ነበር…”
በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት “ወሎ ጠቅላይ ግዛት” ይባል የነበረው፤ በዘመነ ደርግ አስተዳደር ስያሜው ወደ “ወሎ ክፍለ ሀገር” ተቀየረ፡፡ በዚህ ስያሜ አሰብን ጨምሮ 12 አውራጃ አስተዳደሮችን አቅፎ እስከ 1981 ድረስ ከዘለቀ በኋላ፤ ወሎ ክፍለ ሀገር ሦስት ቦታ ላይ ተከፍሎ “ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና አሰብ ራስገዝ” ተብሎ ተዋቀረ፡፡ “ወሎ” የሚለው ማንነት መሸርሸር የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው። ኢህአዴግ የደርግን ስርዓት በኃይል በመጣል አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በተቋቋመው የሽግግር መንግስት፣ የሀገሪቱ ግዛት እንደገና ሲደራጅ፣ የወሎ ጉዳይ በወቅቱ በነበረው ምክር ቤት አጨቃጫቂ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
የወሎ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ በሽግግሩ ወቅት በአጀንዳነት ተነስቶ እንደነበር በወቅቱ ተቋቁሞ በነበረው የሽግግር መንግስት ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ ጉባዔ ላይ ሰፍሯል። ይኸው ቃለ ጉባዔ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ታትሞ ነበር፡፡ መስከረም 27 ቀን 1984 ዓ.ም የተያዘው የ16ኛው መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ እንዲህ ይላል፡- “የክልል አከፋፈሉ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ በተለይ የወሎ ብሔራዊ ክልል ችግር የጎላ በመሆኑ ከሁለት ዓመት በኋላ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ በአማራው ክልል እንዲጠቃለል ተወሰነ” ይላል፡፡ ይህም ውሳኔ በድምፅ ብልጫ የተወሰነ ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረው የድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ “ድጋፍ 44፣ ተቃውሞ 11፣ ድምጸ ተዓቅቦ 1 ነበር” በማለት ውሳኔውን አስፍሯል፡፡
ይህ የቃለ ጉባኤ ሰነድ፣ ያኔ በሽግግሩ መንግሥት የኢፌዴሪ መንግሥት ክልሎችን ሲያዋቅር የተደረገ ውይይትንና ውሳኔን የሚያሳይ ነው፡፡ ውሳኔው ብዙ ክርክር የተደረገበት መሆኑን ከውሳኔው ድምፅ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የሽግግሩ መንግሥት ዋና ፀሐፊ የነበሩትን ክቡር አቶ ተስፋዬ ሐቢሶን ሰሞኑን ጠይቄያቸው በሰጡኝ ምላሽ፤ “የወሎ ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ የወሎ ሳይኮሎጂካል ሜንታሊቲ የተለየ ነው… ለሌላው እንደ በፈር ዞን ሆኖ ያገለግላል፤ እንዳለ እንተወው ተብሎ ክርክር ነበር፡፡ በኋላ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማስታረቅ በሚመስል መልኩ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚወጣው ህገ መንግስት እልባት ያገኛል ተብሎ ታለፈ… በኋላ ሁሉም በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ ስለነበር አጀንዳው ባለበት ተረሳ…”  ብለውኛል፡፡
