Print this page
Saturday, 20 August 2022 12:59

“በመተሳሰብ መተሳሰር”

Written by 
Rate this item
(3 votes)


       አንድ ጊዜ አንድ ንጉስ የአገሩን አዋቂዎች ሁሉ ሰብስበው “ስለ እኔ ዙፋን የሚሰማችሁን ማንኛውምን ነገር ተናገሩ” አሏቸው አሉ። እኚህ ንጉስ፤ “ዙፋኔን ያማሉ፤ ከባለስልጣኖቼ ጋር ሆነው ይዶልቱብኛል… በሚል በየጊዜው እንዲህ እየጠሩ የመጠየቅ ልምድ አላቸው። የአገሩ አዋቂዎች አብዛኞቹ ፈርተዋል። ተጨንቀዋል፤ ተንዘርዝረዋል። ምክንያቱም እኒህ ንጉስ በሶስት ነገር ይታወቃሉ፡
1ኛ ውሸት አይወዱም። 2ኛ ስለመንግስታቸው ድክመት እውነትን የተናገረ ብዙ ጊዜ ነክሰው ይይዛሉ። ሊገድሉትም ይችላሉ። 3ኛ ከስብሰባ የቀረ ሰው ወዮለት።
አብዛኞቹ አዋቂዎች፤ “ምንም ይምጣ ምን እውነት ተናግሮ ከመሞት እሳቸውን ቢያስቀይምም ባያስቀይምም፣ ውሸት ከመናገር የቀጡንን ቢቀጡን ይሻላል ብለዋል። በየሆናቸው። ስለዚህም፡- የላይኛው “እንዲህ ያለ መንግስት ጥንትም አልነበረንም፤ ወደፊትም የሚመጣ አይመስለኝም” አለ።
ንጉሱም፡- “ወደፊትም የሚመጣ አይመስለኝም ስትል ምን ለማለት ነው? እኛ ወዴት ሄደን ነው ሌላ የሚመጣው? ይች ይች ሳትገባን ትቀራለች ብለህ ነው? በል ማነህ ባለሟል? ማረፊያ ቦታ ስጡት!” አሉ። አዋቂው ታሰረ።
ቀሪዎቹ ይንቀጠቀጡ ጀመር። ዞሮ ዞሮ በዚህም ቢባል በዚያ፣ የሀሰት ምስጋና ከሌላ ከምን ይሻላል በሚል፣ ንጉሡንና ዙፋናቸውን “ሺ ዓመት ይኑርልን!” እያሉ መረቁ። ምንም ነቀፋ አልተሰነዘረም። ሁሉም ተናግሮ ጨርሶ አንድ የታወቀ ብልህ ፈላስፋ ብቻ ቀረ። ይህ ፈላስፋ አንዴ መሬት መሬት፣ አንዴ ደግሞ ወደ ንጉሱ እግር ስር አተኩሮ እያየ ጸጥ አለ።

