Sunday, 21 August 2022 00:00

ኦ ቀለሟ!

Written by  ዮፍታሄ ካሳ
Rate this item
(5 votes)

“ሀኒ! ምን ሆነሃል? የሆነ ነገር የሚያባርርህ እኮ ነው የምትመስለው!” ዮዲት በጭንቀት ተውጣ ጠየቀችኝ፡፡
ዓመታዊው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለብዙ ዓመታት የተሰወረ ጓደኛው ወይም ዘመድን በድንገት ማግኘት የተለመደ ነው፡፡
ግን ግን ከስንት ዘመን በኋላ ቀለሟን እዚህ አገኛታለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም፡፡ ድንገት ሳያት መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ በወደድኩ። ለአፍታ እጸ - መሰውር ቢኖረኝ ተመኘሁ! በሰው መሀል ልደበቅ? ልሩጥ? የምሰራውን አላውቅም ነበር። ፍቅረኛዬ ዮዲት በድንጋጤ እስክትርበተበት ድረስ እጇን ይዤ እየጎተትኩ፣ ለውድድሩ ድምቀት በስታዲሙ ዙሪያ ወደተዘጋጁት ምግብ ቤቶች ወሰድኳት፡፡ ሰው ሁሉ እንደአንዳች ነገር እያየን ... በድካም ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ … ወደ ምግብ ቤቱ ገባን፡፡
ምን ሆንክ?  ብትል፣  የምመልስላት ነገር ስላልነበረኝ ለስላሳ ጣቶቿን እያሻሸሁ ዝም ብዬ እያየኋት ቆየሁ፡፡ ባርማኑ ውስኪ በበረዶ አምጥቶልኝ በአንድ ትንፋሽ “ጅው” አድርጌ ስጠጣው፣ ዮዲት በድንጋጤ አይኖቸዋ ፈጠጡጡ፡፡
“ሀኒ! … ምን ሆነሃል? ዋት ዘ ሂል ኢዝ ጎይንግ ኦን?” አንባርቃ ጠየቀችኝ። የወረዛውን ፊቴን በሶፍት እያባበሰች …
“ትንሽ ድ… ድካም ነው መሰለኝ..”
ሁኔታዬ ባያሳምናትም ውብ አይኖቿን ጭፍን ክድን አደረገቻቸው፤ “ምንም አይደል አይዞህ፣ ተረድቼሀለሁ” እንደማለት። የኔ ለስላሳ! እንዲህ ናት ዮዲት! ሁሉንም ነገር በግልጽ ለመነጋገር ተስማንተን ስለነበር ይደብቀኛል ብላ አልገመተችም። ልንገራት ብልስ ምን ብዬ እነግራታለሁ?
“ቀለሟ …” ከስንት ዓመት በፊት የማውቃት፤ አንድ የሰማይ ስባሪ የምታህል የኤለመንታሪ ጓደኛዬ ናት” ብዬ ነው የምነግራት? ሀሳቡ እራሱ ዘገነነኝ፡፡
“ስምንተኛ ክፍል እያለን፣ … ቀለሟ በሆነ ስህተት የፍቅር ደብዳቤ ደርሷት፣ ፍቅረኛዋ እንድሆን ያስገደደችን ጉልቤ ልጅ ናት” ብዬ ነው የምነግራት? “ከወንድ በጠነከረ ጡንቻዋ ፊቴን እየነረተች ለመጀመሪያ ጊዜ ድንግልናዬን የወሰደችው ቀለሟ ናት” ብዬ ነው የምነግራት? ኧረ በስማም! አማተብኩኝ! ምንም እንዳልሆንኩ መስዬ መዋሸቱ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡
ምሳችንን አዝን እዛው መብላት ጀመርን። ገና የመጀመሪያውን ጉርሻ ጠቅልዬ ወደአፌ ለመላክ ስሰናዳ፣ እንደ ብራቅ የሚያስገመግም ድምጽ ከወደበሩ ተሰማ!!!