የወሎ ህዝብ ዘላቂ ተሟጋች ያልነበረው (አሁንም የሌለው) በመሆኑ በ1987 ዓ.ም የወጣው ሕገ መንግሥትም በሽግግሩ ወቅት በጊዜያዊነት የተሰጠውን ውሳኔ በማጽደቅ ወሎ አምስት ቦታ ላይ ተከፍሎ አራቱ (ማለትም፡- ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ እና የኦሮሞ ልዩ ዞን) በአማራ ክልል ስር እንዲሆኑ፣ የተወሰነው መሬትና ህዝብ ያለ ፍላጎቱ ወደ ትግራይ፣ የተወሰነው መሬትና ህዝብ ያለ ፍላጎቱ ወደ አፋር ክልል እንዲከለል ተደርጓል። ይህም አከላለል “ወሎ” የሚለውን ማንነት ይበልጥ ያጠፋ መሆኑ ታይቷል፡፡ በዚህ ወሎን የማጥፋት ዘመቻ ያልረኩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ባለፉት 30 ዓመታት በወሎ ላይ የፈጸሙት ወሎየነትን የማጥፋት ደባ አላንስ ብሎ፣ አሁን ደግሞ ደቡብ ወሎን ለሁለት ከፍሎ “ምዕራብ ወሎ” ወይም “ምስራቅ ግዮን” የተባለ አዲስ ዞን ለመመስረት ሽር ጉድ እየተባለ መሆኑንም እየሰማን ነው፡፡
አንዳንድ ምሁራን የወሎን የቁልቁለት ጉዞ ከተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ጋር ለማያያዝ ቢሞክሩም የሚያቀርቡት ሃሳብ ሁሉንም የሚያሳምን አይመስልም። ከታሪክ አጋጣሚዎች በላይ የወሎን ስመ ገናናነት ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰበት፣ የወሎን ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቅ ተሟጋች የፖለቲካ ኃይል የሌለ በመሆኑ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች፤ ባለፉት 30 ዓመታት የወሎ ህዝብ በአማራ ክልል ስር በመሆኑ ምን አተረፈ? ምንስ አጣ? ወሎ በአማራነትስ ምን ተጠቀመ? ወሎዬ በአማራነት ምን ዋጋ ከፈለ? የወሎ ህዝብ መሰረታዊ ስጋት በምን ሊቀረፍ ይችላል? - በክልል መዋቅር ክለሳ ወይስ በአማራነታዊ ውህደት? ወይስ ራሱን ችሎ ክልል በመሆን?... የሚሉትና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች  ናቸው። አሰላሳይ እና ቆራጥ አመራር ካለ ወሎንም ወሎየነትንም መታደግ ይቻላልና፣ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰብኳቸውን ወሎ ክልል እንዲሆን የተፈለገበትን ምክንያት የሚያሳዩ ሁኔታዎች ቀጥለን እንይ።
“ወሎ ክልል” - ለምን?
ወሎ ክልል እንዲሆን የብዙ ወሎየዎች ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ፍላጎት በስሜታዊነት የሚቀነቀን አጀንዳ አይደለም፡፡ ይህ ፍላጎት የ30 ዓመት በደል የወለደው ነው፡፡ ወሎ ክልል ይሁን እያልን ያለነው፣ ወሎ በአማራ ክልል ካሉ ሌሎች አካባቢዎች በተለይም ከምዕራብ አማራ (የክልሉ ሰዎች ጭምር ምስራቅ አማራ ስለሚሉን) አንጻር ሲታይ በኢኮኖሚ እንዲደቅ፥ ማህበራዊ ስሪትና መስተጋብሩ እንዲናጋ፥ ፖለቲካዊ ተሳትፎው ከዜሮ በታች እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ወሎ ለክልሉ የሰጠውን ያህል እንዳያገኝ ሆን ተብሎ ስለተሰራበትና እየተሰራበት ስለሆነ መገፋት የወለደው የመነጠል ስሜት ነው፡፡
በቀድሞው ብአዴን፣ በመካከለኛው ዘመን አዴፓ እና በአሁኑ የአማራ ብልጽግና፣ በወሎ ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ በደሎችንና የፖለቲካ ደባዎችን አንድ በአንድ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዝርዝር መቅረብ ያለበት ለውሳኔ ሰጪው ህዝባችን መሆን ስለሚገባው በየጋዜጣውና በየሚዲያው ላይ በደል እየቆጠርን፣ በተበዳይነት ስሜት መጯጯህ ትርጉም የለውም፡፡
በሌላ በኩል፤ የአማራ ክልል ዲሞክራታይዜሽን፣ ለወሎየዎች ማህበረሰባዊ ጥያቄ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አማራ ክልል ያለው የገነገነ አምባገነንነትና ጎጠኝነት በዲሞክራታይዜሽን ሂደት የሚቃና እንደማይሆን ባለፉት 30 ዓመታት በጥሩ ሁኔታ ታይቷል፡፡ እናም ወሎ ከዚህ “በሽተኛ ጥምረት” እስካልተፋታ ድረስ ለ30 ዓመታት የወረደበት መከራና የደረሰበት ጉዳት የሚቀጥል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እናም ራሱን የቻለ ክልላዊ አስተዳደርን መመስረት ቀዳሚ መፍትሄ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የወሎ የክልልነት ጥያቄ ከብሄርም ከሃይማኖትም የማይገናኝ በማህበራዊ፥ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን በጉልህ የሚታይ ጥያቄ ነው፡፡ የአማራ ክልል ጉዳዬ ብሎ የማያያቸው፣ ምላሽ ለመስጠትም የማይፈልጋቸው፣ ወሎ ውስጥ ብቻ የሚታዩ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህም ችግሮች የአካባቢውን ማህበረሰብ (በተለይም ወጣቶችን) ለስደትና ለእንግልት ዳርገዋል፤ የስራ እድል ባለመፈጠሩ ለሱስ ተጋላጭ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡ የስራ አጥ ቁጥር ጨምሯል። አካባቢውን ከልማት እንዲርቅ አድርገዋል። ታሪካዊ የሆኑ የወሎ የራያና የዋግ ህዝብና ግዛቶች ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ሲደረግ፣ ክልሉ በቸልተኛነትና በንዝህላልነት አስወስዶ፣ አሁን አላስፈላጊ ንትርክና ጦርነት ውስጥ ማግዶናል። ከሌሎች የክልሉ ዞኖች አንፃር በአራቱ ዞኖች የሚገኘው የወሎ ህዝብ፣ በኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል፡፡
ከመከላከያ ሰራዊት እስከ ክልል ልዩ ኃይል፣ ከፌዴራል ሚኒስቴር እስከ ክልል ባለስልጣን እየተገፋ ያለው የወሎ ተወላጅ ነው። ህዝቡ በጦርነት እየዳሸቀ፣ በርሐብ እየማቀቀ ነው፡፡ በህልውና ዘመቻ ስም በሬውን ሽጦ የታጠቀውን መሳሪያ እየተቀማ ያለው የወሎ ህዝብ ነው። የአማራ ልሂቃን ነን በሚሉ “እውቀት አልባ ምሁራን” እና በአማራ ክልል አመራሮች መርዝ እየተነሰነሰበት ያለውና ጥርስ እየተነከሰበት ያለው የወሎ ህዝብ ነው። ሌላው ቀርቶ ለህክምና እና ለሌላም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ እንዳይገባ እየተከለከለ ያለው የወሎ ህዝብ ነው። ይህ ሲሆን ክልሉ ምን አደረገ? ስለ ወሎ ህዝብ ሆኖ ተከራከረ? ክልሉ ምንም ትንፍሽ ሲል አይሰማም! ስለሆነም፤ በፖለቲካና ኢኮኖሚው የተገፋው፣ ባህልና ማንነቱን ያጣው የወሎ ህዝብ፣ የራሱን የክልል አስተዳደር ለመመስረት ይገደዳል።
እነዚህና መሰል በደሎች በወሎ ህዝብ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ግን የወሎ ህዝብ ፍትህና ርትእ ፍለጋ ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ባህር ዳር ድረስ እንዲሄድ መገደዱ ነው። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በወሎ ምድር በርካታ የምሬት ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ በርካታ ወሎየዎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ብሶታቸውን እያሰሙ  ነው፡፡ ትንሽ ነቃ ነቃ ያሉ ወሎየዎች በየሶሻል ሚዲያው ከሚያነሷቸው የቅሬታና የንትርክ ሃሳቦች ውስጥ የሚከተሉትን ማውሳት ይቻላል፡፡
አንዳንዶቹ “ወሎ ክልል የማይሆን ከሆነ፤ የወሎ ልጆች ስደት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በስደት ጉዞ በየበርሃው የሚሞቱት ወጣቶች፣ በየባህሩ የዓሳ ቀለብ ሆነው የሚቀሩት ዜጎች ቁጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በበረሀ ሽፍታ እየታገቱ ኩላሊታቸው እየወጣ የሚገደሉ፣ ለአስገድዶ መድፈር ሰለባ የሚሆኑ እህቶቻችን ቁጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ወሎ ላይ ልማት የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ ወሎዬው የበይ ተመልካችና ስደተኛ መሆኑ ይቀጥላል። አሁን “ወሎዬ” የሚለውን ማንነታችንን ነጥቀው “አማራ” ሊያደርጉን እየፈለጉ ነው፡፡ ቀጥለው ደግሞ በሚፈለገው መጠን ካዳከሙን በኋላ ርስታችንን ሁሉ ነጥቀውን ሀገር አልባ ያደርጉናል” የሚል ስጋት የወለደው እሮሮ እያሰሙ  ነው፡፡
