Monday, 15 August 2022 00:00

የሼክስፒር ሙሉ ሥራዎች ስብስብ

Written by  በሰር ዶናልድ ዎልፊት ትርጉም- ነቢይ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

መቅድም
በዚህ መጽሐፍ ገጾች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ እጅግ ቆንጆ ቆንጆ ቃላት አሉ። በዚህ መጽሐፍ ገጾች ውስጥ በየትኛውም ቋንቋ ውብ ተደርገው የተፃፉ ታላላቅ ቴአትሮች ይገኛሉ። ይህ የሥነ-ጽሁፍ ቅጽ፤ የቅርሶቻችን አካል ሆኗል። ወደተለያዩ የዓለም ቋንቋዎችም ተተርጉሟል። የእያንዳንዱ ብሔርና ነገድ፣ የእያንዳንዱ ባሕል፣ ሥጋና ደም ሆኗል። የሥነ-ጽሁፍና የድራማ የማዕዘን ደንጊያም ሆኗል። የዊሊያም ሼክስፒር ጽሁፍ ሥራዎች እንደ ባክ(ች) ሙዚቃ፣ ወይም እንደ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ ቅቦች የጊዜንና ቦታን ጠባብ ክልል ጥሰው፣ በማናቸውም ሰዓት፣ ለማናቸውም የሰው ልጅ፣ ዘለዓለማዊ መልዕክት የሚያስተላልፉ ጥበባት ሆነዋል።
ሼክስፒር ሁለንተናዊ የድራማ ሰው ነው። ሼክስፒር ራሱ ከጻፈው በላይ ስለሱ ተጽፏል። ከተማሪ ቤት ልጆች፣ እስከ ተከበሩ ጌታ ባላባቶች፣ ከሊቃውንት እስከ ሳይንቲስቶች፣ የሂሳዊ ተንታኞቹ ቁጥርና የትንታኔው ብዛት በእጅጉ እየሰፋ፣ እያደገ፣ እየተመነደገ ሄዷል።
 ሼክስፒር እጅግ ማራኪ የሆኑትንና ውስብስብ የሚባሉትን ንድፈ-ሃሳቦች፡- በፀሐፊነት ላይ ከሚነሱ ሙግቶች አንስቶ፣ እስከ ምርጥ ምሁራዊ ጥናቶች ያሉ ንድፈ-ሃሳቦችን የማረከና የነቀነቀ ጸሃፊ ነው። ቦውድለር ቴአትሮቹን ሴንሰር አድርጎለታል። ሌሎች ፀሐፊዎች ጭብጦቹን በመውሰድ አዘምነዋቸዋል። አሜሪካኖች ወደ ሙዚቃዊ ድራማ ለውጠዋቸዋል። ጣሊያኖችም ያው ያለጥርጥር እንደተለመደው ኦፔራ ሰርተውባቸዋል። አዋቂ ነን - ባዮችም፣ ፈዛዛ ምሁራዊ ልምምዶች ሲያደርጉባቸው፣ የተማሪ ቤት ኃላፊዎች ደግሞ መስመሮቹን ማስጠናትን እንደ ቅጣት (መቀጣጫ) ተገልግለውበታል። ሆኖም ሼክስፒር ስለሱ ትችትና አጓጉል ወቀሳ የተፃፈ የታተተውንም ሁሉ ተቋቁሞ፣ የተደረገበትን ሁሉ ወደ ጎን ትቶ፣ የምጽፈው ለቴአትር ብዬ ነው ብሎ በአቋሙ ጸና። በየጊዜው ተዋንያን  በተደራሲያን ፊት ለቴአትሩ ህይወት በሰጡለት ቁጥር እንደገና ነብስ ይዘራል። የትወና ስራው የድራማውን ነብስ-አንቂነት ጉልበት ያጎናጽፈዋል። ቃላቶቹም የተዋናዩ ጥበብና የድራማው - ሰው ፍቃደ ልቡና መሳሪያ ይሆናሉ።
