Saturday, 20 August 2022 13:08

“ከመንግስት ይልቅ ጋዜጣ ቢኖር እመርጣለሁ”

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

  አድማስ ትውስታ


                   “ከመንግስት ይልቅ ጋዜጣ ቢኖር እመርጣለሁ”

         “ተመልከቱ! ፈቃዳችንን ለመግለጽ ወይም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲከበር - ነጻ ጋዜጣ። መንግስት እንደ ፈቃዳችን መሄዱን ለመከታተል - ጋዜጣ። ከመንገድ የወጣውን የሚቀጣው ወገን (ፍ/ቤት) ያለ ጭንቀት በተገቢው መንገድ መስራቱን ለማወቅ - ጋዜጣ። በደልና ህገ-ወጥ ድርጊት ከተፈጸመ ያንን ለመቃወም-  ጋዜጣ። በደል ደርሶብን እንደሆነ ያን ለመግለጽ - ጋዜጣ። ነገሮች ሁሉ በፈለግነው አቅጣጫ መሄዳቸውን ለማረጋገጥ - ጋዜጣ።--”
 

         አንዳንድ አሳቦች “የብብትና የቆጥ” ችግር አለባቸው። የቆጡን ልናወርድ ስንል የብብቱን ላለመጣል መጠንቀቅ ይገባናል። “የሁለት ፊት እውቀትና እውቅና የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ” ለማለት ነው። እንዲህ ባሉ ነገሮች ውስጥ፤ አንደኛው ገጽ ለአዎንታ ስንይዘው፣ ሌላኛው አሉታዊ ይሆናል። ይህን የምለው፣ ተቸግሬ እንጂ መጠማዘዝ ፈልጌ አይደለም። እንዲህ ሀሳቤን ያጠመደው ጉዳይ “መብቶች ሰው ከመሆን ይመነጫሉ” የሚሉትና የምለው፤ የዘወትር ጸሎት ያደረግነውን ሀሳብ ነው።
እርግጥ ነው “በማንም ሊጣሱ የማይችሉ ሰው በመሆን የያዝናቸው መብቶች” አሉ። ግን፤ “የማይጣሱ መብቶች” መባላቸው ብቻ፣ እኚህን መብቶች የማይጣሱ አያደርጋቸውም። በሌላ ረገድ፣ በተፈጥሮ የያዝናቸው መሆኑ ብቻ እንደ ንብረት እንድናውቃቸውና እንድንጠብቃቸው ያደርገናል ማለት አይሆንም። መብትና ነጻነት ያሉና የነበሩ ቢሆኑም፣ ሀብት ያደረግናቸው በእውቀት ነው። ግኝት (ወይም Discovery) ናቸው። እንደ መብት ለመጠየቅና ለማክበር፣ እውቀት እንዲሁም ብርታት ይጠይቁናል። “ሰው በመሆን ያገኘናቸው” ሲባል፣ ይህን እውነት ሊያስረሳን አይገባም። መብትና ነጻነት፤ በእውቀት፣ በጥረትና በትግል የምንጎናጸፋቸው ሰብአዊ መብቶች ናቸው።
“በችሮታ የሚሰጡን አይደሉም” ሲባልም፤ ይህን የሰውን ልጅ ተፈጥሮ አውቆ እንዲከበር የሚጣጣር መንግስትን ለመፍጠር መድከም አያስፈልገንም ማለት አይደለም። እነኚህ ሰው በመሆን ብቻ ንብረታችን የሚሆኑ “ሰብአዊ አላባዎች”፣ ከተፈጥሮ እንዴት እንደመነጩ ማወቅ፣ አውቆም ማህበራዊ ስርዓቱን ለመቀየር መታገል አስፈላጊ ነው። እንደዚሁ፤ እውቀቱን ወይም እውነቱን ዘወትር በንቃት ለመጠበቅ የሚታትር ዜጋ ያስፈልገናል። መብትና ነጻነት፤ መቼም ቢሆን የማይዘነጉና የንቁ ዜጎች ሀብት ናቸው።
ወደ ኋላ ዘወር እንበል። እንዲህ ወደ ኋላ ዘወር እንበልና፣ ከእነዚህ መብቶችና ነጻነቶች አንዱን እንምረጥ። የፕሬስ ነጻነት።