ሌሎች ደግሞ “ወሎ ክልል ቢሆን ምን ይገኛል?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ያነሳሉ። ይከራከራሉ፡፡ “ወሎ ክልል ቢሆን ስጋችንን አልፎ አጥንታችንን ከሚግጥ የአማራ ክልል አገዛዝ ነፃ እንወጣለን፡፡ የስራ እድል ይፈጠራል። እህትና ወንድሞቻችን የዓዞ እራት ከመሆን ይተርፋሉ፡፡ ወሎ ትለማለች” የሚል ምላሽ መሰል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ አንዱ ይነሳና ደግሞ፤ “ወሎ ክልል ቢሆን አማራ ተበተነ ማለት ነው። … ወሎ ክልል ቢሆን … እስላማዊ መዋቅር ለመዘርጋት ስለሆነ ይህ የጀዋር ተልእኮ ስለሆነ አደጋ አለው” ይላል፡፡ “ይሄን ከኋላ ሆኖ የሚገፋ የተዳከመ አማራን የሚፈልግ ሌላ ኃይል ነው። ወሎ አማራ ነው። ይሄን ሀሣብ የምታራምዱ የጠላት ምንደኞች ከመሠሪ ተግባራችሁ ተቆጠቡ” ይላል፤ አንዱ ከሌላ አቅጣጫ፡፡ አንዳንዶች “አንተ የአማራ ጠላት ነህ” ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “… አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ አንድ ሆኖ ኢትዮጵያዊነቱን ያለመልማል እንጅ በወያኔ ሴራና ባረጀ ባፈጀ አስተሳሰብና ከፋፋይ በሆኑ ተንኮለኞች አንበታተንም” ይላል፡፡ “የኦነግ ተላላኪዎች አማራን ለማዳከም እየተፍጨረጨሩ ነው” የሚሉም አሉ፡፡
“ወሎ የራሱን እድል ይወስን” የምትለዋን ቃል ሲሰሙ  ብዙዎች ይንጫጫሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ፋይዳቢስ የወሬ ቱማታዎች ናቸው፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮች ሲዘረዘሩ ወሎየዎች ይዘው የተነሱትን የመልማት አጀንዳ በሃሳብ ሞግተው ማሸነፍ ያልቻሉ የአማራ ልሂቃንና ራሳቸውን “አንቂ” ብለው የሰየሙ  የማህበራዊ ሚዲያ “ሊቃውንት”፣ በለመዱት የሴራ ፖለቲካ እየለወሱ፣ በኦነግና በጀዋር ስም ሊያሸማቅቁ ይሞክራሉ፡፡ “ወሎን ገንጥለው ኢስላም ለማድረግ ነው” የሚል ውሃ የማይቋጥር ሃሳብ በመሰንዘር የህዝብን ጥያቄ ሊያዳፍኑ ይሞክራሉ።
ለእንደዚህ ዓይነት አእምሮውን ለዘጋ ሰው፣ ወሎ ክልል ሆነች ማለት ከአማራ ክልል ጋር ፍፁም አትገናኝም ማለት ይመስለዋል፡፡ ወሎ ክልል ሆነ ማለት የጠፋውን የወሎ የንግድና የባህል እሴት ወደነበረበት ከፍታ መመለስ ማለት መሆኑን አይገነዘበውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት በፀረ-ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የታጀሉ ቃላትን የሚወረውሩ ሰዎች አንድም ራሳቸው የሆነ አካል ተላላኪና የወሎ ጠላት ናቸው፤ አሊያም ፖለቲካ የሚባል ነገር ያልገባቸው የዋሆች  ናቸው፡፡ ተላላኪዎቹም ሆኑ የዋሆቹ በወሎ ህዝብ ላይ ሊወስኑ እንደማይችሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
***
አንዲት የተለመደች አባባል አለች- “ወሎ ከአማራ ተገንጥሎ ለብቻው የሚያገኘው ጥቅም፣ አዲስ ሆዳም ባለስልጣኖችን  መፍጠር ነው፤ ለአዲሶቹ ፖለቲከኞች ኮብራ ከመግዛት የዘለለ ፋይዳ የለውም” የምትል። ይህ በሌሎችም አካባቢዎች የመብት ጥያቄ ለሚያነሱ ዜጎች የሚነገር ጉንጭ አልፋ አባባል ነው፡፡ ወሎ ክልል ከሆነ በኋላ ክልሉን ለሚመሩ ባለስልጣኖች፣ ለሌሎች ክልሎች ባለስልጣኖች የሚደረገው ሁሉ ይደረግላቸዋል፡፡ ካስፈለገና አቅም  ካለ ከዚያም በላይ ቤተ-መንግስት ሊታነጽላቸው ይችላል፤ ይገባልም፡፡ እንዲህ ያለው ከኮብራ መግዛት ጋር የተያያዘ የተለመደ የማሸማቀቂያ ሃሳብ፣ ትርጉምም ፋይዳም የለውም፡፡ ወሎ በንጉስ የሚመራ፣ የረጅም ጊዜ የአስተዳደር ተሞክሮ ያለው ማህበረሰብ ነው። ሌሎች ኮብራ ስለገዙ የልማት በጀቱን ኮብራ ለመግዛት የሚያውል የዋህ ወሎዬ ይኖራል ብዬ  አላስብም፡፡
