Saturday, 20 August 2022 13:12

ቀልቤን ሰቅዞ የያዘው የአልጀዚራ ዶክመንታሪ

Written by  ትዕግስቱ
Rate this item
(1 Vote)

 በአይሲስ ህጻንነቱን የተቀማው የ4 ዓመቱ ኢማድ
              
      ከሰሞኑ ምሽት ላይ በሥራ ተጠምጄ ሳለሁ፣ አልጀዚራ አንድ ዶክመንታሪ እያሳየ ነበር፡፡ እንኳንስ ሥራ በዝቶብኝ ለወትሮም የአልጀዚራ ዶክመንተሪ ተመችቶኝ አያውቅም፡፡ ሆነ ብሎ የሰውን ልጅ መከራና ሰቆቃ የሚያነፈንፍ ስለሚመስለኝ አላይም፡፡ ጦርነት፣ ሽምቅ ውጊያ፣ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ህይወት፣ ህገወጥ ስደት ወዘተ፡፡ አልጀዚራ ለምን እኒህ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር አይገባኝም፡፡  
 በኤዲቲንግ ሥራ ተጠምጄ የዶክመንተሪው ድምጽ ብቻ ይሰማኛል፤ አልፎ አልፎ፡፡  መሃል ላይ ግን የአንድ ህጻን ልጅና አዋቂ ምልልስ ትኩረቴን ሳበው፡፡ ቀና ብዬ መመልከት ያዝኩ፡፡  
“ኢማድ፤ ቸኮሌት ትወዳለህ?” ይላል አዋቂው (አባቱ ይሁን የቅርብ ዘመዱ አላወቅሁም)፡፡
“አልወድም!” ይመልሳል፤ ህጻኑ በቁጣ፡፡
በግምት 6 ዓመት ገደማ ቢሆነው ነው፤ ኢማድ፡፡
“አፕልስ ትወዳለህ?” ደግሞ ይጠይቀዋል፡፡
“አልወድም!” ይላል፤ አሁንም በቁጣ፡፡
“ታዲያ የምትወደው ምንድነው?”
“ጠብመንጃ!” አለ ኢማድ፤ ሳይቆጣ።
“ጠብመንጃ ብቻ ነው የምትወደው?”
“ውሻ ማረድም!” አስደንጋጭ ምላሽ፡፡
“ውሻ ማለትህ ነው ኢማድ?” የተሳሳተ መስሎት ለማረም፡፡
“አይ የውሻ አንገት መቁረጥ!” ሲል ፍርጥም ብሎ ተናገረ፤ ህጻኑ፡፡
ያስደነግጣል፤ ህጻን ልጅ “የውሻ አንገት መቁረጥ” ሲል፡፡
ኢማድና ታናሽ ወንድሙ እንዲሁም እናታቸው በአይሲል ወታደሮች ታፍነው ተወስደው ከሁለት ዓመት በላይ በምርኮኝነት ቆይተዋል፡፡ እናታቸው የአይሲል ወታደሮችን በባርነት ማገልገሏን ትናገራለች፡፡ ኢማድ በአይሲል ወታደሮች ታፍነው ሲወሰዱ የሁለት ዓመት ህጻን ነበር፡፡ ከእናቱና ከወንድሙ ተለይቶ ከአይሲል ወታደሮች ጋር ነበር የሚኖረው፡፡ ለህጻናቱ የጦርነት ፊልሞችን ያሳይዋቸው ነበር ትላለች- እናትየዋ፡፡  
አሁን ታዲያ ከትላልቅ ወንዶች በስተቀር ማንንም መቅረብና መጠጋት አይወድም። ፍላጎቱን በጩኸትና በሃይል ነው ማሟላት የሚፈልገው፡፡ ያናደዱት ላይ ሁሉ ምራቁን ይተፋል - እናቱን ጨምሮ፡፡
ኢማድ በአንድ ክፍል ውስጥ በተለያዩ የልጆች መጫወቻዎች ተከብቧል፤ ብቻውን። አሻንጉሊቶች፣ ትላልቅ መኪኖች፣ ትናንሽ መኪኖች ወዘተ--፡፡ ሆኖም ኢማድ እንደ ልጅ የመጫወት ፍላጎትና አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት ጨርሶ አልፈጠረበትም፡፡ ይልቁንም መጫወቻዎቹን ሥራዬ ብሎ ሲሰባብር፣ ከግድግዳ ጋር ሲያጋጭ ነው የሚውለው፡፡
ኢማድና ቤተሰቡ ካሳለፉት የአዕምሮና የሥነ ልቦና ቁስለት ያገገግሙ ዘንድ በተጠለሉበት ካምፕ የባለሙያ ድጋፍ እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ በተለይ ኢማድን በቅርበት ሆና ትከታተለዋለች፡፡ ታጫውተዋለች፡፡
የ4 ዓመቱ ህጻን፣ ጸጉሯን አበጥርላት ተብሎ የሰጠውን አሻንጉሊት፣ በካራቴ ብሎ ሁለት ቦታ ይከፍላታል፡፡  
ይህን ያየችው የሥነልቦና ባለሙያዋ  ወደ ህጻኑ ቀረብ ብላ፤
“ኢማድ፤ ምንድነው ያደረከው?” ብላ ትጠይቀዋለች፡፡
“ገደልኳት!” ይላል፤ ፊደላቱን ረገጥ አድርጎ፡፡
“ለምን?” መልሳ ጠየቀችው።