ለፕሬስ ነጻነት የተደረገውን ጥረት፣ በታሪክ መዝገብ ስንመለከት፣ የሰውን ተፈጥሮ በመመርመር ሰብአዊ አላባዎችን ለይተው፣ እውቀቱን ያገኙ ሰዎች፣ ሀሳቡን በተግባር ለማዋል የተጣጣሩ ትጉሃን መሪዎችና ንቁ ዜጎች የፈጸሙትን ገድል እናስተውላለን።
አሁን፤ “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት” እንዲከበር ጥረት ካደረጉ ሰዎች መካከል ጆን ፒተር ዜንገር አንዱ ነው። የእሱንም፣ እንደ አብነት የሚጠቀስ አንድ ድርጊት መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሃሳብን ከመግለጽ ነጻነት ጋር ተያይዞ እንደ ድንቅ የሚጠቀስ አንድ ታሪካዊ ትግል ያደረገው ጀርመናዊው ጆን ፒተር ዜንገር ነበር። ዜንገር ይህን ድንቅ የተባለ ታሪክ በፈጸመበት ጊዜ አሜሪካ በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ስር ነበረች። በዚህ ጊዜ የአሜሪካ ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሁፎች፣ ከእንግሊዝ ጋዜጦች እየተቀነጨቡ የሚወሰዱ ሃሳቦች ብቻ ናቸው። እንጂ፣ ነጻ የዘገባ ስራ ማቅረቡ ችግር ነበር። ዜንገር በ1735 (እ.ኤ.አ) ዓ.ም አንድ የአፈና ገመድ እንዲበጠስ አደረገ። ለነጻ የዘገባ ስራ በር ተከፈተ።
ይኸው ጀርመናዊ አሳታሚ፣ “የእንግሊዝ ንጉሳዊ አስተዳደርን ስም የሚያጎድፍ ጽሁፍ አትመሃል” በሚል፤ በስም ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ። የዜንገር ደጋፊዎች (ንቁ ዜጎች) አንድ ጠበቃ ገዝተው አቆሙለት። ጠበቃው አንድሪው ሀሚልተን ይግባኝ ጠየቀ። ሀሚልተን፣ በወቅቱ ለስም ማጥፋት ወንጀል ከተሰጠው ትርጉም ለየት ያለ ፍቺ ይዞ መጣ።  በዚህ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ አቤት አለ። የዳኞቹ ትኩረት ዜንገር የገዥዎቹን ቁጣ ሊቀሰቅስ የሚችል ጽሁፍ እንዲታተም ማድረጉን ማረጋገጥ ብቻ ነው። የሃሚልተን መከራከሪያ ግን፣ ቁጣን የሚቀሰቅስ ወይም ሊያስቀይም የሚችል መጻፉ ሳይሆን፤ የተጻፈው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን ነበር።
በወቅቱ በነበረው ትርጓሜ አንድ ጽሁፍ በስም ማጥፋት የሚያስቀጣው እውነትም ሆነ ሀሰት፣ የቀረበው ሃሳብ ንጉሳዊ መስተዳደሩን ሊያስቀይም የሚችል ይዘት ማቅረቡን ለማረጋገጥ ነው። በጽሁፉ የቀረበው ነገር፣ እውነት መሆኑ ነጻ አያወጣም ማለት ነው። ሀሚልተን ግን፣ “እውነት ከሆነ እንደ ስም ማጥፋት ተቆጥሮ ሊያስቀጣው አይገባም።” የሚል ትርጉም ይዞ ቀረበ። ዳኞቹ ተቀበሉት። ስለዚህ፣ “በጽሁፉ የቀረበው ነገር እውነት በመሆኑ፣ ጆን ፒተር ዜንገር በስም ማጥፋት ሊከሰስ አይገባም” ብለው ብይን ሰጡ።