ይልቁንስ የወሎ ክልል መሆን ለሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለው ፋይዳ መታየት የሚገባው  ዋና ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሀገር በፌዴራል መዋቅር እንዲደራጅ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ ስልጣን በማእከላዊ መንግስት እንዳይከማች ለማድረግ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ የመንግስትን አገልግሎቶች ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ህዝብ እንዳይንገላታ ለማድረግ ነው፡፡ በሦስተኛነት የሚጠቀሰው የፌዴራል መዋቅር ትሩፋት ህዝብን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡
አሁን ያለው አጠቃላይ የሀገሪቱ የፌዴራል አከላለል፣ ቋንቋን ብቻ መሰረት አድርጎ የተደራጀ በመሆኑ ህዝብ ከላይ የተጠቀሱትን ትሩፋቶች ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ ሌላ አሁን ያለው የሀገሪቱ የፌዴራል አወቃቀር በህዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት የተመጣጠኑ ክልሎችን መፍጠር ባለመቻሉ፣ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ የበጀት ድልድልና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በየአካባቢው የሚነሳ “የክልል እንሁን” ጥያቄ መንግስትን ፋታ ነስቷል፡፡
እነዚህ አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው  በአማራ ክልል የሚታየው ሁኔታ አንዳንድ የወሎ አካባቢዎችን “ዞን” በማድረግ የሚፈታ አይደለም፡፡ መፍትሄው ወሎ ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን ማድረግ ነው። ወሎ ክልል ቢሆን ይሄ መፍትሄ ለወሎ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኢትዮጵያ የሚበጅ ነው። ጎጃም እና ወለጋ ዘንድ  ተመሳሳይ ክልል እንሁን የሚል ሃሳብና ንቅናቄ እንዳለ ሰምቻለሁ። በቅርቡ ሸዋ ውስጥም ተመሳሳይ ነገር እንዳለ እየሰማን ነው። አቅጣጫው የድሮውን ክፍለ ሀገር - ክልል ማድረግ ነው። ይሄ ደግሞ ለመላዋ ኢትዮጵያ የሚበጅ ጥሩ መፍትሄ ነው!!!
ወሎ ክልል ቢሆን አማራ ይዳከማል?
“ወሎ ክልል ይሁን” የሚለው ሃሳብ ሲነሳ “የትኛው ወሎ?” የሚል ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እንደኔ እንደኔ “ወሎ” ማለት አሁን በአማራ ክልል ስር በዞንነት የሚታወቁትን “ሰሜን ወሎን፣ ደቡብ ወሎን፣ ዋግ ኽምራ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞንን” ማለት ነው። እነዚህ ዞኖች አንድ ላይ “ወሎ” የተሰኘ ክልል ቢመሰርቱ፡- በህዝብ ቁጥር አሁን ክልልሆነው ከተዋቀሩት ከ4 ክልሎች ይበልጣሉ፡፡ በቆዳ ስፋት አሁን ክልል ሆነው ከተዋቀሩት 3 ክልሎች ይበልጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ በአንደኛ ደረጃ ከሚታወቁ የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል ያላቸው እና የተሻለ የሰዎች እንቅስቃሴ ከሚያስተናግዱ 7 ከተሞች ውስጥ ሁለቱ ደሴና ኮምቦልቻ በመሆናቸው፣ ወሎ ክልል ሆኖ ራሱን ቢያስተዳድርና ህዝቡ በመሰረተ ልማትና በህዝባዊ አስተዳደር ቅርበት ተጠቃሚ ቢሆን ማን ይጎዳል?
የወሎ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ከላይ ትግሬ፣ ከጎን አማራ፣ ከታች ኦሮሞ - ወሎ በሦስትዮሽ (triangular) ተወጥሮ ተይዟል። ሲናገሩት ልብ የሚሞላው “ወሎዬ” የሚለው ማንነቱ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ እንዲጠፋ እየተደረገ ነው። ይህ ማንነት ጠፍቶ ልማት ቢመጣ አንድ ነገር ነው። ልማታችንም፣ ስማችንም፣ ማንነታችንም አብሮ እየጠፋ ነው። … ሌላው አካባቢ የጎንደር ልማት ማህበር፣ የትግራይ ልማት ማህበር፣ የሲዳማ ልማት ማህበር … እያለ ሲያቋቁም ምንም አልተባለም፡፡ ወሎ ግን የልማት ማህበር እንኳን ማቋቋም አልቻለም። ወሎ ልልማ ሲል “አማራነትን ልታፈርሱ ነው፣ ኦነግ ናችሁ” ይባላል፡፡ ወሎየው ወለጋ ላይ የተጨፈጨፈው አማራ ነህ ተብሎ ነው፡፡ አማራነት ለወሎ ያመጣለት ሞት ነው፣ ጭፍጨፋ ነው።