“ሄኖክ! ሄኖክ! ሄኖኬ!!!.. አንተ !!!!.... ድንገት አይቼህ ስትሰወር እኮ ፈልጌህ ፈልጌህ ነው እዚህ ያገኘሁህ!!!” … እንደ መብረቅ ያስደነበረን ድምፅ፣ የቀለሟ ድምፅ ነው። ሀሞቴ ፍስስ አለ… የምገባበት ጨነቀኝ …
ረጅምና ወፍራም ሰውነቷ በሩን ሞልቶት ቆማለች! … ፊቷ ላይ ነስነስ ያደረገችው ሻዶ ጥቁረቷን አደበዘዘው እንጂ አላጠፋውም። ቀጥ ብላ መጣች፡፡ የምግብ ቤቱ የጣውላ ወለል እስኪንሳጠጥ እየተራመደች ደረሰች። ዮዲት አጠገብ ደርሳ ተገተረች ከሚዳቋ አጠገብ ዳይኖሰር የቆመ መሰለ፡፡
ጠንካራ እጇ ትከሻዬን ወዘወዘው፡፡ የተረጋጋሁ መሰልኩ፤ ከንፈሬን የግድ አላቅቄ ተነሳሁ … “ኦ! ቀለሟ!!” እጄን ዘረጋሁላት፤ መዳፌን ሳብ አድርጋ በትከሻዋ ትከሻዬን ለተም አደረገችው። ተንገጫገጭኩ። ጥንካሬዋን እድሜ አላላላውም፡፡ በቃ! እንዲህ ነበረች ድሮም!
ቀለሟ የክፍል አለቃችን ነበች - አመሀ ደስታ እየተማርን፡፡ ስምንተኛ ክፍል ስንደርስ ጉርምስና ሁላችንንም ጀማምሮን ነበር፡፡ በአንድ የተረገመ ቀን የፍቅር ደብዳቤ ፃፍኩ ለቀለሟ ሳይን ለትዝታ። በፍቅርሽ አበድኩ ምናምን የሚል፣ በጦር የተወጋ ልብ ያለው፣ በህንድ አክተር ፖስትካርድ ያጌጠ፡፡ ትዝታ ከቀለሟ አጠገብ ነበር የምትቀመጠው፡፡ ትዝታ ለእረፍት ሰዓት ስትወጣ ደብተሯ ውስጥ ከተትኩት፡፡
በነጋታው ደብዳቤ ደረሰኝ፤ መልዕክቱም ደግሞ በእሽታ ቃላት ያሸበረቀ ነበር፡፡ እኔም እወድሃለሁ!! ዛሬ ከክፍል ስንወጣ መታጠፊያው ጋር ጠብቀኝ የሚል። በጣም ተገርሜና ጓጉቼ የቀጠሮው ቦታ ስደርስ ማን ቢጠብቀኝ ጥሩ ነው? ቀለሟ! - ሁላችንም የምንፈራት የክፍል አለቃችን፡፡
እየሳቀች ቀረበችኝ እና ደብተሯ ውስጥ የከተትኩት ደብዳቤ እንደደረሳት አረዳችኝ!! በስህተት እሷ ደብተር ውስጥ ከትቼው ኖሯል!! ላስተባብል ስሞክር ተቆጣች!! ደብዳቤውን ለዳይሬክተራችን ሰጥታ በጎማ እንደምታስለጠልጠኝ እያስፈራራች ጎትታ ከንፈሬን ሳመችኝ! በሚቀጥለው ቀን እንደተሳሳምን እንደምትናገር እያስፈራራች በድጋሚ ሳመችኝ … ከዛ በኋላ …. በቃ!!!