በአሜሪካ የጋዜጠኝነት ስራ ታሪክ እንደ ድንቅና ወሳኝ ነጥብ የሚቆጠረው ይኸው ነው። ይህም ጋዜጠኛው፣ ንቁ ዜጎችና ነጻ ህሊናቸውን ተከትለው ለመስራት የደፈሩ ዳኞች ያስገኙት ውጤት ነው። እናም “ …እውነትን የተመረኮዘ ነገር በስም ማጥፋት ሊያስከስስ አይችልም” የሚል መርህ እንዲጸና ተደረገ። በጆን ዜንገር ድፍረት የፕሬስ ተቋማት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ቆፍጣና አስተያየት ለመስጠት ተደፋፈሩ፡፡ የፕሬስ ነጻነት በዚህ መሰል ትግል እየዳበረ ነው፤ ከዛሬ የደረሰው።
ለዚህ በእኛ ሀገር ለፕሬስ ነጻነት መጠናከር አብነት የሚደረጉ ድርጊቶች ካሉ፣ ገና በወጉ የምናውቃቸው አይመስለኝም። ይሁንና፣ አጭር በሆነው የዲሞክራሲያዊ ሂደት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ (በተለይ የግሉ) ሙሉ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል እገምታለሁ።
እኔ እንደምገምተው፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ከእነ እንከኑ ትልቅ ታሪክ ሰርቷል። አሁን-አሁን ሁነኛ ጥረት እያደረጉ ከሚታዩ ሲቪክ ተቋማትና ጠንካራ ግለሰቦች ሁሉ ቀድሞ ነጻነት ስጋ ለብሶ የታየው በግል ፕሬስ ተቋም ይመስለኛል። ታሪካዊና ወቅታዊ የስነልቦና አጥርን ነቅሎ ለመሄድ የሞከሩት እነሱ ናቸው። ብዙዎች ፍርሃት ባጀበው ሁኔታ የሚያነቡትን እነሱ ጽፈዋል። የሚጽፉት ነገር ትክክል ሆነ አልሆነ በዚህ ሚዛን ለውጥ አያመጣም። ሃሳባቸው ዘለፋ እና እልህ እንዲሁም የልምድ እጥረት ያጠላበት ይሆናል። ግን ከፍርሃት አጥር ቀድመው የወጡት ያው የግል ፕሬስ ተቋማት ናቸው።
ስለዚህ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት ታሪክ ትልቅ ድርሻ እንደሚይዙ አልጠራጠርም። እንዲህ ያለ ድርሻ ከሚጠበቅባቸው ዜጎች፣ ከዳኞች፣ ከማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ አንዳንዴም ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች በላይ ለነጻነት መረጋገጥ ብዙ የተንገላቱ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህንንም እንተወው። ቢያንስ ለንባብ ባህል መዳበር ሊንቁት የማይቻል ትልቅ ድርሻ ስላደረጉ ማህበራዊ ልማቱን አግዘዋል።
ከፋም ለማም ከየትኛውም የህትመት ውጤቶች ሁሉ የመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ አድማጭ ለመያዝ የበቁ ናቸው። ዜጎች በሆነ መንገድ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በር የከፈቱ ናቸው። ብስለት የጎደለው ጥረት ነው ሊሉት ይችላሉ። ቢሆንም፤ ፍትህን ለማስፈንና መልካም አስተዳደርን ለመፍጠር ድርሻቸው ከፍተኛ ነው። እስኪ ጥቅል ወሬ እናውራ።
