Saturday, 13 August 2022 00:00

አዲሱ የአፍሪካ ‹‹ሱፕር ሊግ››

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ስያሜው ወደ አፍሪካን ፉትቦል ሊግ ሊቀየር ይችላል፡፡ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይሆንበታል፡፡ ለካፍ አባል አገራት    በየዓመቱ 1 ሚሊዮን ዶላር በነፍስ ወከፍ ይከፋፈላል፡፡

        የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (CAF) ከዓመት  በኋላ አዲስ አህጉራዊ የክለቦች ውድድር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በታንዛኒያ ዋና ከተማ አሩሻ  በተካሄደው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካ ‹‹ሱፕር ሊግ›› በሚል ስያሜ የተጠነሰሰው ፕሮጀክት ፀድቋል፡፡  በአውሮፓ አህጉር ተሞክሮ በከፍተኛ ተቃውሞ ሳይሳካ የቀረውን ‹‹ሱፕር ሊግ›› የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ‹‹የአፍሪካ ፉትቦል ሊግ›› በሚል ስያሜ ሊያካሂድ መወሰኑን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የካፍ ፕሬዝዳንት የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊው ዶክተር ፓትሪስ ሞትሴፔ በሊጉ ምስረታ የአፍሪካ እግር ኳስ በከፍተኛ የገቢ  ምንጮች የሚነቃቃበት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፈት ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ ‹‹ሱፕር ሊግ›› ምስረታው የካፍ አባል የሆኑት 52 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች፤ የአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች መሪዎች፤ የእግር ኳስ  ባለታሪኮችና የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተሳትፈዋል፡፡
የሞትሶፔና የካፍ አቋም
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሞትሶፔ አዲሱ የአፍሪካ ‹‹ሱፕር ሊጉ›› በስፖንሰርሺፕ የተጠናከረ እንደሚሆን በአፍሪካ እግር ኳስ ታይቶ የማይታወቅ መዋዕለ ንዋይ እንደሚንቀሳቀስበት ቃል ገብተዋል፡፡ ክለቦች ከአውሮፓ እግር ኳስ ጋር የሚመጣጠን ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ፤ ለምርጥ ተጨዋቾቻቸው የተሻለ ደሞዝ በመክፈል ከስደት የሚታደጉበት እድል ይፈጠርላቸዋልም ብለዋል፡፡
አዲሱ አህጉራዊ ውድድር የአፍሪካን ክለቦች በገቢ ሊያጠናክር እንደሚችል በስፋት እየተገለፀ ይገኛል፡፡ ከሁሉም የአፍሪካ ዞኖች የተውጣጡ 24 ክለቦች በሊጉ ላይ እንደሚሳተፉ እየተጠበቀ ሲሆን ለአሸናፊው ክለብ 11.6 ሚሊዮን ዶላር መሰጠቱና በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ በየደረጃው እንደሚከፋፈልበት ተወስቷል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከአዲሱ አህጉራዊ ውድድር ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚጠብቅ በየዓመቱ ለኮንፌደሬሽኑ አባል አገራት 1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚከፋፍልም ተነግሯል፡፡ የካፍ ፕሬዝዳንት ሞትሴፔ በኮንፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ በሊጉ ምስረታ ለስፖርቱ መሰረተልማት፤ ለተጨዋቾች ደሞዝ፤ ለክለብ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ገቢ መፍጠር ዋና እቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል። በየዓመቱ ከ200 እስከ 300  ሚሊዮን ዶላር ገቢ የምንጠብቅበት ይሆናልም ብለዋል፡፡  በአህጉራዊ ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች በነፍስ ወከፍ እስከ 2.4 ሚሊዮን ስለሚሰጣቸው በውድድሮቹ ላይ በመላው አህጉሪቱ ተዟዙር የሚጫወቱበትን የጉዞ ወጭዎች መሸፈን ይችላሉ፡፡ ምርጥ ተጨዋቾችንም ከየአገሩ በተገቢው ክፍያ ማዘዋወር የሚችሉበትን እድል ያገኛሉ ነው የተባለው፡፡ እንደካፍ ገለፃ በቶታል ኤነርጂስ ስፖንሰር የሆኑት ሁለቱ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አህጉራዊ ውድድሮች የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌደሬሽን ካፕ ከሶስተኛው ውድድር ፈሰስ የሚሆንላቸው ጥቅምም ይኖራል፡፡የአፍሪካን እግር ኳስ በቅልጥፍና ለማሳደግ የክለቦችን አቅምና የተጨዋቾችን ብቃት ለመጨመር፤ ለስፖርት መሰረተልማትና ለደጋፊዎች የሚሆኑ ተግባራትን ለማከናወን ያግዛል፡፡ እግር ኳሱን ከደጋፊዎች ጋር በማስተሳሰር አዳዲስ የእግር ኳስ ተሰጥአዎችን ለማፍራት ምክንያት ይሆናል። ለክለቦች እና ለፌደሬሽኖች የገቢ ምንጮችንም በሰፊው የሚፈጥር ይሆናል፡፡
