Wednesday, 17 August 2022 20:15

ትሪ እንደ ዶሚኖ

Written by  አያልቅበት አደም
Rate this item
(0 votes)

 ለሥራ ጉዳይ ወደ ቀድሞው መ/ቤቴ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ አስቸኳይ ጉዳይ ይዤ ያለቀጠሮ ነበር ከረፈደ የደረስኹት፡፡ አለቅየው ከአለቃቸው ዘንድ ስብሰባቸውን ጨርሰው እስኪመጡ ከፀሐፊያቸው ጋር ከመፋጠጥ ክበብ መቀመጡን መረጥሁ፡፡ ሰውየው ግን እስከ ምሳ ሰዓት ከስብሰባ አልወጡም፡፡ ወዳጄ ዳኒ መጣና ምሣ አብረን እንበላ ዘንድ መልካም ፈቃዱ ኾነ፡፡ የፆም በያይነቱ በኒኬል ትሪ ተዘርግቶ መጣልን፡፡ ድሮ የማውቀው ትሪ ነው፡፡ አስተናጋጇ ከጠረጴዛው ላይ ትሪውን ስታስቀምጥ የተሰማው ድምጽ ትሪው “የጠፋ ሰው” ብሎ ሰላምታ የሰጠኝ መሰለኝ፡፡ . . . “ጊዜ በጊዜ ቀለበት ሰተት” እንዲል ጋሽ ደበበ ሰይፉ፣ በትዝታ ዘመናትን ወደ ኋላ መልሼ ሽው በትሪ መስኮት . . . .
ነጋ አጽብሃ
የክበቡ ኃላፊ ነጋ አጽብሃ ይባላል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንደተቀሰቀሰ ከእኛ ወገን የዓይናቸው ቀለም ካላማረን መካከል ቀዳሚው እርሱ ኾነ፡፡ ነጋ ባተሌ የክበብ ሃላፊ ነው፡፡ ክበቡን የሚያስተዳድረው ሣይኾን ጫንቃው ላይ ተሸክሞት የሚኖር ነበር የሚመስለው። የስኳር ህመምተኛ መኾኑ ትዝ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ ፋታ ሲያጣ የኛን ምሣ ላለማጉደል የገብስ ዳቦውን እየገመጠ ምሳ ተሟልቶ እንዲቀርብልን፣ ከአንደኛ በር ሁለተኛ በር እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ቱር ቱር ይል ነበር፡፡
ፊልም፣ ምሣና ተመስጦ
ከምሣው ጋር ደግሞ በየዕለቱ ፊልም ይቀርባል፡፡ ከሲማ አሌክትሮኒክስ እየተከራየ ነበር የሚያመጣው፡፡ ታይታኒክን ከርሱ ላይ ተከራይቼ በጎረቤት ማጫወቻ ነበር ያየሁት (ድሃ በጉልበቱ ሃብታም በንብረቱ መኾኑ ነው አለ ታደሰ ደበሌ)፡፡  በምሣ ሰዓት ወደ ቴሌቭዥኑ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ የሚቀመጡ ሶስት ሰዎች አሉ፡፡ አንደኛው በተመስጦ ነው የሚያየው፣ ሁለተኛው በየንግግሩ መሃል እንዲህ ማለቱ እኮ ነው፤ እንዲያ ማለቱ ነው ማለት ይወድዳል፡፡ ሶስተኛው ሰለ ፊልሙ የታሪክ አወቃቀር፣ የሴራ መዋጣት የሚተነትን ነው። ከእነሱ ጀርባ ግድግዳ ታክከው የሚቀመጡ ሶስት ወይዛዝርት ነበሩ፡፡ የሚታየው ፊልም ላይ የፍቅር ትዕይንት ሲመጣ እነርሱን ማየት ራሱን የቻለ ትርዒት ነው፡፡ አንደኛዋ ጣቶቿ የሚቀጥለውን ጉርሻ ማጅሞልሞላቸውን ያቀሙና፣ ዓይኖቿ በሙሉ ትኩረት የቴሌቭዥኑ መስኮት ላይ ይተከላሉ፡፡ ዓይኖቿ የሲጋራ ጢስ እንደሚከላ አጢያሽ ጨንቆር ብለው፣ ፊቷ ላይ መንገድ የቀረ ፈገግታ ያረብባል፡፡ ሁለተኛዋ በስላች ትቀመጥና፣ ዓይኖቿን አንዴ ወደ ምሣ ዕቃው አንዴ ወደ ቴሌቭዥኑ ትሰዳለች፡፡ ወደ ቴሌቭዥኑ ስተመለከት ትንሽ ፋታ ትወስዳለች። ሶስተኛዋ ለመጉረስ ያጠቀሰችውን ጉርሻ በያዘችበት እጇ አይበሉባ አገጯን ትደግፍና፣ በርቀት ወደሚታየው የመሥሪያ ቤቱ መግቢያ በር ትመለከታለች፡፡
ምሣ የምንበላው ለሶስት ነው፡፡ ታዳ፣ ዳኒ እና እኔ፡፡ ታዴ ምሣ ይቋጥራል፡፡ (ለምሣ ስንነሣ ላፕቶፔን ይዤ መጣሁ ይላል) የሁለታችን የዕለቱ የክበብ ምግብ በትሪ መጥቶ ከጠረጴዛው ላይ ሲሾም፣ ታዴ የምሣ ዕቃውን መፍታት ይጀምራል፡፡ በታዴ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ብሶቶች እያወራረድን ምሣ ይበላል፡፡ ትሪው ላይ መጨባበጥ ሲቀረን እኔ ወይ ዳኒ ቀድመን “በቃኝ” ብለን እናቆማለን፡፡ “ባይበቃህስ” ይላል ታዴ፤ የመጨረሻውን ጉርሻ እያነሣ “እኔን ልትበላ ነው?”