ፕሬስ፣ ሀሳብን በነጻ ከመግለጽ መብት ጋር የተያያዘ ተቋም ነው። ሀሳብን የመግለጽ መብት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጀመሪያና መጨረሻ ነው። ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ሲጣስ የማይጣስ መብት የለም። የማይነካ የማህበረሰብ ክፍል አይኖርም። ውጤቱም አንባገነንነት ነው። ፍላጎታችንን ለማሳየት፣ ፍላጎታችንን የተከተለ ሁነኛ ስርዓት ለመፍጠር፣ ይህን ስርዓት እንዳይታጎል ለመከላከል፤ ሲታጎልም ቁጣን ለመግለጽ፣ የሚሻሻልበትንም መንገድ ለማመላከት፣ አፈጻጸሙን ለመከታተል፣ የምንችለው በፕሬስ ተቋማት ነው- ይበልጡን። እንዲያም ሲል፣ “በማህበራዊ ውል” (Social Contract) የጸናው መንግስት የሚሉት ተቋም እንዲፈርስና እንዲቀየር ለማድረግ ፕሬስ አስፈላጊ ነው።
እናም፣ ከመንግስት ምስረታ እስከ ክንውንና ውጤት ድረስ የፕሬስ ተቋማት ድርሻ ብዙ ነው። መንግስት ወደ አገዛዝ የሚሄደው የዕለት ክንውኑን የምንከታተልበት መንገድ ሲጠፋ ነው። የእኛን እውነተኛ ፍላጎት ተከትለውና አክብረው እንዲመሩን የምንመርጣቸው ሰዎች፣ ገዥዎቻችን መሆን የሚጀምሩት የሚሰሩትን ማወቅ ባልቻልን ጊዜ ነው። የሚሰሩትን እንዳናውቅ ሲፈልጉ፣ ገዥዎች ለመሆንና ለብዝበዛ እየተሰማሩ ነው። ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመው የፕሬስ ነጻነትን ወይም ማስረጃን ይነፍጉናል። እንዲያ ዓይነት ፍላጎት ከሌለ ግን መብትና ነጻነትን ጥሶ ለመሄድ የሚሻ ቡድንና ግለሰብን እንዳይቀናጣ የሚከላከለው ዋናው መንግስት ነው።
የእስካሁን አካሄዴን ስትመለከቱ ነጻነትንና መብትን ሊነፍገን የሚችለው መንግስት ነው። ልክ ነው። ግን ቀዳዳ እንዳይፈጠር ወይም የቆጡን ስናወርድ የብብቱን እንዳንጥል እሰጋለሁ። መንግስት ነጻነትን ሊነፍግ የሚችል ተቋም የሚሆነው አምባገነንን ባህሪ የያዘ ከሆነ ብቻ ነው። ካልሆነ ግን የነጻነት ጠባቂያችን እሱ ነው። እሱ ሳይኖር ነጻነት አደጋ ላይ ትወድቃለች። “ከፍላጎትህና ከጥቅምህ፣ ፍላጎቴና ጥቅሜ ይበልጣል” የሚል አልያም የሚመካውን ተመክቶ “እኔ ልግነን” ባይ ሲመጣ፤ ጋሻችን የሚሆነው፤ ያው መንግስት የምንለው ድርጅት ነው። የምናጥላላው አምባገነን መንግስትን እንጂ መንግስትን አይደለም። አምባገነን እንዳይሆንም በፈቃዳችን አምሳል የሚቀረጽ መንግስት መፍጠር ይገባናል። ይህን ለማድረግ ታዲያ፤ ፍላጎታችን ምን እንደሆነ አስቀድመን መግለጽ አለብን። በፍላጎታችን አምሳል ካቋቋምን በኋላም የሚሰራውን ለማወቅ መረጃ የማግኘት መብት እንዲከበርልን እናደርጋለን። ባገኘነው መረጃ ከመንገድ ወጥቶ መሄዱን ስናውቅ እናወግዛለን። ለፍርድ እናቀርባለን፤ አጥፊው ተገቢውን ቅጣት ማግኘቱን እንከታተላለን።
