Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 October 2012 14:54

ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ዋዜማ ላይ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበት ሰፊ እድል ይዞ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሱዳን አቻውን በመልስ ጨዋታ ሊያስተናግድ ነው፡፡ ከወር በፊት ሁለቱ ቡድኖች በኦምዱርማን ባደረጉት ጨዋታ ሱዳን 5ለ3 ኢትዮጵያን ማሸነፏ የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በመጫወቱ የማለፍ እድሉን ብሩህ ሲያደርገው በግጥሚያው የሱዳን አቻውን በሁለት ንፁህ ጎሎች ለማሸነፍ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ መላኩ አየለ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ ባለሃብቶች ለቡድኑ ውጤታማነት የሚያግዝ የማበረታቻ ሽልማትን ለመስጠት በደብዳቤ እና በቃል ሰሞኑን እያሳወቁ ናቸው፡፡ አቶ ተክለብርሃን አምባዬ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈ ለመላው አባላቱ በነፍስ ወከፍ 25ሺ ብር ለመስጠት ቃል ሲገቡ ሊፋን ሞተርስ በበኩሉ በጨዋታው ጎል ለሚያገቡ ተጨዋቾች ለአንድ ግብ 10ሺ ብር ለመሸለም መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡


አንዳንድ ባለሃብቶች ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ከተሳካለት የቡድኑ አባላት ለማዝናናት እና ለመጋበዝ ፍላጎት እንዳላቸው እየገለፁ መሆኑን ያስታወቀው የኮምኒኬሽን ክፍሉ ፌደሬሽኑ ለማበረታቻ የሚሰጡ ሽልማቶች በተደራጀ ሁኔታ እንዲከናወኑ እና የተጨዋቾቹን ህይወት በሚለውጥ ደረጃ እንዲፈፀሙ በመንቀሳቀስ ላይ ነው ብሏል፡፡ ስፖርት አድማስ ያነጋገራቸው የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በነገው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድዬም በስፖርታዊ ጨዋነት የታጀበ እና ሙሉ 90 ደቂቃን በማበረታት የደመቀ ድጋፍ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በ2013 ደቡብ አፍሪካ ወደ የምታዘጋጀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በመጀመርያ ዙር ከተደረጉ ጨዋታዎች ምርጥ የተባለው በኦምዱርማን ሱዳን 5ለ3 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያን የረታችበት መሆኑን በርካታ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ደርቢ የተባለው የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ፍጥጫ ነገ በመልስ ጨዋታው አሸናፊው ሲለይበት በበርካታ ቅድመ ትንተናዎች ሰፊው የማሸነፍ እድል ለኢትዮጵያ አጋድሏል፡፡ ሁለቱ ጎረቤታማቾች በመጀመርያ ጨዋታቸው ካስመዘገቡት ውጤት አንፃር ባለፉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በመሳተፍ በብቸኛነት ምስራቅ አፍሪካን ከወከለችው ሱዳን ይልቅ ለ31 ዓመታት ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የራቀችው ኢትዮጵያ ለማለፉ የተሻለ አጋጣሚ ተፈጥሮላታል፡፡ ከተሰጡ ግምቶች አንዱ የጎል ስፖርት አንባቢዎች የሰጡት የውጤት ትንበያ ላይ 82 በመቶ የማሸነፍ እድሉ ለኢትዮጵያ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
የናይል አዞዎች ተስፋ አልቆረጡም