በሊጉ ምስረታ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሚና
ሱፕር ሊጉን የሚመሰረበትን ፕሮጀክት ከ2 ዓመት በይፋ ያስታወቁት የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ነበሩ፡፡ በሞሮኮ በተካሄደ የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካ ምርጥ 20 ክለቦች የሚሳተፉበት፤ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝና ከዓለም ምርጥ 10 ሊጎች ተርታ የሚቀመጥ ሊግ አህጉሪቱ እንዲኖራት መክረው ነበር፡፡ ከሊጉ ምስረታ ጋር ተያይዞም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በድጋሚ ለሚወዳደሩበት የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሙሉ ድጋፍ መስጠቱም ተወስቷል፡፡ ፊፋና ካፍ ለ52 ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት አላቸው። በክለብ እግር ኳስ የተያዙ ፕሮጀክቶች ላይ እንደ ቡድን ተጣምረው እየሰሩ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡
ሊጉን በመደገፍ
በአህጉራዊው የሊግ ውድድር ምስረታ ዙርያ በርካታ የድጋፍ አስተያቶች ተሰጥተዋል። ናይጄርያዊው ፊኒዲ ጆርጅ ለጎል ስፖርት በሰጠው አስተያየት ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት የሚረዳ  ውሳኔ መሆኑን ሲያደንቅ፤ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተሳተፉትና የታንዛኒያውን ሲምባ የስፖርት ክለብ የወከሉት ባርባራ ጎንዛሌዝ እግር ኳስ ንግድ መሆኑን በመጥቀስ ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበት ውድድር መፈጠሩ አዎንታዊ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ክለብ ካይዘር ቺፍ ማርኬቲንግ ዲያሬክተር  በበኩላቸው ‹‹ ለአፍሪካ ክለቦች ሌላ አዲስ ውድድር መፈጠሩ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ክለቦች ብዙ ጨዋታዎችን  በማድረግ የተሻለ ገቢ ሊያነጩ ይችላሉ›› ብለው ሲናገሩ፤ ኮትዲቯራዊው የቀድሞ ተጨዋች ቺኮ ታይኔ ደግሞ ትልልቅ ክለቦችን በማገናኘት  ከፍተኛ ገቢ የሚመነጭበት ምርጥ ሐሳብ በማለት ድጋፉን ሰጥቷል፡፡
ሊጉን በመቃወም
የታላላቅ ክለቦችን ሱፕር ሊግ የመመስረት ተመሳሳይ  ሐሳብ ከዓመት በፊት በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ለመተግበር የተደረገው ሙከራ ከፍተኛ ትችት እንደገጠመውም ይታወሳል፡፡  ሱፕር ሊግ የሚለው ስያሜ በአውሮፖ አህጉር ከገጠመው ተቃውሞና ትችት አንፃርም አፍሪካ ላይ ላይቀጥል እንደሚችል የዘገበው ሮይተርስ ነው፤ አህጉራዊ ውድድሩ ምናልባትም አፍሪካ ፉትቦል ሊግ ብሎ ሊሰየም እንደሚችልም ተወስቷል፡፡  የአውሮፓ ሱፕር ሊግን ለማቋቋም ግዙፍ ክለቦች ሲነሱ ለራሳቸው ከፍተኛ ገቢ አመንጭተው የተወሰነ ድርሻ ለአውሮፓ እግር ኳስ በማበርከት ለመስራት በማቀድ ነበር፡፡ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር፤ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ ገጥሟቸው እቅዳቸውን ሳይተገብሩ ቀርተዋል። የአውሮፓ ሱፕር ሊግ ምስረታው የጥቂቶችን ሃያልነት የሚፈጥርና ስኬታማውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚቀናቀንና የሚያጠፋ በሚሉ ትችቶች ተቀባይነት እንዳጣ ይታወሳል። የአፍሪካ ሱፕር ሊግም ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ እየተሰነዘረበት ነው፡፡ በተለይ የደቡብ አፍሪካ ተጨዋቾች ማህበር ትችት በመሰንዘር የመጀመርያው ነው፡፡ ማህበሩ ባወጣው መግለጫ ሱፕር ሊጉ በጉስቅልና ላይ የሚገኘውን እግር ኳስ ወደማይወጣበት አስቸጋሪ አዘቅት ይከተዋል ብሏል፡፡
በሊጉ እነማን ይሳተፋሉ?