ተመልከቱ! ፈቃዳችንን ለመግለጽ ወይም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲከበር - ነጻ ጋዜጣ። መንግስት እንደ ፈቃዳችን መሄዱን ለመከታተል - ጋዜጣ። ከመንገድ የወጣውን የሚቀጣው ወገን (ፍ/ቤት) ያለ ጭንቀት በተገቢው መንገድ መስራቱን ለማወቅ - ጋዜጣ። በደልና ህገ-ወጥ ድርጊት ከተፈጸመ ያንን ለመቃወም-  ጋዜጣ። በደል ደርሶብን እንደሆነ ያን ለመግለጽ - ጋዜጣ። ነገሮች ሁሉ በፈለግነው አቅጣጫ መሄዳቸውን ለማረጋገጥ - ጋዜጣ። ካልሆነም ስልጣን የያዘውን ቡድን እንዲነሳልን ለመመካከርና ለመወሰን - ጋዜጣ። እናም፣ ጋዜጣ ሲጠፋ፤ ሁሉንም እናጣለን። አስተውሉ፤ ጋዜጣ ብቻ አይደለም፤ ከተጽዕኖ የራቀ ነጻ ጋዜጣ። ስለዚህ፤ የፕሬስ ነጻነት ላይ የሚፈጸም በደል፣ የጋዜጠኞች ችግር ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። የጠቅላላው ህብረተሰብ ችግር ነው።
ለዚህ ይመስለኛል፣ “መንግስት ኖሮ-ጋዜጣ ባይኖር ይሻልሃል፤ ወይስ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ባይኖር ትመርጣለህ? ብትሉኝ ምንም ሳላመነታ፣ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ባይኖር ይሻለኛል እላችኋለሁ”  ሲባል የሰማነው። ለምን ቢባል፣ ጋዜጣ የሌለበት የመንግስት አስተዳደር አምባገነን መሆኑ አይቀርም። “ነጻነቴን ወይም ሞቴን ስጡኝ” እንደማለት ነው።
ታዲያ ከሰሞኑ በጦማር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ የተወሰደው እርምጃ ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለበት። ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ፣ በጋዜጠኛው በወጣው አንድ ዜና የተነሳ ለእስር ተዳርጓል። ለእስር የተዳረገበት ምክንያት የቀረበው ዘገባ ስህተት በመሆኑ ወይም የተላለፈው ወንጀል አለ ተብሎ አይደለም። በእርግጥ አይደለም። በግልጽ… “የቤኒሻንጉል ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ያረጋል አይሸሹን … አስመልክቶ ላቀረብከው ዘገባ… ምንጭህ ማነው?” አሉት። ለመልሱ… ቢሆን ይምሩት እንደሆነ አላውቅም። አሁን… የማላደርጋቸውን እውነት ልንገራችሁ።… የመረጃ ምንጩን ሊጠይቁት ይችላሉ።… ስህተት  ፈጽሟል ቢባል እንኳን …ከቤኒሻንጉል ፍ/ቤት በሚሰጥ ትዕዛዝ ሊታሰር… አይችልም። በይፋ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ… (ወንጀል) ለምርመራ ማሰር ተገቢ… በፍጹም-በፍጹም። እኔ እንደማስበው፤ ይህ … ዋጋ የሌለው ጥያቄና መልስ ነው።…”ልታሰር ይገባል እንዴ?” ማለቱም…ስታሰር በህጉ ይተደነገገውን ስርዓት… ወደሚል ወርደናል። በፍቃዱ… ለምን ታሰረ?፤ አሳሪው እከሌ ሊሆን…ጉዳዩ በእስር ታይቶ እንዲመረመር… አይደለም ወዘተ” ከምል ይልቅ ሌላ… ባነሳ እወዳለሁ።  ምነው፤ “ይህን ህገ-ወጥ… ለመከላከል የሚቆምና ጉዳዩ በፍ/ቤት … እንዲታይ ህገ-መንግስቱ እንዲከበር… ሰው እንዴት አልተገኘም?” የሚል።