ሼክስፒር በስራው ዙሪያ “ምን አይነት ተዓምራዊ ነገር እየተከሰተ መሆኑን ሲያይ እንዴት ይደነቅ” ማለቱ አይቀሬ ነው። እስቲ እሱን አስቡት፡- ተዋናይ-ጸሃፊ፣ ለእለት እንጀራ ሲል በቴአትር ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ። ቲያትር መለማመድ፣ መተወን፣ መጓዝ፣ አንዳንዴ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ በሆነ ውጥረት ለተሰመረ የማስረከቢያ ቀን ስራው እንዲደርስ፣ ሌት ተቀን መጻፍ። ምናልባት የመጨረሻው ገቢር ስላላስደሰተው ወደ ልምምዱ መሮጥና የቴአትሩን የመጀመሪያውን ክፍለ ንባብ  ሀ ብሎ ማዳመጥ ይኖርበታል። ተዋንያኑ አስተያየታቸውን በጮክታ ይሰጣሉ። “አንዳንዶቹ መስመሮች ለማለት አስቸጋሪ ናቸው” ወይም “ይሄን ይሄን ትእይንት ለመተወን አዳጋች ነው፤ ለውጥልን” ይሉታል። እናም እሱ በትዕግስት ሲያዳምጥ፣ አስፈላጊ ነው ያለውን ቦታ ሲያርም እና ቴአትሩ ለተመልካች ምቹ የሚሆንበትን ቅጽበት ሲጠብቅ ይቆያል።
መስመሮቹ መቼ እንደሚነገሩና እንደሚሰሙ፣ ያ የሳቅ ጅረት መድረኩን አቋርጦ መቼና እንዴት እንደሚፈስስ አሊያም አንዳች በድን የሚያደርግ ድራማዊ ተአምር እንዴት ሰውን ጨብጦ እንደሚይዝ የሚታይበትን ሰዓት ይጠባበቃል። በተዋናይና በቲያትር ተመልካች መካከል ያለው ግንኙነት፣ያለው ህያው ልምድ ይሄው ነው።
ከዊልያም ሼክስፒር ቴአትር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የምትተዋወቁት በቴአትር ቤት ነው። ተስፋ የማደርገውም፣ የፈጣሪውን ዘላለማዊ ጥራትና ብቃት የምትረዱትም እዚህ ነው። የቴአትሮችን ህይወት ለመጀመሪያ ጊዜ የምትቀምሱት ቴአትር ቤት ነው።
ከዚያ በኋላ ደግሞ፣ ምናልባት ይሄንን ሃተታ ወስዳችሁ ታነቡት ይሆናል። ምነው ቢሉ፣ የተውኔቱ ዘላቂና ኗሪ መዝገብ ነውና። በእነዚህ በታተሙ ገጾች ውስጥ ስሜታችሁን የነኳችሁን ነገሮች ዳግመኛ ታገኙ ይሆናል። እጅግ የወደዳችኋቸውን መስመሮች /ምንባቦች ወደ ማስታወሻ ማህደራችሁ ልትከቷቸውም ትችላላችሁ። ተውኔቱን ባነበባችሁትም ቁጥር፣ እናንተ አብራችሁ ታድማችሁ የነበረውን ተመልካች ዋቤ ታደርጋላችሁ። ሼክስፒር ራሱ ስለ ተዋንያን ሲናገር፡-
“በትንሿ ህይወታችን ላይ ህልማችን እንደተሰራ
የኛም ነገረ-ሥራ ይህንኑ መሳይ ነው
በእንቅልፍ የተከበበ
በመኝታ የታቀበ።”
እነሆ ይህ መጽሐፍ አሁን 400ኛ ዓመት የልደት በዓሉ ለሚከበረው ለታላቁ የድራማ… ሰው ዘላለማዊነት፣ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ እግረ መንገዴን ምስጋናዬንም ለማቅረብ ነው። ይሄ የሱ ስጦታ ነው። የኔ ምኞት፤ መጽሐፉ የረዥም ጊዜ ወዳጃችሁና ተድላ-ደስታችሁ እንዲሆን ነው።
ሰር ዶናልድ ዎልፊት

“የእሱን ፎቶውን አትዩ፤ መፅሐፉን እንጂ”
ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ራሱ ሐምሌትን የጻፈበትን ወቅት ሲያስታውስ እንዲህ ይለናል፡- “ከማክቤዝ በኋላ፣ የከርሞ ሰውን” በአማርኛ፣ “የዋርካ ሥር ትንግርትን” (Oda oak Oracle) በእንግሊዘኛ ጻፍኩ። የሀምሌትን ትራጀዲ ወደ አማርኛ የተረጎምኩት፣ ወይም አዳፕቴሽን እንደሚሰኘው ቋንቋው በቋንቋ የተመለሰው (የተዳቀለው) በ፲፱፻፶፯ ዓ.ም በክረምት ወራት፣ እስራኤል ሆኜ ነው። መልካም ተሰጥዎአቸውን፣ ጊዜያቸውንና ትዕግስታቸውን በመለገስ ዝግጅቱን እንድመራና ለህዝብ እንዳቀርብ ላበቁኝ የሃምሌት ዝግጅት ክበብ አባሎች እድሜ ይስጥልኝ ማለቴን እያስቀደምኩ፣ ከተተረጎመ ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ ሐምሌት፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ሊታይ በቃ።”
በቪተንበርግ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ቤት ህይወት ውስጥ አእምሮ ልቦናው በምርምር የተመሰጠው ጎልማሳው ልዑል ሐምሌት-ያረጋዊ አባቱን ድንገተኛ ሞት እንደተረዳ፤  ኤልሲኖር ወደሚሰኘው  የምድረ-ደን ቤተ-መንግስት በርግጎ ገሰገሰ። አጎቱ ገላውዴዎስም የሐምሌትን እናት፤ መንፈሰ ደካማይቱን ንግስት  ገርትረድን አግብቶ ዘውዱን በመሰሪ ጭኖ፣ ሐምሌትን  በጽኑ ያይን ቁራኛ አስጠብቀው።
ሐምሌት ከሰቀቀኑ ፋታ በተነፈገበት ሰዓት ብቸኛ ልቡን ለአፈ-ንጉስ ለጶሎኔዎስ ሴት ልጅ፤ ለውቢቱ ለወይዘሪት ሆይ - ወፌ-ይላ፣ በፍቅር ከፈተላት። ወጣቷ ወፌ-ይላም በጮርቃ ስሜቷ መሸበር እንጂ ከሐምሌት የመንፈስ ድቀትና ግለኛ ባሕረ-ትካዜ ጋር ስላልተመጣጠነች ከቶውንም ሊግባቡ አልቻሉም። በተጨማሪም አፈ-ንጉስ አባቷና ዓለመኛ ወንድሟ ልጅ ላርቆስ፣ በሃምሌት ደረጃ ከፍተኛነት እያሳበቡ፣ የፍቅር ስሜቷን ስላጥላሉባት መራራቃቸው ጠና።
የሼክስፒርን ህይወት በተመለከተ ያሉት ኦፊሴላዊ ሬኮርዶችና የቀደሙ ጊዜያዊ ማመላከቻዎች እኒሁ ናቸው፡፡  የስትራትፎርዱ ሼክስፒር ከአቮን ዥረት በላይ የኖረው ፀሃፊ፣ የልጅነት ታሪኩ ለግምት የተተወ ነው - በአብዛኛው። ከ1592 ዓ.ም ጥቂት ቀደም ብሎ የተሳካለት የድራማ ሰውና ገጣሚ ሆነ፡፡  የኤልዛቤታን ለንደን ቴአትር ኩባንያ መሪ አባል ነበር፡፡ የሚያገኘውንም ገንዘብ  ለስትራትፎርድ ንብረት መግዛት ላይ ያውል የነበረው ሲሆን፤ የሞተውም በተወለደባት ከተማ  በስትራትፎርድ ነው፡፡ (የተወለደው አፕሪል 26 1564 ነበር) በዝርዝር  አተረጓጎም ላይ ከየአቅጣጫው ልዩነት ቢኖርም፣ በኦተመን 1592 የተዋጣለት ተዋናይና ፀሐፌ-ተውኔት ሆኗል!
