Print this page
Sunday, 21 August 2022 00:00

ለኢትዮጵያ “ፈዋሽ ታሪክ” እንደሚያስፈልጋት የሚሞግተው “ጽዋዔ”

Written by 
Rate this item
(3 votes)


      የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘመነ ክህነት፣ የአንጾኪያ ቀውስ በጥልቀት ተዳሶበታል፤
ከአገራችንና ከቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ኹኔታ ጋራ በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፤
ተቋማት እና ልሂቃን፣ ማኅበረ ፖለቲካውን ማረቅ ባለመቻላቸው ዕዳ ኾነዋል፤
የሃይማኖት ልሂቃንም የፖሊቲካዊ መካሰስ አዋላጅ መኾናቸው እጅግ ያሳስባል፤
ከሚያቋስለን ርእዮተ ዓለማዊ ታሪክ ወደ ፈዋሽ ታሪክ ሽግግር ማድረግ አለብን፤

ከታሪክ እና ከታሪካዊ ትርክቶች በመነጩ ማኅበረ ፖሊቲካዊ ቀውሶች እየተናጠች ለምትገኘው ኢትዮጵያ መድኃኒቱ፣ “ፈዋሽ ታሪክ” መቀመም እንደኾነ ተጠቆመ፡፡
ጸሐፊ እና መምህር ዲያቆን ታደሰ ወርቁ፣ “ጽዋዔ” በሚል ርእስ ሰሞኑን ለኅትመት በአበቁት እና በሥርጭት ላይ በሚገኘው መጽሐፋቸው፣ ታሪክንና ትርክትን ለፖሊቲካዊ ውጥረት እና የእርስ በርስ ፍጅት ከመጠቀም ልሂቃን-መር ብሔራዊ እብደት በመውጣት፣ ከታሪክ የሚወለዱ ማኅበረ ፖሊቲካዊ መድኃኒቶችን በፈዋሽ የታሪክ ፈለግ ማሠሥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ያለፉት ኀምሳ ዓመታት የሀገራችን ፖለቲካ፣ በርእዮተ ዓለማዊ ታሪክ (Ideological History) የሚመራ እንደኾነ ጸሐፊው አመልክተዋል፡፡ ይህም፣ ታሪክን የፖሊቲካዊ ርእዮተ ዓለም ማስፈጸሚያ በማድረጉ እና ታሪካዊ በደሎችንና ቁስሎችን ብቻ በማነሣሻ መሣሪያነት በመጠቀሙ፣ በሒደት ወደ አስከፊው ማኅበራዊ ኢ-እኩያዊነት ሊባባስ የሚችል ፖሊቲካዊ ኢ-እኩያዊነት እያሰፈነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡ በደስታውም በኀዘኑም ‘የእኛ’ እና ‘የእነርሱ’ የሚል ፍንክት ማኅበረሰባዊ ሥነ ልቡና መቀረጹን፣ የአዝማናት ዕሴቶቻችንና ጥሪቶቻችን አውዳሚ ማኅበረ ፖሊቲካዊ ሥርዓት ማዋለዱን ገልጸዋል፡፡
የግራ ፖለቲከኞች ለአገዛዝ የበቁበት የርእዮተ ዓለማዊ ታሪክ ፈርጅ፣ ሀገራዊ አንድነትንና የሕዝብን አብሮነት በመስበር፣ ብዝኀ ማኅበረሰብ የኾነውን ኢትዮጵያዊ ለጉስቁልናና ለእልቂት፣ የሃይማኖት ተቋማቱንም ለዘውጌያዊ ልዩነት እና ክፍፍል የሚዳርግ ነዳጅ ኾኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አትተዋል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝም፣ ከቅርጹ በቀር በይዘቱ ሳይለወጥ፣ ዘውጌያዊ ማንነትን ከሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ጋራ የሚያቆራኝ አማሳኝ ፖሊቲካዊ ሥርዓት እና ሥነ ልቡና (Ethnodoxy) በመተግበሩ፣ የአገራችንም ኾነ የቤተ ክርስቲያናችን ዘመንና መስክ ወለድ ችግር፣ ከቀን ወደ ቀን በለየለት መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ ጥቃት (አድልዎ እና ማግለል፤ ማሳነስ እና ማንኳሰስ) የበለጠ እየተወሳሰበ እና በጥልቀት እየተባባሰ መቀጠሉን ጸሐፊው አስታውቀዋል፡፡
ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ወደማይኾን አቅጣጫ የሚወስደውን ይህን ስሑት እና እጅግ አሳሳቢ ማኅበረ ፖሊቲካዊ ቀውስ የሚያርቅና መላ የሚመታ ዕሴታዊ እና ክሂሎታዊ ብቃት ያለው ተቋም፤ በርቱዓዊ መንገድ እና ማዕከላዊ ፈሊጥ የግፉዓን ድምፅ እና የማኅበራዊ ፍትሕ አራማጅ የኾነ የሃይማኖትም ኾነ የፖሊቲካ ልሂቅ በየደረጃው አለመፍጠራችን እንደሚያሳስባቸው ዲያቆን ታደሰ ገልጸዋል፡፡ “በተለይ በእንዲህ ያለ ወቅት ለአገራችን ጸጋ መኾን የሚገባው ቤተ ክህነት እና ሌሎችም ተቋማት፥ ተፈጭተው ያልተነፉ ዱቄት፤ የሃይማኖት እና የፖሊቲካ ልሂቃኑም ቢኾኑ፥ ተበራይተው ያልተመተሩ የሀገር እና የቤተ ክርስቲያን እብቅ እና ግርድ ኾነው ተገኝተዋል፤” ሲሉ ተችተዋል፡፡ ስለ ዕርቀ ሰላም የሚሰብኩ ዜጎች ተሸማቀው እና ተሳቀው የሚኖሩበት፤ ካህኑ፣ ሼሁ፣ ፓስተሩ ሳይቀር ተጨምረውበት ጥላቻንና ዕልቂትን የሚያውጁ ወገኖች ደግሞ ታፍረው እና ተከብረው የሚንጎማለሉባት ሀገር እና ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥነ ልቡና አዋልደናል፤ ብለዋል፡፡
“ሀገር እና ቤተ ክርስቲያን ከገቡበት ማኅበረ ፖሊቲካዊ ቅርቃር የሚወጡበትን መፍትሔ የመፈለግ ጽኑዕ ረኀብ አለብኝ፤” ያሉት ጸሐፊው እና መምህሩ ዲያቆን ታደሰ ወርቁ፣ “ጽዋዔ - የማኅበረ ፖለቲካዊ ቀውስ ምንጭ፣ ተገብሮት፣ ክትያ እና ምላሽ በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘመነ ክህነት” በሚል ርእስ፣ በአንጾኪያ እና በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መስተዋትነት፣ ባለፈው ሒደታችን፣ በደረስንበት ኅሊናዊ እና ነባራዊ ኹኔታ እንዲሁም በወደፊት አዝማሚያችን ላይ ሰፊ ጥናት እና ዳሰሳ ያደረጉበት መጽሐፋቸው ታትሞ በሥርጭት ላይ ይገኛል፡፡
ከዛሬ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት በፊት፣ በቅዱስ ዮሐንስ ዘመነ ቅስና፣ አንጾኪያ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የነበሩበት እያንዳንዱ ታሪካዊ ክሥተት እና ኹነት፣ ለዘመናችን ቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥት ትእምርታዊ ውክልና ያለው የአኹኑ ኹኔታችን የካርቦን ግልባጭ እንደኾነ ጸሐፊው አስረድተዋል፡፡ በማኅበራዊ ፍትሕ ትምህርቱ እና የድኾች ጠበቃ ሊያሰኘው በሚችለው ሥራው የታወቀው ቅዱስ ዮሐንስ፣ ከአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ፍልቪያኖስ እና ከጊዜው ባሕታውያን ጋራ በመኾን፣ ለማኅበረ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲ‘ኮ’ ሃይማኖታዊ ስንጥቆች መፍትሔ የኾኑበት ዕሴታዊ እና ክሂሎታዊ ብቃት፣ ለሀገራችን የሃይማኖት እና የፖሊቲካ ልሂቃን ትምህርት ሊኾን እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
በሮም ግዛተ ዐፄ ጂኦፖለቲካዊ ተፈላጊነት የነበራት ሦስተኛዋ መናገሻ ከተማዪቱ አንጾኪያ፥ ብዝኀ ማኅበረሰብ እና ብዝኀ ሃይማኖት (የአሕዛብ፣ የአይሁድ እና የክርስቲያኖች መናኸርያ) የነበረች፤ የግሪካውያንና የሮማውያን ልሂቃንን የተዋሥኦ ፍጥጫ ያስተናገደች የጠበብት መዲና እንደመኾኗ፣ የብዝኀነት ጸጋዎችንና ዕዳዎችን የማስተዳደር እሳቤዎችን፣ ተግባራዊ ልምዶችንና ክሂሎችን ለመቅሰም እንደምታስችል ዲያቆን ታደሰ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚኽ ረገድ፣ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያናዊ እና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠበቅ፣ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተከተለውን የማዕከላዊነት ፈሊጥ እና የከፈለውን ዋጋ በጉልሕ በማውሳት፣ ለታሪካዊ እና ወቅታዊ ሕመሞቻችን፣ ፈውስ የሚኾን ታሪክ ለመቀመም፣ እንደ ዜጋ ለኢትዮጵያውያን፣ እንደ አማኝ ለኦርቶዶክሳውያን ልሂቃን ጥሪ (ጽዋዔ) መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡
ፈዋሽ የታሪክ ፈለግ (Healing History)፣ ታሪካዊ በደሎችንና ቁስሎችን በማከም ላይ የሚያተኩር ሲኾን፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ማኅበረሰብን የሚያጣብቅ ሙጫ ኾኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡ ከማኅበረ ፖሊቲካ ታሪክ የሚወለዱ ዕዳዎችን በመገነዛዘብ የመዝጋት እና ከማኅበረ ፖሊቲካ ታሪክ የሚወለዱ ጸጋዎችን በመድኃኒትነት የመጠቀም ባህል፣ በሃይማኖት እና በፖለቲካ ልሂቃን ሲዳብር፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ሰላማዊ ነፋስ የሚነፍስባቸው የተረጋጉ ወደቦች ማድረግ እንደሚቻል ጸሐፊው አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖት እና የፖሊቲካ ልሂቃን ከዘውጌያዊ ወገንተኝነት ርቀው፣ ቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥት ከሥርዓተ ሙሱን (አማሳኝነት) ተላቀው፣ ከማኅበረ ፖሊቲካ ታሪክ የሚወለዱ ዕዳዎችን በመገነዛዘብ የሚዘጉበት የተዋሥኦ መድረኮችን እንዲያበጃጁ ጥሪ (ጽዋዔ) አቅርበዋል፡፡
በመኾኑም፣ ጸሐፊው ዲያቆን ታደሰ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደጠቆሙት፣ የተላለፈው ጥሪ፣ ሀገራዊ መተማመንን መሠረት በማድረግ ከማኅበረ ፖሊቲካዊ ቀውስ ሙሻዙር የመውጣት፤ በብሔራዊ መግባባት እና እርቅ ታሪካዊ እና አኹናዊ ቁርሾን የማከም፤ በማዕከላዊነት እና በገለልተኝነት ሕዝባዊ በደልን የማበስ እና የመሻር ነው፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ከብተና፣ ከመፈናቀል፣ ከስደት እና ከእልቂት የመታደግ፤ ሀገራዊ አንድነትንና የሕዝብ አብሮነትን የሚያጸኑ፣ የሃይማኖት እና የፖሊቲካ ልሂቃንን የማበጃጀት አማናዊ ጥሪ ነው፡፡ መጽሐፉም በየምዕራፎቹ እንዲህ ዓይነቱን ጥሪ ስለሚያዘክር፣ “ጽዋዔ” ተብሏል፤ ትርጓሜውም ጥሪ ማለት ነው፡፡
የመጽሐፉ በኩረ አሳብ፣ በትምህርተ መለኰታዊ ፖሊቲካ የተቀነበበ በመኾኑ፣ “መነበብም ያለበት በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችንን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲ‘ኮ’ ሃይማኖታዊ ማሕቀፈ እይታ እና መጽሔተ አእምሮ ነው፤” ብለዋል ጸሐፊው። አያይዘውም፣ “የመጽሐፉ ወገንተኝነቱ እና ትኩረቱ ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ማንንም የማኮሰስ፣ ማንንም አክሊል የማቀዳጀት ሥራ አይደለም፤ መነሻዬ፣ መገስገሻዬ እና መድረሻዬ ቤተ ክርስቲያንና ሀገር ናቸው፤” በማለት አሳስበዋል፡፡
ስለ መጽሐፉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሓላፊዎች እና የነገረ መለኰት ምሁራን በበኩላቸው፣ መጽሐፉ፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የአንጾኪያ የተጋድሎ ሕይወት አንጻር ካህናት ሕዝባቸውን በአስቸጋሪ ኹኔታዎች ውስጥ እንዴት መምራት እና ማሻገር እንደሚገባቸው፣ በሰፊ ጥናት እና ዳሰሳ ተደግፎ ተግባራዊ ትምህርት ሊሰጥ በሚችል መልኩ በመዘጋጀቱ ጸሐፊውን አመስግነዋል፡፡ የታሪኩ ፍሰት፣ በየገጹ የሚታዩት ማራኪ ንኡሳን አርእስት እና የተወሳሰበው ታሪክ ተብራርቶ የቀረበበት መንገድ፣ መጽሐፉን በብዙ አንባብያን ዘንድ ተወዳጅ እንደሚያደርገው ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ የነገረ መለኰት ተማሪዎች እና መምህራን፣ ሰባክያን፣ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያናቸው ታሪክ አካል የኾነውን የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ዕድገት፣ ትምህርት እና የክህነት አገልግሎት፣ እንዲሁም በማኅበራዊ እኩልነት እና በምጣኔ ሀብት ፍትሐዊ ክፍፍል ላይ ያለውን አስተምህሮ እና ሙግት በአጽንዖት እንዲያጠኑት ለማድረግ ታላቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ብለዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከአሰፈሩት አንዱ የኾኑት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጀት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ “ጽዋዔን ሳነብ ሀገሬ ትዝ አለችኝ፤” ይላሉ፡፡ አክለውም፣ “ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት በፊት አንጾኪያ እና አንጾኪያውያን የገቡበትን ኹለንተናዊ አረንቋ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ዛሬ ገብተንበታል፡፡ በርግጥም ከልብ አንብቦ ለተረዳው ለትንሣኤያችን መነሻ አሳብ አበርካች መጽሐፍ ነው፡፡ የጳጳሳቱን፣ የካህናቱን፣ የምእመናኑን፣ የመለካውያኑን ጠባዕያት በገሃድ ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከአዚማችን ከአልነቃን፣ እንደ አንጾኪያ የሰዓታት ሳይኾን የዓመታት ዐመፅ አይቀሬ መኾኑን ያመላክታል፡፡ ሀገሬ ዛሬም ዮሐንስ አፈወ ርቅን ታሥሣለች፡፡ ዘረኝነት፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ መጠፋፋት፣ አሳልፎ መሰጣጣት፣ ኀጢአት የተባለው ሁሉ የሚከወንባት ሀገሬ ከመጥፋቷ፤ እኛም ከመጥፋታችን በፊት መድኃኒት የሚኾን መጽሐፍ ነው፤” በማለት አንብበው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል።
በ10 ምዕራፎች እና በ415 ገጾች የተቀናበረው “ጽዋዔ” መጽሐፍ፣ ከ200 በላይ በሀገር ውሰጥ እና በባዕዳን ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍትን በማጣቀሻ ምንጭነት ተጠቅሟል፡፡ ከእኒህም ውስጥ፣ በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በራሱ የተጻፉ እና በዘመኑ የነበሩ ጸሐፍት የጻፏቸው ቀዳሚ ምንጮች፤ በርካታ ጥንታውያን ድርሳናት፣ የጥናት እና ምርምር መጣጥፎች፣ የጥናት መጽሔቶች፣ የዐረብ ተጓዦች የጉዞ ማስታወሻዎች፣ በሮማ ግዛተ ዐፄ የአንጾኪያንና የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ዘመንና ሕይወት በተመለከተ የተሠሩ ዘጋቢ ፊልሞች፣ በኦርቶዶክሳውያን አብያተ አክርስቲያንና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረ ገጾች የተጫኑ ሕዝባዊ እና ትምህርታዊ ገለጻዎች ይገኙበታል። የተጣረሱ የታሪክ እይታዎችን ይፈትሻል፤ ይሞግታል፤ ይበይናል፡፡ ዐዲስ ቃላት፣ ፅንሰ ሐሳቦች፣ ኹነቶች፣ የሰው እና የቦታ ስሞች በ644 የግርጌ ማስታወሻዎች ተተርጉመዋል፤ ተብራርተዋል፡፡
በ385 ብር የሽፋን ዋጋ ለገበያ የቀረበው መጽሐፉ፣ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ሸዋ ዳቦ ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው አርጋኖን መጻሕፍት መደብር በዋና አከፋፋይነት እያሰራጨው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሥራዎች ጋራ የሚተዋወቁት ከኹለተኛ ደረጃ ተማሪነታቸው ጀምሮ እንደነበር ያወሱት ጸሐፊ እና መምህር ዲያቆን ታደሰ ወርቁ፣ የቅዱሱ ሥራዎች አእምሯዊ ሥሪቴንና ሥነ ልቡናዊ ውቅሬን ቀርጸዋል፤ ብለው ያምናሉ፡፡ በመንፈሳዊ እና ዓለማዊ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ላይ ያቀረቧቸው ወደ 170 ያህል ልዩ ልዩ መጣጥፎችም፣ የዚኹ ሥሪት እና ውቅር ተገብሮት ይመስሉኛል፤ ብለዋል፡፡


Read 1278 times
Administrator

Latest from Administrator