በአዲሱ የአፍሪካ ‹‹ሱፕር ሊግ››  የውድድር አመራር  መሰረት በ10 ወራት ውስጥ በመላው አፍሪካ 197 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በ3 የአፍሪካ ዞኖች ከሚገኙ 16 አገራት የተወከሉ 24 ክለቦች  3 ምድቦች  የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም 16 ክለቦች በሚፋለሙበት የጥሎ ማለፍ ውድድር ይገባሉ፡፡ በመጨረሻም የዋንጫው ፍልሚያ በተመረጠ የአፍሪካ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ አዲሱ አህጉራዊ ሊግ ከዓመት በኋላ 24 ክለቦችን በማሳተፍ እንደሚጀመር ከተገለፀ በኋላ እነማን ይሳተፋሉ? በሚለው ጉዳይ በርካታ ትንታኔዎች ተሰራጭተዋል። በአህጉራዊ ውድድሩ ለመሳተፍ የፉትቦል አካዳሚ እና የሴቶች ቡድን የመሰረተ ክለቦች ከዋናዎቹ መስፈርቶች እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ውድድሮች ካላቸው ጠንካራ ተሳትፎ በመነሳት የታዋቂ ክለቦችና የምርጥ ሊጎች የተሳትፎ ኮታም እየተገመተ ነው፡፡ 10 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነው የግብፁ አል አሃሊ፤ የደቡብ አፍሪካዎቹ ኦርላንዶ ፓይሬትስና ሜመሎዲ ሰንዳውንሰ፤ የሞሮኮዎቹ ዋይዳድ ካዛብላንካና ራጃ ካዛብላንካ፤ የኮንፌደሬሽን ካፕ ሻምፒዮኑ አርኤስ ቤርካኔ፤ የኡጋንዳው ሲምባ፤ የታንዛኒያው ያንጋ፤ 5 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነው ቲፒ ማዜምቤ መሳተፋቸው እንደማይቀር የተዘገበላቸው 10 ክለቦች ናቸው፡፡
ፉትቦል ዳታቤዝ በሰራው ትንታኔ በአዲሱ ውድድር መሳተፍ የሚችሉ አገራትን በነጥብ ደረጃ አውጥቶላቸዋል፡፡ ድረገፁ የአፍሪካ ምርጥ 10 ሊጎች ናቸው በሚል የዘረዘራቸውን ክለቦች ነጥብ የሰጠው በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌደሬሽን ካፕ እንዲሁም በካፍ የአምስት አመት የውጤት ደረጃ ያለቸውን መረጃ በመንተራስ ነው፡፡ በ‹‹ሱፕር ሊጉ›› ላይ እያንዳንዳቸው ሁለት ክለቦችን ለማሳተፍ የሚችሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡ የሞሮኮው ቦቶላ ፕሮ  የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግን 6 ጊዜ ያሸነፉ ክለቦችን በመያዝ በ190 ነጥብ የመጀመርያውን ደረጃ ይወስዳል፡፡ የግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ የአፍሪካ ሻምፒዮን 15 ጊዜ 167 ነጥብ፤ የቱኒዚያ ሊግ ፕሮፌሽናሌ 1  የአፍሪካ ሻምፒዮን 6 ጊዜ 140 ነጥብ፤ የዲአርሲ ኮንጎ ሊና ፉት ቮዳኮም ሊግ 1 የአፍሪካ ሻምፒዮን 6 ጊዜ 83 ነጥብ፤ የአልጄርያ ሊግ 1 የአፍሪካ ሻምፒዮን 5 ጊዜ 81 ነጥብ፤ የደቡብ አፍሪካ ፕሪሚዬር ሶከር ሊግ የአፍሪካ ሻምፒዮን 2 ጊዜ  65.8 ነጥብ፤ የዛምቢያ ሱፕር ሊግ 43 ነጥብ፤ የናይጄርያ ፕሪሚዬር ፉትቦል ሊግ የአፍሪካ ሻምፒዮን 2 ጊዜ 39 ነጥብ፤ የጊኒ ሊግ 1  የአፍሪካ ሻምፒዮን 3 ጊዜ  34 ነጥብ እንዲሁም የአንጎላ ጊራቦላ  36 ነጥብ በማስመዝገብ እስከ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሱዳን 29.5፤ ሊቢያ 16.5፤ ታንዛኒያ ሊግ  14፤ አይቬሪኮስት 13፤ ኬንያ 11፤ ዚምባቡዌ 11፤ ሞዛምቢክ 9፤ ሪፖብሊክ ኮንጎ 8፤ ኡጋንዳ  8 እና ጋና 6.5 ነጥብ ይዘው እስከ 20ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

Read 16310 times