“የተለመደ ነዋ!” መለሰላት።
ከዚህችው የሥነልቦና ባለሙያ ጋር ውጭ ሜዳ ላይ ደግሞ ይታያሉ። ከአንዲት በራሪ ነፍሳት ጋር ልታስተዋውቀው፤ልታለማምደው ትሞክራለች። በራሪዋን ነፍሳት በተደጋጋሚ በጣቶቹ ጨፍልቆ ሊገድላት ሲሞክር ታስጥለዋለች።
“ትወድሃለች እኮ… አየህ በክንዶችህ ላይ ስትሄድ… ደሞ እኮ ትበራለች” እያለች ነፍሳቷን እንዳይገድላት ትጥራለች። ለአፍታ ያህል ልቡን የገዛችው መስሏት ሳትደሰት አትቀርም። ደስታዋ ግን ብዙም አልዘለቀም። ድንገት ሳታስበው ያቺን በራሪ ነፍሳት በጣቱ ጨፍልቆ ገደላት--ገላገላት፡፡ የእርካታ ስሜት በህጻን ገጽታው ላይ ይነበባል።
“ምነው ኢማድ… ለምን ገደልካት?” በማሳዘን ስሜት ጠየቀችው
“የተለመደ ነው” እረገጥ አድርጎ መለሰላት።
ይሄ እምቢተኛ፣እልኸኛና ሁከት ወዳጅ ህጻን፣የአይሲስ አረመኔ ወታደሮች ሆነ ብሎ  ካደረሱበት የአዕምሮ መቃወስ ለማገገም ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅበት ይታመናል፡፡
  በህፃናት መዋያ ውስጥ ከሌሎች የዕድሜ እኩዮቹ ጋር መዋል አልቻለም - ኢማድ። ህጻናቱን በሙሉ እየዞረ ይቀጠቅጣቸዋል። ከማንም አይወዳጅም- ተሳስቶ እንኳ፡፡ የሚያሳየው የጠብ ጫሪነትና ተደባዳቢነት ባህርይ ብቻ ነው፡፡
“እነሱ እኮ ይወዱሃል፤ ጓደኞችህ ናቸው ምናምን…” ቢባል፤ “ኖኖኖ!” እያለ ይጮሃል። ህጻናቱን ከመቀጥቀጥና ከመደብደብ ውጭ የሚታየው ነገር የለም።
ይሄ ህፃን ከዕድሜው ጋር የማይመጣጠን ቁጣ፣ ብስጭት፣ ንዴት፣ እልኸኝነት፣ ጉልበተኝነት ነው የሚንጸባረቅበት፡፡ ሞትና ግድያ ለዚህ እምቦቀቅላ ህፃን የተለመደ ወይም Normal ነው፤ በእጁ የገባችውን ነፍሳት ጨፍልቆ ገድሎ የተለመደ ነው እንዳለው፡፡
ህፃኑ አንድ የሆነ እንጨት ይዞ አውራ ጎዳና ዳር ላይ ቆሞ ይታያል። ምናልባት  እየተጫወተ ሊመስላችሁ ይችላል። ግን ተሳስታችኋል። ህፃኑ ጨዋታውን በአይስሊስ ወታደሮች ተነጥቋል። ህፃንነቱን ተሰርቋል። ወደዚህ አውራ ጎዳና የመጣው ለተልዕኮ መሆኑን የምትገነዘቡት ብዙም ሳትቆዩ ነው፡፡ ከርቀት መኪና መምጣቱን ሲመለከት የያዘውን እንጨት በፍጥነት መንገዱ መሃል ላይ ያስቀምጥና ዳር ሆኖ መመልከት ይጀምራል፡፡ መኪናው ደፍጥጦት እንዲሄድ ነው የፈለገው፡፡ ይሄ ምን ይገርማል፣ማንኛውም ጤነኛ ልጅ የሚያደርገው ነገር አይደለም ወይ፣ ካላችሁ አልተሳሳታችሁም፡፡
መኪናው ግን እንዳጋጣሚ እንጨቱን ሳይደፈጥጠው አለፈ፡፡ ኢማድም  እንጨቱን ከመንገዱ ላይ እያነሳ፤ “ረግጦት ቢያልፍ ኖሮ፣ መኪናው ይጋይ ነበር!” ሲል ከራሱ ጋር አወራ። አያችሁልኝ፤ ህጻኑ ወዲህ የመጣው ለተልዕኮ ነው፤ መኪና ለማጋየት፡፡ እንጨቱ ደግሞ ቦንብ ወይም ፈንጂ ነው፡፡
ይሄ እምቦቀቅላ ህፃን አዕምሮው ተበላሽቷል። ሥነ-ልቦናው ተዛብቷል። ጥልቅና ተከታታይ የሥነ-አዕምሮ ህክምና በቶሎ ካላገኘ፣ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ይከብዳል። የእናቱም ጭንቀትና ስጋት ይኸው ነው፡፡ ሰው ይሆንልኝ ይሆን? ያድግልኝ ይሆን? ስትል ትጨነቃለች፤ትጠበባለች፡፡
ስለዚህ ህጻን እያሰብኩ፣ ባለፈው ሰሞን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ጦረኛ ትውልድ አገር አያቀናም” ሲሉ የተናገሩት ትዝ አለኝ። አልተሳሳቱም፡፡ አገር ማቅናቱም ቀርቶ ከጦርነት ውስጥ ጤነኛ ዜጎችን ማግኘት በራሱ አዳጋች ነው፡፡
ከጦርነት ይሰውረን!
ፈጣሪ ሰላም ይስጠን!


Read 11850 times