ከተፈነከትኩ እሷ በወረወረችው ድንጋይ ነው፣ ከንፈሬ ከደማ እሷ በሰነዘረችው ቡጢ ነው! በቃ መከራዬን በላሁ!!!  ኦ ቀለሟ!  አሁን  ከፊቴ ቆማለች፡፡
“ሄኖኬ! አንተ አትወፍርም እንዴ? ኸኸኸኸኸ” ብላ ጀርባዬን ቸብ ቸብ አደረገችኝ! … “ምንድነው ጉዳዩን አበዛሽ እንዴ??? ኸኸኸኸኸ” ሳቋ ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡
“ቁ…ቁጭ …ቁ…ጭ በያ!” አልኳት አፌ እንዳመጣልኝ።
“እንዴ! ቀላል እቀመጣለሁ! በስንት ጊዜያችን ተገናኝተንማ እንዲህ በቀላሉ አንላቀቀም! ስንትና ስንት ታሪክ ያለን ሰዎች እኮ ነን!! ኸኸኸኸኸኸኸ” … ስንትና ስንት ስትል ህልቆ መሳፍርት የሆነ የታሪክ ገፅ አብረን እንደገለጥን እጆቿን አስፍታ ነው፡፡
“እ..እሷ…እጮኛዬ … ዮ ዮዲት ናት!” አልኳት ተሽቀዳድሜ፡፡
ቀለሟ ግድ አልሰጣትም፡፡ ወንበር ስባ ተቀመጠችና መአዱን ተጋራችን። ዮዲት አጎራረሷን በመገረም እያስተዋለች በአይኗ ጠቀስ አደረገችኝ፡፡ “ምን ጉድ ነው የማየው?” የሚል ትርጉም አለው ጥቅሻም፡፡
“ቆየሽ እዚ ከመጣሽ?” ዮዲት ጠየቀቻት
“ብዙም አልቆየሁም ለነገሩ… አንድ ሁለት ዓመት ነው ያደረግኩት!”
“ከሃኒ ጋ የት ነው የምትተዋወቁት”
ዮዲት ወደእኔ እያሳየች ጠየቀቻት፡፡
ላብ ላብ አለኝ፡፡ የምገባበት ጨነቀኝ፡፡
“እ.. ከሳቸው ጋማ ለብዙ አመታት ነው የምንተዋወቀው!!! ኸኸኸኸኸኸኸ” ቀለሟ ሳቋን ለቀቀችው … ቦርጯን በእጇ ደግፋ ከጣሪያ በላይ ሳቀች፡፡
“አብሮ አደግ ናችሁ?
“አብሮ አደግ ብቻ? አብሮ አበድም ጭምር! የመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ነበር! እሱነው ሴት ያደረገኝ ኸኸኸኸ” … ቀለሟ ከመጠን በላይ እያስካካች ባሩን ድብልቅልቅ አደረገችው። አይኖች ሁሉ ወደኔ የተወረወሩ መሰለኝ፡፡
ዮዲት አናቷን በድንጋይ የተመታች ያህል ደንግጣ ስታያት ቆየች፡፡ ምን እያለች ነው ኢቺ ሴት የሚል ድንጋጤ ጭንቅላቷን እንደሞላው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
“ትዝ ይልሃል ለመጀመሪያ ጊዜ እንትን ስንል? … አቤት እንዴት ነበር ያሳመምከኝ?” ቀለሟ መለፍለፏን ቀጠለች፡፡
የምገባበት ጠፋኝ፡፡ የዮዲት ነጭ አይኖች ሲደፈርሱ ይታወቀኛል …
ኦ ቀለሟ!! ዛሬም አልተለወጠችም፡፡ ስምንተኛ ክፍል ‹ሚንስትሪ› ከወሰድን በኋላ ከቀለሟ ዱላና የግዞት ፍቅር እንደማመልጥ ተስፋ ነበረኝ፡፡ ቀጫጫ ሰውነቴ በቀለሟ ቁጣና ተግሳፅ ይበልጥ ሟሽሾ ቤተሰቤን አስጨንቄ ነበር፡፡ ግን ለማንም ትንፍሽ ብዬ አላልኩም የቀለሟን ምስጢር አልተነፈስኩም፡፡ ምን ተብሎስ ይወራል? ወንዲላ! ከቤ! የሚል ቅፅል ስም ያላት ቀለሟን ማን በፍቅር ይቀርባል?
ቀለሟ እንደሌሎቹ ሴቶች መቧጨር፣ መናከስ … ምናምን የሚል መዝገበ ቃላት አታውቅም፡፡ በቡጢ ነርታኝ ስታበቃ … ነው ፍቅር የሚታያት ካበሳጨኋት፣ … በቴስታ አናቴን በጥብጣ፣ ወይ በቡጢ ከንፈሬን ሰንጥቃ ትልከኛለች … አፍንጫዬ በቡጢ ተጣሞ፣ ወይ ነስር ከአፍንጫዬ እየፈሰሰ ወደቤቴ የማልገባበት ሳምንት በጣት የሚቆጠር ነበር፡፡ ሚንስትሪ ውጤት ከታወቀ በኋላ ከሰፈራችን ከመነን ራቅ ብሎ በሚገኘው ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዘገብኩ፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀለሟን እንደማመልጣት ነበር ተስፋዬ … አዲስ ዓመት መጥቶ የዘጠነኛ ክፍል ሲጀመር ግን መሳሳቴ ገባኝ፡፡ ቀለሟ የተመዘገብኩበትን ትምህርት ቤት አጣርታ እሷም ተመዝግባ ቆየችኝ፡፡
አካሌ እየጎረመሰ ሲመጣ ሰውነቴም እየፈረጠመ ቢመጣም ቀለሟን የምቋቋምበት አቅም አልነበረኝም። በሷ አቅመቢስነት የፈጠረብኝን ሽንፈት ለመቋቋም መሰለኝ፣ መጠጣት፣ ማጨስ ምናምን ጀመርኩ። ሀይስኩል እንደጨረስኩ ቤተሰቦቼ ወደ አሜሪካ ላኩኝ። ለአስር አመታት ያህል ስለቀለሟ አልሰማሁም ነበር! እንደ ጥላ ተጣብቃኝ እዚህ አገኘኋት፡፡ “እንዴት ግን ወደዚህ መጣሽ?” አልኳት ጨዋታ ለማስቀየርና የተረበሸውን የዮዲት ስሜት ለማረጋጋት
“አንተ ከኢትዮጵያ ከወጣህ በኋላ በቃ ሁሉ ነገር አስጠላኝ፡፡ የዘወትር ህልሜ አንተን ማግኘት ነበር፡፡ እዚ ለመግባት የከፈልኩትን መስዋዕትነት ብታውቅ ትገረማለህ። ይሁን! ለፍቅር የተከፈለ መስዋዕትነት ነው …” ድምጿ ደከም ብሏል - በለው!!
“ምን?! እና እሱን ለማግኘት ነው የመጣሽው?” ዮዲት ባለማመን ጠየቀቻት፡፡
ቀለሟ አንገቷን ላይና ታች ነቀነቀች፡፡ ዮዲት ከተቀመጠችበት ተፈናጥራ ተነሳች፡፡ “ከዚ በላይ!.. የናንተን የፍቅር ገድል የምሰማበት ጊዜ የለኝም!” ዮዲት ተቆናጥራ ተነስታ ወጣች። እሷን ተከትዬ ለመውጣት ብድግ ስል ቀለሟ ትከሻዬን ጨምድዳ አስቀመጠችኝ!!
“ተዋት ትሂድ!!! እኔ ስንት ሀገር አቋርጬ የመጣሁት አንተን ለማግኘት አይደል እንዴ?” ዮዲት እየራቀች ነበር፡፡ ዮዲትን ማጣቴ ለኔ ሞት ነበር፡፡ ቀለሟ ለዘመናት ከፈጠረችብኝ ህመም ያገገምኩት በዮዲት ነው፡፡ ፈውስ ሆና ያዳነችኝ እሷ ናት፡፡
ከወንበሬ እንደ አነር ዘልዬ ተነሳሁ፡፡ ቀለሟ ትከሻዬን እንደቅድሙ ተጭና ልታስቀምጠኝ ሞከረች - አልቻለችም!! በሁለት እጆቼ አንስቼ ወደ ግድግዳው ገፋኋት፡፡ አይኗ ውስጥ መገረም ነበር! በዚህ ብቻ አልበቃኝም!! ተንደርድሬ በጥፊ ፊቷ ላይ አላስኳት!! ደገምኳት!!! በልጅነቴ ያሰቃየችኝን ባያካክስልኝም፣ የመንፈስ ቁስልን ባይፈውስም ለሶስተኛ ጊዜ አላስኳት። የጨው አምድ ሆና ተገትራ ቆመች!!
“ኧረ ሴት ልጅ እንደዚ አትመታም!” አንድ ድምፅ ያለ መሰለኝ፡፡ የኔን አላየህ!
“ሁለተኛ አጠገቤ ብትደርሺ…!!!” እንደቆሰለ አንበሳ አጓርቼ ከሬስቶራንቱ ተተኩሼ ወጣሁ። ፍቅር ጉልበት ሆነኝ፡፡ ያኔ ጉልበት ያጣሁት ፍቅር ስላልነበረኝ እንደሆነ እያሰብኩ ወደ ዮዲት ሮጥኩ …


Read 970 times