Mgt201 አጠናብን
ክክበቡ በስተቀኝ ከሰው ሃብት አስተዳደር ዋና ክፍል አጠገብ፣ የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል ይገኛል፡፡ እዚያ የጋሽ ተመስገን ቢሮ አለ፡፡ ጋሽ ተመስገን ፀጉሩ ሙሉ ሽበት ነው፡፡ ቁመቱ ደግሞ ረዥም፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ ሶስዮሎጂ ያጠና ነበር፡፡ (ከግቢ ውጭ፡- አንድ ቀን ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ከሌላ ሰው ጋር ቆሞ የነበረ አንድ የማውቀው ወዳጄን ጋሽ ተመስገን ሰላም ብሎት ያልፋል፡፡ ልጁ ወዳጄን “አስተማሪህ ናቸው ወይ?” ብሎ ቢጠይቀው አብረው የሚወስዱት ኮርስ እንዳለና አንድ ባች መኾናቸውን ቢነግረው፤ “ምነው ዲግሪ የሌለው መንግስተ ሰማያት አይገባም ተባለ ወይ?” ብሎ እንደመለሰለት አጫውቶኛል፡፡) አንድ ቀን የመሥሪያ ቤቱ ሥራ አመራር አጠቃላይ ስብሰባ ጠራ፡፡ መ/ቤቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ምን ይደረግ? እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ሥራውን በብቃት እንዴት ይወጣ? የመሳሰሉት ሃሣቦች የስብሰባው አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ የሥራ አመራር ሰዎች ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ ሠራተኞች ሃሣብ እንዲሰጡ መድረኩ ክፍት ኾነ፡፡ ጋሽ ተመስገን እጁን ከፍ አድርጎ ዘረጋው። ከፍ ብሎ የተዘረጋው እጁ ከሸበተ ጠጉሩ ጋር የተዘቀዘቀ እንዝርት መሰለ፡፡ “አንድ ድርጅት ሶስት የማኔጅመንት ደረጃ አለው፡፡ Top level Management; Middle Level Management; እና Low Level Management ናቸው፡፡ እነ ፍሬዴሪከ ቴይለርን ጠቅሶ፣ እነ ሔነሪክ ፋዮልን አክሎ፣ ቻርስ ባቤጅን ሰልሶ፣ የአብርሃም ማስሎውን የፍላጎት እርከን ከሰራተኛው ሥነ ልቡና ጋር አስተማስሎ፣ ብዙ ተነተነ፡፡ እና ይኽንን የሥራ አመራር መርህ ጠንቅቆ ማወቅ የተገባ እንደኾነ አሣስቦ ጨረሰ፡፡ ውይይቱ ሞቅ ብሎ ቀጠለ፡፡ ከአራት ወይንም አምስት ተናጋሪዎች በኋላ ጋሽ ተመስገን እጁን አወጣ። “ቅድም ስናገር የሰማችሁኝ አልመሰለኝም፡፡ ለዚህ ነው ተደጋጋሚ ሃሣብ እየቀረበ ያለው” ብሎ የቀደመውን ትንታኔ ደገመው፡፡ “ጋሽ ተሜ Mid exam ደርሶበታል መሰለኝ Mgt201 አጠናብን” አለ አንድ ታዛቢ፡፡
ማገደን
ስብሰባው ሊጠናቀቅ ሥራ አስፈፃሚው የመዝጊያ ንግግር ሊያደርጉ ድምጽ ማጉያ ሲያስተካክሉ፣ አንድ ሰው እጁን አወጣ። “እንደሚታወቀው ከድርጅታችን ጋር ተመሣሣይ ሥራ የማሰሩ በርካታ የግል ድርጅቶች ተቋቁመው ገበያውን ተቀላቅለዋል። እነርሱ ቅዳሜ ቀን ሲሰሩ እኛ ቅዳሜ ሥራ የለንም፡፡ ይህን ነገር በየክፍላችን ተማክረንበት ለምን ቅዳሜ የሥራ ቀን አይኾንም፡፡” አዳራሹን ህምምታ ሞላው፡፡
“አይ ድርጅታዊ ሥራ . . . ባለቀ ሰዓት ይማግደን?” አለ አንዱ የገባው፡፡
***
በትዝታ መርከብ ያሣፈረን ትሪ ላይ ከመጨባበጣችን በፊት ምሣው አበቃ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 831 times