ወሎን ማዳን ኢትዮጵያን ማትረፍ ነው። ስለ መቻቻል ስለ አብሮ መኖር ሲዘመርላት የቆየችው ኢትዮጵያ፤ የመቻቻልም አብሮ የመኖርም መነሻ መሰረቱ ወሎ ላይ ነው። ወሎ ውህድነቱና ባለድርብርብ ማንነትነቱ  ፅንፈኛ ሊያደርገው የማይችል ተፈጥሯዊ መገጣጠም አለው። ወሎ ውስጥ በሃይማኖት መለያየት ብርቅም እንቅፋትም አይደለም። በሃይማኖት፣ በብሔርና ደም፣ በቋንቋና ባህል ቅልቅልነቱ ነው፤ የወሎ ውል! የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአገው፣ የአርጎባ፣ የአፋር፣ የራያ ህዝቦች ተዋህደው የሰሩት ቀጠና ነው ወሎ። የዛግዌዎች ሮሓ፣ የሶሎሞናዊዎቹ ቤተ—አምሓራ፣ የወረ-ሼኾቹ የጁ፣ የማመዶዎቹ ወረ-ሂመኖ ታሪክ እና አሻራ ነው ወሎ። ወሎን በአማራ ክልል ስር አድርጎ መከለል ከጅምሩ ስህተት ነበር። የአማራ ክልል ፖለቲካና አስተዳደር አሁን ባለው  ተክለ ቁመናው የሚቀጥል ከሆነ፣ ወሎ እየተጎዳ እንጅ እያተረፈ አይሄድም። እንኳን ተጨማሪ ነገር ሊያገኝ ወሎ ያለውንም አጥቶ ሙልጩን ይቀራል፡፡
ወሎ ክልል ቢሆን አማራ ይዳከማል የሚሉትን በተመለከተ ከሁሉ አስቀድመው አንድ ነገር ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ ይኸውም፡- “አማራነት” እና “አምሓራነት” ለየቅል ናቸው። የአማራ ፖለቲካ “አማራነትን” ከ“አምሓራነት” መለየት ተስኖታል፡፡ ወሎ አምሓራ እንጂ አማራ አይደለም፡፡ “ልሙጥ አማራነትን” ለሚያቀነቅነው የአማራ ፖለቲካ፣ የወሎ ስሪት ምቹ አይደለም። ወሎየ ያልሰፈረበት የኢትዮጵያ መሃልም ዳርም አካባቢ የለም፡፡ ሁሉም ቦታ ላይ ወሎዬ አለ፡፡ ሁሉም አካባቢ ላይ ሰፍሯል።
የአማራ ክልል በአስተዳደራዊ በደሉ፣ በትኩረት ነፈጋው፣ በፖለቲካ ቁማሩ ወሎን የግጭት አውድማ እያደረገ የመቀጠል በሽታው እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ፣ የህዝብ ትግል የወሎን ክልልነት እውን ያደርገዋል።
ለወሎ ብልጽግና…
ወሎ በአማራ ክልላዊ መንግስት የደረሰበት መገፋትና መገለል ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ባለፉት 27 ዓመታት የደረሰበት ደባ በህወሃት ብቻ ሳይሆን በክልሉ ባለስልጣኖች እንደሆነ የወሎ ህዝብ ያውቃል። የአማራ ክልል ወሎን የሚያይበት መነፅር የተበላሸና ጤናማ ያልሆነ መሆኑን የወሎ ህዝብ በብዙ ነገር ታዝቧል። ወሎ በአማራ ክልል ያለ አንድ ግዛት መሆኑ ቀርቶ እንደ ጎረቤት ክልልም አይታይም ማለት ይቻላል። አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ የአማራ ክልል የወሎን ህዝብ የሚፈልገው ለግብር (ለታክስ) እና ከፌዴደራል መንግስት ጠቀም ያለ በጀት ለማግኘት ለህዝብ ቁጥር ማሟያነት ነው።
በመሆኑም፤ ከአጭር ጊዜም ይሁን ከረዥም ጊዜ አኳያ ሊታዩ በሚችሉ ሁኔታዎች የወሎ ፖለቲካ አዲስ ቅኝት ፈልጓል። ወሎ መሬት ላይ ያሉ የብልጽግናም ይሁን የሌላ ፓርቲ ፖለቲከኞች ድምጻቸው ሰላላ፣ እጃቸው አጭር ነው። በብልጽግና ውስጥ የዋግ ኽምራ፣ የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ፖለቲከኞች የማህበረሰባቸውን ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል የስልጣን አቅም የላቸውም።
የወሎ ፖለቲከኞችን የማሳደግም ይሁን የማሳነስ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ከህዝብ ይልቅ የክልሉ መንግስት በመሆኑ የወሎ ፖለቲከኞች የህዝባቸውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችላቸውን የልማት ስራ ከመስራት ይልቅ ለክልል አለቆቻቸው ወሬ በማቀበል የተጠመዱ ናቸው እየተባሉ ይታማሉ። ምክንያቱም ህዝብ አይሾም አይሽር። የልማት ጥያቄን ለመመለስ ከክልሉ በጀትና ሀብት ማስመደብ፣ መደራደርና መገዳደር ያስፈልጋል። ይሄን ያደረገ ባለስልጣን ስለሚወገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት ዝምታ እና አድር ባይነት በነዚህ አራት ዞኖች እንደ አስፈላጊ ባህሪ ተወስዷል።