የሱዳኑ አሰልጣኝ ሞሃመድ ‹ማዝዳ› አብደላህ ቡድናቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እንደሚችል አምናለሁ ሲሉ መናገራቸውን ከትናንት በስቲያ የዘገበው ሱፕር ስፖርት ነው፡፡ የናይል አዞዎች በሚል ቅፅል ስሙ የሚጠራው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው በናይሮቢ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ትናንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ለማረፍያው የጊዮን ሆቴልን ምርጫ ማድረጉ ታውቋል፡፡
‹‹ትንቅንቁ ገና ነው፡፡ እኛም አላበቃልንም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የምንገባው ከመጀመርያው ጨዋታ ስህተታችን ብዙ ተምረን ነው፡፡ ለተቃናቃኞቻችን ሰፊ እድል የፈጠሩት በሜዳችን ላይ የገቡት ጎሎች ናቸው፡፡ በመልሱ ጨዋታ እንደዚያ ግብ እንዳይቆጠርብን ተጠንቅቀን እንጫወታለን›› በማለት ለሱፕር ስፖርት ሞሃመድ ማዝዳ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ቡድን በምንም አይነት ሁኔታ ዝቅ አድርገው እንደማይመለከቱና እንደሚያከብሩ የተናገሩት አሰልጣኙ፤ በጣም ወሳኝ ጨዋታ ላይ ስንፋጠጥ ረጅም ግዜ ሆኖናል ብለው ቡድናቸው ሙሉ ለሙሉ ከጉዳት ነፃ በሆነ አቋም ላይ እንደሚገኝ፤በሳኡዲ አረቢያ የሚጫወት አዲስ ተጨዋች መጨመሩንና በመልሱ ጨዋታ ከነበረው ውጭ የተለየ አሰላለፍ ለመጠቀም እንዳላሰቡም አብራርተዋል፡፡
የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ሲዘጋጅ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከዛምቢያ ባደረገው ጨዋታ 2ለ0 ያሸነፈበት ውጤት ያልተገባ ተጨዋች በማሰለፍ ፊፋና ካፍ በአገሪቱ ላይ የጣሉት ቅጣት መጠነኛ መረበሽ ፈጥሮበታል፡፡ በሱዳን ብሄራዊ ቡድን ላይ በተላለፈው ቅጣት ለዛምቢያ የ3ለ0 የፎርፌ ውጤት በመስጠት፤ ሱዳን 3 ነጥብ እንዲቀነስባትና 6430 ዶላር እንድትከፍል የተወሰነበት ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ሱዳን በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ካለችበት የምድብ 4 የመሪነት ስፍራ ወደ ሶስተኛ ደረጃ በ1 ነጥብ መውረድ ግድ ሆኖባታል፡፡
ሰውነት በቡድናቸው ተማምነዋል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በካፍ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ባደረጉት ቃለምልልስ ቡድናቸው በመልሱ ጨዋታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበትን እድል ቢያንስ 2ለ0 በቀላሉ በማሸነፍ ማረጋገጥ እንደሚችል እምነቴ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የመጀመርያው ግብ ጠባቂ በቅጣት አይሰለፍም፤ ሁለተኛ ምርጫ የሆነው ደረጀ አለሙም በእግር ጉዳት ላይ ነው፡፡ ወሳኙ ተከላካይ አበባው ቡጣቆም በቅጣት መሰለፍ አይችልም፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች አለመኖራቸው በቡድኑ ላይ ተፅእኖ አይፈጥርም›› የሚል ጥያቄን ካፍኦንላይን ለአሰልጣኝ ሰውነት አቅርቦ ነበር፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምላሽ ሲሰጡ ሁለት ምርጥ ብቃት ያላቸውን በረኞች ዘሪሁን ታደለና ጀማል ጣሰውን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ መቀላቀላቸውን ጠቁመው በአበባው ቡጣቆ ቦታ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ደግሞ ጥሩ ተከላካይ ተጨዋች የሆነውን ያሬድ ዝናቡን ማስገባታቸውን ገልፀዋል፡፡ በመጀመርያው ጨዋታ ሱዳን ላይ ያልነበረው ወሳኝ አጥቂያችን ሳላዲን ሰኢድ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ መመለሱ ውጤታማ ለመሆናችን