…እውነቱ ስለነጻነታቸው መከበር የሚቆሙ…የሌለበት አገር ውስጥ ነን። አቃቢያንን-ህግ፣…ለሙያ ዜጎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እንዴት ዝም አሉ? ለምን ድምጻቸው አልተሰማም። ከሞት የመጨረሻው እረድፍ… ከሞት አይን መሰወር ነው እንዴ? እንዲህ…የሚገፋፋ ነገር ነው። ይህንን ልተወው።…የጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ ነገር አድርጎት። የታሰረበትን ምክንያት የመረጃ ምንጩን አልናገርም።” ማለቱን… ይህን በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ታሪክ ለአብነት የሚሆን አንድ እርምጃ መሆኑን…
…ጋዜጠኛ ለኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ… አብነት ያለው ውሳኔ አድርጓ።
ለኢትዮጵያ የፕሬስ ተቋማት ብርታት ፈርቀዳጅ ድርጊት ፈጽሟል።” ለማለት ያበቃኝን ምክንያት ልግለጽ። በፍቃዱ “ምንጭህን ግለጽ” ሲባል፣ “ምንጩን ከምገልጽ እታሰራለሁ” ብሎ ወስኗል።
አስቀድሜ እንደገለጽኩት፤ የፕሬስ ነጻነት ሲሸራረፍ ሌሎቹ መብቶች ሁሉ አብረው ይናዳሉ።
ዛሬ እንደምናስተውለው፣ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች፣ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኞች አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ እናስተውላለን። የበታቾቹ “የበላይ አካል ካልፈቀደ በቀር መረጃ እንድንሰጥ ተከልክለናል” በሚል መረጃ ይነፍጋሉ። የመንግስት መ/ቤቶች ኃላፊዎች መረጃን ከኛ ለመደበቅ የሚያስችላቸውን ሞራላዊ ወኔ፣ ህጋዊ ድጋፍ ከየት እንደሚያገኙ አናውቅም። እኛ በሰጠናቸው ወንበር ወይም ሃላፊነት ላይ ተቀምጠው እንደ ግል ቤታቸው “መረጃ አልሰጥም”፤ “እከሌ ካልፈቀደ መረጃ አላወጣም” ሲሉ ያስገርማል። የመንግስት መ/ቤቶች ወደ ግል ኩባንያ የተዛወሩ ይመስላል። መረጃ የመስጠት የህግ ግዴታ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ግን እንቢ ለማለት አያመነቱም። ህግ ጥሳችኋል ብሎ ፍ/ቤት ሊያቆማቸው የሚገባው ተቋሙም እንዲሁ መረጃ አንሰጥም የማለት “መብቱን” አስከብሯል። እንዲህ ያለ አገር ውስጥ ነን።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን “የመረጃ ምንጭህን ካልገለጽክ” ብሎ የሚያስር ሹም ደግሞ ይገጥመናል። እጅግ የከበደ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ፍ/ቤት እንኳን ሊጠይቅ የማይገባውን ጥያቄ፤ የፖለቲካ ሹመኞች ከህግ በላይ ሆነው “ምንጫችሁን ተናገሩ” ሊሉ ይደፍራሉ። በዚህ ነገር ውርደቱ፣ ፍትህን ሊያስከብሩ የቆሙት አካላት ጭምር ነው። የእነሱን ልተውና ወደ ፕሬሱ ልመለስ።
