Saturday, 20 August 2022 14:01

የማለዳ እንጉርጉሮ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    የማለዳ እንጉርጉሮ

አንዳንዴ ደግሞ ጎህ ቀዶ
አብሮኝ ያደረው ደወል ፥ ከራስጌየ ተጠምዶ
ከወፍ ቀድሞ ሲያመጣልኝ፥ ነግቶብሀል የሚል መርዶ
ብትት ብየ ደንብሬ፥
ግማሽ ፊቴን፥ ትራሴ ውስጥ ቀብሬ
“ እኮ ዛሬም እንደ ወትሮ
ካውቶቢስ ወደ ቢሮ
ከኬላ ወደ ኬላ
ዛሬም በግንባሬ ወዝ ልበላ
እሺ ከዚያስ በሁዋላ
እያልሁ ስሞግት ልቤን፥ መልሱን አያመለከትተኝ
ይሄን ያህል ነው የታከተኝ።
ጉዞየ ካዋላጅ እቅፍ፥ እስከ ገናዦች አልጋ
ባራት እግር ተጀምሮ፤ ባራት ሰው ሸክም እስኪዘጋ
መንገዱ መንገድ እየሳበ
ትንንሹ ዳገትም፤ ለትልቁ እያስረከበ
እንደ ሐረግ ስጎተት፥ እንደ ጥንቸል ስፈጥን፥
ምን ሽልማት ታሰበልኝ ?” ይህ ልፋቴን የሚመጥን፥
እያልሁኝ ሳውጠነጥን ፥
አንዳንዴ ደግሞ ሲመረኝ፥
እንደ ለማዳ ፈረስ ፥ ሞትን በፉጨት መጥራት ሲያምረኝ፥
ዛፉን የተቀማ አሞራ
በኮረንቲ ምሶሶ ላይ፥ ቤቱን ባዲስ መልክ ሲሰራ
ማሯን የተዘረፈች ንብ፥ በያበባው ስትሰማራ
አይና
እንዲህ እንዲህ እላለሁኝ፤ ራሴን በራስ ሳጽናና
‘ ሺህ ጊዜ ብትራቀቅ፥ ቃላት መርጠህ ብትገጥም
ከዚህ አሞራ አታንስም፥ ከዚች ንብም አትበልጥም
ተፈጥሮ ትግልን እንጂ፥ የድል ዋስትናን አትሰጥም’’
ቻለው!
(በእውቀቱ ስዩም)

Read 1667 times