ማስተማመኛ ነው በማለትም ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በካምፓችን ያለው ሞራልና የመነቃቃት ስሜት ከፍተኛ ነው ያሉት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በስራ ዘመናቸው እንዲህ በቁርጠኝነት እና በከፍተኛ የህብረት መንፈስ ውስጥ የሚገኝ ቡድን ሲያዩ የመጀመርያቸው እንደሆነ ጠቅሰው ቡድኑ ላለፉት ሁለት ወራት አብሮ በመቆየቱ ልዩ ጥንካሬ እንደፈጠረለትና ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማስገባት ጉጉት በሁሉም ተጨዋቾች በመስፈኑ ይሳካልናል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
ከ31 ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ ብዙም ሳይጠበቅ ጊኒን አሸንፎ በሊቢያ ለተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የበቃበትን ታሪክ ያስታወሱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ ተጨዋቾቼ ታሪክ ለመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተነሳስተዋል ብለው በቡድኑ ያለው አንድነትና የመንፈስ ጥንካሬ የሱዳንን ጠንካራ የተከላካይ መስመር በመስበርና ሙሉ ሜዳውን በሚሸፍን የማጥቃት ጨዋታ ለመተግበር ስለሚያበቃ የምንፈልገውን ታሪካዊ ድል ለማስመዝገብ እንደምንችል ያስተማምናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ትውልድ አዲስ ምእራፍ ይከፍታል- ደጉ ደበበ (የብሔራዊ ቡድን አምበል)
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል የሆነው ደጉ ደበበ ይህ ትውልድ ለ31 ዓመታት ወደራቅንበት የአፍሪካ ዋንጫ የመግባት ፍላጎት እንዳለው ሰሞኑን ለካፍ ኦን ላይን በሰጠው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡
ለመልሱ ጨዋታ በጣም ጥሩ ዝግጅት መደረጉን፤ በየልምምዱ የቡድኑን ቅንጅትና አብሮ የመጫወት ጥንካሬ ለማዳበር መሰራቱን ለካፍ ኦፊሴላዊ ድረገፅ የገለፀው ደጉ፤ በመልስ ጨዋታው ያለን እድል አንድ ብቻ እንደሆነ፤ የሚያስፈልገውን የግብ ብዛት በማስቆጠር ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመግባት የመልሱ ጨዋታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በከፍተኛ የማጥቃት አጨዋወት መስራት እንዳለብን ሁላችንም እናውቃለን ይላል፡፡
በማንኛውም የአግር ኳስ ጨዋታ ማሸነፍ የእድል ጉዳይ ቢሆንም ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ኦምዱርማን ላይ ያገባቸው 3 ጎሎች፤ እዚህ በሜዳችን ከቤኒን ጋር ብዙ የግብ እደሎችን ፈጥረን ሳይገባብን 0ለ0 አቻ መለያየታችንና በመልሱ ከሜዳ ውጭ ያገባነው አንድ ጎል ፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ መካከለኛው አፍሪካ በአዲስ አበባ 2ለ0 አሸንፈን እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1 እኩል አቻ በወጣንባቸው ጨዋታዎች ያገኘናቸው ልምዶች በተቃራኒ ቡድን ላይ ጎል ለማግባት ብዙም እንደማንቸገር ያመለክታሉ በማለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ደጉ ደበበ ለካፍ ኦን ላይን ማብራርያ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላለፉት 2 ዓመታት በአምበልነት የመራው ደጉ ደበበ በነገው ጨዋታ እንማንኛውም ቡድን ሁሉ የማሸነፍ ፍላጐት ይዘን ወደ ሜዳ እንገባለን በማለት ለስፖርት አድማስ ሲናገር አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ጊዜ አብሮ ሲሰራ በመቆየቱ በህብረቱ ተጠናክሯል