ከለውጡ በኋላ ይሄን ልማድ የሚያስተካክል ሪፎርምን እየጠበቅን ባለበት ሰዓት አዳዲስ ተግዳሮቶች ብቅ አሉ። በመጀመሪያው ዓመት በኦሮሞ እና በአማራ ፖለቲከኞች መካከል በነበረው እጅ መጠማዘዝ ወሎየው አሳሩን አየ። ወሎየውን ወለጋ ላይ ነፍጠኛ ብለው ይገድሉታል። ከሚሴ ላይ ኦሮሞ ብለው ይገድሉታል።  በዚህ መልኩ በሚነሱ ቀውሶች እሳቱ አጣየና ከሚሴን ሲያነድ፣ ጭሱ ደሴና ኮምቦልቻንም ያፍናል።
በራያ ጉዳይም ተመሳሳይ ነገር ነበር። የመቀሌና የባህር ዳር ፖለቲከኞች ለራያ ህዝብ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የለም፡፡ ማንነቱ ከወሎ ጋር የተሳሰረው የራያ ህዝብ ላለፉት 30 ዓመታት ያለ ፍላጎቱ ትግራይ ተብሎ ከረመ፡፡ ከለውጡ በኋላ ሙሉውን ራያ ሳይሆን አላማጣና ኮረምን በአማራ ክልል ስር እንደሆኑ ተደርጎ በየቦታው  ታፔላ ተለጠፈ። እንደ እርጥብ እቅማዳ ውል አልባ ፖለቲካ ስናለፋ ቆየን። ጦርነቱ መጀመሪያ ራያን አቃጠለና ጭሱ ድፍን ወሎን አፈነ። ቀጥሎም አፋርን ጨምሮ መላዋ ወሎ ጭሱም ነዲዱም የሚጓፈጥባት ምድጃ ሆነች!
ይህ የወሎ ፖለቲካ በተለይም የራያዉና የከሚሴዉ ፖለቲካ በተነሳ ቁጥር ኢትዮጵያ ትናጣለች፡፡ በወጉ ካልተያዘ የማፍረስም አቅም አለዉ፡፡ ከረዥም ጊዜ አኳያ የወሎ ፖለቲካ ጠንክሮ ቢወጣ የከሚሴዉ ኦሮሞ፣ ወደ ወለጋ ከሚያማትር ይልቅ ወደ ደሴ ቢያማትር ደስታው ነዉ፡፡ የራያዉ ወገን ወደ መቀሌም ይሁን ወደ ባህር ዳር ከመሄድ ይልቅ ወደ ለመደው ወደ ደሴ ቢመጣ እልል በቅምጤ ነዉ። ስለዚህም በነዚህ የወሎ አካባቢዎች ያለዉን የፖለቲካ ሳንካ ለማከም፣ ወሎ ጠንካራ የፖለቲካ ማእከል እንዲኖረዉ ካደረግን፣ ለወሎም ይሁን ለኢትዮጵያ ፋይዳዉ ትልቅ ነዉ፡፡
ከአጭር ጊዜ አኳያም በጦርነቱ ሳቢያ የመጡብን ሰብአዊ ቀዉሶችና የክልሉና የፌደራል መንግስቱ ዳተኝነት ባለዉ የፖለቲካ ምህዳር ችግራችንን መፍታት አንችልም። የወሎየዉን ህመም የሚረዱና ህመሙ የሚያማቸዉ፣ ህዝብ የሚቀበላቸዉ ጠንካራ ፖለቲከኞችን ወደፊት በማምጣት ከቀዉሱ በአጭር ጊዜ መዉጣት የግድ ነዉ፡፡
አንዳንዶች ይህንን የመፍትሄ ሃሳብ እንደ ችግር ሊያዩት ይችላሉ፡፡ አንዱ ችግር አማራን ያዳክማል የሚል ነዉ፡፡ አማራ፣ ወሎ ክልል በመሆኑ አይዳከምም፡፡ እንኳን ወሎ ብቻ መላው አማራ ክልል አራት ቦታ ቢከፈል አማራ አይዳከምም፡፡ (ይህንን በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡- “አረብ” የሚባለው ማህበረሰብ በቱኒዝያ፣ በግብጽ፣ በሱዳን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በየመን፣… መገኘቱ የአረብን አንድነት አልበተነውም)
ዘረኝነትን ሊያጠፋ የሚችለው “ክፍለ ሀገራዊ ማንነት” (ማለትም፡- ወሎየነት፣ ጎጃሜነት፣ የወለጋ ልጅ፣ የባሌ ልጅ፣ የአርሲ ልጅነት ወዘተ.) እንዲያብብና እንዲጎለብት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ወሎን መነሻ ያደረገ ፌዴራላዊ አደረጃጀት፣ በክልል አደረጃጀት ምክንያት በአማራ ላይ የተጫኑበትን ጎጠኞች ይገላግለዋል። የወሎ ቤተ-አምሓራም ይሁን ሌላ ብሄር ያኔ አብሮ ይበለጽጋል፡፡ አካባቢዉ የግጭት ቀጠናና የፖለቲካ ኃይሎች መራኮቻ መሆኑ ይቀራል። ቀልጣፋና አካባቢዉን የሚመጥን አስተዳደር ይቋቋማል፡፡ በቡድንተኛነት የሚዘወሩ አጎብዳጆች ሳይሆኑ ለህዝብ የሚበጁ መሪዎችን ያገኛል፡፡ በዚህ መልኩ የተደራጀና ከታች ወደ ላይ የተገነባ ወሎ፣ ለአማራ ክልል ጠንካራ አጋርና መከታ ይሆናል፡፡
ውድ የወሎ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ሆይ!