ንጉሡም፡-
“አንተ የምትናገረው የለህም እንዴ? ምን እግር እግሬን ታያለህ?” ብለው ጠየቁት።
ፈላስፋውም፤
“ንጉሥ ሆይ፤ ስለ ዙፋንዎ ለመናገር ወደ ዙፋንዎ ዘንድ ለመድረስ የሄዱበትን መንገድ፣ የረገጡትን ምንጣፍ ባይ ይሻላል ብዬ ነው፤ እግርዎንና ደረጃ ደረጃውን የማስተውለው”
ንጉሥ፡- “ለምን?” ብለው በጉጉት ጠየቁ።
ፈላስፋ፡- “ወደ ዙፋኑ የመጡበት የመንገድዎ ቀና መሆን አልያም እሾህ እንቅፋት የበዛበት መሆን የዙፋኑን ጥንካሬ ያሳያል። የእርስዎንም ማንነት ይገልጻል። ምንም አይነት ለውጥ ቢመጣ ፍጥረትን አይለውጠውም። እንዲያውም የበለጠ ወደ አደባባይ ያወጣል” አላቸው።
ንጉሡም፤ አመስግነው ሸለሙትና “ከሌሎቹ ምስጋና ሁሉ ያንተ ነቀፋ ይሻለኛል። ሌሎች አስብቶ አራጆች ናቸው። አንተ ትክክል ነህ። የትላንቱ እኔ ነኝ” ብለው አሰናበቱት።
ይህ የሀበሻ ምሳሌ የአንድ የፈረንጆች ምሳሌ ተገላቢጦሽ ነው። “ውጤትና ፍጻሜው አካሄዱን ያሳየናል” (The end Justify the means) ይላሉ። አበሾች ደግሞ “አካሄዱ ውጤትና ፍጻሜውን ነግረናል” (The means justify the end) ይላሉ። ያም ሆነ ይህ ሀበሾችም ፈረንጆችም ፍጻሜውና መንገዱ የተያያዙና የተሳሰሩ መሆናቸውን ነው በምሳሌዎቹ የሚያስረዱት። ለልጅ አስተዳደግ ወሳኝ እንደሆነና ወደ ማንኛውም የስልጣንና የኃላፊነት ሰገነት ለሹመትም ሆነ ለልፋ፣ በእድገትም ሆነ በእርገት. በእድልም በትግል ሲወጣ የሚኬድበት መንገድ ንጹህ ቀናና አድልኦ- አልባ ካልሆነ፣ ውሎ አድሮ ድክመትና ችሎታ ማነስ መከሰቱ አይቀርም። የሃላፊነት ቦታ ላይ ከተቀመጡ በኋላ “የዛሬ እኔ የትላንቱ እኔ ነኝ” ማለት ግድ ይሆናል። ያ መንገድ ዝምድናና ወገናዊነት ሙስናና እከክልኝ- ልከክልህ የነበረበት ከሆነ፣ ሃላፊነቱን እንደዚያው ድክመት የበዛበት መሆኑ አይቀርም። ሹሙ ዜጋውን የሚበድለውና “ ስለ እኔ ምን ታስባለህ” እያለ የሚጠይቀው የራሱን ችሎታ፣ ወንበሩንና ማንነቱን ሲጠራጠር ነው። ባለስልጣን ነጋዴውን ለምን አተረፍክ?” ብሎ የሚያኮርፈው፣ እንደዚሁ ከራሱ አሉታዊ አንጻር እያየ ነው። ወደ ታች የሰራተኛ ደመወዝ የማይጨመረውም ይህንኑ መሰረት በማድረግ ነው። ፖለቲከኛም ቢሆን የጧት የማታ መመሪያው “ጠርጥር!” ብቻ ነው። ይህም ግንኙነታቸውም አንድም የጌታና የሎሌ፣ አንድም የሌባና የፖሊስ ያደርገዋል። አንድ መስሪያ ቤትና ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ አለቃና ምንዝር፣ ለአንድ መስሪያ ቤት አንድ አላማ ብለው በመተሳሰብ አይሰሩም። ለአንድ መንግስት ለአንድ አገር ብለው አይፈቅዱም። የየራሳቸውም ጠባብ ጎጆ እንጂ ስለቀረው ሰፊ አዳራሽ አያስቡም። የበታቹ ሰራኛ “ዜጋና ሹም ተጋጭቶ ድንጋይና ቅል ተላፍቶ አይሆንም” ብሎ በፍርሃት እንደተሸማቀቀ ይከርማታል እንጂ የበላዩን ድክመት አይናገርም። አለመተማመን፣ መካካድና መወነጃጀል ይለመዳል። ድክመቶችና ችግሮች ካልተወሰኑና በጊዜ ካልፈቱ አለመያዝ መያዣ መጨበጫ የሌለው፣ መግቢያና መውጪያው የማይወቅና የበለጠ በነገርና በተንኮል የተተበተበ ስርዓት ውስጥ ይከተናል። ወጣም ወረደ ሁሉም የመጣንበትን መንገድና ጥንካሬ ነው የሚናገሩት። “ እባብን መቅጨት እንጭጩ እንዲሉ ይህ ዘመዴ፣ ይህ የስልጣን-ይህ አማቼ ይህ የድክመት-አጋሬ፣ ይህ የግምገማ ቀኝ እጄ- ሳይሉ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየድርጅቱና በየመስተዳድሩ ያሉትን ድክመቶች፣ ያለ-ጉቦ አንስቶ የመወያየት ባህል በተለይ ዛሬ እጅግ ያስፈልጋል። ይሄ ደግሞ ት/ቤት፣ ልጆች ስናስገባ፣ ሆስፒታል በሽተኛ ልንጠይቅ ስንሄድ ወይም ሰው ለማስተኛት ስንቸገር፣ በንግድ ቦታ ገማች ሲመጣብን፣ ሰራተኛ ሲቀጠርና ሲባረር፣ ምርጫ ሲካሄድ፣ የፍ/ቤት ፋይል ሲመረመር… ሁሉ የሚያጋጥመን ችግር ነው። ትላንት ዜጋ የነበረው የበታች ሰራተኛ “ ስልጣን በሸተተው ማግስት አካሄዱ ሁሉ እንደ ድመት ኮርማ መጎማለል” ሆኖ ሲገኝ፣ ይሄስ የጤና አገር አይደለም ያሰኛል። ነገ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ሲነጋ ልፍለጥ- ልቁረጥ- ልዘዝ- ላናዝ ማለት ያመጣል። መቆራቆዝ ፣ መመራረዝ፣ መውጋት፣ መወጋጋት፣ መጠላለፍ፣ መዝረፍ፣ መዘራረፍ፣ መመዝበር ይከተላል። ከዚያ “ መንገዶች ሁሉ ወደ ወህኒ ቤት ያመራሉ” ማለት ብቻ ይተርፈናል። አንድ እውቅ የሀገራችን ገጣሚና የቴአት ደራሲ በአንደኛው ተውኔት ውስጥ፤ የሀገሪቱ ንጉሥ ወህኒ ቤት ሲመርቁ የተናገሩት ነው በሚል እንደሚከተለው በገጸ- ባህሪው ልሳን ያናግራቸዋል፡-
“ይህን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ እናንተም በተለመደው ጨዋ ባህላችሁ በመተሳሰብ እንድትተሳሰሩበት!”
ከመተሳሰር ይሰውረን!!

Read 11852 times
Administrator

Latest from Administrator