ብሎ በአፍሪካ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ውጤታማ እየሆነ መቆየቱ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል ሲል ያስረዳል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ማለት እግር ኳሳችን እንዳያድግ እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን በመስበር አዲስ ምዕራፍ መክፈት ነው ያሉ ደጉ ደበበ፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ለመጭው ትውልድ ለፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ደረጃ አዲስ ምዕራፍ መክፈት እንደሚሆን ገልፆ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈን ስንታይ የተጨዋቾች ኤጀንቶች ወደ አገራችን ትኩረት እንዲያገኙ በማስቻል ወጣት ተጨዋቾች የፕሮፌሽናልነት ዕድል የማግኘታቸው ተስፋ ይለመልማል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተያያዘው የውጤታማነት ጎዳና ከፌዴሬሽን እና ከአንዳንድ ባለሀብቶች እያገኛቸው የሚገኙ የገንዘብ ማበረታታቻዎችና ልዩ ሽልማቶች ጥሩ ድጋፎች መሆናቸውን የሚናገረው ደጉ የምንሰራው በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስና ፈር ቀዳጅ ታሪክ በማስመዝገብ ለስፖርቱ ለውጥ ለመፍጠር በማሰብ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ብሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድጋፍ እየሰጡ ያሉት የስነልቦና አማካሪዎች የአመጋገብ ባለሙያ በተለይ ለአሰልጣኞችና ቡድን በአምበልነት ለምንመራ ተጨዋቾች ከፍተኛ እገዛ ፈጥረዋል የሚለው ደጉ ደበበ በአመጋገባችን መስተካከል የአካል ብቃታችን ላይ ግልጽ ለውጥ መፈጠሩ እና በቡድኑ ውስጥ የሰፈነው የአሸናፊነት እና ሃላፊነትን በትኩረት የመወጣት ፍላጎት በስነልቦና አማካሪዎቻችን ጥረት መገኘቱን እመሰክራለሁ ብሏል፡፡
ከጨዋታው የምንፈልገውን ውጤት እናውቃለን፤ በህብረት በመስራት እናሳካዋለን -አዳነ ግርማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በህብረት ተጋግዞ የሚሠራበት ጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ ለስፖርት አድማስ የተናገረው የአጥቂ መስመር ተሰላፊው አዳነ ግርማ ነው፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ በጥሩ የሞራል ብቃት መገኘት ምክንያት ያላቸው ነገሮች ሲዘረዝርም
ያሁኑ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በወዳጅነት እና በውድድር ጨዋታዎች 7 እና 8 ግጥሚያዎች በማድረጋቸው በየግጥሚያው በተሻለ አቅም ተግባብተው እንዲሠሩ ማገዙን በመጥቀስ፤ በተጨዋቾች መካከል ያለው ህብረት እና በአሰልጣኞች ከሚሰጠው ድጋፍ ባሻገር አጋዥ አካላት ሆነው አብረው እየሰሩት ያሉት የስነልቦና እና የአመጋገብ ባለሙያዎች በብዙ መልኩ ለውጠውናል ብሏል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫና በዓለም ዋንጫ በነበረው ዝግጅት የስነልቦና አማካሪዎች እና የአመጋገብ ባለሙያ ጉልህ ለውጥ መፍጠራቸውንም ያስረዳል፡፡ የስነልቦና አማካሪዎች ለብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በየቀኑ ከ45 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት የሚወሰድ ትምህርት በመስጠት መሰንበታቸውን የሚገልፀው አዳነ ተጨዋቾች ከግጥሚያዎች በፊት ሊኖራቸው በሚገባ የመንፈስ ጥንካሬ፣ የአሸናፊነት ስነልቦና እና ዝግጁነት የተሻለ ብቃት እና ትኩረት እንዲያገኙ ማስቻሉን መስክሯል፡፡ የምግብ ባለሙያ ከብሔራዊ ቡድን ጋር አብሮ መስራት በመጀመሩ ትልልቅ ለውጦች ታይተዋል፡፡