ምንም እንኳን ይህ ጉዳይ ለ”አዘቦቱ አንባቢ” (“genral reader”) እሱ ሁሌም ሼክስፒር መልኩ ምን መሳይ ነው ሲያሰኝ የኖረው ሰውዬ ነው። የሼክስፒር ህይወት ታሪክ ንድፉ ብቻ ነው የታወቀው፡፡ ያም ቢሆን በፈርጀ ብዙ ግምት የተሞላ ነው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በዝርዝር ጥናት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ማለትም ሥረ መሰረቱንና ሥራዎቹን ከዘመነኞች ኤልዛቤታውያን ጋር በማነፃጸር የተፈረጁ ናቸው፡፡ በመጨረሻም የሼክስፒርን ግጥሞች እንደ ቀጥተኛ የግለ ህይወቱ ልምድ ነፀብራቅ (ማሚቶ) አድርጎ ወስዶ በማብራራት ነው። መቼም ማንም ሰው ቢሆን የሼክስፒርን ተጨባጭ ሕይወት ዳግም ለመገንባት የሚሻ ሁሉ “ስለ ሼክስፒር ተምኔታዊ ዕይታውን” ማስገባቱ አይቀሬ ነው፡፡
በሼክስፒር ግጥሞች ውስጥ የሚገኙት የበለፀጉና መልከ-ብዙ አስተሳሰቦችና በነሱም ውስጥ የሚንፀባረቁ ቀለመ-ብዙና መጠነ ሠፊ ልምዶች፣ ለበርካታ  የግምት ሥራዎች የትየለሌ ዕድል ይሰጣሉ። እነዚህ እስከዛሬ ለመቆየት የቻሉ ሬከርዶች የሼክስፒርን እጅግ ፋይዳ ያለውን የሕይወቱን አንጓ የሚያሳዩ ክስተቶች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ እስከ አሁን ስለ ገጣሚው የጋብቻ ሕይወት ምንም እንዳልተባለ ልብ በሉ፡- እስከዛሬ ምንም ሬከርድ አልተገኘም። መዝገቡ አያሳይም። በእርግጥ በቅዱስ ማርቲን ባህረ-መዝገብ ላይ ይህን ጉዳይ የሚመለከት አስገራሚ መጠቆሚያ ቢከሰትም፡- እጅግ ወሳኙን ዓመት 1582 የሚያሳዩት ሁለት ገፆች ተገንጥለው ተወስደዋል። እግረ-መንገዳችንንም ይህ ጋብቻ  ምናልባት የተፈፀመው ቴምፕል ግራፍተን (በግራፍተን መቅደስ) ውስጥ ሊሆን እንደሚችልም እናስታውስ፡፡ ሆኖም አንዳችም ምዝገባ አልተደረገበትም፤ ወቅቱ አልተዘገበምና። ስለሆነም በሼክስፒር ሙሉ የህይወት ታሪክ ውስጥ ጉዞ ስንጀምር እጅግ ጠንቃቃ መሆን አለብን። የመዛግብቱ ቁልፍ ጊዜያዊ የማዕዘን ድንጋዮች በራሳቸው አሳሳች ባይሆኑም፣ የተሳሳተ አቅጣጫ የሚያሳዩን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የቤን ጆንሰንን የማስጠንቀቂያ ቃላት እዚህ ላይ እናንሳቸው፡፡ ቤን ጆንሰን ማስጠንቀቂያውን የተናገረው፤ “ሼክስፒር ምን መሳይ ነው? መልኩ ምን ይመስል ይሆን?” ለሚሉት ሁሉ ነው፡-
“የእሱን ፎቶውን አትዩ፤ መፅሐፉን እንጂ፡፡”
Read 1018 times