ዛሬ፣ እንደ ልማት ሊቆጠሩ ከሚችሉ የጋዜጠኞች ቋንቋ መሃል፣ “አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ (ባለጉዳይ)” የሚለው አንዱ ነው። ጋዜጠኞች፤ “ስሜ እንዳይገለጽ” ተብለን ስንጠየቅ፣ ለቃሉ ፍጹም ተገዢ ልንሆን የሚገባው፣ Off the record ሲባል፣ ቅር እያለንም ቢሆን የምንቀበለው ለፕሬስ ተቋማት ጥንካሬ ሲባል መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። ይህን የህግ ዋስትና ያለው ስነምግባራዊ መመሪያን እስካላከበርን ድረስ ብዙ መረጃዎች ከዜጎች ጆሮ ላይደርሱ ይችላሉ። “ስሜ እንዳይገለጽ” ብለው መረጃ ሲነግሩኝ፣ ታማኝ ካልሆንኩኝ፣ ነገ ማንም ሰው መረጃ ሊሰጠኝ አይደፍርም፣ አይፈልግም። ፕሬሱ የዜጎችን አመኔታ ባገኘ ቁጥር መረጃዎች የሚወጡበት ሁኔታ ይጠናከራል።
በሀገራችን የፕሬስ ህግ “ጋዜጠኛው በህግ ተለይቶ በተጠቀሰ ምክንያት በቀር የመረጃ ምንጩን እንዲገልጽ አይጠየቅም።” ይህ ድንጋጌ የወጣው በአስተዳደራዊ ጫና ወይም በሌሎች ስጋቶች የተነሳ ነው። በምንም መንገድ ሊገኙ የማይችሉና ለዜጎች ደህንነት ወይም ለሀገር ጥቅም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ታፍነው እንዲቀሩ ሲባል ነው። ጋዜጠኛ የመረጃ ምንጩን አጋልጦ ከሰጠ ዜጎች በተቆርቋሪነት ሊገልጡት የሚፈልጉትን እውነት ከመግለጽ ይቆጠባሉ። ጋዜጠኛ በፍቃዱ “የመረጃ ምንጩን አልገልጥም” ሲል አገሩን የሚታደግ ውሳኔ አድርጓል ማለት ነው። በዚህ ረገድ እንደ አብነት የሚጠቀስ ድርጊት ላውሳላችሁ።
ምናልባት ከ200 ዓመት በፊት አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ፣ በጋዜጣው ላይ ያወጣውን መረጃ ከየት እንዳገኘው እንዲገልጽ ከመንግስት ኃላፊዎችና ከፍ/ቤት የቀረበለትን ጥያቄ እምቢ አለ። ለፍ/ቤቱ የመረጃ ምንጩን ካልገለጸ በቀር ለእስር እንደሚዳረግ ያውቃል። ግን “እኔ ዛሬ ይህንን ሰው አሳልፌ ብሰጠው ነገ ለሀገር እጅግ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ታፍነው ይቀራሉ። የሃገሬን የፕሬስ ተቋማት እገድላለሁ። ዛሬ ይህንን ሰው አሳልፌ ከሰጠሁ ማንኛውም ሰው መረጃዎችን ከመስጠት ያፈገፍጋል። የሀገሬ ፕሬስ ከሚጎዳ እኔ ብጎዳ እመርጣለሁ” አለ።
አዎ! ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የመረጃ ምንጮች እንድንገልጽ የምንገደድ ከሆነ፣ የሀገራችንን ጥቅም የሚያስጠብቁ መረጃዎች እንዳይወጡ እናደርጋለን። ስለዚህ “አገር ከምትጎዳ እኔ ብጎዳ እመርጣለሁ” ማለት አብነት የሚሆን ውሳኔ ነው።
ከአዘጋጁ፡ ከላይ የቀረበው ጽሁፍ የዛሬ 21 ዓመት፣ የካቲት 24 ቀን 1993 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤በድጋሚ ያወጣነው በአሁኑ ወቅት የህትመት ዋጋ መናርን ተከትሎ፣ የግል ጋዜጦች ህልውና ለአደጋ መጋለጡን በድጋሚ ለማስታወስ ነው፡፡



Read 1307 times