አዳነ ግርማ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው በተለይ ዘንድሮ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሚበሉትን ምግብ ጥቅም አውቀው አካል ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የተነሳም ተጨዋቾች የማይጠቅማቸውን እንጀራ፣ ቀይ ወጥና ለስላሳ መጠቀም ትተዋል፡፡ በአንጻሩ በምግብ ባለሙያቸው በሚወጣላቸው ፕሮግራም የተመጣጣነ የምግብ ሜኑ ተዘጋጅቶላቸው መመገብ ጀምረዋል፡፡ አስቀድሞ ብዙ ውሃ መጠጣት ያልለመደባቸው ተጨዋቾቹ ዛሬ በቀን እስከ 4 ሊትር ውሃ እየወሰዱ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን ከህፃንነቴ ጀምሮ በቴሌቭዥን እያየሁ አድጌያለሁ የሚለው አዳነ ግርማ ዛሬ ለውድድሩ ተሳትፎ የምነበቃበት ዋዜማ ላይ ስንደርስ የብሔራዊ ቡድን አንዱ ተጨዋች ለመሆን በመቻሌ ከፍተኛ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል ብሏል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍ ከሆነ እንደህልም የሚሆንብኝ ትልቅ ስኬት ነው ሲል የተናገረው አዳነ፤ ከእናት ክለቡ ሃዋሣ ከነማ ጀምሮ በቅ/ጊዮርጊስም በርካታ የዋንጫ ድሎችን ሲያጣጥም ቢኖርም ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ደግሞ የእግር ኳስ ህይወቴ ቀጣይ የስኬት ጉዞ በር ከፋች ስለሚሆን ያጓጓኛል ብሏል፡፡
በሜዳችን በምናደርገው ወሳኙ ጨዋታ ላይ ከህዝባችን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያልተቆጠበ ድጋፍ ያስፈልገናል የሚለው አዳነ ግርማ በመልሱ ጨዋታ ከአሰልጣኛችን የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ በህብረት በማጥቃት እና በመከላከል ተጫውተን ውጤታማ ለመሆን በስፋት ስንዘጋጅ ቆይተናል ይላል፡፡
በነገው ጨዋታ ጐል ካንተ እንጠብቅ ወይ በሚል ከስፖርት አድማስ ለቀረበበት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ‹‹ጐል አገባለሁ ብሎ ከጨዋታ በፊት ለመናገር ይከብዳል፣ ሁላችንም የቡድናችን አባላት ከጨዋታው የምንፈልገውን ውጤት እናውቃለን፡፡ በህብረት በመስራት እናሳካዋለን›› ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በዋዜማው ላይ የሚገኘው በዕድል ነው አፍሪካ ዋንጫ ቢገባ እንኳን ያሳፍረናል የሚሉ አስተያየቶችን በተመለከተ አዳነ ግርማ ሲናገር ያን አይነት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ባይሆኑ ነው ብሎ ቡድናችን አሁን ላለበት ደረጃ የበቃው ሁሉም ተጨዋቾች ጠንካራ ዝግጅትና ትኩረት በመስራታቸው፤ ለተሻለ ውጤት መስዋዕትነት በመክፈል በመቆየታቸው እንጂ ዕድለኛነት ብቻውን ለስኬቱ መገለጫ አይሆንም ሲል አብራርቷል፡፡
እጃችን የገባውን እድል አሳልፈን አንሰጥም -
ምንያህል ተሾመ
ለነገው ጨዋታ ከባድ አደራ ስላለብን በበኩላችን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረው በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአጭር ጊዜ ጐልተው ሊወጡ ከቻሉ ወጣት ኮከቦች አንዱ የሆነው የደደቢቱ ምንያህል ተሾመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለ31 ዓመታት ሳትካፈል ከቀረችበት የአፍሪካ ዋንጫ በመመለስ ታሪክ መቀየር እንፈልጋለን የሚለው ምንያህል ተሾመ መገናኛ አካባቢ የሚገኘው 24 የተባለ ቀበሌ ልጅ ነው፡፡ እኔም እዚያ ሠፈር ነው ያደግኩት፡፡