ይህንን ሁኔታ በአንክሮ አጢናችሁ፣ የህዝባችሁን መብትና ጥቅም ከምታገኙት የስልጣን ፍርፋሪ በላይ ቅድሚያ ሰጥታችሁ ልትታገሉለትና ልታታግሉለት ይገባል፡፡ ስደት ባህል እስከሚመስል ድረስ የወላጆቹን ቋሚ ንብረት እየሸጠ በየበረሀዉና በየባህሩ ሞቶ የቀረዉን ወጣት ወሎዬ ቤት ይቁጠረው፡፡ ስራ አጥቶ በየመንገዱ እያወራ የሚሄደዉን የተማረ ወጣት ወሎዬ ቤት ይቁጠረዉ፡፡ በዚሁ ከቀጠልን ችግራችን ሁላችንንም አፍኖ እንደሚገድል አትጠራጠሩ፡፡ ግልጽ ለሆነ ዉይይት ራሳችሁን ብታዘጋጁና የታሪክ አጋጣሚ ባስገኘላችሁ የፖለቲካ ስልጣን፣ ከኅዝብ ጎን በመሆን አቋም ይዛችሁ በአራቱም ዞኖች የወሎን የክልልነት ውሳኔ ብትወስኑ፣ ከታሪክ ተጠያቂነት ትድናላችሁ፡፡ ወገናችሁንም ተጠቃሚ  ታደርጋላችሁ፡፡ በዚህ መልኩ የምታገኙት ስልጣን ከአጎብዳጅነት የራቀ ስለሚሆን ለህዝባችሁ ለዉጥ ለማምጣትና ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተካሄደ ላለዉ ሪፎርም ትርጉም ያለዉ አስተዋጽዖ ለማድረግ ትችላላችሁ፡፡
በእኔ እዪታ “ወሎየነት”  ፍቅርን፣ ሰላምን፣ መተሳሰብን፣ አንድነትን፣ መከባበርንና መቻልን የሚያስተናግድ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የሆነ “ማንነት” ነው፡፡ ወሎየው ከሌሎችም  ጋር ኖረ ብቻውን ይህንን ለዘመናት አብሮት የኖረ ማንነቱን የትም የማይጥለው  በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በወሎ ማህበረሰብ እየተነሳ ያለው የክልልነት ጥያቄ እንደ አፈንጋጭነት መታየት የለበትም። ወሎ ራሱን አደራጅቶ እና ብቁ አድርጎ ወደፊት የሚመጣውን እድሉን በራሱ እንዲወስን መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ያኔ አግላዩ የአማራ ክልል መንግስት እንዴት ወሎን ጨቁኖት እንደኖረ ይገባናል።
ወሎ የክርስትናና እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተከባብረውና ተዋደው በጋራ የሚኖሩበት የመቻቻል ተምሳሌት የሆኑ ማህበረሰቦች መገኛ ድንቅ አካባቢ ነው። ከሀይማኖቱ ውጭ ካለ የሌላ እምነት ተከታይ ማህበረሰብ ጋር በሰላም በመኖርም ለዓለም ምሳሌ የሆነ ህዝብ ነው። ዶናልድ ሌቪን የተባለው እውቅ ጸሐፊ፤ “የአሁኗን ኢትዮጵያ የሰሯት ወሎዎች ናቸው፣ ልታመሰግኗቸው  ይገባል” ይላል፡፡ መመስገኑ ይቅርብንና ሰላም  ስጡን  እያለ ነው  ወሎ!!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራ ሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 9032 times