የሠፈሩ ወጣቶች ብዙ መልካም ስም የላቸውም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ደረጃ ያለው የስፖርት ማዕከል የሚገነባበትና ጨፌ የሚባል ሜዳ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ15ኛው የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ ባሸነፈበት ወቅት በዚህ ሜዳ ላይ የቀድሞው መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም 100ሺ ሰው የሚይዝ ስታድዬም እገነባለሁ ብሎ ቃል የገባበትም ነበር፡፡
ምንያህል ተሾመ በዚያ ሜዳ ላይ ልምምድ የሚሠሩ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ተጨዋቾች ጋር ኳስ እየቀበለ አደገ፡፡ ከዚያም በፕሮጀክት ታቅፎ መስራት ቀጠለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ ቡና ቢ ቡድንን ተቀላቀለ፡፡ ከዚያ ወደ ዋናው ቡድን በማደግም በታላቁ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለ5 ዓመታት ሲጫወት ቆይቶ ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ከመብቃቱም በላይ ክለቡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን አስደናቂ አስተዋጽኦ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመፈፀም ተሳካለት፡፡ ከዚያም ቡናን ለቅቆ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አዲስ ሪኮርድ በነበረ የ350ሺ ብር የፊርማ ክፍያ በማግኘት ወደ ደደቢትን ክለብ ተዛውሮ እየተጫወተ ይገኛል፡፡በእግር ኳስ ከሰፈር ወጥቶ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ብቃት ላይ መድረስ ቀላል አይደለም የሚለው ምንያህል አሁን በደረሰበት ደረጃ ግን ለብዙ ታዳጊዎች መነቃቃት መፍጠሩን ይገልፃል፡፡ የሠፈሩ 24 ቀበሌ ልጆች በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች እየተከታታሉ ድጋፍ እንደሚሰጡት የሚናገረው ምንያህል እያገኘ ባለው ስኬት በስፖርቱ የመንቀሳቀስ ጉጉት ሲፈጥርባቸው ማስተዋሉን ይገልፃል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች በእኛ አገር እግር ኳስ ለተጨዋቾችና ለአሰልጣኞች የፊርማ ክፍያ እየተባለ የሚሰጠው ገንዘብ ተጋንኗል በሚል ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ዙርያ አንተ ምን ታስባለህ በሚል ከስፖርት አድማስ ለምንያህል ተሾመ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ ‹‹ለማንኛውም ተጨዋች ሆነ አሰልጣኝ የፊርማ ክፍያ ስለሚገባው ነው የሚከፈለው፡፡ በስፖርቱ የገንዘብ እንቅስቃሴ መጠናከሩ ለዕድገት እንደሚበጅ መታሰብ አለበት›› ብሏል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን የማውቀው በቲቪ ነበር ያለው ምንያህል አሁን ለመሳተፍ የምንችልበት አጋጣሚ ሲፈጠር የታሪክ ሰው ያደርጋል ብሎ ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማብቃት ታሪክ ለመስራት እኔም ሆነ መላው የቡድናችን አባላት ከፍተኛ ፍላጐት አለን ብሏል፡፡
‹‹በእርግጥ የነገውን ጨዋታ ጫና ውስጥ ሆነን ነው የምናደርገው፡፡ ጫናው ደግሞ ትልቅ ህዝባዊ አደራ ስላለብን ነው፡፡ ይህን አደራ በብቃት ለመወጣት ሁሉንም ትኩረት ለጨዋታ አድርገናል፡፡ በሜዳችን በምናደርገው ጨዋታ እጃችን የገባውን ዕድል አሳልፈን አንሰጥም፡፡ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለን ውጤታማ ለመሆን ሁላችንም እንፈልጋለን›› በማለትም ምን ያህል ተሾመ ለነገው ጨዋታ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የሰጡትን ትኩረት አብራርቶታል፡፡
ለአፍሪካ ጨዋታ መብቃት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩትም ምን ያህል ተሾመ ይናገራል፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ መቻል ለቀጣይ ትውልድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈት መሆኑን የገለፀው ምንያህል ተሾመ ታዳጊዎችና ወጣቶች በኛ ውጤት ተነሳስተውና ተበረታተው ለተሻለ ታሪክና ስኬት እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል ብሏል፡፡ በነገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜታዊ ቢሆን ለምናሳየው ውጤት በመጓጓት ሊሆን ይችላል ብሎ የተናገረው ምንያህል ተሾመ ብሔራዊ ቡድናችን ዘና ብሎ ተጫውቶ፣ ህግ አክብሮና ስፖርታዊ ጨዋነት አሳይቶ በሚያሳምን ብቃት ውጤቱን አስጠብቆ በመውጣት እንደሚያሸንፍ አምናለሁ ብሏል፡፡
ስታድዬም ገብተን አርዓያነት ያለው ድጋፍ እናሳያለን-አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ኃይማኖት
ለ8ኛው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕ ተሳትፎ የበቃውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የሚመራው አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከጫፍ የደረሰበት ሁኔታን ጅማሮው ጥሩ መሆኑን፣ በእግር ኳስ ጥሩ ተነሳሽነት መፈጠሩን የሚያሳይ የዕድገት አመላካች ነው በሚል ገልጾታል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ለውጥና የእድገት አቅጣጫ የሚወስዱ ፍንጮች መታየታቸውን አምንበታለሁ ብሎ የሚናገረው አሰልጣኝ አብርሃም በሴቶችም ሆነ በወንዶቹ ብሄራዊ ቡድኖች በአህጉራዊ ውድድሮች የታየው ውጤታማነት ዘላቂነት እንዲኖረው ብዙ መሰራት እንዳለበት ግን ያሳስባል፡፡
ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍ አስደሳች ዜና ነው ግን ለእግር ኳስ ዘላቂ ዕድገት የሚበጁ ተግባራት ላይ ያሉብን ድክመቶችን እንዳይሸፈኑ ያሰጋኛል የሚለው አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ኃይማኖት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በፕሮፌሽናል አደረጃጀት፤ በበቂ የፋይናንስ አቅም፤ ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ ድጋፍ የተጠናከረ አለመሆኑን ለማሻሻል ትኩረት ያስፈልገናል የሚል ምክር ይሰጣል፡፡ ክለቦች ከመንግስት ጥገኝነት ተላቅቀው የሚሠሩበት የፋይናንስና የድጋፍ አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ባለሀብቶች ወደ ስፖርቱ እንዲቀርቡ እንጂ እንዲርቁ ከሚያደርጉ ተግባራት በመቆጠብ የስፖርት ቤተሰቡ ስርነቀል ለውጥ ማሳየት ይጠበቅበታል ብሏል አሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት
ለነገው ጨዋታ ልጆቼን ይዤ እገባለሁ ያለው አሰልጣኝ አብርሃም ተክለኃይማኖት (ልጆቼ ያላቸው ሉሲዊችን ነው) በድጋፍ አሰጣጣችን ስታዲዬም የገባውን ህዝብ የሚነያሳሳ ተግባር በማሳየት አርአያ ለመሆን እየተዘጋጀን ነው ብሏል፡፡ ብሔራዊ ቡድን ስንደግፍ ያለማቋረጥ 90ውን ደቂቃ እንደ 12ኛ ተጨዋች ሆነን በመልካም የስፖርት ባህርይ መሆን አለበት የሚለው አብርሃም ተ/ኃይማኖት ደጋፊዎች የግለሰቦችን ስም አየጠሩ፣ በአሰልጣኞች ስራ እየገቡ፤ እየተሳደቡና በስም እየተጣሩ የቡድኑን ትኩረት በሚረብሽ አጓጉል ድጋፍ የሚያዘናጋ ተግባር እንዳይፈፅሙ አሳስቧል፡፡ የስፖርት ቤተሰቡ የሚደግፈው ብሔራዊ ቡድን በሚያሳየው የጨዋታ ብቃት ሙሉ ብልጫ ወስዶ ተጋጣሚውን እንዲያሸንፍ የሚሰጠው ድጋፍ በስፖርታዊ ጨዋነት መታጀቡ ክብርና ሞገስ ነውም ብሏል፡፡

Read 4865 times